Font size: +
14 minutes reading time (2845 words)

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አስጣጥ በአንድ መስኮት አገልግሎት መሆን መልካም አጋጣሚዎች እና ፈተናው

መግቢያ

ኢንቨስትመንት ቃሉ እንግሊዝኛ ሲሆን አሁን አሁን ግን በአማርኛ ሥነ ጽሑፍም በጣም እየተለመደ በመምጣቱ የአማርኛውን አቻ ቃል ማለትም “ምዋዕለ-ንዋይ” የሚለው መጠሪያ እስከሚዘነጋ ድረስ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በየእለቱ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት አዋጅ ቁ.769/2005 ሳይቀር መዋዕለ ንዋይ ከማለት ይልቅ ኢንቨስትመንት የሚለውን ቃል ሙሉ በሙል ተጠቅሟል፤ ስለዚህ በዚህ ረገድ አንባቢውን ግራ ላለማጋባት ሲባል ጸሐፊው ኢንቨስትመንት የሚለውን ቃል ለመጠቀም ተገዷል፡፡ የዚህ ጹሑፍ ዓለማ ለምን ምዋዕለ-ንዋይ የሚለው ቃል ኢንቨስትመንት እየተባለ ተጠራ የሚለው ጉዳይ ባይሆንም አገር በቀል መጠሪያዎችን መጠቀም እንድንለምድና እንድናዳብር አስተያየት ለመጠቆም ነው፡፡

የአንድ ሃገር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተፈለጊ እና ሳቢ የሚያደርጋት የዘረጋችው ሃገራዊ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ነው፡፡ ሆኖም ግን ምቹ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ መኖሩ ብቻ ፍሰቱን እንዲጨምር ላያደርግ ይችላል፡፡ ለምን ቢባል በተግባር የወጡት ፖሊሲዎች እና ሕጎች በአስፈጻሚው አካል ዘንድ የመተግበራቸው ሁኔታ ስለሚያጠያይቅ ጭምር ነው፡፡ እነዚህ አስተዳደራዊ ሥነ ሥርዓቶች ነጻ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሰጡ አገራት ጭምር ከፍተኛ ስጋት ያጭራሉ፡፡ በብዙ ሃገራትም በርካታ ኢንቬስተሮች የሚያቀርቡት ስሞታ እና እሮሮ በተለይም አሰልቺ ከሆኑ አሰራሮች (hectic bureaucracy) መኖር ጋር ይያያዛል፡፡

እርግጥ ነው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥሩ የሕዝብ ግንኙነት  ወይም የገበያ ጥናት ባለሙያዎች መኖራቸው መልካም ተግባር ነው፡፡ በተለየም ቢዝነስ ተኮር የሕዝብ ዲፕሎማሲ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ የማስተዋዋቅ ተግባር የተመሰጡ የውጭ ኢንቬስተሮች የተባለችውን አገር ሄዶ ሁኔታውን ለማየት ከመቼው ጊዜ ልባቸው ይነሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ የሚሄዱበት አገር አስተዳደራዊ ችግር በስፋት የሚታይበት ከሆነ ኢንቬስተሩ አስቀድሞ ስለሁኔታው ሊወስን ይችላል፡፡ ለአብነት ያህልም ኢንቬስተሩ/ሯ ወደ ተባለው አገር ለማምራት ቪዛ ተይቀው በጣም አሰልቺ ነገር ቢገጥማቸው ከራስ ተሞክሮ ውሳኔ ሊዎስኑ ይችላሉ፡፡ (ፍራንክ ሳደር፡እኤአ 2003፡2)

የተባለውን እሰቸጋሪ ውጣ ውረድ አልፈውም ወደ አገር ቤት ሲገቡ ከሌሎች ቀደምት ኢንቨስተሮች ተሞክሮ በመውሰድ ሊያውጡ የሚችሉትን ወጪ፣ መዘግየት፣ የመንግስት ምላሽ እና ለችግሮች የሚሰጠውን መልስ ከግምት በማስገባት አስቀድመው ትረፍና ኪሳራ (cost-benefit analysis) በመስራት የተባለው አስተዳደራዊ ችግር ይኖራል ብለው ካመኑ ልክ እንደ ሌሎች ተጎጂ ላለመሆን ባመጣቸው እግር ወደ መጡበት አገር ይመለሳሉ፡፡

ሌላው ጉዳይ ፈቃድ ሰጭው አካል የቀረበለትን ማመልከቻ ቶሎ መልስ ካልሰጠበት፣ ግለጸኝነት የሚጎድለው ከሆነ እና በጣም ሰፊ የሆነ ፈቅደ ስልጣን (discretionary power) ሚስተዋል ከሆነ ለሌላ ብልሹ አሰራር ማለትም ጉዳይን በቶሎ ከፍሎ ማስፈጸም (practice of “speed payments”) ተግባር አምርቶ ኢንቨስተሮች ፈቃድ ለማግ ኘት ሲሉ መደለያ እና ማግባቢያ ገንዘብ ለነቀዙ ባለስልጣናት ወይም ወኪሎች እንዲከፍሉ ሊገደዱ ይችላል፡፡

ስለዚህ ዋናው የኢንቨስትመንት ኤጄኒሲዎች/ኮሚሽኖች ሥራ የሚሆነው ወደ እራስ ዞር ብሎ መመልከት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለምን ቢባል በኢንቨስትመንት ሊሰማሩ የነበሩ ባለሃብቶች የተባለው ማስታወቂያ እና በተግባር ያዩት ነገር ያልተጣጣመ እነደሆነ በኢንቨስተመንት ኢጄንሲዎች ላይ ተስፋ መቆረጥን ጨምሮ ተከድተኛል የሚል ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡

ይህንን አስተዳደራዊ ችግር ለማስቀረት በማሰብ በተለየም ለውጭ ኢንቬስተሮች የኢንቨስትመንት ኤጄንሲ የመጀመሪያው መግቢያ እንደ መሆኑ መጠን የተባሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ አካባቢ የአስተዳደራዊ እንቅፋቶችን ለማስቀረት በማስብ የአንድ መስኮት አገልግሎት (“One-Stop Shop Service”) ተጀመረ በዚህ የተነሳ በርካታ የኢንቬስተሮችን እሮሮ እና እንግልት ሊቀንስ ችሏል፡፡

የዚህ ጹሑፍ ዋና ዓላማ ስለ አንድ መስኮት አገልግሎት ምንነት መዳሰስ ቢሆንም በመጠኑም  ቢሆን ስለ ኢንቨስትመንት ምንነት ከዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆዎች አንጻር አጭር ዳሰሳ ካደርገ በኋላ፣ የኢንቨስትመንት አይነቶችን ይዘት፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የሌሎች አገራት ተሞክሮን የሚዳስስ ይሆናል፡፡

1.  የኢንቨስትመንት ምንነትና አስፈላጊነት ከዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆች አንጻር

በዚህ ክፍል የምንመለከተው ደግሞ ስለ ኢንቨስትመነት ምንነት እና አስፈላጊነት ሲሆን በተለይም የታወቁ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መርሆ አንጻርም በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

ስለ ኢንቨስትመንት ትርጓሜ የተለያዩ ድርሳናት የተለያዩ ትርጉም ሰጥተውት እናገኛለን፡፡ የቢዝነስ መዝገበ ቃላትም ኢንቨስትመንት ማለት ገንዘብን ፈሰስ አድርጎ ንብረት ወይም ዋስትናን(security)መግዛት ሲሆን አላማውም ትርፍን ማካበት ነው፡፡ /Investment means putting  money into a business venture, or to buy property or securities, with the intention and expectation of making a profit./

ከላይ ከተቀመጠው ትርጓሜ የምንረዳው ነገር ኢንቨስትመንት ማለት አንድ ባለሃብት ያለውን ንዋይ (ገንዘብ) ወጪ በማድረግ ሌላ ንብረት ለማግኘት የሚያደረገው እንቅስቃሴ ነው፡፡

ሌላው የኢንቨስትመንትን ትርጓሜና ይዘትን አስመልክቶ አገራት በሁለትዮሽ ስምምነቶች ሊወሰኑት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡-የኢትዮ-እንግሊዝ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት አንቀጽ 1(ሀ) ላይ ኢንቨስትመንት የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ተርጉሞት እናገኛለን፡-

“ኢንቨስትመንት ማለት ምንም እንኳን በሚከተለው ዝርዝር ባይገደብም ማነኛውም ዓይነት የንብረት ፈሰስ በተለይም ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ጨምሮ ሌሎች የንብርት መብቶች እንደ መያዣ ያሉትን፤በስቶክ ገበያ ያለ አክሲዮን እና የአክሲዮን ማህበራት የብድር ቦንድ( debentures) ፤ በውል አፈጻጸም ላይ ያለ ገንዘብ መብት ጥያቄ( Claims to money)፤የአዕምሮዊ ንብረት መብቶች፤መልካም ስም( goodwill)፤የቴክኒክ አካሄዶች እና የአሰራር እውቀት እንዲሁም የቢዝነስ ኮንሲሼዮን ማለትም የተፈጥሮ ሃብትን ለማውጣት የሚደረጉ የኮንሴሺዮን ውሎች( business concessions contracts) ሊይዝ ይችላል፡፡ ”

ከላይ ከተቀመጠው ትርጓሜ በአብዛኛው ሁሉንም ንብረቶች ማለት ይቻላል ጥበቃ እና ከለላ ይሰጣል፡፡ ወደ በኋላ የምናነሳው ቢሆንም ቅሉ ትርጓሜው ከዓለም አቀፍ መርሆዎች አንጻር በአገራት ቀዳሚነት(realism theory) የተቃኘ ይመስላል፡፡

በአብዛኛው የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች መጀመሪያ አናቅጽ ላይ ትርጓሜ ሲሰጡ የሚያስቀምጡት ሀረግ ኢንቨስትመንት ማለት መነኛውም ወይም ሁሉም ዓይነት ንብረት investment means “every kind of asset” or “any kind of asset” የሚል ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁ.769/2005 አንቀጽ 2(1) ላይ ኢንቨስትመንት የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፡-

“ኢንቨስትመንት ማለት አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ወይም ነባር ድርጅትን ለማስፋፋት ወይም ለማሻሻል በባለሃብት በገንዘብ ወይም በዓይነት ወይመ በሁለቱም የሚደረግ የካፒታል ወጪ ነው፡፡ ”

ይህ ዓይነቱ ትርጓሜ ደግሞ ከላይ በሁለትዮሽ ስምምነቶች ከተገለጸው ወጣ ባለመልኩ ማለትም አንድን ድርጅት ማቋቋምና ማሻሻል ይህም የንግድ ማሃበራትን ማቋቋም ጨምሮ በግል ካፒታልን ወጪ በማድረግ ሊሆንይቻላል፡፡

ይህም ሲሆን የመዋጮው ዓይነትም ወይ በጥሬ ገንዝብ አሊያም በዓይነት ወይም በሁለቱም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ካፒታል ስንል ማነኛውም የአገር ውስጥ ወይም የውጭ አገርገንዘብ፣ ተላላፊ ሰነድ( negotiable instruments) ፣ የማምረቻ ወይም የመስሪያ ዕቃዎች፣ ግንባታዎች፣ የመስሪያ ገንዘብ፣ የንብረት መብቶች፣ የፈጠራ መብቶች(Patent rights)  ወይም ሌሎች የንግድ ሃብቶች ሊሆን ይችላል፡፡ (የአዋጅ ቁ.769/2005 አንቀጽ 2(3) ይመለከተዋል፡፡ )

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢንቨስትመንት ለአንድ አገር እድግት ወሳኝ በመሆኑ በሌላ አባባል የውጭ ምንዛሬ ማምጣቱ፤የሥራ እድል መፍጠሩ፤የከተሞች መስፋፋትን ማፋጠኑ ወዘተ በማምጣቱ  አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም ሆኖም ግን ከአካባቢያዊ ጥበቃ ሥራዎች እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ አንጻር በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ጥላ ቢያጠላም ከእነ ጥቅም እና መዘዙ ክርክሩ አሁንም ቀጥሏል፡፡

እንደሚታወቀው የኢንቨስትመንት አስፈላጊነት በተመለከት የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ በተለይም በዓለም አቀፍ ግንኙነትም የሚጠቀሱ በርካታ ንድፈ ሃሳቦች አሉ፡፡ በዚህ ጹሑፍ ሦስቱን ብቻ ማለትም ሪያሊዝም (realism) አስተሳሰብ፣ ሊብራሊዝም(liberalism) እና ማርክሲስ (Marxism) አስተሳሰብን ከዓለምአቀፍ የፖለቲካ ምጣኔ ሃብት ንድፈ ሃሳቦች አንጻር በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡

1.1.        ሪያሊዝም(realism) ንድፈ ሃሳብ

በዚህ አስተሳሰብ የሰው ልጅ ታሪክ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት ሲባል በጦርነቶች የታጀበ ነው፡፡ የዚህ አስተሳሰብ በተለይም ኢንቨስትመንትን ጨምሮ መሰልኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከት መርካነታይል (mercantilism) ስርዓት ማለትም የንግድ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ ሲባል ወደ ውጭ አገራት ምርቶች እና ዕቃዎችን መላክ ላይ ትኩረቱን አድረጎ ይሰራል፡፡ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት አገራት እራሳቸው በኢንቨስትመንቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ ይሆኑበታል፡፡ በተለይም አገራቱ በኮንሲሽናዊ ውሎች (concession contracts) ላይ ተሳታፊ በሚሆኑበት ወቅት ከኢንቨስትመንቱ ተቀባይ አገር (host state) ያለው ግንኙነት በቁልምጫ ካልሆነም በቁንጥጫ ወይም በመላ ካልሆነም በዱላ መርሆ (carrot and stick doctrine) ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

በተለይም የዓለም ንግድ አባል ሆነው ንግድን የሚመለከቱ የኢንቨስትመንት እርምጃዎች ስምምነትን(Trade related investment measures agreement) የፈረሙ አገራት ስለሚሰጡት የኢንቨስትመንት ጥበቃ እና ከለላ አንድም ልክ ለአገራቸው ዜጋ እንደሚያደረጉት(National treatment) በአንቀጽ 2 እንደተመለከተው ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ አሊያም ድግሞ ልዩ ጥበቃና ጥቅም የሚያስፈልጋቸው አገራት (Most favored Nation) የሚሉ መርሆዎችን የሚያስቀምጡበት ምክንያትም ለአገራቸው በአጻፈው(tit-for-tat investment) የሚያገኙት ጥቅም ስላለ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-በኢትዮ-እስራኤል የሁለትዮሽ የኢንቨስትመንት ስምምነት አንቀጽ 3 ላይ እንዲህ የሚል ዐ.ነገር እናገኛለኝ፡-“Neither Contracting Party shall, in its territory, …[sic]… to treatment less favorable than that which it accords …to investments or returns of  investments of an investor of any third state.”ይህም ማለት ሁለቱ አገራት ለሌላ ለሦስተኛ አገር እንደሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ጥበቃ ሁሉ እርስ በእርሳቸውም ይህንን ለማድረግ ተስማምተዋል ማለት ነው፡፡

በአጭሩ በሪያሊዝም አስተሳሰብ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ የሚሆነው የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚስከብር ሲሆን ነው፡፡

1.2.       ሊበራሊዝም (Liberalism) አስተሳሰብ

በዚህ አስተሳሰብ ደግሞ ኢንቨስትመንት ነጻውን የንግድ አካሄድ(free trade thesis) መሰረት በማድረግ መከናወን አለበት፡፡ ይህንንም እንቅስቃሴ አገራትም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማትምንም እንኳን ለአፈጻጸሙ ሕግጋትን እና ስታንዳርዶችን የማውጣታ አላፊነት ቢኖርባቸውም አተገባበሩን ማደናቀፍ የለባቸውም፡፡ ይህ አስተሳሰብ ኢንቨስትመንትን በተለያየ ምክንያት መገደቡን አጥብቆ ይቃወማል፡፡ ለምን የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ የሚችለው ኢንቨስትመንትን ጨምሮ መሰል የንግድ እንቅስቃሴዎችን ነጻ በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁ.769/2005 አንቀጽ 7 እና የኢንቨስተመንት ደንብ ቁ.270/2005 አንቀጽ 3 በተለይም የባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ ብሮድ-ካስቲንግ፣ ወዘተ ዘርፎች ለአገር ውስጥ ባለሃብት ብቻ መሰጠቱ በዚህ ንድፈ ሃሳብ መሰረት ተቀባይነት የለውም፡፡

1.3.       ማርክሳዊ (Marxism) አስተሳሰብ

ይህ ግራ ዘመም አስተሳሰብ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱት በተቃራኒው ኢንቨስትመንት የጥቂቶች መጠቀሚያ እና የካፒታሊስቶች መመዝበሪያ መንገድ( investment as a means of exploitation) አድረጎ ያቀርባል፡፡ በተለይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስተምነት እየተባለ የሚደረገው የኢኮኖሚ ዘረፋ ካፒታሊስቱን የበላይ ቀሪውን ሕዝብ ደግሞ ጥገኛ ያደርጋል ብለው ይሞግታሉ፡፡

2.  የኢንቨስትመንት ዓይነቶች

በዚህ ክፍል ደግሞ ስለ ኢንቨስትመንት አመዳደብ በአጭሩ የምንመለከት ይሆናል፡፡ በታወቁ ድርሳናት ላይ ሰፍሮ እንደምናገኘው ኢንቨስትመንት ከገንዘብ ምንጭ አንጻር በሁለት ዐበይት ዘርፎች ይመደባል፡፡ እነዚህም፡- የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት እና የውጭ ኢንቨስትመንት ናቸው፡፡

የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት የሚባለውም ፈሰስ የሚደረገው የካፒታል ወይምየገንዘብ ምንጭ ከአገር ውስጥ ሲሆን ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚባለው የካፒታል ምንጩ ከባህር ማዶ ሲሆን ነው፡፡

የውጭ ኢንቨስትመንት በስፋት ስንመለከተው እንደገና በሁለት ዘርፎች ይከፈላል፡፡ ይህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት( foreign direct investment /FDI/) እና የተላላፊ ሰነዶች ኢንቨስትመንት     (portfolio investment) በመባል ይመደባሉ፡፡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ሚባለው ኢንቬስተሩ ወደ ኢንቨስትመነትቱ ተቀባይ አገር በቀጥታ በማምራት ለፕሮጀክቱ የሚውሉ መሳሪያዎችን በመትከል እንዲሁም በማቋቋም ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን በተላላፊ ሰነዶች የሚከናወነው ኢንቨስትመንት የሚባለው ደግሞ ኢንቬስተሩ ከባህር ማዶ ከሚገኝ አንድ ኩባንያ አክሲዮን(share) ወይም የግምጃቤት ሰነድ(bond) በመግዛት የሚያደርገው የገንዘብ ፍሰት ነው፡፡ የሆነው ሆኖ አሁን አሁን በሚፈረሙ በርካታ የሁለትሽ የኢንቨስትመንት ሥምምነት ሰነዶች ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናገኘው በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና በተላላፊ ሰነዶች የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች መካከል በተግባርም ሆነ በሕግ ጥበቃ ልዩነት አይደረግም፡፡ /አንቀጽ 1 ኢትዮ-እስራዔል ስምምነት ይመለከቷል፡፡ /

በመጨረሻም ከላይ የተጠቀሱት የአገር ውስጥም ሆነ የባሀር ማዶ ኢንቨስትመንት ከሚከተሉት ቅርጾች ውስጥ በአንደኛው መልክ ሊከናወን ይችላል፡፡ እነዚህም በግለሰብ(sole proprietorship) ፣ አገር ውስጥ ወይም ባህር ማዶ በተመሰረተ የንግድ ማህበር(business organizations) ፣ በሕግ በተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት(Public enterprises) እና አግባብነት ባለው ሕግ የተመሰረት ህብረት ሥራ ማሀበር(cooperatives’) ናቸው፡፡ (አንቀጽ 10 የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁ.769/2005 ይመለከተዋል፡፡ )

3.  የአንድ-መስኮት አገልግሎት

በዚህ ክፍል የምንመለከተው ደግሞ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ስለ አንድ መስኮት አገልግሎት ጽንሰ ሃሳባዊ ምንነት፣ የሌሎች አገራት ተሞክሮ እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎቹ እና ፈተናው ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

3.1.       ጽንሰ-ሃሳባዊ ምንነት

የአንድ መስኮት አገልግሎት በመግቢያው ላይ ለማመልከት እንደተሞከረው አስተዳደራዊ ቅሬታዎችን አስቀድሞ ለመፍታት በማስብ የተወጠነ ዘዴ ነው፡፡ ይህም ኢንቬስተሩ አንድን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ወጥኖ ተግባራዊ ሊያደርግ ሲል አጅግ በርካታ የሚባሉ ቅድመ ሁኔታዎች ከፊቱ ተጋርጠው ይጠብቁታል፡፡ በዚህም መሰረት አሰፈላጊውን ፈቃድ፣ ምዝገባ፣ እውቅና እንዲሁም የመሸኛ ፈቃድ (clearance)ለማግኘት እና ለማስፈጸም የተለያዩ የመንግስት መ/ቤቶችን በር ሊያንኳኳ ይችላል፡፡

ነገሩ ወዲህ ነው! በመጀመሪያ ኢንቬስተሩ የቪዛና የሥራ ፈቃድ ካገኘ በኋላ ወደ ሚቀጥለው ሂደት ያመራል፡፡ ከዚያም ኢንቨስትመንቱ በማህበር የሚከናወን ከሆነ አንድም የሚቋቋመው ማህበር እንደገና መመዝገብ (registration) እና በተቀባይ አገር ሕግ መቋቋም(incorporation) ይጠበቅበታል፡፡ ቀራጮችም(tax authorities) የተባለውን ድርጅት ግብር ለመሰብሰብ እና ለማስከፈል ሲባል መመዝገብ አለባቸው፡፡

እነዚህ የምዝገባ እና የፍቃድ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ሁኔታዎች በተለይም የውጭ ምንዛሬ እና የገቢና ወጭ ግብይቶችን በተመለከተ ከፋይናንስ፣ ባንክ እንዲሁም የንግድ ጉዳዮች ቢሮ ዘንድ ቀርበው መጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚያም በየደረጃው ያሉ ባለስልጣናት ኢንቨስትመንቱ የሚያርፍበትን ቦታ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ከተማ ነክ የሆኑ ድጋፎችን ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ሌላው ሥራውን ለማስጀመርም የሚሆን የሰው ሃይል አስፈላጊ በመሆኑ በተለይም የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የውጭ አገር ሰራተኞች የሚቀጠሩ ከሆነ ደግሞ የኢሚግሬሽንና ደህንነት ኤጄንሲዎች በጉዳዩ ላይ መፍቀድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨመሪም አሁን አሁን ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት እየተሠጠ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የአካባቢ ተጽኖ ግምገማ(environmental impact assessment) መካሄድ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በባለሙያ ጥናት እና ክትትል ማድረግ ይጠበቃል፡፡

ታዲያ ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ ለመቅረፍ በማሰብ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ እየሆነ ሊመጣ ችሏል፡፡ በጽንሰ-ሃሳብ ደረጃ የአንድ መስኮት አገልግሎት ማለት በአንድ መስሪያ ቤት ሁሉምን ጉዳዮች ማለትም ኢንቬስተሩ የትም ቦት ሳይሄድ የምዝገባ፣ የሥራ ፈቃድ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጥናት እንዲሁም የመሸኛ ፈቃድ በአንድ ጣራ፣ በር ወይም መስኮት ስር  አገልግሎት የሚያገኝበት አሰራር ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ በተግባር እንደሚታየው ከሆነ የተለያዩ የአስተዳደር አካላት በሕግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት ይህንን ፈቃድ የመስጠቱን ጉዳይ በአንድ ማዕከል መሰብስብ መደበኛውን አስራር ሊያፋልስ ስለሚችል ላይቀበሉት ይችላል፡፡ እንዳንዴም በአስተዳድራዊ መ/ቤቶች የቢሮክራሲ ግትር አቋም የአንድ መስኮት አገልግሎት ወደ በርካታ መስኮቶች ሊያመራ ይችላል፡፡ (ፍራንክ ሳደር፡እኤአ 2003፡3) The “One-Stop Shop” has actually turned into a “one more stop”, as investors are now forced to interact with one more entity in the process of implementing their projects.”

በኢትዮጵያም የዚህ መሰሉ አገልግሎት ከተጀመረ ሃያ(20) ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤በይፋ የታወቀው ግን በአዋጅ ቁ.280/1994 ነበር፡፡ በተለይም በአንቀጽ 24 ላይየአንድ መስኮት አገልግሎት መጀምሩን እንዲህ ይገልጸዋል፡-

“የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸውን ባለሃብቶች በሚመለከት አግባብ ባለቸው ህጎች መሰረት የሚሰጡ የንግድ ሥራ ፈቃዶችን መስጠት፣ ለውጭ ዜጋ ተቀጣሪዎች የሚሠጡ የሥራ ፍቃዶችን መስጠትና የንግድ ማህበራትን መመዝገብ የሚመለከታቸውን የፌዴራል መንግስትን ወይም የክልል አስፈጻሚ አካላትን በመወከል እንደአግባቡ በባልስልጣኑ ወይም በክልል የኢንቨስትመንት አካላት ይከናወናል፡፡ ”

ከላይ በድንጋጌው ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደምናገኘው የአንድ መስኮት አገልግሎት በፌዴራሉ ኢንቨስትመንት ባለስልጣን ወይም በክልሉ ባለስልጣናት ይከናወናል፡፡ ይሀም የሆነበት ምክንያት አዋጁ የፌዴራል እና የክልል የኢንቨስትመንት ፈቃድ የመስጠት ስልጣን ብሎ በመክፈሉ ነው፡፡

በተለይም በይዘት ረገድ አዋጁ የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ዘርፎች በጣም ጠበብ ያሉ ናቸው፡፡ አነዚህም የንግድ ፈቃድ የመስጠት፣ ከስራ ፈቃድ እና ከንግድ ማሀበራት ምዝገባ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብቻ ናቸው፡፡

በአንጻሩ ደግሞ አዋጅ ቁ.769/2005 የቀደመውን አዋጅ ቁ.280/1994 ሽሮ ከጸደቀ በኋላ የአንድ መስኮት አገልግሎትንበአንቀጽ 30 ላይ በይዘትም ጭምር አሻሽሎታል፡፡ በተለይም አገልግሎቱ ወደ ከጉምሩክ ነጻ የመሆን ማበረታቻ የመፍቀድ፣ የግንባታ ፈቃድ መስጠት፣ መመስረቻ ጹሑፍና የመተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም ማሻሻያዎችን ማቅረብ፣ የንግድ ምዝገባ ማካሄድ፣ የንግድ ፈቃድ መስጠት፣ ለውጭ ዜጋ ተቀጣሪዎች የሥራ ፈቃድ መስጠት፣ ለኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭነት ለሚሰማሩ ደረጃ መስጠት እና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር(tax identification number/TIN/ መስጠትን ይጨምራል፡፡

ሆኖም ግን ከላይ በአንቀጽ 30(2) የተዘረዘሩ የአንድ መስኮት አገልግሎቶችን የሚያገኙ ባለሃብቶች በማምረቻ ዘርፍ (areas of manufacturing) የተሰማሩ ኢንቬስተሮች ናቸው፡፡ ይህም በአንቀጽ 30(1) ላይ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ታዲያ ይህ ማለት ኢንቬስተሮቹ ከማምረቻ ዘርፍ ውጪ ያሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የሚሰማሩ ከሆነ የአንድ መስኮት አገልግሎት አያገኙም ማለት ይሆን? አዋጁ ወሳኝ የአገሪቱን የወደፊት አቅጣጫ በሚያመላክትበት በመግቢያው ላይ እንዲህ ይላል፡-የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠንና የሕዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ኢንቨስትመንትንና በተለይም የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍን በማበረታታትና በማስፋፋት የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማጠናከር በማስፈለጉ እንደሆነ ይነግረናል፡፡

ታዲያ ከዚህ የፖሊሲ እሳቤ በመነሳት ይሆን እንዴ የማምረቻው ዘርፍ የአንደ መስኮት አገልግሎት እንዲያገኝ አዋጁ በግልጽ እውቅና ለመስጠት የሞከረው ወይስ ሕጉ በግልጽ የማምረቻ ዘርፍ ይበል እንጂ በተግባር ግን በማነኛውም ዘርፍ የተሰማሩ ኢንቬስተሮችን የአንድ መስኮት አገልግሎት ይሰጥ ይሆን? ቀኝም ነፈሰ ግራ በሕግ አተረጓጎም ቀኖና (canons of interpretation) መሠረት ህጉ ግልጽ ከሆነ መተርጎም አይሰፈልግም ስለዚህ አንቀጽ 30(1) ላይ ህጉ በግልጽ የማምረቻ ብሎ ስላስቀመጠ አገልግሎቱም መሆን ያለበት በዚሁ ዘርፍ ለተሳማሩ ባለሃብቶች ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአንድ መስኮት አገልግሎት ዓለማው የአስተዳደራዊ ውጣ ውረድን ለመቀነስ የሚተገበር ሥነ-ስርዓት እንጂ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ አይደለም ስለዚህ ለማምረቻ ኢንዱስትሪ ብቻ ፈቅዶ ለሌሎች መስኮች ዝግ ማድረግ ከአጠቃላይ የኢንቨስትመንት ዓላማ አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡

3.2.      የሌሎች አገራት ተሞክሮ

በአለም ባንክ በተካሄደ ጥናት መሰረት በዓለም ላይ የአንድ መስኮት አገልግሎትን በተመከተ በርካታ ሞዴሎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የአንድ በር አገልግሎት/one door or one roof approach/ ሲሆን ኢንቨስትመንትን የሚመለከቱ ፈቃድ ሰጭ አካላት በአንድ ጥላ ስር ሆነው ያለምንም መጉላላት ኢንቬስተሩ ጉዳዩን የሚያስፈጽምበት አካሄድ ነው፡፡ በዚህም አካሄድ የሚመለከታቸው ሚኒስቴር መ/ቤቶች እና ኤጄንሲዎች መተባበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ አመልካቹ በአንድ በኩል በአንድ ማዕከል ውስጥ ሆኖ የተለያዩ የመንግስት አካላትን ለየብቻ ሊያገኝ የሚችልበት መንገድ ነው፡፡ ምሳሌ፡-አንጎላ በዚህ ሞዴል ትጠቀሳለች፡፡

ሁለተኛው ደግሞ የአንድ መስኮት አገልግሎት ሞዴል/one window shop/ የሚባለው ደግሞ ኢንቬስተሩ አገልግሎት ለማግኘት ብሎ ጥያቄ በሚያቀርብበት ጊዜ ወደ አንድ የመንግስት ተቋም ያመራና ከዚያም ማመልከቻው የቀረበለት አካል የራሱን የፈቃድ መስጠት አገልግሎት ጨምሮ የሌሎችንም ኤጄንሲዎች ሥራ ደርቦ በማከናወን ተገልጋዩ ኢነቬስተር ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ሳያስፈልገው ጉዳዩን የሚያስጨርስበት አካሄድ ነው፡፡ በዚህም ፈቃድ ሰጭው አካል ስለሌሎች አካላት ፈቃድ አሰጣጥ ማወቅ እንዲሁም ስልጠና መውሰድ አለበት፡፡ ምሳሌ፡-ሮማኒያ

ሦስተኛው ሞዴል ደግሞ ከአንድ መስኮት ወደ ሌላ መስኮት ማለትም ክልዔ መስኮት/one more stop service/የሚስተናገድበት መንገድ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሞዴል የምዝገባ ተግባራትን ለማስተባበር የሚመሰረት ማህበር ይኖራል፡፡ ይህም ማለት የንግድ ምዝገባ፣ የግብር ከፋይነት ምዝገባ እና ሌሎችንም ምዝገባዎች የሚያከናውን አዲስ ማህበር ይመሰረታል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ይህንን ጉዳይ የሚያስፈጽምየኩባንያዎች ፎርማሊቲ ማዕከል/Center for Company Formalities/ የተባለ ማህበር አላቸው፡፡

አራተኛ ደግሞ የተቀናጀ አገልግሎት (integrated functions) የሚባለው ደግሞ አንድ ወጥ የሆነ የምዝገባ ሥርዓት ያለው አገርዓቀፍ የመረጃ ዳታ ቤዝ የምዝገባ ተግባራትን ሲያከናውን ነው፡፡ የምዝገባ ማዕከሉ የግብር ምዝገባ፣ የውጭ ሰራተኞች ምዝገባ እንዲሁም የንግድ ምዝገባ በተመሳሳይ ጊዜ ያከናውናል፡፡ ሌሎች የኩባንያ ምዝገባዎችን ደግሞ በሕግ ባለሙያ እገዛ በሌላ ጊዜ ይከናወናል፡፡ ምሳሌ፡-ሩሲያ፣ አልባኒያ እና አዛርባጃን ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የመጨረሻው ሞዴል ደግሞ የመረጃ ቴክኖሎጂ ማደግ ጋር ተያይዞ በዌብሳይት አማካኝነት የሚከናወነው ስርዓት ነው፡፡ በዚህ ሞዴል መሰረት አመልካቹ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በቀጥታ የመረጃ መረብ ምዝገባ (online registration services) አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ፡ሲንጋፖር ማነኛውም የቢዝነስ ተኮር ምዝገባ በቀጥታ መረጃ መረብ ይከናወናል፡፡ ልሎችም አገራት እንደ ካናዳ እና ሃንጋሪ የዌብሳይት ምዝገባ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በመጨረሻም ጸሀፊው ከላይ በአቀረባቸው ሞዴሎች መሰረት የሌሎች አገራት ተሞክሮ የሚያሳየው የአንድ መስኮት አገልግሎቱ አሰጣጥ ለሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያው የአንድ መስኮት አገልግሎት ውሱኑነት ይታይበታል ለምን ቢባል የአንድ መስኮት አገልግሎቱ በማምረቻ ዘርፍ ለሚሰማሩ ኢንቬስተሮች ብቻ መሆኑ ነው፡፡

3.3.      መልካም አጋጣሚዎች እና ፈተናው

የአንድ መስኮት አገልግሎት ሲከናወን አልጋ በአልጋ የሆነ ሁኔታዎችን አግኝቶ ብቻ ሳይሆን ብዙ ውጣ ውረዶች እና ፈተናዎችን ተቋቁሞ ነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ መልካም አጋጣሚዎችንና ምቹ ሁኔታዎችን በጥቂቱ መለከት እናድርግ፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት ጊዜና ገንዘብን የሚቆጥብ አሰራርበመሆኑ እንዲሁም ኢንቬስተሩ የሚፈልገውን አገልግሎት የሚያገኝበትበመሆኑ ሂደቱን ተጠባቂ (predictable process) ያደርገዋል፡፡ ሌላው ምቹ አጋጣሚ የሚሆነው በመላው የአለም አገራት ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ተገባራዊ የሆነ አሰራር በመሆኑና ይህንን አሰራር የዘረጉ አገራት እንደ ኢንቨስትመንት ወዳጅ ተደርገው መወሰዳቸው ነው፡፡

ወደ ተግዳሮቶቹ ስናመራ ደግሞ እንደሚታወቀው የአንድ መስኮት አገልግሎት ጥልቁ ጋሬጣ የአስተዳደር ሕግ ብሂሎች ማለትም የሥልጣን ክፍፍል መርሆ(principle of separation of power) እንዲሁም የውክልና ሥልጣን አለመወከሉ(non-delegablity of delegated power doctrine) የተባሉት አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት ታዲያ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች፣ የታክስና ገብር ስወራ ጉዳዮች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ልዩ ችሎታ(specialized expertise) የሚጠይቁ በመሆናቸው የአንድ መስኮት አገልግሎት በመስጠት የተጠመዱ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን/ኤጄንሲ ሰራተኞች የተባሉ ጉዳዮችን ለማስተናገድ የተባሉትን ጥንቃቄና ዝግጅት ማድረግ አለበቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ ግን የመንግስት ፖሊሲንና ስትራቴጂዎች የሚያፋልስ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም የሚነሳው ችግር የአንድ መስኮት አገልገሎትን ለመስጠት የሚፈጀው ጊዜ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት አገልግሎቱን ለመስጠት የሚታዩ መዘግየቶች እንደ ፈተና ይወሰዳል፡፡

4.  ማጠቃለያ

ኢንቨስትመንት ማለት ገንዘብን ፈሰስ አድርጎ ንብረት ወይም የዋስትናን መብቶችን መግዛት ሲሆን አላማውም ትርፍን ማካበት ነው፡፡ የኢንቨስትመንትን አስፈላጊነት አስመልክቶ በርካታ ንድፈ ሃሳቦች ይቀርባሉ፡፡ ለአብነት ያህልም የሪያሊዝም (realism) አስተሳሰብ፣ የሊብራሊዝም (liberalism) እና ማርክሲስ (Marxism) ንድፈሃሳቦች ሲሆኑ በሪያሊዝም አስተሳሰብ መሰረት ኢንቨስትመንት የአገራትን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ አለበት ሲል ሊብራሊዝም በአንጻሩ የአንቨስትመንትን አስፈላጊነት ከነጻ ንግድ ጋር ያያይዙታል በመጨረሻም ማርክሲዝም የተባለው አስተሳሰብ ደግሞ ኢንቨስትመንት አስፈላጊ ቢሆንም የካፒታል መደቡ መጠቀሚያ መሆኑን ግን ንደፈሃሳቡ ይቃወመዋል፡፡ ኢንቨስትመንት ከምንጩ በመነሳት የውጭ ኢንቨስትመንትና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ተብሎ ሊመደብ ይችላል፡፡ ኢንቨስትመንት በሚከተሉት ቅርጾች ሊከናወን ይችላል፡፡ እነዚህም በግለሰብ፣ በንግድ ማህበር፣ በሕግ በተቋቋመ የመንግስት የልማት ድርጅት እና በህብረት ሥራ ማህበር መልኩ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ የአንድ መስኮት አገልግሎት እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ አካባቢ ከተጀመረ አንስቶ በርካታ የሆኑ የአስተዳደራዊ እንቅፋቶችን በማስቀረት ረገድ የጎላ ሚና መጫወቱ የሚታወስነው፡፡ በአገራችንም የኢንቨስትመንትን ፈቃድ አሰጣጥን አስመልክቶ የአንድ መስኮት አገልግሎት ከተጀመረ ሁለት አስርት አመታትን ቢያስቆጥርም አሁን አሁን አገልግሎቱ ለማምረቻ ዘርፍ መደረጉ የአገልግሎቱን አድማስ ጠበብ አድርጎታል፡፡ በመጨረሻም የአንድ መስኮት አገልግሎት በማምረቻ ዘርፍ ብቻ የሚለው አሰራር በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ኢንቨስተሮችን ገና ከጅምሩ ላያበረታታ ከማስቻሉ ባሻገር ኢንቬስተሮች በተለመደው የመንግስት አሰራር መሰላቸት የተነሳ ያላቸውን ንዋይ(ገንዘብ) ፈሰስ ላያደርጉ ወደ መጡበት አገር ሊያመሩ ይችላል፡፡ ስለዚህ የዚህን መሰሉ አገልግሎት ለሁሉም የኢንቨስትመንት ዘርፎች ቢሆን መልካም ነው፡፡ 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ተከላካይ ጠበቃ ስለማግኘት መብት ጥቅል እይታ
The Application of other public international laws...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 12 October 2024