“Law is nothing else, but the best reason of wise men applied for ages to the transaction and business of mankind” Abraham Lincoln

መነሻ ክስተት

ነገሩ እንዲህ ነው! የሙያ ባልደረቦቼ ደንበኞቻቸው ተከሳሽ በሆኑባቸው የፍትሐብሔር የፍርድ ሂደት ላይ መከላከያ መልሳቸውን ሲያቀርቡ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 244(2) (ለ) መሠረት “ክስ የቀረበበት ጉዳይ አስቀድሞ በፍርድ የተወሰነ” መሆኑን እና (ሠ) መሠረት የቀረበው ክስ “በይርጋ የታገደ” መሆኑን ጠቅሰው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያቸውን በዋናው ክርክር ላይ ካላቸው መልስ ጋር አያይዘው አቅረበው ነበር፡፡ ነገር ግን ፍ/ቤቶች በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ክርክር ለመስማት በተያዘ ቀነ ቀጠሮ ከሳሾች ሳይገኙ በመቅረታቸው ምክንያት ጉዳዩን እየመረመሩ የነበሩት ፍ/ቤቶች ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ እንደሚክዱ ከጠየቁ በኃላ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 73 መሠረት ክስ ለመስማት በተያዘ ቀነ-ቀጠሮ ከሳሾች ባለመቅረባቸው እና ተከሳሾች ክደው በመከራከራቸው መዝገቡን ዘግተናል በማለት ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

ተከሳሽ ባልቀረበበትና የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ክርክር ለማድረግ ቀጠሮ የያዘው ጉዳዩን ሲያይ የነበረው ፍ/ቤት ደግሞ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 70 መሠረት የተከሳሽን በክርክሩ የመካፈል መብት አግዶ ጉዳዩ በሌሉበት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡        

 የጹሑፍ ዓላማ

የዚህ ጹሑፍ ዓላማው ከላይ የተመለከቱትን ነባራዊ ሁኔታዎች መሠረት በማድረግ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይሞክራል፡፡

ሀተታ

በፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጋችን የክርክር ሂደቱ ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነርሱም፡- የአቤቱታና የሰነድ ማስረጃዎች ልውውጥ የሚደረግበት (Pleading stage)፣ የክስ የሚሰማበት (Trial stage) እና የፍርድ የሚሰጥበት ክፍል ተብለው መከፈል ይችላሉ፡፡ በእነዚህ እያንዳንዱ ክፍሎች ልንከተላቸው የሚገቡን ሥነ-ሥርዓታዊ ሂደቶች አስመልክቶ ገዢ የሆኑ እና ልንከተላቸው የሚገቡ ድንጋጌዎች በሥነ-ሥርዓቱ ሕግ ላይ ተደንግገዋል፡፡ ነገር ግን በሁለተኛውና በክስ መስማት ወይም ቃል ክርክር ክፍሉ ውስጥ ግን ሁለት ክፍሎች ያሉ ሲሆን እነርሱም ወደ የክስ መስማት ሂደት የሚወስዱ ነገሮች መኖር አለመኖራቸው የሚጣራበትና ክስ የሚሰማበት ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የክስ መሰማት ሂደት በእነዚህ ሁለት ክፍሎች ግልጽ ድንበር አስምሮ የተለየ ቢሆንም በተለይም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በሚደረግ ክርክር  ሂደት ላይ የምንከተላቸው እና ተግባራዊ የምናደርጋቸው የሕግ ድንጋጌዎች በሂደቱ በክርክሩ ዋና ጭብጥና ፍሬ-ጉዳይ ላይ በሚኖረን የሙግት ወይም ክስ መስማት ላይ ተፈጻሚ የምናደርጋቸውን ነው፡፡ ለመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ክርክር ከፍሬ-ነገር ማስረጃና ሙግት የሚለያቸው ምንድን ነው?

ቁልፍ ቃላት (key words)

የቃል ክርክር/ክስ መስማት፣የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ እና የሕግ/ፍሬ-ነገር ማስረጃና ሙግት  

ሀ. የቃል ክርክር  

 የቃል ክርክር ትርጉምን በተመለከተ የሕግ መዝገበ ቃላት የሆነው Black’s Law Dictionary

“Statements that are given orally by an attorney, either in defense of a client or rebut the opposing party’s statement”

“ጠበቃው ደንበኛውን ለመከላከል ወይም በተቃራኒ ወገን የቀረበውን ክርክር ለማስተባበል በቃል የሚያቀርበው ክርክር/መግለጫ ነው” (ሠረዝ የተጨመረና ትርጉም ከራሴ)

በማለት ትርጉም ከሚሰጠው ውጪ የሀገራችን ሁለቱ (የወንጀልና የፍትሐብሔር) የፍ/ቤት ክርክሮች ሥርዓት የሚመሩባቸው የሥነ-ሥርዓት ህጎች የቃል ክርክር መቼና በምን ሁኔታ እንደሚቀርቡ ከመደንገግ ባለፈ የቃል ክርክር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በእነዚህም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ህጎች ትርጉም አልተሰጠውም፡፡

ነገር ግን ከየዝነው የፍትሐብሔር የክርክር ሂደት ስርዓት አኳያ ይህ በተከራካሪዎች የሚቀርበው የቃል ክርክር የሚከናወንባቸው ጊዜዎችና ሁኔታዎች ሁለት ሲሆኑ እነዚህ የፍርድ ሂደቶች ቅድመ ክርክር(First Hearing) እና ክርክር(Hearing) ተብለው ይከፈላሉ፡፡

በቅድመ ክርክር ጊዜ ከሚከናወን የቃል ክርክር ተግባራት ዋነኛው በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በተከራካሪዎች የሚቀርብ ነው፡፡ የዚህ ጹሁፍ ዓላማ በዚህ ደረጃ በሚደረገው ክርክር ላይ በመሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ምንድን ነው? በዚህ መቃወሚያ ላይስ የሚደረግ የቃል ክርክር ዓላማውስ? የሚለውን በቅድሚያ መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡

  ለ/ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ

የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ወደ ዋናው የክስ ፍሬ ነገር ፍ/ቤቱ ገብቶ ሳያከራክር የፍርድ ሂደቱን እንዲያቋርጥ በተከሳሹ የሚቀርቡ የሕግና የፍሬ-ነገር ይዘቶች ስለመሆኑ ሴድለር እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡

“it may defined as an objection not going to the merits of the case, that   is, no involving the question of whether the defendant is liable to the plaintiff under the substantive law” “ወደ ዋና የክርክር ጉዳይ እንዳይገባ የሚቀርብ መቃወሚያ ማለት ሲሆን ይህ ግን ተከሳሹ በከሳሽ ለቀረበበት ክስ በዋና ህጎች ሀላፊነት ያለበት ስለመሆኑ እና ስላለመሆኑ የሚነሱ ጥያቄዎችን አያካትትም” (ትርጉም ከራሴ እና ሠረዝ የተጨመረ)

ሌላውና ሁለተኛው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ለየት የሚያደርገው ባህሪ በውጤት ደረጃ ሁልጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርገው መቃወሚያ አቅራቢውን ብቻ አለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍርድ ቤቱን የቀረበለትን ጉዳይ ለማየት የፍሬ-ነገርም (material jurisdiction) ሆነ ብሔራዊ የዳኘነት (judicial jurisdiction) ስልጣን በሌለው ጉዳይ ላይ መቃወሚያ መቅረቡ የተከሳሹን ጥቅም የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን የፍርድ ቤቱን ጊዜና ጉልበት እንዳይባክን የማድረግ ውጤት ነው ያለው፡፡ ከዚህ ልዩ ባህሪያቸውም አኳያም በተከራካሪዎች ሊተው የሚችሉ(waiveable preliminary objection) እና ሊተው የማይችሉ (Unwaiveable preliminary objection) የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ብለን በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ 

እነዚህንም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ባህሪያትን ስንመዝን በተከራካሪው የቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ በጽሁፍ ከቀረበው ክርክር ውጪ ክርክር የሚቀርብባቸው ሳይሆኑ ይልቁንም በመቃወሚያነት የቀረበው ኩነት (facts) በቀላል የቃል ማጣሪያ እና ፍሬ-ነገሩን ለማስረዳት የሚችሉ ማስረጃዎችን በማቅረብ እና በማስቀረብ ብቻ ብይን የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡

በዚህም የፍርድ ሂደትም ሙሉ ክርክሩን የሚመራው ዳኛው ሲሆን ተከራካሪወቹ ከዳኛው ለሚጠየቁት ማጣሪያ ጥያቄ ከመመለስና ማስረጃ እንዲያቀርቡ በታዘዙ ጊዜ ይህን ማስረጃ ከማቅረብ ያለፈ በመካከላቸው የሚያደርጉት ክርክር የለም፡፡

ሐ/ የፍሬ-ነገር ማስረጃና ሙግት (Hearing)

ይህ በቃል እንደዚሁም ምስክሮችና ሰነድ ማስረጃን በማቅረብ የሚደረግ ሙግት ሲሆን የሚከናወነው በክርክሩ ዋና ጉዳይ (merit of the case) ላይ እና ፍርድ ቤቱ ተከራካሪዎች ያልተስማሙበትን የፍሬ-ነገርና የሕግ ነጥቦች በለየው ወይም በመሰረተው የነገር ጭብጥ (on the framed issue) ላይ የሚያከናወን ሂደት ስለመሆኑ Black’s Law Dictionary እንደሚከተለው ይተረጉመዋል፡፡

“A judicial session held for the purpose of deciding issues of facts or laws, sometimes with witness testifying”

“በሕግ ወይም በፍሬ-ነገር ጭብጥ ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንዲረዳ የሚከናወን የፍርድ ሂደት ክፍለ ጊዜ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የምስክሮች ቃል መቀበልንም ይጨምራል”(ትርጉም ከራሴ)

የጭብጥ የሚመሰረተውም ደግሞ በአንደኛው ተከራካሪ ታምኖ በሌላኛው ተከራካሪ በተካደው እና ለጉዳዩ አግባብነት ባላቸው (material proposition) የሕግ/የፍሬ-ነገር ጉዳዮች ላይ ብቻ ሲሆን መመስረቻው ግዜም በቀረበው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ከተሰጠ በኃላ መሆኑን ሕጉ ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም በዚህ የሙግት ሂደት የሚከናወነው የቃል ክርክር/ክስ መስማት በቀረበው የክስ ዋና ፍሬ ነገር ላይና ፍ/ቤቱ በያዘው ጭብጥ ላይ በተከራካሪዎች መካከል የሚቀርብ ሲሆን በተለይም ደግሞ የቀረበ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ያለ እንደሆነ በመቃወሚያው ላይ ብይን ከተሰጠ በኃላ የሚከናወን የፍርድ ሂደት መሆኑን ነው፡፡       

የባለሙያዎች እይታ

 ነገር ግን ይህ የቃል ክርክር/የክስ መስማት ሂደት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያም ሆነ በፍሬ-ነገሩም ላይ በአንድ ላይ  ሊከናወን ነው የሚገባው ወይስ በቅድሚያ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብቻ ክርክር ተደርጎ ይህን መቃወሚያ ፍ/ቤት ያልተቀበለው እንደ ሆነ ብቻ ነው ወደ ፍሬ-ጉዳይ ክስ መስማት መሻገር ያለብን የሚለውን የሕግ ትርጉም አስመልክቶ በባለሙያዎች መካከል ያለውን አቋም በሁለት መመደብ ይቻላል፡፡

 

  1. 1. መደብ አንድ

 

በመጀመሪያው መደብ ያሉት ባለሙያዎች የሚያነሱት መከራከርያ የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉን የተፈጠነ ፍትሕን የመስጠት ዓላማ ከማስከበር አኳያ ነው፡፡ የሕጉ ዓላማ ለፍ/ቤቶች ምቹ ሁኔታን በመዘርጋት ለተገልጋይ የተፋጠነ ፍትሕን (speedy justice) መስጠት ዋና ዓላማው ነው ፡፡ በዚህም “የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል” የሚለውን ብሂል ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም የሥነ-ሥርዓት ሕጉ በግልጽ በአንድ ክርክር የክስ መሰማት ሊከናወን የሚገባው አንድ ጊዜ ብቻ መሆን እንዳለበት ገልጾ አስቀምጦ ሳለ “ለመጀመሪያ ደረጃ” እና “በፍሬ-ጉዳይ” በማለት የክስ መስማት ቀጠሮን ለሁለት የተለያዩ ቀጠሮ ቀኖች መክፈል የፍርድ ሂደቱን ማርዘም እና ሕግ መሠረት ያላደረገ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

  1. መደብ ሁለት

በሁለተኛው መደብ ያሉት ባለሞያዎችም ዋና መከራከርያቸው የጠራና የተፈጠነ ፍትሕ (speedy justice) ነው፡፡ መከራከርያቸውም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ዋና ዓላማ ወደ ክርከሩ ፍሬ-ጉዳዩ እንዳንገባ ማድረግና ጥቅማቸውም ተከራካሪን ብቻ ሳይሆን የፍ/ቤቱን ተቋም ጊዜና ጉልበት አለአግባብ እንዳይባክን የሚቀርቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም ፍ/ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ውድቅ የሚደረግ ክርክር ቀርቦ ሳለ ውድቅ በሚሆን እና ሊታይ በማይገባው ጉዳይ ላይ ክርክር ከመስማት እና ከመመርመር በላይ ፍ/ቤቶች የተፈጠነ ፍትሕን እንዳይሰጡ የሚያደናቅፋቸው ነገር የለም፡፡ በመቃወሚያ ላይ ብይን ሳይሰጥ በዋናው ጉዳይ ላይ ማከራከር በግልጽ ሕግን መቃረን አይደለም? ይህ ከሆነ መቃወሚዎች ከሁሉ አስቀድመው እንዲቀርቡ በልዩ ሁኔታ መታዘዙ ለምን አስፈለገ? በማለት ጥያቄ በማንሳት ይሞግታሉ::

  1. የፌ/ሰ/ሰ/ችሎት አቋም

እንዲህ ዓይነት የተለያዩ የሕግ ትርጉሞችን መሠረት ባደረገ ሁናቴ በባለሙያው ዘንድ በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያየ አተገባበር በሚፈጥርበት ጊዜ በፍ/ቤቶች ዙሪያ ወጥ የሆነ አሰራር ለመፍጠርና በተገልጋዩ ዘንድ ታማኝነትን ለመፈጠር በሀገሪቱ በማንኛውም ፍ/ቤቶች ላይ አስገዳጅና ተፈጻሚ የሆኑ የሕግ ትርጉሞችን እንዲሰጥ ይህ የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተቋቁሟል፡፡   

 ይሁን እንጂ ይህ ችሎት ለያዝነው ጉዳይ በቀረበ ደረጃ የተመለከተው ጉዳይ

በመልካችና በተጠሪ መካከል በነበረው በሱሉልታ ወረዳ ፍ/ቤት በነበረ ክርክር የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ቀረቦ ሳለ ፍ/ቤቱ በቀረበለት መቃወሚያ ላይ ብይን ሳይሰጥ በማለፍ በቀጥታ በዋናው የፍሬ-ነገር ክርክር ላይ ውሳኔ መስጠቱን ተከትሎ ለቀረበው ቅሬታ ጉዳዩ ለፌ/ሰ/ሰ/ችሎት የቀረበ እና ችሎቱም በቀረበ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብይን ሳይሰጥ በዋናው ጉዳይ ላይ ውሳኔ መስጠት መሰረታዊ ሥነ-ሥርዓታዊ የሕግ ስህተት ነው በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ የሻረበት

ብቻ ቢሆንም በዚህ ሁኔታ እንኳ ችሎቱ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የክርክር ጊዜ እና የፍሬ-ነገር ክስ መስማትን የጊዜ ሁኔታ አስመልክቶ በውሳኔው በዝምታ ማለፍ መምረጡ ወጥ የሆነ የሕግ ትርጉሙና አተገባበር ክፍተቱ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡ ምክያቱ ደግሞ በሁለቱም መደብ በሚገኙ ባለሙያዎች የሕግ አተረጓጓም እና አተገባበር በቀረበ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በቅድሚያ ብይን መሰጠቱ ክፍተት አለመሆኑ ነው፡፡

ምንአልባትም ይህ በባለሙያዎች መካከል ያለው የሕግ አተረጓጎምና አተገባበር ልዩነት በውጤት ደረጃ መሰረታዊ የሕግ አተረጓጎምን ስህተት ሊያመጣ አይችልም ከሚል እሳቤ በዝምታ ታልፎ ከሆነ ከላይ በመግቢያው ለዚህ ጹሁፍ መነሻ የሆኑኝ ክስተቶችን በገለጽኩበት ሁኔታዎች የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ብቻ ክርክር ተደርጎ መቃወሚያው በብይን ውድቅ ከተደረገ በኃላ ብቻ ነው በፍሬ-ጉዳዩ ላይ ክስ የመሰማት ሂደት ሊከናወን የሚገባው በሚል ትርጉም የፍርድ ሂደትን እየመሩ የሚገኙ ፍ/ቤቶች በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ክርክር ለመስማት በያዙት ቀጠሮ የከሳሽና የተከሳሽ ያለመቅረብን ተከትሎ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 70 እና 73 ተፈጻሚነት ማድረጋቸውን አስከትሏል፡፡

ይህ የፍ/ቤቶቹ ድርጊት ደግሞ ‘የተከራካሪዎችን የመብት ጥሰት ያስከተለ እና ፍትሕን ያጓደለ በመሆኑና ተከራካሪዎቹ በጉዳዩ የመከራከር መብታቸው ቢጠበቅ ኖሮ የቀረበውን ጉዳይ የፍርድ  ይዘቱን፣ዉጤቱን የማሻሻል ወይም የመሻር የሚያስከትል ስህተት በመሆኑ መሰረታዊ የሕግ ስህተት ይሆናል፡፡’

ለመሆኑ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 69፣ 70 እና 73 አፈጻጸም የሚከናወነው መቼ ነው?

  እነዚህ የፍትሐብሔር ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች አፈጻጸም ሁኔታን ለመወሰን መሰረታዊ የሆነው እና በሶስቱ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ የተገለጸው የተወሰነው ቀነ ቀጠሮ “ክርክሩን ለመስማት” ስለመሆኑ ድንጋጌዎቹ እንደሚመለከተው ይገልጹታል፡-

 

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 69 ስለ ተከራካሪዎች ወገኖች መቅረብ

1/ ነገሩን ለማየት ፍ/ቤቱ በወሰነው ቀጠሮ…….

2/ ግራ ቀኙ ተከራካሪዎች በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርቡ የቀሩ እንደሆነ ፍ/ቤቱ መዝገቡን ይዘጋዎል፡፡

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 70 የተከሳሽ አለመቅረብ

ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ከሳሽ ቀርቦ ተከሳሹ ያልቀረበ እንደሆነ ለጉዳዩ ውሳኔ የሚሰጠው እንደሚከተለው ነው፡፡

ሀ/….. በሌሉበት የነገሩ መሰማት ይቀጥላል፡፡

የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 73 የከሳሽ ያለመቅረብ

ባንድ ነገር ክስ ያቀረበው ሰው ክርክሩ እንዲሰማ በተወሰነው ቀነ ቀጠሮ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ……..፡፡ ተከሳሹ የካደ እንደሆነ ግን መዘገቡን በመዝጋት ያሰናብተዋል፡፡

  ይሁን እንጂ ይህ የክስ መስማት የፍርድ ሂደት ሁለት ክፍሎች ያሉት እንደሆነና እነርሱም የክስ መስማት ሂደት የሚወስዱ ነገሮች መኖር አለመኖራቸው የሚጣራበትና በክርክሩ ጭብጥ ላይ ክርክር የሚከናወንበት ስለመሆኑ ከላይ በዝርዝር በተገለጸው መሠረት በእነዚህ ድንጋጌ ላይ የተገለጹት የክርክር መስማት ሂደት የየትኛውን ክፍል ላይ የሚከናወነዉን የክስ መስማት ሂደት ስለመሆኑ መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡           

  በዚህ ጹሁፍ የመጀመሪያው ክፍል በክስ መስማት ሂደት ውስጥ ካሉት ክፍሎች ውስጥ ያለው የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ የሚደረገው እና በቅድመ-ምርመራ (pre-trial) የሚጣራው ወደ ክርክር የሚወስዱ ነገሮች መኖር አለመኖራቸው ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ ደርሰን ነበር፡፡ ነገር ግን ከላይ የተመለከቱት የሕግ ድንጋጌዎች በሙሉ በቀረበው ጉዳይ “ክርክር በሚሰማበት” ወይም “ጉዳዩን ለማየት” የተቀጠሩበት ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡ በቀረበው ጉዳይ ላይ ክርክር የሚከናወነው ደግሞ ወደ ክርክር የሚወስድ ነገር መኖሩ ተጣርቶና የቀረቡት መቃወሚያዎች በብይን ውድቅ በመሆን ፍ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ጭብጥ የያዘበት እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከላይ የተመለከቱት የሕግ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚገቡት ፍ/ቤቱ በመሰረተው ጭብጥ ላይ ክርክር ለመስማት ቀጠሮ በያዘበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በሚቀርብ ክርክር ላይ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 69፣ 70 እና 73 ተፈጻሚነት

    ወደዚህ ርዕስ ከመግባታች በፊት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በሚቀርብ ክርክር እና በጭብጥነት በተያዘ የሕግ/ፍሬ-ጉዳይ ላይ በሚደረግ የቃል ክርክር ልዩነት ከላይ በዝርዝር ከተገለጹት ሁኔታዎች አኳያ የሚያስማሙን ድምዳሜዎች አሉ፡፡ እነዚህም፡-    

1ኛ/ ፍ/ቤት በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የቀረቡለትን ኩነቶች ለማጣራት ለተከራካሪዎች ጥያቄ የሚያቀርበብት ወይም ለበለጠ ማጣራት ማስረጃ እንዲቀርበለት በማዘዝ የቀረበውን መቃወሚያ እውነትነት የሚያረጋግጥበት ነው፡፡ ስለሆነም ተከራካሪዎች በቀነ-ቀጠሮ ዕለት ፍ/ቤቱ ጥያቄ ያለው እንደሆነ ጉዳዩን ለማጥራት መልስ የሚሰጡበት ነው እንጂ በመካከላቸው የሕግም/ፍሬ-ነገር ክርክር የሚያካሄዱበት አይደለም፡፡

2ኛ/ በዋናው ጉዳይ ላይ የሕግ/የፍሬ-ነገር የቃል ክርክር የሚደረገው ደግሞ ፍ/ቤቱ በመሰረተው ጭብጥ ላይ የሚደረግ ክርክር ሲሆን ፍ/ቤቱ የክርክር ሂደቱን ከመምራት ውጪ ሙሉ ክርክር በተከራካሪዎች የሚቀርብበት የፍርድ ሂደት ነው፡፡ ፍ/ቤቱ በቀረበው ክርክር ላይ እንዲጠራለት የሚፈልገውን ጥያቄ የማቅረብ የማይነካና የማይገረሰስ (absolute right) መብቱ ግን እንደተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡ 

3ኛ/ “ክርክሩ እንዲሰማ” የተቀጠረበት ቀነ ቀጠሮ በተከራካሪዎች መካከል ፍ/ቤቱ በመሰረተው ጭብጥ ላይ ክርክር እንዲደረግ ቀነ-ቀጠሮ የተሰጠበት መሆኑ ነው፡፡        

  ከእነዚህ መደምደሚያዎች ተነስተን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ፍ/ቤቱ ማጥራት የሚፈልገውን ጥያቄ ተከራካሪዎችን ለመጠየቅና በማስረጃነት እንዲቀርበለት የሚፈልገውን ደግሞ እንዲቀርብለት ለማዘዝ በተያዘ ቀነ-ቀጠሮ የተከሳሽ አለመቅረብ ፍ/ቤቱ በሚመሰርተው ጭብጥና በዋናው ክርክር ላይ ገብቶ የመከራከር የተከሳሽን መብት የሚያሳጣ ወይም ባልተያዘ ጭብጥ ተከሳሽን ታምናለህ ወይስ ትክዳለህ በማለት ጥያቄ በማቅረብ የተካደ ሲሆን የክሱን መዝገብ መዝጋት የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዓላማ አይደለም፡፡

 በተጨማሪም የሥነ-ሥርዓት ሕጉ በዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ነገርን ለማጥራት በያዘው ቀጠሮ ነገሩን ለማጥራት የሚፈለገው ተከራካሪ ከሳሽ ብቻ ስለመሆኑ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም የተከሳሽ አለመቅረብ በቀረበበት ክስ ላይና በዋናው ፍሬ-ጉዳይ ላይ ራሱን ለመከላከል አለመቻል እስኪደርስ ድረስ ዋጋ ሊያስከፍለው አይገባም፡፡    

  እንደዚሁም ተከሳሽን የማመን እና የመከድ ጥያቄ መጠየቅ አግባብ የሚሆነው በቀረበው መቃወሚያ ላይ ብይን ተሰጥቶ ከታለፈ በኃላ እና ለክርክሩ ዋና ጉዳይ የሆነው ጭብጥ ከተመሠረት በኃላ ነው፡፡ በመሆኑም ብይን ባልተሰጠበት፣ ጭብጥ ባልተመሰረተበት ሂደት ምን እንደሚያምን ምንስ አንደሚክድ ባልተለየበት ክርክር በደፈናው ተከሳሽን መካዱ ተጠይቆና ተረጋግጦ የከሳሽን የክስ መዝገብ መዝጋት ፍ/ቤት ፍትሕን ለመስጠት ከተቋቋመበት ዓላማ አኳያ አግባብ አይደለም፡፡ እንደዚሁም የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች አበዛኛዎቹ የሕግ ክርክሮች በመሆኑና የፍሬ-ነገር መቃወሚያዎችም በማስረጃ ተደግፈው የሚቀርቡ ወይም በተከሳሽ እጅ የማይገኙ ከሆነ ደግሞ በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ እንዲቀርቡ በማስረጃ ዝርዝር ላይ የሚገለጹ በመሆናቸው ፍ/ቤቱ እነዚህ ማስረጃ መዝኖ እና ሕግን መሠረት አድርጎ ብይን ለመስጠት የከሳሽ መቅረብና አለመቅረብ መዝገብ እስከማዘጋት ዋጋ ሊያስከፍል አይገባም፡፡ በፍ/ቤት የስር-ነገር ስልጣን አለመኖር፣ በሥነ-ሥርዓታዊ ይርጋ፣ በጉዳዩ ላይ ክስ ቀርቦ ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑ በማስረጃነት በተያያዘበት ሁኔታ፣ በተመሳሳይ ጉዳይ በሌላ ፍ/ቤት ክርክር ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ተጠይቆና እንዲቀርብ ትእዛዝ ለመስጠት…ወ.ዘ.ተ የከሳሽ አለመቅረብ ለውጥ አያመጣም፡፡ ፍ/ቤት በቀረበለት ጉዳይ ሁሉ ሕግን መሠረት በማድረግ ፍትሕ የመስጠት ህገ-መንግስታዊ ግዴታ ያለበት ከመሆኑ አኳያ ሕግን መሠረት አድርጎ በብይን ለሚዘጋው መዝገብ የከሳሽ አለመቅረብ ፋይዳው ምንድን ነው?

 በተለይም ደግሞ ስልጣን ለሌለው ፍ/ቤት ክስ ማቅረብ የይርጋ ጊዜን የሚያቋርጥ ስለመሆኑ የፌ/ሰ/ሰ/ች 36730(ቅጽ 9)  በሰጠው አስገዳጀነት ያለው ውሳኔ መሠረት ከሳሽ ስልጣን ለሌለው ፍ/ቤት አቤቱታውን አስገብቶ ፍ/ቤቱ ስልጣን የለኝም በማለት መዝገቡን ሊዘጋው ሲገባ ከሳሽ ባለመቅረቡ ምክንያት የዘጋው መዝገብ የይርጋ ጊዜን ከማቋረጥ ባለፈ ስልጣን ላለው ፍ/ቤት ክሱ በሚቀርብበት ጊዜ መቼም ክስ ቀርቦበት በፍርድ ያለቀ ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ስለሆነም ከመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ባህሪና ዓላማ እንደዚሁም ፍ/ቤቶች ፍትሕን የመስጠት ዋና ዓለማ አኳያ በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ የቀረበውን መቃወሚያ ለማጥራት በተያዘ ቀነ-ቀጠሮ የፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 69፣70 እና 73 ተፈጻሚ ማድረጉ አግባብ አይደለም፡፡    

ታዲያ ይህ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ግዜ ልናደርግ የሚገባው ምንድን ነው?     

በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ በሚቀርብ ክርክር የተከራካሪዎች

አለመቅረብ ወጤቱ

  ሀ/ የከሳሽ አለመቅረብ  

በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ላይ ፍ/ቤት ቀነ,ቀጠሮ በመያዝ በቀረበው መቃወሚያ ላይ የሚያቀርበው መከራከርያን እንዲሰጥና ነገሩን እንዲያበራራ የሚፈለገው በመርህ ደረጃ ከሳሽ ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው የሚያቀርበው መከራከርያ ያለው እንደሆነ ነው፡፡ እንደዚሁም ፍ/ቤቶች በቀረበላቸው ጉዳይ እውነቱን በማወቅ ፍትሕ ለመስጠት ማንኛውም ማስረጃ በማስቀረብ መመርመር ያለባቸው በመሆኑ በቀረበው መቃወሚያ ላይ ማስረጃ መቅረቡ አስፈላጊ መሆኑ ከታመነ ይህን የማዘዝ ስልጣን አላቸው፡፡ በመሆኑም ከተከሳሽ ለቀረበው መቃወሚያ ከሳሽ የሚያቀርበው መከራከርያ ካለ ፍ/ቤቱ ይህን መከራከርያ ለመስማት በያዘው ቀጠሮ ከሳሽ ሳይቀርብ ቢቀር ፍ/ቤቱ የከሳሽን ይህን መከራከርያ የማቅረብና የማስደመጥ መብቱን በማለፍ በቀጥታ ብይን ለመስጠት መቅጠር ብቻ ነው ያለበት እንጂ ዋናውን ጉዳይ ጨምሮ መዝገቡ እንዳይታይ መዝገቡን በመዝጋት የከሳሽን ፍትሕ የማግኘት ህገ,መንግስታዊ መብቱን ማሳጣት  ሕግ የተቋቋመበት የፍትሕ ስርዓት የተዘረጋበትም ዓላማ አይደለም፡፡

 

ለ/ የተከሳሽ አለመቅረብ

  በተመሳሳይ ሁናቴ ተከሳሽ በመርህ ደረጃ ክርክሩን የሚያቀርብበት ሂደት ስላልሆነ በቀነ-ቀጠሮ የመቅረብና አለመቅረቡ ምንም ዓይነት ውጤትን ሊያስከትል አይገባውም፡፡ ተከሳሽም በይዘቱ ላቀረበው መቃወሚያ የፍሬ,ነገር ከሆነ አለኝ የሚለውን ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ ያለበት ሲሆን በእጁ የሌለና በሌላ ተቋማት የሚገኝ ማስረጃ ከሆነ ደግሞ ፍ/ቤቱ በትእዛዝ እንዲያቀርብለት የመጠየቅ መብቱን ተጠቅሞ በማስረጃ የተደገፈ መቃወሚያ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ፍ/ቤቱ የቀረበውን ወይም ያስቀረበውን ማስረጃ በመመርመር ብይን ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ የቀረበው መቃወሚያ ደግሞ የሕግ ጉዳይ ከሆነ ፍ/ቤቱ በራሱ ሕግን የመተርጎም ስልጣኑን መሠረት በማድረግ ብይን የሚሰጥበት ነው እንጂ ተከሳሽ ጉዳዩ የሚጣራበት ክርክር አይደለም፡፡ ስለሆነም ሕጉ የተከሳሽን ቀርቦ ክርክር ማሰማት ባልደነገገበት ሁኔታ ክርክርህን ልታሰማ በተቀጠረ ቀነ-ቀጠሮ ባለመገኘትህ በክርክሩ ዋና ጉዳይ ገብተህ የመከራከር መብትህ ይታለፋል ተብሎ ትእዛዝ መሰጠቱ ሕግን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ በመሆኑም የተከሳሽ አለመቅረብ ምንም የሕግ ውጤት ሊኖረው አይገባም፡፡ ስለሆነም ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም ፍ/ቤቶች በቀረበው መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ መያዝ ወይም እንዲቀርብ የሚፈልጉት ማስረጃ ካለና በተከሳሽ ከተጠየቀ የዚህን ማስረጃ መቅረብ ለመጠባበቅ ቀነ-ቀጠሮ መያዝ ብቻ ነው ማድረግ ያለባቸው፡፡

ማጠቃለያ

 የፍትሀብሄር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ ዓላማ በክርክሮች የተፋጠነ ፍትሕ ወጪና ጉልበትን በቀነሰ ሁኔታ ለማስገኘት ቢሆንም ሕጉ ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ ሲውል አይታይም፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መካከል በተለይ በቅድመ ምርመራ(first hearing) ጊዜ በሚከናወኑ የፍርድ ሂደቶች ላይ የሚፈጸም ሲሆን ፍ/ቤቶች ከክስ መስማት በፊት መፈጸም የሚገባውን እና በክስ መስማት ጊዜ የሚፈጸመውን ስርዓት በመጨፍለቅ ክርክር ሲመሩና ለጉዳዮች መንዛዛትና መዘግየት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

 በተለይም ደግሞ ይህ የሥነ-ሥርዓት ሕግ የዋና ህጎችን (substantive laws) አፈጻጸም በተመለከተ የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌን የያዘ በመሆኑ ይህ የሥነ-ሥርዓት ሕግ አተረጓጎም ሰዎች ወይም ተከራካሪዎች በዋና ህጎችን ያገኙትን መብት በሚያሳጣበትና በሚያጠብበት ሁናቴ ሊተረጎሙ አይገባም፡፡

 ስለሆነም ተከራካሪዎች(ተከሳሽ) ክርክራቸውን እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ባልተያዘበት ሁናቴ አልቀረቡም በማለት አግባብ ያልሆነ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌን ተፈጻሚ በማድረግ የተከሳሹን በቀረበበት ጉዳይ ራሱን የመከላከል ህገ-መንግስታዊ መብቱን ማሳጣት አግባብ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በቀረበ መቃወሚያ ላይ ብቻ ክርክር ያለው እንደሆነ ለመስማት በተያዘ ቀነ-ቀጠሮ ከሳሹ የሚያቀርበው ክርክር ሳይኖር ወይም ክርክሩ የሕግ ብቻ በመሆኑ ጉዳይን ፍ/ቤቱ በራሱ አይቶ ብይን መስጠት ሲችል ይህን በመተው የከሳሽን ፍትሕ የማግኘት ህገ-መንግስታዊ መብት መግፈፉ አግባብ አይደለም፡፡

   ከመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ ባህሪያት እና ዓላማ አኳያም እንደዚሁም ከፍ/ቤቶች በሕግ ብቻ በመመራት ፍትሕን የመስጠት ለዚህም ተገቢ የሚሉትን ማስረጃ ሁሉ አስቀርቦ የመመርመር ስልጣናቸው አኳያን መጀመሪያ ደረጃን መቃወሚያ ላይ ብቻ በሚደረግ የማጣራት የፍርድ ሂደት በዋናው ጉዳይ ላይ በሚደረግ ክርክር ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ማድረግ አግባብ አይደለም፡፡

“ዕውቀት ብርሀን ነው ያቀራርባል ድንቁርና ግን ጨለማ ነው ያራርቃል ” ሲል ተወዳጁ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የአዲስ አበባ ውሾች በሚለው መጻፍ ስለዕውቀትና ፍሬዎ ውብ አድርጎ ገልጾታል:: ይሁን እንጂ ዕውቀቱ ሳይቸግረን በልማድ ተጠፍንገን የምናነክስባቸው ሁናቴዎች በአደባባይ፡ ፍትሕን ለሽያጭ እውነትንም ለስቅላት ያበቁበት ጊዜዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ለዚህ  ሁላችንም በጋራ ሀላፊነት በመውሰድ ይህን ለመቅረፍ ጥቆማ በመስጠትና መፍትሔ በመጠቆም የተሻለ የፍትሕ ስርዓት ለመፍጠር የበኩላችንን እገዛ እንድናደርግ እየጠቆምኩ  በዚህ ጹሁፍ ሊታረም ይገባል የምለውን በፍትሐብሔር የፍርድ ሥነ-ሥርዓት ሂደት መካከል አንዱን ብቻ ከሕጉ ጋር እያነጻጸርኩ አቅርቤያለው፡፡    

  በዚህም መሠረት በቀረበው ርዕስ ላይ ያላችሁን ዕውቀት በአስተያየት እና ሙግት በማቅረብ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር በባለሙያዎች ዘንድ የጋራ መግባባትና መቀራረብ እንዲኖር እንድናደርግ እየጋበዝኩ ይህን ጽሁፍ አጠናቅቃለሁ፡