Font size: +
10 minutes reading time (2085 words)

የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና በተግባር የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች - ክፍል 2

በክፍል 1 ላይ ጸሐፊው ስለ አጠቃላይ የዋስትና የሕግ ማዕቀፍ በአጭሩ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ስለ ኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነት፣ ዓይነቶች እንዲሁም በተግባር የሚታዩ ክፍተቶች ይዳስሳል፡፡

1. የኮንስትራክሽን ዋስትና (Construction security)

በኮንስትራክሽን ውል አፈጻጸም ወቅት በርካታ የዋስትና ዓይነቶች ሲተገበሩ ይታያል፡፡ ከቅድመ ግንባታ ጀምሮ በግንባታ ወቅት አንዳንዴም ከግንባታ በኋላ ለሚከሰቱ ችግሮች ዋስትና ጥቅም ላይ ሲውል ይሰተዋላል፡፡ በተለይም የህንጻ አሰሪዎች (Clients) ግንባታው በፈለጉት ጊዜና ዕቅድ መሰረት እንዲካናወንላቸው ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ውሉ እንዲፈጸምላቸው አሰፈላጊ ከለላ እንዲኖራቸው ይሻሉ፡፡

በኢትዮጵያም አብዛኛው የኮንስትራክሽን ውሎች መንግስት አሰሪ በመሆን የሚቀርብባቸው ናቸው፡፡ ለማሳያ ያህል የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ፣ የኢንዲስትሪ ፓርኮች ግንባታ፣ የባቡር ዝርጋታ፣ የመንገድ ግንባታዎች ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለምዶው የመንግስት ኪስ እርጥብ (solvent) ነው ቢባልም በውል አስተዳደር ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የክፍያ መዘግየት ይስተዋላል፡፡ በዚህ ጊዜም ሥራ ተቋራጩ ልክ እንደ አሰሪው ሁሉ ግዴታ አለተፈጸመልኝም ብሎ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል፡፡ በመርህ ደረጃ አሰሪ ሆኖ የቀረበው የመንግስት መስሪያ ቤት ውል ባለመፈጸሙ ምክንያት ሥራ ተቋራጩ ውል አልተፈጸም በሚል መከራከሪያ ሊያቀርብ እንደማይችል ከፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 3177 ድንጋጌ እና ከተለመደው የላቲን አባባል፡- ‘Exceptio non adimpleti contractus’ (ግዴታ አለተፈጸመልኝምን እንደ መከራከሪያ አለማቅረብ) መረዳት ይቻላል፡፡

ታዲያ ከላይ ያሉት ስጋቶች የሚከሰቱ ከሆነ፣ አሰሪውም ሆነ ሥራ ተቋራጮች ሁነኛ የሚሉትን የኮንስትራክሽን ዋስትና ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የታወቁ የዋስትና ዓይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ እነዚህም የዉል ማስከበሪያ፣ የጨረታ ማስከበሪያ፣ የቅድሚያ ክፍያ፣ የዋናው ገንዘብ መያዣ እና የጥገና/ብልሽት ዋስትናዎች ናቸው፡፡

 

የውል ማስከበሪያ ዋስትና (Contract security/ Performance Bond)

 

የውል ማስከበሪያ ዋስትና (contract security) ወይም የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና (performance bond) የሚባለው አንድም ግራ ቀኙ ለገቡት ውል መልካም አፈጻጸም ሲባል በአንድ ሦስተኛ ወገን የሚሰጥ ዋስትና ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜም ሥራ ተቋራጮች ለፕሮጀክት ባለቤቶች ወይም ንዑስ ተቋራጮች ለዋናው ሥራ ተቋራጭ ውል ለመፈጸም ብለው ከአንድ የፍይናንስ ተቋም ወይም ሌላ ሦስተኛ ወገን አማካኝነት የሚቀርብ ዋስትና ነው፡፡

ሁኖም ግን ቀደም ሲል እንደተገለጸው የውል ማስከበሪያ ዋስትና ተፈጻሚ የሚሆነው ዋናው ባለዕዳ(ለምሳሌ፡-ሥራ ተቋራጭ) ግዴታውን ባይወጣ ነው፡፡ ይህም ጉዳይ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በሰበር ተመልክቶታል፡፡ ቅጽ 12 በሰ/መ/ቁ 60951 በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እና በካንትሪ ትሬዲንግ መካከል በነበረው ክርክር ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል፡-

“ከመንግስት አስተዳደር መ/ቤት ጋር የሥራ ውል ያደረገ ወገን እንደውሉ መፈጸም ባልቻለ ጊዜ የአስተዳደር መ/ቤቱ ተዋዋዩ የውል ማስከበሪያ (contract security) በሚል ካስያዘው ገንዘብ ላይ ውል ባለመፈጸሙ የደረሰበትን የጉዳት ኪሣራ መቀነስ ይችላል፡፡ ”

በፌደራል የመንግስት የግዥ እና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁ.649/2001 አንቀጽ 47 ላይ በግልጽ እንደተመለከው በተለይም የመንግስት ግንባታ ውሎች ላይ አቅራቢ (ውል ተቀባይ) ሆኖ የሚቀርብ ወገን ግዴታውን ባለመፈጸሙ ምክንያት በውል ሰጪው መንግስት መ/ቤት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የውል ማስከበሪያ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

መጠኑን በተመለከተም የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡ እኤአ በ ሰኔ ወር 2010 የወጣው የገ/ኢ/ል/ሚ መመሪያ አንቀጽ 16.25 ላይ እንደተመለከው አሸናፊው ሥራ ተቋራጭ ጨረታውን አሸንፎ ውል በተዋዋለ በ 15 ቀናት ውስጥ ቢያንስ የውሉን 10ፐርሰንት እንደ ውል ማስከበሪያ(Performance security) ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ የዋስትናው መክፈያ መንገድም በመመሪያው አንቀጽ 16.16.4 በተመለከተው መሰረት በተጫራቹ ምርጫ በጥሬ ገንዘብ፣ በቼክ፣ የባንክ ዋስትና ሰነድ፣ ክሬዲ ወይም በቅድመ ሁኔታ በሚዘገጅ የመድን ቦንድ ሊሆን ይችላል፡፡

በተጨማሪም መመሪያው በአንቀጽ 16.25.3 ላይ ውል ሰጪው የመንግስት መ/ቤት አቅራቢው (ሥራ ተቋራጩ) በውሉ በተቀመጠው መሰረት ግዴታውን መወጣት ካልቻለ የያዘውን ውል ማስከበሪያ ገንዘብ እንደነገሩ ሁኔታ መጠቀም ወይም መውረስ ይችላል፡፡ እንዲሁም ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ሥራ ተቋራጩ ውሉን በተወጣ ጊዜ ያስያዘው ገንዘብ ይመለስለታል፡፡ /የመመሪያው አንቀጽ 16.25.7 ይመለከተዋል፡፡ /

ሌላው ጉዳይ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና (Performance bond) በመድን ድርጅቶች መውጣታቸው የዋሱን እና ባለገንዘቡን ግዴታ የሚገዛውን የሕግ ማዕቀፍ ይቀይራል ወይስ አይቀይርም? የሚለው ነጥብ ነው፡፡

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቅጽ 13 ላይ በሰ/መ/ቁ 47004 በኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና በባሌ ገጠር ልማት ድርጅት መካከል በነበረው ክርክር ላይ አክሱም ኮንስትራክሽን ለሚሰራው የመንገድ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ቦንድ ማውጣቱ ጉዳዩን የሚገዛው የንግድ ሕጉ ወይስ የፍትሐብሔር ሕጉ(ስለ ሰው ዋስትና የተመለከተው የፍ/ህ/ቁ 1920-1951)? የሚል ነበር፡፡ ሰበርም አከራካሪውን ጉዳይ ለመወሰን ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የተለያዩ ሕግጋት እና መዝገበ ቃላትን ከተመለከተ በኋላ በመድን ድርጅቶች የሚዘጋጅ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትናን የሚገዛው የፍትሐብሔር ሕጉ በመሆኑ ከይርጋ ጋር የሚነሱ ክርክሮችም በዚሁ ሕግ እንደሚስተናገድ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ለመስጠት ሞክሯል፡፡ ሆኖም ግን የዋስትናውን ዓይነትና ወሰን እንዲሁም ከሰው ዋስትና ጋር ያለውን ንጽጽራዊ ልዩነት በተመለከተ ፍርድ ቤቱ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡

ሲጠቃለልም የውል ማስከበሪያ ዋስትና ስለፕሮጀክቱ መልካም አፈጻጸም ውል ተቀባዩ ከአንድ ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር በሚደርገው ግንኙነት ሊቋቋም ይችላል፡፡

 

የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና (Bid Bond)

 

የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ማለት ጨረታ ተወዳድሮ ያሸነፈ ተጫራች ለምሳሌ ሥራ ተቋራጩ በአሸነፈው መሰረት ውሉ ቢሰጠው ግዴታውን ስለመፈጸሙ የሚያቀርበው ዋስትና ነው፡፡ በሌላ አባባል ይህ ዋስትና ሥራ ተቋራጩ ለአሰሪው ጨረታውን በማሸነፉ ወደ ውሉ እገባለሁ ሲል የሚገባው የዋስትና ግዴታ ነው፡፡

ይህም ጉዳይ በመንግስት ግዥ አዋጅ ላይ በአንቀጽ 40 በስፋት ተመልክቷል፡፡ የመንግስት መ/ቤቶች ለሚያሰሩት ግንባታ በሚያዘጋጁት የጨረታ ሰነድ ተጫራቾች ከመጫረቻ ሰነዶቻቸው ጋር የጨረታ ማስከበሪያ የማቅረብ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም መያዣ ተጫራቹ ጨረታው አየር ላይ እያለ ከውድድሩ ከወጣ ወይም ከአሸነፈ በኋላ ውሉን ለመፈጸም ፈቃደኛ ካልሆነ የጨረታ መያዣ ገንዘቡ ሊወረስ ይችላል፡፡

በሌላ አባባል የጨረታ ማስከበሪያ በሚል የሚያዝ ገንዘብ ጨረታውን ባዘጋጀው አካል ሊወሰድ የሚችለው ተወዳዳሪው ጨረታውን ባሸነፈው መጠን ሆኖ በጨረታው መሠረት  መፈጸም ካልቻለ ወይም አስቀድሞ ከወጣ ነው፡፡ ይህንንም ጉዳይ በተመለከተ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ቅጽ 10 ላይ በሰ/መ/ቁ 40947 በእነ አቶ መዝገቡ መድህኔ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል በነበረው ክርክር ከሕጉ ጋር የሚጣጣም ውሳኔ አስተላልፋል፡፡

የጨረታ ዋስትናው መጠኑን በተመለከተም እኤአ በ2010ዓ.ም በወጣው የገ/ኢ/ል/ሚ የግዥ መመሪያ አንቀጽ 16.16.2 ላይ እንደተገለጸው የጨረታ ዋስትና የውሉን አጠቃላይ ግምት ወስጥ 0.5 (ግማሽ) እሰከ 2(ሁለት) ፐርሰንት ሊደርስ ይችላል፡፡ ነገር ግን የተባለው የመንግስት መ/ቤት የጨረታ ዋስትናውን መጠን በሚወስንበት ጊዜ ከ500,000.00 (አምስት መቶ ሺ) ብር መብለጥ የለበትም፡፡

የጨረታው አካሄድ ሚዛናዊ እንዲሆን መመሪያው እንደሚለው የመንግስት የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ለማከናወን የሚወጣ ጨረታ ቢያንስ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በግዥ የሚሰራው ሥራ የዋጋ አስተማማኝነት ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ ሁለተኛ በጨረታው በቂ ቁጥር ያላቸው ተጫራቾች እንዲኖሩ ግድ ይላል፡፡ የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘቡ ተጫራቾችን እንዳይሳተፋ አስቀድሞ የሚከለክል መሆን የለበትም፡፡ ሌላው የጨረታ ማስከበሪያ ገንዘቡ አጫራቹ የመንግስት መ/ቤት በጨረታው አሸናፊ የሆነው ተጫራች ጨረታውን ባለመፈጸሙ ምክንያት ሊደርስበት የሚችልን ጉዳት መሸፈን ይኖርበታል፡፡

 

የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና (Advance Payment Guarantee)

 

የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ሲባል ሥራ ተቋራጩ ጨረታውን አሸንፎ ውል ተፈርሞ ወደ ሥራው ሊገባ ሲል የፕሮጀክቱ ባለቤት ለሥራ ተቋራጩ የተወሰነ የቅድሚያ ገንዘብ በመስጠቱ ምክንያት ሥራ ተቋራጩ በአንጻሩ ለወሰደው ገንዝብ የሚያቀርበው ዋስትና ነው፡፡

በመሰረቱ በኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ጅማሮ የቅድሚያ ክፍያ መኖር በአንድ በኩል ሥራ ተቋራጩ ያለምንም የገንዘብ ችግር ለሥራው የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች መግዣ ይሆነዋል፡፡ ወይም ደግሞ ሥራ ተቋራጩ ሥራውን ከፍሎ ለንዑስ ተቋራጮች በሚሰጥበት ጊዜ እንደ ሥራ ማስጀመሪያ (mobilization commission) ይሆናቸዋል፡፡

ስለ ቅድሚያ ክፍያ አስፈላጊነት ታዋቂው የኮንስትራክሽን ክሌም ጸሀፊ ጆን ስካይስ እ.ኤ.አ 1999 በወጣው መጽሀፋቸው እንዳብራሩት ቅድሚያ ክፍያ መኖር ለሥራ ተቋራጮች ከመጥቀሙ ባሻገር የጨረታ ወጥ መለኪያ (tender standardization) ተድርጎ ስለሚወሰድ ጭምር ነው፡፡

የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና መኖረን አስመልክቶ የመንግስት ግዥ አዋጅ ቁ.649/2001 በአንቀጽ 48 እንደተመለከተው የቅድመ ክፍያ ሊፈጸም የሚችለው ሥራ ተቋራጩ በቅድሚያ ክፍያ መልክ ከሚወስደው ገንዘብ መጠን ጋር እኩል የሆነ ዋስትና ሲያቀርብ እንደሆነ ይናገራል፡፡

የመንግስት የኮንስትራክሽን ውሎችን የቅድሚያ ክፍያ መጠንን በተመለከተ እኤአ በ2010 የወጣው የገ/ኢ/ል/ሚ የግዥ መመሪያ አንቀጽ 16.26 ላይ የቅድመ ክፍያ መጠን የውሉን 30(ሰላሣ) ፐርሰንት መብለጥ የለበትም፡፡ ሆኖም ግን በአገር በቀል የሥራ ተቋራጮች የሚሰራ የመንገድ ግንባታ ሲሆን ግን የቅድሚያ ክፍያ ገንዘቡ እስከ 50(ሃምሳ) ፐርሰንት ይደርሳል፡፡ ዝርዝር ሁኔታው በእያንዳንዱ ጨረታ ይገለጻል፡፡ በሥራ ተቋራጩ የሚቀርበው የቅድሚያ ክፍያ ዋስትናው መጠን የተከፈለውን የቅድሚያ ክፍያ ገንዘብ ጋር እኩል መሆን አለበት፡፡ የዋትናው አቀራረብም በቼክ፣ ያል ቅደመ ሁኔታ የሚቀርብ የባንክ ዋስትና ወይም በቅድመ ሁኔታ የሚዘጋጅ የመድን ዋስትና ሊሆን ይችላል፡፡

ሌላው የቅድሚያ ክፍያ ገንዘቡ ለምን ዓላማ መዋል እንደለበትና በምን አግባብ ሊሰጥ እንደሚችል መመሪያው በአንቀጽ 16.26.7 ተመልክቶታል፡፡ በተለይም የመንገድ እና ህንጻ ግንባታ የሚሰሩ ሥራ ተቋራጮች በቅድሚያ ክፍያው ገንዘብ ስለሚገዙት የማሽነሪ ዝርዝር በመመሪያው አባሪ 4 መሰረት በተዘረዘረው ብቻ ይሆናል፡፡

 

 የዋናው ገንዘብ መያዣ (Retention Money Bond)

 

የዋናው ገንዘብ መያዣ የሚባለው ደግሞ በውል አስተዳደር ወቅት ሥራ ተቋራጩ ሥራውን ፈጽሞ ክፍያ በሚጠይቅበት ወቅት የፕሮጀክቱ ባለቤት ከግንባታው አማካሪ መሀንዲስ ጋር በመሆን ስለ ሥራው ጥራት ደረጃ በሚል ሊይዘው የሚችለው ዋስትና ነው፡፡ የዋና ገንዘብ መያዣ ዋስትና (retention) ዓላማ የግንባታውን ጥራት ለማስጠበቅ ሲባል ሥራ ተቋራጮች ለአሰሪዎች የሚገቡት ዋስትና ነው፡፡

የግዥ መመሪያውም በአንቀጽ 28.5(ለ) ላይ በግልጽ እንደሚደነግገው በእያንዳንዱ የክፍያ ሰርተፍኬት ላይ 5(አምስት) ፐርሰንት የክፍያው ገንዘብ የሚያዝ ይሆናል፡፡ በዋናነት ከተያዘው ገንዘብ ውስጥ 50(ሃምሳ) ፐርሰንት የሚሆነው ገንዘብ ሥራው እንደተጠናቀቀ እና ጊዚያዊ የርክክብ ምስክር ወረቀት (provisional acceptance certificate) ከተሰጠ በኋላ ለሥራ ተቋራጩ ይመለስለታል፡፡ የቀረው ገንዘብ ደግሞ እስከ አንድ አመት ድረስ ዋቢ ሆኖ ይቆያል፡፡ ነገር ግን የተቀረው የመያዣ ገንዘብን አስቀድሞ ሥራ ተቋራጩ ለአንድ አመት የሚጸና ዋስትና ማቅረብ ከቻለ የተያዘበትን ቀሪ ገንዘብ ማስለቀቅ ይችላል፡፡

በተመሳሳይ መልኩም የሲቪል ሥራዎችን በተመለከተም እኤአ በ1994 ዓ.ም የወጣው የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ወጥ ውልም ስለ የዋና ገንዘብ መያዣ ዋስትና በአንቀጽ 59(5) እና 60 ላይ ተቀራራቢ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡

 

የጥገና ወይም የብልሽት አላፊነት መያዣ (Maintenance or Defect Liability Bond)

 

የጥገና ዋስትና የተበላሹ የግንባታ ግብዓቶችንና የሥራ አሰራር ግድፈቶችን ለመከላከል በሚል ሥራ ተቋራጩ ለፕሮጀክት ባለቤቱ የሚገባው ዋስትና ነው፡፡ በተለይም ከላይ ስለዋና ገንዘብ መያዣ (retention) ቆይታ እንደተመለከተው ለአንድ ዓመት ጊዜ የሚያዝበት ምክንያት ከጥራት ጉድለት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለመጠገን ነው፡፡ በሚለቀቅበትም ጊዜ ያለቅድመ ሁኔታ ዋስትና ሥራ ተቋራጩ እንዲያቀርብ የሚደረግበት ምክንያት በህንጻው ግንባታ ላይ የሚታዩ ግድፈቶችን ለመጠገን በሚል ነው፡፡

የጥገና እና ብልሽጽ አላፊነት መያዣ በዋናነት የዋና ገንዘብ መያዣ ቆይታ እንዳበቃ የሚጀምር ነው፡፡ በርግጥ ሥራ ተቋራጩ ለባለቤቱ ለተወሰኑ ዓመታት ዋቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡-በሲቪል የግንባታ ሥራዎች በተለይም በፍ/ህ/ቁ 3039 እንዲህ የሚል ዐ.ነገር ይነበባል፡-

“ሥራ ተቋራጩ ሥራውን ካስረከበበት ጊዜ ጀምሮ ስለመልካም አሰራር፣ ስለሥራው እና ስለጠንካራነቱ ለ10 (አስር) አመት መድን (guarantee/ warranty) ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ በሥራው ጉድለት ወይም በተሰራበት መሬት ዓይነት ምክንያት በተሰራው ሥራ ላይ ለሚደርሰው መጥፋት ወይም መበላሸት አላፊ ነው፡፡ ”

በተመሳሳይ መልኩ የመንግስት የግንባታ ውሎችንም በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 3277-3282 ላይ የ10 (አስር) አመት የብልሽት መድን ጊዜ ያስቀምጣል፡፡

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት በቅጽ 18 በሰ/መ/ቁ 101378  በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እና ናሰው ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር መካከል በነበረው ክርክር የጥገና ዋስትና(maintenance bond) ሊኖር እንደሚችል ካተተ በኋላ አንድ ሥራ ተቋራጭ በሠራው ህንጻ ላይ የተከሠተ እርግጠኛ የአሰራር ጉድለት በሌለበት ሁኔታ ወደፊት የሚታይና የሚከሰት የአሰራር ጉድለት ሊኖር ይችላል በሚል ምክንያት ሥራ ተቋራጮች ለሰሩት ሥራ የመጨረሻ ክፍያ የማግኘት መብት መከልከል አግባብነት የሌለው መሆኑን እሰገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡

 

ከኮንስትራክሽን ዋስትና አፈጻጸም ወቅት በተግባር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች

 

በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዲስትሪ ገና ዳዴ እያለ ያለ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው፡፡ ሆኖም ግን ዘርፋ ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት (Gross Domestic Product) ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡

ዳሩ ግን በዘርፋ የሚታዩ በርካታ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ችግሮችም ከኮንስትራክሽን ዋስትና ጋር የተያያዙም ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ፡-በመንግስት የጋራ ቤቶች ግንባታ የዋናው ገንዘብ መያዣ (retention) የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቆ የጊዜያዊ እና የመጨረሻ ርክክብ ከተፈጸመ በኋላ የተያዘው 5(አምስት) ፐርሰንት ገንዘብ አብዛኛውን ጊዜ ተመላሽ አይሆንም፡፡ (አቶ ቴዎድሮስ፡ ወርቁ፡2009፡38) በዚህ ሳቢያም ሥራ ተቋራጮች ለሌላ ወጪ የሚዳረጉበት ሁኔታ አለ፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ አብዛኛው የግንባታ ውሎች የመንግስት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለያዩ የመንግስት መ/ቤቶች ከግዥ እና ውል አስተዳደር ያለው ከፍተኛ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ከላይ የተባሉትን የዋስትና መንገዶች በአግባቡ እንዳይተገብሩ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ፡፡

ሌላው ድግሞ በፍ/ቤቶች ዘንድ የሚታዩ የአተረጓጎም ክፍተቶች ናቸው፡፡ ወሰኑ ያለየለት የኮንስትራክሽን ዋስትና በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-በአንድ የኮንስትራክሽን ፕሮጅክት አፈጻጸም የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትናን በተመለከተ በንግድ ሕግ ወይስ በፍትሐብሔር ሕግ ይገዛ የሚለው ነጥብ ነው፡፡ በተለይም የመድን ድርጅቶች ከሚሰጧቸው ዋስትናዎች ጋር ተያይዞ የሚነሳ ክርክር ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በመድን ድርጅት የወጣ ቦንድን እንደ የመድን ሥራ አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ አለ፡፡

በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ የመድን ድርጅቶች ያለቅድመ ሁኔታ ዋስትናዎችን ጨምሮ የገንዘብ እዳ ማስከበሪያ ቦንድ ከማውጣት ቢከለከሉም በቅድመ ሁኔታ የተመሰረቱ ቦንዶች ማውጣት ይችላሉ፡፡ ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ የሰው ዋስትናም ሆነ የመድን ውል ሁለቱም የካሳ ውሎች (contract of indemnity) ናቸው፡፡ እንዲሁም ምንጫቸው ከተለየ ልዩነታቸውን ማቋቋም የሚከብድ አይደልም፡፡ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና አብዛኛውን ጊዜ በችሮታ (gratuitous) ሊቋቋም ይችላል፡፡ በፋይናንስ ተቋማት በሚዘጋጅበት ጊዜ ድግሞ በክፍያ (consideration) ይሆናል፡፡ በዚህ ሳቢያ ለተባለው የፍይናንስ ተቋም ኮሚሽን ሊከፍል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው የሕግ ማዕቀፍ የፍትሐብሔር ሕግ ከአንቀጽ 1920-1951 ያለው ነው፡፡ በእርግጥ የፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌዎች በፍይናንስ ተቋማት በሚሰጡ ዋስትናዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ባይፈጸምም የግዴታውን ሁኔታ ይገዛል፡፡

በአንጻሩ ግን የመድን ግዴታ ቀዳማዊ እንጂ ደባል አይደለም፡፡ ተራ የውል ጥሰትም የመድን ውል ተፈጻሚ ሊያደርግ አይችልም ለምን ቢባል በቅን ልቡና መግባትን ጨምሮ የመድን የሚገባበት ጥቅም መኖር (insurable interest) ግድ ይላል፡፡ ስለሆነም ተገቢውን የሕግ ማዕቀፋ ከጉዳዩ አላማ ጋር ታይቶ ትርጉም ቢሰጠበት መልካም ነው፡፡

ሌላው ደግሞ የመልካም ሥራ አፈፃፀም ዋስትና በመድን ድርጅቶች በሚሠጥበት ወቅት እስከ -------- ብር ተብሎ የሚገለፅ ሲሆን፣ በአሠሪዎች በኩል ያለው ሃሣብ ግን ሙሉ ክፍያው ስለተሠራው ስራም ሆነ ስለደረሠው ጉዳት መጠን ከግምት ሣይገባ እንዲከፈል የሚጠየቅበት ሁኔታ እና የቅድሚያ ክፍያ ለሥራ ተቋራጩ በሚሠጥበት ጊዜ ስለተጨማሪ እሴት ታክስ መታከል ወይም ያለመታክል ወጥ አሠራር ያለመኖርን በተግባር ማየት ይቻላል፡፡ (አቶ በቃሉ፡ጥላሁን፡2009)

በመጨረሻም በአገራችን የዋስትና ገበያ የመንግስት ክትትል አናሳ መሆን ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሥራ ተቋራጩ በርካታ ሠራተኞችን በሥሩ ቀጥሮ ሊያሰራ ይችላል፡፡ ዳሩ ግን በሠራተኞች የማጭበርበር ወይም ብልሹ አሰራር ምክንያት ለሚደርስበት ጉዳት ማካካሻ የሚሆን የመተማመን ዋስትና (Fidelity bond) አለመኖር ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ብዙ ሥራ ተቋራጮች የመክስር አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡

 

ማጠቃለያ

 

ዋስትና በውል አፈጻጸም ወቅት እንደ ተጨማሪ(ደባል) የሚቆጠር ግዴታ ነው፡፡ ባለዕዳው በውሉ መሰረት ላለበት ግዴታ ማስከበሪያ የሚሆን ዋስ ጠርቶ የባለገንዘቡን ስጋት የሚቀንስበት መንገድ ነው፡፡ ዋስትና ዓይነቱና መልኩ ይለያይ እንጂ ሁሉም ዓይነት ዋስትና ቀዳማዊው ግዴታ ባለመፈጸሙ የሚከተል ግዴታ ነው፡፡ ዋስትና ከሚሰጠው ፈርጀ ብዙ ጥቅም አንጻር የሰው፣ የንብረት፣ የፍይናንስ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ብለን መፈረጅ እንችላለን፡፡ በእርግጥ የኮንስትራክሽን ዋስትና በአተገባበሩ በአንድ በኩል የሰው ዋስትና የሚመስል ይዘት ያለው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኛውን የኮንስትራክሽን ዋስትና የሚሰጠው በፋይናንስ ተቋማት በመሆኑ ወሰኑን በወል መለየት አዳጋች ያደርገዋል፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የታወቁ የዋስትና ዓይነቶች የሚባሉት የውል ማስከበሪያ፣ የጨረታ ማስከበሪያ፣ የቅድሚያ ክፍያ፣ የዋናው ገንዘብ መያዣ እና የጥገና/ብልሽት ዋስትናዎች ናቸው፡፡ ዳሩ ግን በተግባር አብዛኛውን ጊዜ የመንግስት ፕሮጀክቶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ውልን በሚያስተዳድሩና ጨረታን በሚመሩ ሰዎች ከሕግ የወጡ ሥራዎች ሲሰሩ ይስተዋላል፡፡ በተለይም የዋና ገንዘብ ዋስትና(retention) በጊዜዉ አለመመለስ አንዳንዴም የውሃ ሽታ ሆኖ መቅረት ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌላው ጉልህ ችግር በሥራ ተቋራጮች ለሚደርሱ ከሠራተኛ ጋር የተያያዙ ጥፋቶችን ለመቀነስ የመተማመኛ ዋስትና(fidelity bond) ቢጀመር መልካም ነው፡፡ በመጨረሻም መንግስት የዋስትናን ገበያ ከፍተኛ ድጋፋ ቢያደርግ እና የግሉን ዘርፍ ቢያጠናክር አሁን ያለውን የዋስትና ሽፋን ያጠናክራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የቴዲ አፍሮ አልበም ምርቃት ክልከላ እና የመሰብሰብ መብት
የኮንስትራክሽን ዋስትና ምንነትና በተግባር የሚስተዋሉ የሕግ ክፍተቶች - ክፍል ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 12 December 2024