Font size: +
4 minutes reading time (704 words)

የሁለት ኢትዮጵያውያን ወግ: የቀድሞውና አዲሱ ኢትዮጵያዊነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሊታረቅ ይችላል ወይ?

የዛሬ ሳምንት "የሁለት ኢትዮጵያውያን ወግ፡ የቀድሞውና አዲሱ ኢትዮጵያዊነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሊታረቅ ይችላል ወይ?" በሚል ርእስ ላይ ንግግር (public lecture) አድርጌ ነበረ። ንግግሩ እንደወረደ ነበረ፣ በኋላ አዘጋጁ የሬይ ዊተን ፎረም አጠር ያለ መግለጫ ስጠን ብለውኝ እንደምንም (የማስታውሰውን) ፃፍኩት። የሥራ ጥድፊያ ምናምን ስለነበረ በጽሑፉ አልረካሁም፣ እንዳወራሁት አልሆነም ቢሆንም ብዙ ጓደኞቼ በቦታው ባትኖሩም ለምን እንደብቃለን ብለን እነሆ ጀባ ብለናል፡፡ 

አገራችን ኢትዮጵያ ዜጎቿ (በተለይ ልሂቃኑ) ለሁለት ተከፍለው ሁለቱም የየራሳቸውን ትክክለኛ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚሉትን ማንነት አንዱ በሌላው ላይ እና በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ ለመጫን እየሞከሩ ነው። አንዱ ሌላውን በማንኛውም መንገድ ለመርታት ስለሆነ ትግላቸው የመጠፋፋት ፖለቲካ ነው የያዙት። አንደኛው ወገን ከጥንት እስከ ደርግ መንግሥት ድረስ የዘለቀውን ኢትዮጵያዊነት እንደ እውነተኛ ይወስዳል። ሁለተኛው ደግሞ አሁን በተለይ ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በኋላ የተፈጠረውን ኢትዮጵያዊነት እንደ እውነተኛ ይቆጥራል። አንደኛው ሁለተኛውን በታኝ፣ ከፋፋይ፣ የረጅም ዘመን አኩሪ ታሪካችንን የካደ እና ያዋረደ ነው ይለዋል። በተጨማሪም ብሔር ወይም ጎሳ ዘመናዊ ያልሆነ ጥንታዊና ለሰው በሰውነቱ እውቅና እንዲሁም ክብር የማይሰጥ ኋላቀር መገለጫ ነው ይላል። ስለዚህ ሕገ መንግሥት የግለሰብ ነፃነትን ብቻ ማስከበር ሲገባው የጋራ በተለይ የብሔር መብት ማካተቱ ያለተገባና የግል ነፃነትን ለመጨፍለቅ ያለመ ነው ብሎ ያምናል። ሁለተኛው አንደኛውን በጨቋኝነት ወይ ለጨቋኞች ሥርዓት ተቆርቋሪነት ይከሰዋል። የቀድሞው ኢትዮጵያዊነት የብሔሮችን ማንነት የካደ፣ ንብረታቸውን የዘረፈ፣ ልጆቻቸውን የገደለ፣ ግፈኛ እና በግድ የተጫነ ነው ይለዋል። ስለዚህ የአገሪቱ ችግር በዋናነት የብሔር ጭቆና በመሆኑ እሱን የሚያስወግድ በብሔሮች ነፃ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አዲስ ኢትዮጵያዊነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ተፈጥሯል ብሎ ያውጃል። የግለሰብ ነፃነት ቢኖርም ከዛ ይልቅ የጋራ መብቶች ላይ ትኩረቱን በማድረግ የሕገ መንግሥቱን ልደት እንኳ በብሔር ብሔረሰቦች ቀን ተሰይሟል። ግለሰቦች የግድ በብሔር አማካኝነት ኢትዮጵያዊ የሚሆኑ ተደርጎ ይወሰዳል። በአጠቃላይ አንዱ ሌላውን እውነተኛ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ እና ጠላት እንደሆነ ይወተውታል፣ ለማጥፋትም ተግቶ ይሠራል።

የእነዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነቶች ትልቅ ስህተት አንዱ በአንዱ ላይ አሸናፊ ለመሆን መሞከራቸው ነው። በተጨማሪ ሁለቱም ስለሕገ መንግሥት የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘዋል። ሕገ መንግሥት የግል እና የጋራ መብቶችን አንድ ላይ ያከብራል፣ በምዕራፍ ሦስት ሳያበላልጥ እኩል ክብር ይሰጣቸዋል። በዛ ላይ ሕገ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ስለሆነ እራሱ ካላዘዘ በቀር በአንቀፆቹ መካከል ማበላለጥ የበላይነቱን መካድ ነው። ሌላው መብቶች የጋራ መሠረተ ሐሳብ አላቸው፣ ይኸውም የመምረጥ እና የአማራጭ ነፃነት (freedom of choice) ነው። ሁሉም ሰው እኩል ነው። ስብእናውን፣ እድሉን፣ እምነቱን፣ ከሌሎች ጋር የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም ማንነቱን የመምረጥ ወይ የመወሰን ሥልጣን ወይ ነፃነት አለው። ይሄ በተለያዩ መብቶች ውስጥ ይገለፃል። ስለዚህ ብቸኛው ወሳኝ እራሱ ግለሰቡ ብቻ ነው። ሐይማኖት ይኑረው አይኑረው፣ ካለው የትኛው ይሁን የሚለውን የሚወስነው ግለሰቡ ነው። ይህ የሐይማኖት ነፃነት ነው። ይናገር ወይ ዝም ይበል መወሰን የመናገር ነፃነቱ ነው። ስለዚህም ማንነቱን መወሰን፣ በብሔር ይሁን በሌላ መገለጫ ይሁን ብሎ መወሰን የግለሰቡ ነፃነት ነው። የብሔር ማንነት ከመረጠ ግን እሱ ሊከበር የሚችለው በጋራ ተመሳሳይ ማንነት ካላቸው ጋር ነው። ምክንያቱም በዛ ውስጥ ያሉት መብቶች የባህል፣ የቋንቋና ራስን በራስ የማስተዳደር ስለሆኑ ነው። የግል መብቶች፣ ለምሳሌ የመዘዋወር እና በፈለጉበት የመኖር መብት በመላ አገሪቱ ሲከበር የጋራ መብት የሆነው የብሔር ማንነት መብት ግን ብሔሩ በሰፈረበት አካባቢ የተወሰነ ነው። ግን መጀመሪያ ላይ የመወሰን ነፃነቱ ግለሰባዊነቱ የተከበረ ነው፣ ምሳሌ ሐይማኖት ይኑረኝ አይኑረኝ ወይም ምንነቱን ብጠየቅ ያለመመለስ መብት እንዳለኝ ሁሉ ለብሔር ወይ ሌላ ማንነትም ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ መንግሥት በየመሥሪያ ቤቱ የሚጠቀማቸው ፎርሞች በግለሰቦች ሲሞሉ ሐይማኖት እና ብሔር የሚሉ ቦታዎች የግድ መሆን አይችሉም። ለግለሰቡ ምርጫ የተተዉ ናቸው። ሲፈልግ ብሔር የለኝም፣ ወይ አለኝ ካለ ብሄሩን፣ ካሰኘው ኢትዮጵያዊ፣ አሊያም ዝም ማለት መብቱ ነው። ይሄን የሚቃረን አንድም አንቀፅ ወይ እንድምታ በሕገ መንግሥቱ የለም። የመዘዋወር ነፃነት እና የመምረጥ ነፃነትን ያለ ምንም የብሔር ቅድመሁኔታ ተፈፃሚ የሚሆኑ መብቶች (የብሔር መብት ገደብ) ናቸው፣ የእኩልነት መብት ለሁሉም መብቶች እንደሚሠራም መረዳት ያስፈልጋል።

በዚህ አረዳድ ከሄድን አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሊስማሙ ወይ ሊታረቁ ይችላሉ። ዋናው የሚያስወግዱት ማስገደድን ነው። በግለሰብ ወይ በሕዝብ ላይ አመለካከቱን ለመጫን መሞከር ነው የኢትዮጵያዊያን ትልቁ ችግር። ባየነው መሠረት ደግሞ የነፃነት ተፃራሪ ማስገደድ ነው፣ በማንኛውም መልኩ ሰውን ማስገደድ ክልክልም ነው። የፈለግነውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ይዘን መቀጠል መብታችን ነው። የቀድሞው ታሪካችንን በግልፅ እየተወያየን፣ በሚያኮራው እየኮራን፣ በሚያሳፍረው እያፈርን፣ ከአሁኑ ማንነታችን የተነጠለ ሳይሆን አንድ ወጥ ታሪክ በተለያየ ምእራፍ እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው።

ይህ አረዳድ በኢትዮጵያ ማንኛውም ዜጋ በአመለካከቱ ወይም በማንነቱ ምክንያት እንዳይገለል፣ ታሪክን ለማረም ሌላ ታሪካዊ ስህተት እንዳይደገም ይረዳል። ሌላው እስካሁን ሕገ መንግሥትን የገዥው ፓርቲ አድርጎ በመውሰድ ፓርቲው የሚሰራው ሥራ (ስህተት) የሕገ መንግስቱ እንደሆነ ማሰብ የለብንም። በተመሳሳይ ገዥው ፓርቲ ሲፈልግ የራሱ ብቻ አድርጎ ሲያቀርበውም ስህተት በመሆኑ ልንከላከል ይገባል። ሕገ መንግሥት አንዴ ተፅፎ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ትርጉሙ የሁላችንም ነው፣ ነገር ግን ሥልጣን ያለው ተርጓሚ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። በቤኒሻንጉል ክልል ምርጫ ጋር ተያይዞ የቀረበለትን የመመረጥ መብት ጉዳይ በ1995 ዓ.ም ምክር ቤቱ ሲወስን የሰጠው ማብራሪያ ይህን የኔን አረዳድ ያጠናከረልኝ ነበረ። ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ ላይ ተመርኩዤ ያለጥርጥር ይህን ማለት እችላለሁ: ኢትዮጵያዊ እህቴ ወይ ወንድሜ መሆኑ ብሔር ወይም ሌላ ማንነት ስላለው ወይ ስለሌለው አይቀየርም።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሕግ ሙያ አገልግሎትን መቆጣጠር፣ የሕዝብ ጥቅም፣ የግለሰብ ፍላጎትና የውድድር ...
የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ በኢትዮጵያ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 15 June 2024