Font size: +
15 minutes reading time (3004 words)

የተሻሻለው የአማራ ክልል የገጠር መሬት አዋጅ እና አከራካሪው የይርጋ ድንጋጌ

የአማራ ክልል የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 133/98 የተካው የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 ቀደም ሲል በሕግ ደረጃ ሽፋን ያላገኙ አዲስ ነገሮችን ይዞ እንደወጣ ይታወቃል፡፡ አዲስ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ በገጠር መሬት ላይ በሚነሱ ክርክሮች ላይ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚ ሊሆን እንደማይችል ያስቀመጠው ነገር ነው፡፡ ይህ የይርጋ ድንጋጌ በሕጉ የተካተተ አዲስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ገና ከጅምሩ አከራካሪ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አከራካሪነቱም በባለሙያዎች መካከል ሁለት ጫፍ የያዙ አቋም እንዲኖር ከማድረግ አልፎ አዲስ የክርክር ምክንያትም እየሆነ ነው፡፡ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮም የገጠር መሬትን ተከትሎ የሚቀርቡ ክሶች ላይ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚነት የለውም በሚል  ብዙ ዶሴዎች ከተዳፈኑበት አቧራቸውን እያራገፉ በክስ መልክ  እየቀረቡ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም በባለሙያዎች መካከል በይርጋው ተፈፃሚነት ላይ  ባለ ሁለት ጫፍ የያዘ አቋም ምክንያት ከወዲሁ ተገማችነታቸውና ወጥነታቸው አደጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ ስለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ  የሚነሱ አቋሞችን እና ምክንያቶችን በማየት ሃሳቡን መመልከቱ አስፈላጊ እና ትኩረት የሚያስፈልገው ነው፡፡ የፁሁፉ ዋና ትኩረትም በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ላይ የተቀመጠጠው የይርጋ ድንጋጌ ወሰን አለው ወይስ የለውም የሚል ይሆናል፡፡

በቅድሚያ የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 55 ስለይርጋ ያስቀመጠውን የድንጋጌውን ሙሉ ይዘት መመልከት ተገቢ ነው፡፡

አንቀፅ 55 ስለይርጋ

የገጠር መሬትን በወረራ ወይም በሌላ በማናቸውም ህገ ወጥ መንገድ ይዞ በመገልገል ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው መሬቱን እንዲለቅ በማንኛውም ሌላ ሰው ወይም ሥልጣን ባለው የመንግሥት አስተዳደር አካል ሲጠየቅ ወይም በመደበኛ ፍርድ ቤት ሲከሰስ የይርጋ ጊዜ ገደብን በሥነ ስርዓት መቃወሚያነት ሊያነሳ አይችልም፡፡

የድንጋጌው ይዘት በተጠቀሰው መልኩ የቀረበ ሲሆን አንደኛው አቋም ይህ የይርጋ ድንጋጌ  በማንኛውም ከገጠር መሬት ላይ የሚነሳ ክርክርን የይርጋ መቃወሚያ እንዳይቀርበበት እና ይርጋን መቃወሚያ ማድረግ እንደማይቻል ተደርጎ እንደተደነገገ የሚገልፅ ነው፡፡ እንደዚህ አቋም አራማጆች ሕጉ በግልፅ የገጠር መሬትን በወረራ ወይም በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ የያዘ ሰው የይርጋ መቃወሚያ ሊያነሳ እንደማይችል ስለሚናገር በመሬት ክርክር ይርጋ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በማለት ይገልፃሉ፡፡  በድንጋጌው “በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ መያዝ” የሚለው ሃረግ  የሚያመለክተው የገጠር መሬት ሊያዝ ከሚችልባቸው መንገዶች ማለትም (በድልድል፣ በስጦታ፣ በውርስ፣ በኪራይ) ውጪ የገጠር መሬትን ይዞ መገኘት እንደሆነ ተደርጎ የተቀመጠ ነው፡፡ በተሻሻለው አዋጅ አንቀፅ 2(39) በተቀመጠው የትርጓሜ ክፍል “ህገ ወጥ ይዞታ” ማለት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተያዘና አግባብ ባለው አካል እውቅና ያልተሰጠው ማናቸውም የገጠር መሬት ይዞታ ስለመሆኑ ይናገራል፡፡  ይሕ የትርጓሜ ክፍል በሕጉ መሬት ከሚገኝባቸው መንገዶች ወይም ሥርዓት ውጪ የሚያዙና አግባብ ባለው አካል እውቅና ያልተሰጠው የገጠር መሬት እንደ ሕገ ወጥ ይዞታ የሚቆጠር ስለሆነ የይርጋው ድንጋጌም ሕገ ወጥ ይዞታ ከሚለው ትርጉም ጋር ተናዝቦ ሊታይ የሚገባ ነው፡፡ በይርጋ ድንጋጌውም የተቀመጠው በማናቸውም መንገድ በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ የሚለው በሕግ ከተቀመጠው መሬት ከሚያዝበት ውጪ መያዝ ስለሆነ ከሕግ ውጪ የገጠር መሬትን ይዞ ይርጋን መከራከሪያ ማድረግ አይቻልም፡፡ በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ የሚለውም ሁሉንም ከሕግ ውጪ የሚያዙበትን መንገዶች ክፍተት እንዳኖራቸው ዝግ አድርጎ ያስቀመጠ ስለሆነ የይርጋ መቃወሚያ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡ በተጨማሪም የመሬት ክርክር ይርጋ ሊያግደው እንደማይገባ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሳይቀር ውሳኔ የሰጠ ስለሆነ በመሬት ክርክር በሁሉም ጉዳዮች ይርጋ ተፈፃሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡

ሁለተኛው አቋም ደግሞ በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ላይ ይርጋ ተፈፃሚነት የማይኖርበትን ሁኔታ ያስቀመጠ ቢሆንም በሁሉም የገጠር መሬት ክርክሮች ዓይነት ላይ ይርጋ ተፈፃሚ አይሆንም ወደ ሚል መደምደሚያ መድረስ አይቻልም የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱን ሲገልፁም የይርጋ መቃወሚያ ድንጋጌው ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በማለት ያስቀመጠው የወል መሬት በወረራ ሲያዝና በመሬት ላይ በሕግ የተቀመጡ ክልከላዎችን መሸጥና መለወጥን መሰረት አድርጎ ተይዞ ሲገኝ እንጅ ለሁሉም የክርክር ዓይነቶች አይደለም፡፡ በአዋጁ የተቀመጠው የይርጋ ድንጋጌ የውርስ፣ ስጦታ እና ኪራይ ክርክሮችን የሚመለከት አይደለም በማለት ምክንያታቸውን ያቀርባሉ፡፡

የዚህ ፁሁፍ አዘጋጅም ሁለተኛውን አቋም የሚደግፍ በመሆኑ አከራካሪውን ጉዳይ ከሕጉ አቀራረጽ፣ ዓላማ እና ሕጉን ለማውጣት ገፊ ከሆኑ ምክንያች እንዲሁም ከሌሎች ሁኔታዎች አንፃር መመልከት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናል፡፡

በቅድሚያ በአዋጁ የተቀመጠው የይርጋ ድንጋጌ አከራካሪ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ድንጋጌው ሲረቀቅ ግልፅ እና አሻሚ ያልሆኑ ቃላቶችን መጠቀም እያለበት አለመጠቀሙ እንዲሁም በትርጓሜ ክፍሉ ግልፅ የሆነ መግለጫ አለማስቀመጡ ዋና ለችግሩ መንስኤ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም በአዋጁ በተመሳሳይ ጉዳይ ተፈፃሚ ሊሆን የሚችል ድንጋጌ ማስቀመጡና የድንጋጌዎቹ አወቃቀር በሥርዓትና በግልፅ አለመቀመጣቸው ሌላው ጉዳዩን ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከድንጋጌዎቹ አወቃቀር ብንነሳ   በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ተብለው ከተቀመጡት ዝርዝሮች ስር ስለፍትሐብሔር ሕግ ተፈፃሚነት የሚናገረው  አንቀፅ 54 እና ስለይርጋ የሚገልፀው አንቀፅ 55 ተገቢውን መንገድ ተከትለው የተዋቀሩ አይመስሉም፡፡ አንቀጽ 54 በአዋጁ አንቀፅ 15፣ 16 እና 17 ስር ያልተሸፈኑ የገጠር መሬት ኪራይ፣ ስጦታ፣ ውርስና ሌሎች የፍትሐ ብሔር ነክ ጉዳዮችን በተመለከተ እንደነገሩ ሁኔታ አግባነት የፍትሐ ብሔር ሕግ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ይናገራል፡፡ እንደዚህ ድንጋጌ የመሬት ኪራይ፣ ስጦታ፣ ውርስ ተከትለው የሚነሱ ክርክሮችን በተመለከተ የሚነሳ ይርጋ መቃወሚያ በእያንዳንዱ ድንጋጌ ያልተካተተ በመሆኑ ይርጋን በተመለከተ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ተፈፃሚ ሊሆን እንደሚችል መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ሆኖም ግን የአዋጁ አንቀፅ 55 ስለይርጋ የተቀመጠው  በአንቀፅ 54 ለተቀመጠው ድንጋጌ እንደ ልዩ ሁኔታ (exception) ሳይሆን ራሱን ችሎ እንደ መርሕ ነው፡፡ አንቀፅ 54 የፍትሐ ብሔር ሕጉ በአዋጁ ስለውርስ፣ ስጦታና ኪራይ በተቀመጡ ድንጋጌዎች ያልተሸፈኑ ጉዳዮች(ይርጋን ይጨምራል) የሚነሱ ክርክሮች ላይ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ተፈፃሚ እንደሚሆን ሲገልፅ በልዩ ሁኔታ ሳይሆን ራሱን ችሎ የጠቀመጠው አንቀጽ 55 ደግሞ ስለይርጋ ራሱን ችሎ ተቀምጧል፡፡ አንቀፅ 55 አወቃቀሩ ሆነ ይዘቱ እንደ ልዩ ሁኔታ (exception) ባልተቀመጠበት ሁኔታ ለሁሉም ዓይነት ክርክሮች ተፈፃሚ ይደረግ ከተባለ ከአንቀጽ 54 ጋር በግልፅ የሚጋጭ ይመስላል፡፡ አንቀፅ 54 የኪራይ፣ የስጦታ እና የውርስ ድንጋጌዎችን በግልፅ አንቀፅ 15፣ 16፣ 17 በማለት ገልፆና በተገለፁት ድንጋጌዎች ያልተሸፈኑ ጉዳዮች(ይርጋም በድንጋጌዎቹ አልተገለፀም) የፍትሐ ብሔር ሕግ ተፈፃሚ እንደሚሆን በግልጽ ያስቀመጠ ስለሆነ ከአንቀፅ 55 ጋር በጥምረት ሲታይ በገጠር መሬት ኪራይ፣ ስጦታ እና ውርስ ጉዳዮችም በአንቀፅ 55 የተቀመጠው የይርጋ ድንጋጌ ተፈፃሚ ይሆናል አይሆንም የሚል ክርክር እንዲነሳ ያደርገዋል፡፡ በዚህም መሰረት የአንቀጽ 55 ይርጋ ድንጋጌ ተፈፃሚነት ወሰን (scope) እስከምን ድረስ ነው ሕግ አውጭውስ በመሬት ላይ የሚነሱ ክርክሮችን አጠቃላይ ይርጋ መቃወሚያ እንዳይቀርብባቸው ፍላጎት ነበረው ወይ የሚሉት ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጉዳይ ይሆናል፡፡

በቅድሚያ ጉዳዩን ከይርጋ ጽንሰ ሃሳብ መነሻ አድርጎ ማየቱ ነገሩን ቀለል ያደርገዋል፡፡   በይርጋ ፅንሰ ሃሳብ ሁለት ዓይነት ይርጋ ደንቦች ያሉ ሲሆን አንደኛው ያልነበረ መብትን የሚያስገኝ (acquisitive prescription) ሁለተኛው ደግሞ ግዴታ አስቀሪ ይርጋ ደንብ (liberative prescription) በመባል ይታወቃሉ፡፡ ያልነበርን መብት የሚያስገኝ ይርጋ ደንብ ጠያቂ ያልነበረውን ንብረት በሕግ በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ የእኔ ባይ ካልጠየቀው በንብረቱ ላይ የባለቤትነት መብት የሚመሰርለት ነው፡፡ ግዴታ አስቀሪ ይርጋ ደንብ ደግሞ ባለመብቱ መብት አለኝ የሚለው ነገርን በተመለከተ በሕግ በተቀመጠ ጊዜ ውስጥ ካልጠየቀ መብቱን የሚያጣበት የይርጋ ሥርዓት ነው፡፡ የገጠር መሬት ላይም የመሬቱ ባለቤት የመንግስትና የሕዝብ እንደመሆኑ እና የገጠር መሬትም ሕጋዊ ባለይዞታ ለመሆን የገጠር መሬት የሚያዝባቸውን መንገድ የግድ መጠበቅ ያለባቸው ስለሆነ በገጠር መሬት ላይ ተፈፃሚ የሚሆነው ደንብ መብት የሚመሰርተው   ሳይሆን የጠያቂውን መብት የሚያስቀረው የይርጋ ደንብ ነው፡፡ ግዴታ አስቀሪ ይርጋ ደንብ (liberative prescription) ዋና ዓላማው መሬቱን የያዘውን ሰው ይዞታ መብት መመስረት ሳይሆን ዳተኛ የሆነው ባለመብት ቆይቶ የሚያቀርበው ይገባኛል ክስ ከቅን ልቦና ጋር ተቃራኒ በመሆኑ ያለውን መብት ማስቀረት ነው፡፡ በዚህም መሰረት በገጠር መሬት ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ሊታይ የሚገባው መብቱን በጊዜው መጠየቅ እየቻለ ያልጠቀን ባለይዞታ መብት ማስቀረት  እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ መሬቱን ይዞ የቆየው ሰው ክስ ሲቀርበብት ባለመብቱ መብቱ በይርጋ ቀሪ ቢሆንም መሬቱን ይዞ ለቆየው ሰው መብት ሊመሰርትለት ስለማይችል በመሬቱ ላይ የባለቤትነት መብት ያለው አካል መሬቱን ከያዘው ሰው አስለቅቆ  ወደ መሬት ባንክ ማስገባት እንደሚችል መረዳት ይቻላል፡፡

በተጨማሪም ሕግ አውጭው በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ 252/2009 አንቀፅ 21(1)(ሀ)(መ) አንድ የመሬት ባለይዞታ መሬቱን ለአምስት ዓመት ጥሎ ከአካባቢው ከጠፋና ለሶስት ዓመት ፆሙን ካሳደረ ይዞታ መብቱን ያጣል በማለት ጥብቅ ሁኔታዎችን ያስቀምጣል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዳተኛነት መሬትን ጦም ማሳደር እና ጥሎ መጥፋት ይዞታ መብትን ከማስነጠቅ አልፎ ሕግ አውጭው መብታቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ ግለሰቦችን ለማበረታታት ፍላጎት እንደሌለው የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህም በገጠር መሬት ላይ ተፈፃሚ የሚሆነው የይርጋ በጊዜው መጠየቅ እየቻለ ያልጠየቀን ዳተኛ ባለመብት መብት የሚያስቀር በመሆኑ ዳተኛ ባለመብትን አይደለም ይርጋን በሚያስቆጥር ረጅም ጊዜ መሬቱን ጦሙን በማሳደሩና ለአጭር ጊዜ ከአካባቢው መልቀቁ ይዞታውን የሚያጣበት ሁኔታ በአዋጁ በግልፅ ስለተቀመጠ ሕግ አውጭው ዳተኛን ባለመብት በሚጠብቅና በሚያበረታታ መልኩ ሁሉንም የክርክር ዓይነቶች ከይርጋ ነፃ የሚደርግበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በሌላ አገላለፅ መሬቱን ለአምስት ዓመት ጥሎ የጠፋ እና ሶስት ዓመት ጦሙን ያሳደረ ሰው የይዞታ መብቱን እያጣ ለረጅም ጊዜ ከአስር ዓመት በላይ መብቱን ያልጠየቀን ሰው ይዞታ መብቱ እንዲከበርለት የይርጋ መቃወሚያን ተፈፃሚ አለማድረግ ፍትሐዊ ሆነ ምክንያታዊ አይሆንም፡፡ በአንድ አዋጅ ስር የሚቀመጡ ሕጎች ዓላማቸው አንድ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ድንጋጌዎች እርስ በእርስ የሚጣረሱ ዓላማዎችን ይዘው ሊወጡ አይችሉም፡፡ በአንድ አዋጅ ስር አንዱ የሕግ ድንጋጌ ዳተኛ ባለመብት መሬቱን ለአጭር ጊዜ ባለመጠቀሙ ይዞታ መብቱን እንዲያጣ ሲያስቀምጥ በሌላኛው ድንጋጌ  ደግሞ ረጅም ጊዜ መብቱን ሳይጠይቅ የቆዬ የባሰን ዳተኛ መብቱን መጠየቅ እንደሚችል ልቅ የሆነ ሁኔታ  የሚያስቀምጥ ከሆነ ሕጉ የጠራ ዓላማ እንዳይኖረው የሚየደርገው ነው፡፡ ሕግ አውጭውም እነዚህን የሚጋጩ ሁለት ዓላማዎች ይዞ ሕግ ያወጣል ተብሎ የሚገመት ስላልሆነ በትክክል በአዋጁ የተቀመጠው የይርጋ ድንጋጌ ተፈፃሚነት ወሰን እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡

በአዋጁ የተቀመጠው የይርጋ ድንጋጌ ተፈፃሚነት ወሰን!

በድንጋጌው የገጠር መሬትን  “በወረራ” ወይም “በሌላ በማናቸውም ሕገ ወጥ መንገድ” መያዝ ይርጋን ተፈጻሚ  እንዳይሆን ለማድረግ የተቀመጡ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ መሬትን በወረራና በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ይርጋን ተፈፃሚ እንደማያደርጉ በድንጋጌው በግልፅ የተቀመጠ ቢሆንም “በወረራ መያዝ፣ በሕገ ወጥ መያዝ” ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ የሆነ ትርጉም በሕጉ አልተቀመጠም፡፡ በአዋጁ የትርጓሜ ክፍል የተቀመጠው የገጠር መሬትን በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ምን እንደሆነ በግልፅ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡  በሕጉ ግልፅ ነገር ወይም ትርጓሜ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ሕጉን ተፈፃሚ ከማድረጋቸው በፊት ሕጉ የወጣበትን ዓለማ ከሕግ አውጭው ሃሳብ ወይም ሕጉ ሲወጣ መነሻ የተደረጉ የሕጉ ዓላማ ምን እንደሆነ መመልከት ይኖርባቸዋል፡፡

የአዋጁ ደንጋጌ  “የገጠር መሬትን በወረራ መያዝ” በማለት ሲያስቀምጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከወል መሬት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ የገጠር መሬትን በወረራ መያዝ ከወል መሬት ጋር ተያይዞ እንደሚነሳና የሕግ አውጭው ዓላማም ወረራን ከወል መሬት ጋር በማገናኘት እንዳስቀመጠው ከተሻሻለው የአዋጁ የዓላማ መግለጫ (preamble) መረዳት ይቻላል፡፡ በአዋጁ መግቢያ የዓላማ መግለጫ አምስተኛ አንቀፅ ፁሁፍ ላይ “ህገወጥ የወል መሬት ወረራን መከላከል” የቀደመውን አዋጅ ለማሻሻል አንዱ ገፊ ምክንያት እንደነበር ተቀምጧል፡፡ ከዚህ መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው ሕግ አውጩ የገጠር መሬት ወረራ እያለ የሚገልፀው ከወል መሬት ጋር በተገናኘ እንደሆነ ግንዛቤ የሚያስወስድ ነው፡፡ 

በተጨማሪም የገጠር መሬትን “በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ” የሚለው የአዋጁ ድንጋጌ በግልፅ በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ ምን እንደሆነ ባያስቀምጥም ሕግ አውጭው ሁሉንም ክርክሮች ከይርጋ በማጽዳት ዳተኛ ባለመብትን የማበረታት ዓላማ አለው ተብሎ ስለማይገመት ከሌሎች ሁኔታዎች አንፃርም ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 54 በግልፅ አንቀጽ 15 ስለኪራይ፣ አንቀፅ 16 ስለስጦታ፣ አንቀፅ 17 ስለውርስ በተቀመጡ ድንጋጌዎችን ጠቅሶ በድንጋጌዎቹ ያልተሸፈኑ ጉዳዮች(ይርጋን ጨምሮ) የፍትሐ ብሔር ሕጉ ተፈፃሚ እንደሚሆን ሲናገር አንቀፅ 55 ስለ ይርጋ ያስቀመጠው ድንጋጌ ደግሞ ከኪራይ፣ ስጦታና ውርስ የሚነሱ ክርክሮችን ይርጋ እንደማያግዳቸው በግልፅ ስላልከለከለ በሕገ ወጥ መንገድ መያዝ የሚለው ፍሬ ነገር ሊታይ የሚገባው ከክርክሩ ዓይነት ሳይሆን መሬቱን ይዞ ይርጋውን የሚያነሳው ሰው መሬቱን ያዝኩበት ከሚለው መንገድ በመነሳት ነው፡፡ ስለዚህም በሕገ ወጥ መንገድ ይዞ ይርጋን መቃወሚያ ማንሳት አይቻልም ሲል በገጠር መሬት ላይ  በሕግ  ክልከላ የተደረገበትን ወይም እንዲደረግ ያልተፈቀደለትን ተግባር  በመፈፀም (የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 40(3) በተቀመጠው መሬትን መሸጥ መለወጥ ገደብ በመተላለፍ) መያዝን የሚያመላክት ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የገጠር መሬትን በሽያጭ ወይም ከመሬት ውጪ ባሉ ንብረቶች በመለወጥ የያዘ ሰው በመሬት ላይ የተደረገን የሕግ ክልከላ በመጣስ የያዘው ስለሆነ በሕገ-ወጥ መንገድ እንደያዘው የሚያሰቆጥረው ነው፡፡ የገጠር መሬት ሊያዝና ሕጋዊ ይዞታ ሊመሰርትበት የሚችለው በአዋጁ በተቀመጠው ሥርዓት በኪራይ፣ በስጦታ፣ በውርስ እና በድልድል በመሆኑ ከነዚህ መንገዶች ውጪ መያዝ ከሕግ ውጪ እና መብት የማይመሰርት ቢሆንም ጉዳዩ የይርጋ ጉዳይ ስለሆነ ሊታይ የሚገባው ከይርጋ ፅንሰ ሐሳብ በመነሳት ነው፡፡ መሬትን በመሸጥ እና በመለወጥ ማስተላለፍ እንደማይቻል ደግሞ ገና ከጅምሩ በሕግ የተከለከለ ስለሆነ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውጤት የሚኖረው ስለማይሆን ይርጋ ተፈፃሚ የሚሆንበት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ከመሸጥ መለወጥ ውጪ የገጠር መሬትን መያዝ ምንም እንኳን መሬቱን ለያዘው ሰው የይዞታ መብት ሊመሰርትለት ባይችልም ባለመብቱ ላይ ግን መብት የማሳጣት ውጤት ያመጣል፡፡ ስለዚህም በሕገ ወጥ መንገድ መሬትን መያዝ የሚለው የድንጋጌው ሃረግ ሊታይ የሚገባው በሕገ መንግስቱ መሬት አይሸጥም አይለወጥም ከሚለው ክልከላ ጋር ተገናዝቦ እንጅ እንዲሁ በመሬት አዋጅ ከተቀመጠው መሬት ከሚገኝባቸው መንገዶች ውጪ ሁሉ በሚል ሊሆን አይገባም፡፡

በተጨማሪም በአዋጁ ይርጋ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው የወል መሬትን በወረራ መያዝና በመሬት ላይ የተደረጉ የመሸጥና መለወጥ ክልከላዎችን  በመጣስ መያዝ ብቻ እንደሆነ እና የተለመዱ ከፍትሐ ብሔር ጋር የተገናኙ የውርስ፣ የይዞታ፣ የውል እና ሌሎች ክርክሮችን የአዋጁ የይርጋ ድንጋጌ እንደማይመለከት  የፌደራል ገጠር መሬት ማሻሻያ አዋጅ ሐተታ ዘምክንያት ሃሳቡን ያጠናክርልናል፡፡ 

አዲሱ የፌደራል የገጠር መሬት አስተዳደር፣ አጠቃቀም፣ ምዝገባ እና ልኬት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ገፅ 33 የፍትሐ ብሔር ሕግ አግባብነት እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፡-

ከአዋጁ ጋር ግንኙነት እና አግባብነት ያላቸው እንደ ውሃ አጠቃቀም፣ የይርጋ ጊዜ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የፍትሃ ብሔር ህጉ ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ የይርጋ ድንጋጌዎች ለምሳሌ ጉዳዩ ከውል ጋር የተያያዘ ከሆነ የፍ/ብሄር ህጉ አንቀጽ 1845 አግባብነት ይኖረዋል፡፡ ሌሎች ከወል መሬት ወረራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከመጀመሪያም ህገ-ወጥ እና ወንጀል በመሆናቸው መሬቱን ለማስመለስ የሚደረግ ክርክር በይርጋ የሚታገድ አይሆንም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እንደ ሁኔታው የፍ/ብሄር ህጉን የይርጋ ድንጋጌ ህጉ ይቀበላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች በፍ/ብሄር ሀጉ የተቀመጡ ጉዳዮችን እንደ አግባብነታቸው ተፈጻሚነት ይኖራቸዋል፡፡ 

ከተጠቀሰው የፌደራል የገጠር መሬት አስተዳደር፣ አጠቃቀም፣ ምዝገባ እና ልኬት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ  ወይም ሐተታ ዘምክንያት የገጠር መሬትን በወረራ መያዝ በግልፅ ከወል መሬት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረዳት የሚቻል ነው፡፡ ሌሎች ፍትሐ ብሔራዊ የሆኑ የውርስ፣ የውል፣ የይዞታ ክርክሮችን በተመለከተ የፍትሐ ብሔር ሕጎች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በተሻሻለው የክልሉ የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 54 ስለውርስ፣ ስጦታ፣ ኪራይ እና ሌሎች ክርክሮች እንደ አግባብነታቸው የፍትሐ ብሔር ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ሃሰቡን በሚያጠናክር መልኩ ያስቀምጣል፡፡

በዚህም መሰረት በተሻሻለው የክልሉ አዋጅ አንቀፅ 55 ይርጋ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ጉዳዮች የወል መሬትን በወረራ መያዝ እንዲሁም በመሬት ላይ እንዳይፈፀሙ በሕግ ክልከላ የተደረገባቸውን ተግባሮች (መሸጥ እና መለወጥ) መሰረት አድረጎ ይዞ መገኘት እንጅ ሌሎች ፍትሐ ብሔር ነክ የሆኑ ጉዳዮችን እንዳልሆነ መረዳት የሚቻል ነው፡፡

በተጨማሪም የተሻሻለው አዋጅ የይርጋ ድንጋጌ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመሬት ክርክር ይርጋ ላይ ከተሰጡ ውሳኔዎች ጋር ተጣጥሞ የወጣ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡  ለማሳያም ሶስት የሰበር ውሳኔዎችን እንመልከት፡፡

  1. በሰ/መ/ቁ 112906 የካቲት 16-2008 ዓ.ም በሰጠው የሕግ ትርጉም የመንግስትና የሕዝብ (የወል) መሬትን ለረዥም ጊዜ ይዤዋለሁ በማለት ይርጋን መቃወሚያ ማንሳት እንደማይቻል ይናገራል፤  
  2. ሰ/መ/ቁ 79394 ጥቅምት 06-2006 ዓ.ም በተሰጠው የሕግ ትርጉም ደግሞ በመሬት ላይ በሕግ ክልከላ የተደረገበትን ወይም እንዲደረግ ያልተፈቀደለትን ተግባር በመፈፀም መሬትን የያዘ አካል ይርጋን ማንሳት እንደማይችል ይገልፃል፡፡
  3. በሌላ በኩል በሰ/መ/ቁ 69302  ታህሳስ 20-2004 ዓ.ም በተሰጠ  የሕግ ትርጉም  ይዞታው በሌላ ሰው የተነጠቀ አርሶ አደር ወይም ወራሾች ይዞታው ከውል ወይም ከሕግ ውጪ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በአስር ዓመት ውስጥ በመሬቱ ላይ ያለውን የይዞታ ወይም የመጠቀም መብቱን ለማስከበር በአስር ዓመት ውስጥ ክስ ካላቀረበ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 መሰረት በይርጋ እንደሚታገድ ይገልፃል፡፡

በተራ ቁጥር 1 እና 2 የተጠቀሱ  የሰበር ውሳኔዎች በወረራ እና በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ መሬቶች የይርጋ መቃወሚያ ሊቀርብባቸው እንደማይገባ የሚያሳስቡ ናቸው፡፡ በተራ ቁጥር 3 የተጠቀሰው ውሳኔ ደግሞ ከወል መሬት ክርክር ውጪ ባሉ ጉዳዮች እና መሬትን በሕግ ክልከላ ከተደረገባቸው የመሸጥ የመለውጥ ስርዓት ውጪ ባሉ የይዞታ እና የውርስ ክርክሮች የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚ እንዲሆን የሚያሳስብ ነው፡፡ በተጠቀሱት የሰበር ውሳኔዎች በግልፅ ከተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ የይርጋ ድንጋጌ ጋር የሚጣጣሙ ሲሆን አዋጁም የይርጋውን ድንጋጌ ያስቀመጠው በሰበር የተሰጡትን ውሳኔዎች ባገናዘበ መልኩ ይመስላል፡፡

በፌደሬሽን ምክር ቤት ስለመሬት ይርጋ ጉዳይ ተሰጡ የተባሉ ውሳኔዎችም ቢሆን አብዛኞች ይርጋ ተፈፃሚ አይሆንም በማለት የተሰጡት መሬትን በመሸጥ እና በእዳ ማስያዣነት በተላለፉበት ሁኔታ እና በሕገ መንግስቱ ስለ መሬት የተቀመጡ ክልከላዎችን በመጣስ የተፈፀሙ ድርጊቶች እንዳልተፈጸሙ የሚቆጠሩና ለይርጋ መከራከሪያ ሊሆኑ አይችሉም በሚል ነው፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጡ ውሳኔዎች በተለይም የገጠር መሬትን በተመለከተ ይርጋ ተፈፃሚነት የላቸውም እየተባሉ በባለሙያዎች ሳይቀር ከሚጠቀሱ ውሳኔዎች ውስጥ አንዳንዶቹን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡

  1. የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ሰብሰባ ሰኔ 18-2007 ዓ.ም የሰጠው ውሳኔ (በወ/ሮ ማሚቴ ሰብለ እና ወ/ሮ ሙሉ ጉርሙ) ሲሆን የዚህ ውሳኔ መነሻ ከወረዳ ፍርድ ቤት የተጀመረ የገጠር መሬት ይለቀቅልኝ ክርክር ነው፡፡ በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የመሬት ይለቀቅልኝ ክርክር የጀመረው 12(አስራ ሁለት) ዓመት ካለፈ በኋላ የቀረበ ስለሆነ በይርጋ ይታገዳል ተብሎ ውሳኔ ተሰጥቶ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ፀንቶ የነበረ ነው፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ተብሎ ቀርቦ ክስ አቅራቢዋ አመልካች መሬቱን ከ1971 ዓ.ም ከባለቤቷ ጋር ተደልድላ ቆይታ ባለቤቷ ሲሞት ለልጇ በእኩል እያረሰ እንዲያካፍላት ሰጥታው እያረሰላት ስትጠቀም ቆይታ ልጇ ሲሞት የልጇ ሚስት በሆነችው ተጠሪ እንዳትጠቀም ተከለከለች እንጇ መሬቱን ሳትጠቀምበት አልቆየችም፤ ተጠሪ እና የአመልካች ልጅ መሬቱን ለ12 ዓመት የያዙት በእኩል ተከራይተው ስለሆነ እና ባለመሬቷ አመልካችም እኩል በመሬቷ ስትጠቀም ቆይታ ባለችበት ሁኔታ መሬቷን ለ12 ዓመት ሳትጠቀምበት እንደቆየችበት ተቆጥሮ መብቷ በይርጋ ይታገዳል መባሉ ተገቢነት የለውም የሚል ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በዚህ ውሳኔ በግልፅ እንደተቀመጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይርጋው ተፈፃሚ አይሆንም በማለት ያስቀመጠው ለመሬት ክርክር ይርጋ ተፈፃሚ አይሆንም በሚል ሳይሆን ባለመሬቷ መሬቱን ከተጠሪና ባለቤቷ ጋር እየተጠቀመችበት ባለችበት ሁኔታ ይርጋ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በሚል ነው፡፡

በግልፅ እንሚታወቀው የይርጋ ደንብ ተፈፃሚ የሚሆነው ከፈቃድ፣ ከውል ወይም ከሕግ ውጪ ንብረት ተይዞ በሚቆይበት ሁኔታ እንጅ ባለንብረቱ መሬቱን በጋራ እየተጠቀመና ፈቃዱ ባለበት ሁኔታ ስላልሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔም ይርጋን ተፈፃሚ የሚያደርግ ሁኔታ የለም አለ እንጅ ለመሬት ክርክር ይርጋ ተፈፃሚ አይሆንም አላለም፡፡ ይህ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠው ውሳኔ አብዛኛው የሕግ ባለሙያ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የመሬት ክርክር ይርጋ እንዳይኖር ተደርጓል በማለት የሚጠቀሰው ሲሆን በአማራ ክልል የፍትሕ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት የሕግ መፅሔት (ቅፅ 3፣ ሰኔ 2008 ዓ.ም)ሳይቀር ታትሞ ወጥቷል፡፡ የሕግ ምርምር ተቋሙ መፅሔት ላይ በወጣው ፁሁፍ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ ይርጋው ተፈፃሚ አይሆንም ያለው ባለመሬቷ ከመሬቷ ያለመነቀል መብት አላት በሚል እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ሆኖም ግን ፀሃፊው እንደገለፁት ፌዴሬሽን ምክር ቤት በውሳኔ ሃተታው ከመሬት ያለመነቀል መብት እንዳላት ቢገልፅም ይርጋው ተፈፃሚ አይሆንም በማለት ድምዳሜ ላይ የደረሰው ባለመሬቷ ይዞታዋን ሳትለቅ እየተጠቀመችበት የነበር መሆኑን ከክልሉ ሕግ ጋር አገናዝቦ በማስቀመጥ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ይርጋ በመሬት ክርክር ላይ ተፈፃሚ እንደማይሆን የተገለፀ ሳይሆን በመሬቱ እየተጠቀሙ መኖር ይርጋን ተፈፃሚ የማያደርግ ስለመሆኑ ነው፡፡

በተመሳሳይ የፌደሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ሌላ ውሳኔ (ወ/ሮ ወደሬ ታችበሌና ወ/ሮ ልኬ ጉሩሙ ጉዳይ) አመልካች በጤና ምክንያት ከባለቤቷ ጋር ከተለያየች ከ18(አስራ ስምንት) ዓመት በኋላ መሬቱን የጠየቀች ቢሆንም ከባለቤቷ ጋር ከተለያየች ጀምሮ በመሬቱ ሟች ባለቤቷ አማካኝነት ቀለብ ሲቆረጥላት የነበርና በመሬቱም ስትጠቀም የቆየች ስለሆነ ባለቤቷ ከሞተ በኋላ የባለቤቷ ልጆች መከልከላቸው በመሬቱ አልተጠቀመችም ለማለት አይቻልም፡፡ መብቱን የሚያጣው በመሬቱ በይዞታ መብቱ መጠቀም ያቆመ እንጅ በመሬቱ እየተጠቀመ የቆየን ባለመብት ይርጋ አያግደውም በማለት የወሰነበት ሁኔታ አለ፡፡

  1. የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ሰብሰባ ሰኔ 18-2007 ዓ.ም እና 5ኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት 2ኛ መደብኛ ስብሰባ መጋቢት 03-2008 የመሬት ሽያጭን ተከትለው  (በእነአልይ ዳዌ፣ እነሐሳይ ዶዬ ጉዳይ) የተሰጡ ውሳኔዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ውሳኔዎች ይርጋ መቃወሚያ ያነሱት ተጠሪዎች መሬቱን የያዙት በሽያጭ ለመሆኑ ተረጋግጦ እያለ ይርጋ መቃወሚያውን ፍርድ ቤቶች መቀበላቸው ተገቢ አይደለም፤ በመሬት ላይ በሕገ መንግስቱ የተደረጉትን ክልከላዎች በጣሰ መልኩ የተደረጉ ድርጊቶች ሁሉ እንዳልተደረጉ ስለሚቆጠሩ የይርጋ መቃወሚያ ተፈፃሚ ሊሆንባቸው አይገባም በማለት የተሰጠ ውሳኔ ነው፡፡
  2. የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ሰብሰባ ሰኔ 18-2007 ዓ.ም እና 5ኛ የፓርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት 2ኛ መደብኛ ስብሰባ መጋቢት 03-2008  በመሬት ዕዳ መያዣን ተከትለው የተደረጉ ክርክሮች (በእነ ቀለቤ ተስፋ፣ እነእማሖይ ባጫምላክ) ጉዳይ ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ ውሳኔ የገጠር መሬትን በእዳ መያዣነት በማድረግ ማስተላለፍ መሬትን ከመሸጥ መለወጥ የተለዬ ውጤት ስለሌለው እና በሕገ መንግስቱ ከተቀመጠው ክልከላ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ፍርድ ቤቶቹ የዕዳ መያዣውን ውል ማጽናታቸው ተገቢት የለውም በማለት የተሰጡ ውሳኔዎች ናቸው፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት በመሬት ላይ ከሰጣቸው ውሳኔዎች ዋናወቹ ከላይ ተገለፁት ሲሆን በአንዱም ውሳኔ ፌደሬሽን ምክር ቤቱ የገጠር መሬትን በተመለከተ የሚደረጉ ክርክሮች የይርጋ ደንብ አይፈፀምባቸውም የሚል መደምደሚያ አልደረሰም፡፡ ፌደሬሽን ምክር ቤቱ በሰጣቸው ውሳኔዎች በገጠር መሬት ላይ ይርጋውን ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በማለት ሁለት ዋና ምክንያቶችን አስቀምጧል፡፡ አንደኛው ምክንያት አንድ የመሬት ባለይዞታ መብቱን ሊያጣ የሚችለው በመሬቱ መጠቀም ሲያቆም እንጅ መሬቱን እየተጠቀመ ባለበት ሁኔታ ይርጋ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም በማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በገጠር መሬት ላይ በሕገ መንግስቱ የተቀመጡ የመሸጥ እና የመለወጥ ክልከላዎችን በመተላለፍ መሬትን በሽያጭ እና በመለወጥ መያዝ ውጤቱ ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ የሚያስቆጥር ስለሆነ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ይርጋ ተፈፃሚ ሊሆን አይገባም የሚል ነው፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት በሰጣቸው ውሳኔዎች የቀረቡለትን ጉዳዮች ሲወስን በዋናነት መሬቱ የተያዘበትን አግባብ በጭብጥነት በመያዝ እንዴት እንደተያዘ በመመርመር ነው፡፡ በፌደሬሽን ምክር ቤት የተሰጡ ውሳኔዎች ቀደም ሲል በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ተወስነው በማሳያነት እንደቀረቡት ውሳኔዎች ሁሉ በተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ ቁጥር 252/2009 አንቀፅ 55 የተቀመጠውን የይርጋ ድንጋጌ ወሰን ወይም ተፈፃሚነት ለመወሰን አመላካች ነው፡፡ በዚህም መሰረት የተሻሻለው የገጠር መሬት አዋጅ የይርጋ ድንገጌ የገጠር መሬት ክርክርን ተከትለው የሚነሱ ክርክሮች ሁሉ ይርጋ ተፈጻሚ አይሆንባቸውም ወደ ሚል መደምደሚያ የማያደርስ ሲሆን የይርጋ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው የወል መሬትን በወረራ እና የግለሰቦችን ይዞታ በሕገ ወጥ(በመሸጥ እና በመለወጥ) መንገድ መያዝ ብቻ እንደሆኑና ከነዚህ ውጪ  ያሉ ከይዞታና ከመጠቀም መብት መከበር ጋር የተገናኙ ክርክሮች ሁሉ የአስር ዓመቱ ይርጋ ተፈፃሚ የሚሆንባቸው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ተደራሽ ግን ርካሽ ዳኝነት - የኦሮሚያ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ምልከታ
የፍርድ ቤት ወይስ የችሎት ስልጣን? (Jurisdiction of Courts or ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024