በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔን እንደገና ስለማየትና በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ

በወንጀል ጉዳይ  የፍርድ ውሳኔ የሰጠው ፍርድ ቤት በድጋሜ ጉዳዩን ማየት ማለት ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ የፍርድ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የግዜ ገደብ ሳይኖረው ጉዳዩን በድጋሜ በተለያዩ ምክንያቶች ማየትና በድጋሜ ውሳኔ መስጠት ማለት ነው፡፡ በተለይም በዚህ ዘመን የሐሰት ሰነዶች የመቅረባቸው ጉዳይ እራስ ምታት በሆነበት፣ ሐሰተኛ ምስክርነትን መሠረት በማድረግ በተቃራኒ ተከራካሪ ወገንም ሆነ በፍርድ ቤቱ ሊደረስበት ባለመቻሉ የተሳሳተና የተዛባ የፍርድ ውሳኔ በሚሰጥበት ዘመን የእነዚህን ሐሰተኛ ማስረጃዎች ግዜ ሳይገድበው የሚያገኝ የወንጀል ጉዳይ ተከራካሪ ወደዛው ፍርድ ቤት በመሄድ የተገኘውን አዲስ ማስረጃ መሠረት በማድረግ ክርክር በድጋሜ አድርጎ ውሳኔው እንዲሰተካከል ለማድረግ የሚያስችል የሕግ አካሔድ መኖሩን አስፈላጊነት ሁሉም የሚስማማበት ነው፡፡ አንዳዴም እንደሚሰማው በህይወት ያለን ግለሰብ ገድለኃል ተብሎ ጥፋተኛ የተባለን ግለሰብ ሞተ የተባለው ግለሰብ በህይወት መኖሩ ቢታወቅ እንኳን ጥፋተኛ የተባለውን ግለሰብ ነፃ የሚያወጣ የሕግ አካሔድ ሊኖር የሚገባ ስለመሆኑም የሚያስማማ ነው፡፡ በቅርብ ግዜ በተላለፈ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ከሚያጋጥማቸው ጉዳዮች በመነሳት የሐሰት ሰነዶች እና የሐሰት ምስክርነት ጉዳይ ከግዜ ወደ ግዜ እየተበራከተ መምጣቱን ሲናገሩ መስማቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ይህን መሰል የፍትሕ ጠር የሆነ ተግባር ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳን ይህ ሁኔታ በታወቀ ግዜ ግን ጉዳዩን ውሳኔውን የሰጠው ፍርድ ቤት በድጋሜ እንዲያይ የሚያስችልና ሐሰተኛውን ማስረጃ እና የተሳሳተውን ውሳኔ ለማስተካከል የሕግ መሠረት ሊኖረን ይገባል፡፡

የሕጎች አጭር ቅኝት

አሁን በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ፍርድ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ በይግባኝ በተቀመጠው በ15 ቀን ውስጥ የውሳኔውን ግልባጭ መጠየቂያ እንዲሁም የውሳኔ ግልባጩ ከደረሰ በ30 ቀን ውስጥ የይግባኝ አቤቱታውን ውሳኔውን ከሰጠው ፍርድ ቤት አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ላለ ፍርድ ቤት በተሰጠው ወሳኔ ላይ ውሰኔውን በሰጠው ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት በኩል ይግባኝ ከማለት በስተቀር (የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 182፣ 187/1/ እና /2/ን መመልከት ይቻላል) አዲስ የሆነና ሐሰተኛ ማስረጃ ስለመቅረቡ የሚያስረዳ ማስረጃ አግኝቻለሁ በማለት ፍርዱን ለሰጠው ፍርድ ቤት ውሳኔውን በድጋሜ ለማየት አቤቱታ ለማቅረብ የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ የለም፡፡ በይግባኝ ቢታይም እንኳን አዲስ ማስረጃ ሊሰማ የሚችለው የይግባኝ ፍርድ ቤቱ የመሰማቱን ጉዳይ ካመነበት ብቻ ነው ይህም ሁኔታ በጠባቡ የሚታይ ነው(የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 194/1/ን መመልከት ይቻላል)፡፡ ከወንጀል ጉዳይ በተቃራኒው በፍትሐብሔር ጉዳይ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 6(1)(ሀ) እና (ለ) የመጨረሻ ፍርድ ወይም ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ የተሰጠው በሐሰት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሰነድ ወይም ሐሰተኛ ምስክርነት ቃልን ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቀስ የሆነ ተግባርን መሠረት በማድረግ ሲሆንና አቤት ባዩም ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት አስፈላጊውን ትጋት አድርጎ ለማወቅ ያለመቻሉን ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ እና እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ተግባሮች መፈፀማቸው ቢገለፅ ኖሮ ለፍርዱ መለወጥ ወይም መሻሻል በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችሉ እንደነበረ ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ በእነዚህ ምክንያቶች መነሻነት ፍርዱን ለፈረደው ወይም ትዕዛዝ ወይም ውሳኔውን ለሠጠው ፍርድ ቤት የተወሰነውን የዳኝነት ክፍያ በመክፈል አቤቱታውን ለማቅረብ እንደሚችል በግልፅ ያስቀምጣሉ፡፡

በዚህ ሕግ መነሻነት ሐሰተኛ ማስረጃን መሠረት አድርጎ የተወሰነበት የፍትሐብሔር ተከራካሪ የማስረጃውን ሐሰተኛነትና የማስረጃው ሐሰተኛነት በውሳኔው ላይ ያለውን ተፅዕኖ በማስረዳት ጉዳዩን ላየው ፍርድ ቤት በድጋሜ እንዲያየው ሊያቀርበው ይችላል ማለት ነው፡፡ በፍትሐብሔር መብቶች ላይ በሚደረጉ ክርክሮች ሐሰተኛ ማስረጃ ቢቀርብና ውሳኔ ቢያሳስት የማስተካከያ ሥርዓት ሲኖረው በወንጀል ጉዳይ ያውም በሰው ህይወትና ነፃነት ላይ በሚወሰንበት ጉዳይ ግን ካላይ እንዳየነው ሐሰተኛ ማስረጃን መሠረት አድርጎ የተሰጠን ፍርድ የማስረጃውን ሐሰተኝነትና በፍርዱ ላይ ያለውን ተፅዕኖ በማስረዳትም ጭምር ውሳኔውን ለሰጠው ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚያስችል ሕግ እስከ አሁንም የለም፡፡ በተለይም አሁንም በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት በወጣበት ግዜ ይህን ዓይነት አካሔድ ለምን እንዳላስቀመጠ የሚያስገርም ሲሆን ከዛ በኋላም ቢሆን በፍጥነት ጉዳዩን የሕግ አካል አለማድረግ ለችግሮች መነሻ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የአሠራሩ መኖር አስፈላጊነትና ሊሟሉ የሚገቡ ሁኔታዎች

ምንም ያክል ጠንካራ ጥረት ቢደረግ ሐሰተኛ ሰነድንንና በሐሰተኛ ምስክርነት መሠረት በማድረግ ጥቂትም ቢሆን የተሳሳተ ውሳኔ መሰጠቱ የማይቀር ነገር ነው፡፡ ፖሊስ በከባድ ጥንቃቄ ከዐቃቤ ሕግ ጋር ሆኖ ቢመረምርም ዐቃቤ ሕግም የጉዳዩን እውነትነት በማመን ክስ ቢመሰርትም ፍርድ ቤትም በዛው ልክ በጥንቃቄ ጉዳዩን ቢመለከትም አልፎ አልፎ እንደሚሰማው ሐሰተኛ ማስረጃን መሠረት አድርጎ የሚሰጥ ፍርድ እንደሚኖር ግን እሙን ነው፡፡ ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት በድጋሜ ግዜ ገደብ ሳይኖረው አዲስ ማስረጃ በተገኘ ግዜ እንዲያየው የሚያስልገውም ለዚህ ነው፡፡ የይግባኝ መብት መኖሩም ይህንን ችግር ሙሉ ለሙሉ ሊፈታው አይችልም፡፡ ምክንያቱም የሚገኘው አዲስ ማስረጃ ይግባኝ ሊቀርብ ከሚገባው ግዜ ገደብ (period of limitation) ካለፈ በኋላ ሊሆን የሚችልና የዚህን ዓይነት አሠራርም ብዙውን ግዜ የግዜ ገደብ ስለማይኖርበት፡፡ ሁለተኛ የይግባኝ ፍርድ ቤት አዲስ ማስረጃን ለመስማት የማይገደድ መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት አሠራር ባለመኖሩ ግን አንድ ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ ጥፋተኛ የተባለው የሐሰት ማስረጃን መሠረት አድርጎ እንደሆነ የሚያስረዳበት የቱንም ያህል ማስረጃ ቢኖረው በተለይም የይግባኝ ግዜው ያለፈ እንደሆነ ምንም ዓይነት ነፃ የሚወጣበት አሠራር አይኖርም፡፡ ስለዚህ ከላይ በምሳሌነት እንደገለጽነው በሐሰት ሰው ገድሏል ተብሎ የተመሰከረበትና ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ ሞተ የተባለው ግለሰብ በህይወት መኖሩን አስረድቶ ጉዳዩን ያየው ፍርድ ቤት በነፃ እንዲያሰናብተው የሚያስችል ሕግ የለም ማለት ነው፡፡ ምናልባት በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 9(1) መሠረት ቀድሞ ጥፋተኛ ተብሎ ቅጣት ተወስኖበት የነበረው ድርጊት በአዲስ ሕግ የማያስቀጣ እንደሆነ ቅጣቱ ሊፈፀም አይችልም፤ የተጀመረው ቅጣትም ወዲያውኑ ይቋረጣል ከሚለው በቀር ወይም በተግባር ይደረጋል እንደሚባለው በይቅርታ (ይቅርታ የማያሰጡ ወንጀሎች መኖራቸው ልብ ይሏል) ካልሆነ በቀር ጉዳዩን ላየው ፍርድ ቤት ማስረጃ አቅርቦ ነፃ መውጣት ወይም ነፃ የተባለን ጥፋተኛ ማሰኘት የሚያስችል የሕግ አሠራር የለም ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አሠራሩ የሕግ ድጋፍ ኖሮት በፍጥነት ወደ ሥራ ላይ ሊውል የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

ሊሟሉ የሚገባቸውን ሁኔታዎች በተመለከተ ከፍትሕብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ አዲስ ይወጣል ተብሎ ሲጠበቅ ከነበረው ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ እንዲሁም ከሌሎች ሀገሮች ልምዶች ስናይ ሁኔታዎቹ፡-

አንደኛ የመጨረሻ ፍርድ የተሰጠው በሐሰት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ሰነድ ወይም ሐሰተኛ ምስክርነት ቃልን የሞያ ምስክርነትን ጨምሮ ወይም ለፍርድ  ምክንያት የሆነው ትርጉም ሐሰተኛ እንደሆነ ወይም መደለያን ወይም ወንጀል ጠቀስ የሆነ ተግባርን መሠረት በማድረግ ሲሆን፣

ሁለተኛ  ተከሳሹ ወይም ዐቃቤ ሕግ  ፍርድ ከመሰጠቱ በፊት አስፈላጊውን ትጋት አድርጎ ለማወቅ ያለመቻሉን ለማስረዳት የቻለ እንደሆነ፣

ሦስተኛ የተዘረዘሩት ተግባሮች መፈፀማቸው ቢገለፅ ኖሮ ለፍርዱ መለወጥ ወይም መሻሻል በቂ ምክንያት ሊሆኑ ይችሉ እንደነበረ ለማስረዳት ተከሳሹ ወይም ዐቃቤ ሕግ የቻለ እንደሆነ ጉዳዩ ላይ ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት ግዜ ገደብ ሳይኖረው ጉዳዩን በድጋሜ አይቶ የተሳሳተ ማስረጃውን ለማስተካከልና በድጋሜ ማስረጃውን ለመመዘን ያስችለዋል ማለት ነው፡፡ (የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 6 እንዲሁም በ2001 (እ.አ.አ) ተዘጋጅቶ ቀርቦ የነበረው ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ የእንግሊዝኛ ትርጉም አንቀጽ 240ን መመልከት ይቻላል)፡፡

አቤቱታው ሊቀርብ የሚችለውም በሐሰት የተዘጋጀው ማስረጃ የቀረበበትና በዛም ምክንያት የተፈረደበት ወገን ይሆናል፡፡ በዚህም መሠረት ሐሰተኛው ማስረጃ የቀረረበት ተከሳሹ ከሆነ ተከሳሹ ለድጋሜ እይታ ለዛው ፍርድ ቤት ማመልከት ሲችል የተሳሳተው ማስረጃ የቀረበው በተከሳሽ ወገን ከሆነ ደግሞ ዐቃቤ ሕግ ወይም እንደ ነገሩ ሁኔታ የግል ክስ አቅራቢ (የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 44(1) መሠረት) ለድጋሜ እይታ ለዛው ፍርድ ቤት አቤቱታውን እንዲያቀርብ ይረዳዋል ማለት ነው፡፡

ማጠቃለያ

የወንጀል የፍርድ ጉዳይ በተለይም በተከሳሽ ላይ በሚፈረድ ወቅት በህይወትና ነፃነት ላይ እንደሚወሰን ሁሉ በሌላ በኩልም ተከሳሽ በነፃ ሲሰናበትም በተለይም የሐሰት ማስረጃ አቅርቦ ከሆነ በህዝብ ፍላጎትና በፍትሕ ሥርዓት ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ አኳያ በፍርድ ለሚፈጠሩ ስህተቶች የማስተካከያ መንገዱ እጅግ ሰፊ መሆን አለበት፡፡

ከዚህም በላይ የሐሰት ማስረጃዎችን የማቅረብ ልማድ ማደጉ እየተነገረ ባለበት ለእነዚህ አዳጊ የሆኑ ያልተገቡ አሰራሮችና አስተሳሰቦች ማምከኛውን መንገድ መዘየድም ብልህነት ነው፡፡ ከእነዚህ ማምከኛ መንገዶች አንዱም ይኸው ከላይ ያቀረብነው የመጨረሻ ፍርዱን የሰጠው ፍርድ ቤት የሐሰት ማስረጃ የቀረበበት ወገን የማስረጃውን ሐሰተኛነት የሚያስረዳበት አዲስ ማስረጃ ባገኘ ግዜ በማስረዳት ለድጋሜ እይታ የሚቀርብበት አሠራር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ይህ ጉዳይ የተካተተ በሕግጋት ውስጥም እንዲካተት የሚያመላክት ቢሆንም (በ2003 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ገፅ 61 መመልከት ይቻላል)  በአስገዳጅ ሕግጋት ውስጥ አሁንም ድረስ ተካቶ በፍርድ ቤቶች እየተሰራበት አይገኝም፡፡ እየተስተዋሉ ካሉት ችግሮች አንፃር አሠራሩን በፍጥነት በሕግ ድጋፍ ተሰጥቶት በፍርድ ቤቶች ውስጥ ሊሰራበት ይገባል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ችሎት መድፈር፡- ሕጉ እና የአሠራር ግድፈቶች
ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩ ፊልሞች ላይ የሚታዩ የሕግ ግንዛቤ ክፍተቶች
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 28 February 2024