Font size: +
5 minutes reading time (1076 words)

ሕዝባዊ ፍርድ፣ ፍርድ ቤቶች እና ገላጋይ ዳኞች

የፍርድ ቤቶችን ችግር ለመፍታት፣ ጫናቸዉን ለመቀነስ፣ የሚያቀርቡትን የዳኝነት አገልግሎት ጥራት ለመጨመር ከሚቀርቡት የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል አማራጭ የሙግት መፍቻ ስልቶችን (ለምሳሌ ግልግል ዳኝነት) ማበረታት ነዉ። አማራጭ ስልቶችን ማበረታታት ተገቢ ነዉ፣ ጠቃሚ እስከሆነ ድረስ።  ነገር ግን ፍርድ ቤቶች በችግሮች በተተበተቡበት ሁኔታ፣ ምንም እንኳን ሕጉ ለአማራጭ ስልቶች እውቅና እና ድጋፍ ቢሰጥም፣ የፍድ ቤቶችን ችግር በመፍታት ወይም አለመግባባትን በመቀነስና በመፍታት ረገድ ግን የሚፈይደው ነገር ጥቂት ነው፡፡

የፍርድ ቤቶች መጠናከር ነዉ ቅድሚያ ሊስጠዉ የሚገባዉ። ፍርድ ቤቶች ሲጠናከሩ (ለምሳሌ በፍጥነት ዉሳኔ ሲሰጡ፣ ዉሳኔዎቻቸዉ ግልጽ፣ ተደራሽ፣ ተገማች ሲሆኑ፤ ሙስና ሲቀንስ) ብቻ ነዉ፤ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሌሎች አማራጭ የግጭት መፍቻ ስልቶችን ሊጠቀሙ የሚችሉት። ፍርድ ቤት ቢሄዱ፤ መቼ፣ እና ምን አይነት ዉሳኔ፣ በምን ዋጋ ማግኘት እንደሚችሉ መገመት ሲችሉ ብቻ ነዉ አማራጭ መንገዶችን ለመጠቀም ሊወስኑ የሚችሉት።

ወደ ፍርድ ቤት ነዉ የሚሄዱት። ፍርድ ቤቶችራሳቸዉ በችግሮች በተተበተቡበት ሁኔታ፣ ምንም እንኳን አንደኛዉ ወገን ዉጭ በገላጋይ ዳኞች መዳኘት ቢፈልገም፣ ሌላኛው በተለይ ደግሞ የፍርድ ቤቶችን ችግር የሚፈልገው ላይስማማ ይችላል፡፡ በዚህም የበለጠ ፍርድ ቤት እንዲጨናነቅ ያደርገል፡፡

ለምሳሌ ፍርድ ቤቶች አንድን ጉዳይ መርምረዉ ዉሳኔ ፍርድ ለመስጠት የሚወስድባቸዉ ጊዜ በአማካኝ ከአምስት ዓመት ይበልጣል እንበል፡፡ በሁለት ወገኖች (በመንግሥት እና በከበደ) መካከል ያለን አለመግባባት እንውሰድ፡፡ ከበደ ከመንግሥት የሚጠይቀው ክፍያ አለ፡፡ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ ቢቀርብ፤ መንግሥት የተጠየቀውን ክፍያ እንዲከፍል እንደሚፈረድበት መገመት ይቻላል እንበል፡፡ ነገር ግን ይህን ፍርድ ለማግኘት በአማካኝ አምስት አመት ይወስዳል። በዚህ ሁኔታ ከበደ ጉዳዩን ወደ ግልግል ዳኞች ለመውሰድ ይፈልግ ይሆናል፡፡ ከፍርድ ቤቱ ሊያገኝ የሚችለውን ፍርድ እና የገንዘብ መጠን ወይም ያነሰ ወይም ከፍ ያለ ዳኞች ሊያገኘው ይችላል፡፡

በተጨማሪም ገላጋይ ዳኞች በጉዳዩ ላይ ዉሳኔ ለመስጠት በአማካኝ ሦስት ወር ይወስድባቸዋል እንበል፡፡

የግልግል ዳኝነት እና መሰል ስልቶች ተመራጭ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች መካካል ፍጥነታቸው ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ተሟጋቾች ወጪያቸውን ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡ አሰቀድሞ በከበደ እና በመንግሥት መካከል በሕግ ፊት ተቀባይነት ያለው የግልግል ስምምነት ከሌለ፤ እነዚህ ወገኖች በግልግል ሊዳኙ የሚችሉት ሁለቱም ሲስማሙ ነው፡፡ አሁን መንግሥት ሁለት  ምርጫ አለው፡፡ በሦስት ወር ውስጥ የተጠየቀውን ብር (ወይም ያነሰ ወይም የበዛ) በግልግል ቢከፍል ወይስ በአምስት አመት ወይም ከዚያ በላይ እዳውን በተመለከተ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥበት መጠበቅ?

ፍርድ ቤቶች በጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ በግልጽነት፣ በነጻነት፣ ተደራሽነት፣ ተገማችነት እና በመሳሰሉት ችግር ሲኖርባቸዉ፣ ዜጎች ከግጭት በሁዋላ ግጭታቸዉን ከፍርድ ቤት ዉጭ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመፍታት እድላቸዉን ይቀንሰዋል። በሌላ መልኩ ፍርድ ቤቶች ፈጣን፣ ግልጽ፣ ተደራሽ፣ ተገማች፣ ከአድልዎ ንጹ ፍርድ በሚሰጡበት ሁኔታ፣ አንደኛ በዜጎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን (በተለይ የሕግ ጭብጦችን አስመልክቶ) ይቀንሳሉ። በጥንቃቄ በመደራደር፣ በማቀድ፣ እና ሰነዶችን በጥራት በማዘጋጀት። ሁለተኛ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም፣ በስምምነት እና በሌሎች ስልቶች የመፍታት እድላቸዉ ይጨምራል። ድርድሮች/ስምምነቶች እንዲፈርሱ ከሚያደርጋቸዉ ምክንያቶች መካከል፣ የመረጃ ልዩነት ነዉ። ፍርድ ቤቶች ጥራት ያለዉ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት በሚችሉበት ሁኔታ፣ ፍርድ ቤቱ ሊያስተላልፈዉ የሚችለዉ ዉሳኔ ለድርድሩ መነሻ ይሆናል። መንግስት እና ከበደ የአንድ መኪና ሽያጭን በተመለከት እየተደራደሩ ናቸዉ እንበል። የመኪናዉ ባለቤት የሆነዉ ከበደ መኪናዉን የገዛበት ዋጋን፣ ምን ያህል እንደነዳዉ፣ በአጠቃቀም ምን ያህል ዋጋዉ እንደጨመረ ወይም እንደቀነሰ፣ ተመሳሳይ አይነት መኪኖች ወይም አማራጭ መኪኖች በገበያ በምን ያህል እንደሚሸጡ፣ ባልታወቀበት ሁኔታ ድርድሩ ወደ ሽያጭ የመቀየሩ እድል ዝቅተኛ ነዉ። ነገር ግን አነዚህን ጉዳዮች አስመልክቶ ምንም እንኩዋን ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም መረጃዉ ካለ፣ ያ መረጃ ለድርድር መነሻ ይሆናል። ገላጋይ ዳኞች በፍርድ ቤት ጥላ ስር ነዉ የሚሰሩት ስንል፣ ይህን ለማለት ነዉ።

ስለዚህ ፍርድ ቤቶች ሲበላሹ፤ ዜጎች ወደ ገላጋይ ዳኞች ይሄዳሉ ማለት አይደለም። በሌላ አነጋገር የፍርድ ቤቶችን ጥራት ለመጨመር የሚወሰድ አንድ እርምጃ፤ ራሱን እያራባ በጊዜ ሂደት የፍርድ ቤት ጥራት ያለማቁዋረጥ እንዲጨምር ያደርጋል፤ ዛሬ የታየዉ የጥራት መሻሻል ትናንት ከታየዉ በአይነትም በመጠንም ይበልጣል፣ ነገ የሚጠበቀዉ የጥራት መሻሻል ዛሬ ከታየዉ በተመሳሳይ መልኩ ይበልጣል። ምክንያቱም ግጭትና በማስቀረትና ስምምነትን በማበረታታት በየጊዜዉ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚሄዱትን ጉዳዮች መጠን እየቀነሰ እንዲሄድ በማድረግ። ገላጋይ ዳኞች የዚህ ሂደት የሃይል ምንጭ ሳይሆኑ፤ ሃይል ጨማሪ አጋዦች ይሆናሉ። በተቃራኒዉ ፍርድ ቤቶች በአንድ ደረጃ መበላሸት፣ በጥንቃቄና በስምምነት ልናስቀራቸዉ እንችል የነበሩ ጉድዮች ወደ ፍርድ ቤት በመምጣትና ፍርድ ቤቶቻችንን በማጨናነቅ የጥራት ችግሩን የበለጠ ያባብሰዋል።

 

የቆሻሻ ነገር ነዉ። ንጹህ ቦታ ላይ ቆሻሻ ለመጣል/ለማራገፍ ሰዎች ይፈራሉ፤ ይጠነቀቃሉ። ነገር ግን አንዴ ከቆሸሸ፣ ሁሉም አየመጣ ስለሚጥል፣ የቆሻሻዉ ችግር አየባሰ ይሄዳል። በየቀኑ የሚጨመረዉ የቆሻሻ መጠን እያደገ ይሄዳል። ስለዚህ በጠቅላላዉ አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች የፍርድ ቤትን ጫና ሊቀንሱ የሚችሉት፤ ፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ባለዉ የጥራት ደረጃ ላይ ሲገኙ ብቻ ነዉ። በዚህ ሁኔታ አማራጭ መንገዶች ፍርድ ቤቶች የበለጠ ዉጤታማ አየሆኑ እንዲሄዱ ያደርጋል። አንዴ ፍርድ ቤቶች ከቆሸሹ በሁዋላ ግን፤ ቆሻሻዉ ይበዛል እንጂ፤ በሕግ ደረጃ እዉቅና የተሰጣቸዉ አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶች ፋይዳ እጅግ ጥቂት ነዉ።

 

የፍርድ ቤቶች ተልእኮ ሙግቶችን መርምሮ ዉሳኔ/ፍርድ በመስጠት፣ አለመግባባትን በቀጥታ መፍታት አይደለም። አለመግባባት ተፈታ የሚባለዉ ሁለቱ ወገኖች ከአለመግባባት ወደ መግባባት ሲመጡ ነዉ። ነገር ግን ፍርዱ በራሱ፤ ቅድመ ፍርድ ያልተግባቡ ሰዎችን እንዲግባቡ ማድረግ አይችልም። እንደዉም ድህረ ፍርድ፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለዉ ጥል፤ አለመግባባት፤ ጥላቻ፤ ሊብስበት፤ ግንኙነታቸዉ የበለጠ ሊሻክር ወይም ሊበጠስ ይችላል። ስለዚህ የፍርድ ቤቶች ተልእኮ ዉሳኔ/ፍርድ መስጠት ነዉ። ይህን በጥራት ሲያከናዉኑ ግን፤ ሕጉን የበለጠ ግልጽ በማድረግና ሌሎች ሰዎች አለመግባባትን ለማስወገድ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፤ አለመግባባቱ በጥንቃቄ ጉድለት ወይም በሌላ ማስቀረት ባልተቻለበት ሁኔታ ደግሞ፤ ወገኖቹ በስምምነት አለመግባባታቸዉን እንዲፈቱ ያግዛል። ስለዚህ የፍርድ ቤት ዉሳኔ አለመግባባትን የሚፈታዉ በቀጥታ አይደለም።

ምንም እንኩዋን በአንድ ጉዳይ ላይ የሚሙዋገቱት ሁለት የተለዩ ግለሰቦች ቢሆኑም፣ ምንም እንኩዋን ጉዳዩ የፍትሃብሄር ቢሆንም፣ የፍርዱ ተጠቃሚዎች ግን በአጠቃላይ ሕዝቡ ነዉ። የፍርድ ቤት ዉሳኔዎች/ፍርዶች የሕዝባዊ ምርት እና አገልግሎት ጸባይ አላቸዉ። ጉዳዩ ስለሁለቱ ተሙዋጋች ወገኖች ብቻ አይደለም። ይህን ሃሳብ ከተቀበልን፣ የሃሳቡን አንድምታዎች እንመልከት።

የመንግስት ጣልቃገብነት በሌለበት ሁኔታ ሕዝባዊ ባህሪ ያላቸዉ ምርቶችና አገልግሎቶች በሚፈለገዉ መጠን አይቀርቡም፤ በጠቅላላዉ። ለምሳሌ መንገድ። ስለዚህ መንግስት በተለያየ መንገድ ተፈላጊ ሕዝባዊ ምርቶችና አገልግሎቶች በተፈላጊ መጠን መቅረባቸዉን ለማረጋገጥ ሊሰራ ይገባዋል። ከዚህ አንጻር፤ በወንጀል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በፍትሃብሄርም ቢሆን ዜጎች የሕግ አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ፣ አቅም የሌላቸዉ ደግሞ በድጎማ እንዲያገኙ መስራት ይኖርበታል። ሌላዉ የተደራሽነት እና የፍትህ ዋጋ/ወጪን ይመለከታል። ብዙ ጊዜ እነዚህ ጉዳዮች የፍትሃዊነት ጉዳይ ተደርገዉ ይወሰዳሉ። ግን ጥቅማቸዉ ከዛም በላይ ነዉ።

 

የፍርድ ቤት ዉሳኔዎች ሕዝባዊ ባህሪ እንዳላቸዉ ከዚህ በላይ ባለው ክፍል አይተናል። ነገር ግን አማራጭ የግጭት መፍቻ ስልቶች (ለምሳሌ ገላጋይ ዳኞች) ይህን ባህሪ በተመሳሳይ ጥራትና መጠን አያሙዋሉም። የግልግል ዉሳኔዎች ሚስጥራዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ወይም ደግሞ ምንም እንኩዋን ግልጽ ቢሆኑም፣ ገላጋይ ዳኞች ተገማች የመሆን ፍላጎት የላቸዉም። በአንድ ጉዳይ ላይ እንዴት እንደሚወስን ተገማች የሆነን ገላጋይ ዳኞ ሁለቱም ወገኖች በስምምነት ሊመርጡት አይችሉም። ይህ ማለት፣ ተገማች በመሆን፣ ገላጋይ ዳኛዉ የመመረጥ እድሉን ይቀንሳል።

ይህ ማለት ግን የግልግል ዉሳኔዎች፤ ምንም አይነት ሕዝባዊ ባህሪ የላቸዉም ማለት አይደለም። አንድ አለመግባባት ከፍርድ ቤት ይልቅ ወደ ግልግል ሄደ ማለት፣ ፍርድ ቤቶች በአንድ ጉዳይ ጫናቸዉ ቀነሰ ማለት ነዉ፤ በዚህም ለሌሎች የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት እንዲያሻሽሉ እድል ይሰጣቸዋል። አንድ ጥራት ያለዉ የፍርድ ቤት ዉሳኔ፣ ብዙ አለመግባባቶችን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንዲፈቱ ወይም አንዳይፈጠሩ ያደርጋል። ነገር ግን አንድ የግልግል ዳኝነት ውሳኔ የፍርድ ቤትን ጫና የሚቀንሰዉ በዛዉ ልክ ብቻ ነዉ። ይህ መጀመሪያ የተጠቀሰዉን ነጥብ የሚያጠናክር ነዉ። ገላጋይ ዳኞች ፍርድ ቤቶችን በእኩል ሊተኩ አይችሉም።

የፍርድ ቤት ዉሳኔዎች ህዝባዊ ባህሪ አላቸዉ። ነገር ግን ይህ የማይቀር ባህሪ አይደለም። ህዝባዊ ባህሪያቸዉን ለማጠናከር መወሰድ ያለባቸዉ እርምጃዎች አሉ። የዳኝነት አገልግሎት መስጠት ብቻዉን ሕዝባዊ አይደለም። አገልግሎቱ ተደራሽ፣ ርካሽ፤ ፈጣን፣ ግልጽ፣ ከአድልዎ ንጹ፤ ተገማች፣ እና የመሳሰሉት ባህሪዎች ሊኖሩት ይገባል። ሲሚንቶ ፈላጊ መገናኛ፣ የጽህፈት መሳሪያዎች ፈላጊ ካዛንቺስ፣ የባህል ልብስ ፈላጊ ሽሮ ሜዳ እንደሚሄደዉ፣ ፍርድ ቤቶች ዳኛ የፈለገ ሰዉ የሚሄድባቸዉ የታወቀ/ልዩ ቦታዎች ሳይሆኑ፣ በእርግጥም ፍርድ ቤቶች መሆናቸዉን ማረጋገጥ አለባቸዉ።

የዳኝነት አገልግሎት ሕዝባዊ ባህሪ፣ በመንግስት ሚና እና በሌሎች ጉዳዮች ያለዉን አንድምታዎች ለአንባቢ ልተወዉ።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በሕግ አምላክ!
Book Review-Unholy Trinity: The IMF, World Bank an...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 12 October 2024