Font size: +
9 minutes reading time (1847 words)

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩ ፊልሞች ላይ የሚታዩ የሕግ ግንዛቤ ክፍተቶች

ፊልሞችን ሰርቶ ለሕዝብ ማቅረብ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ የተቀመጠው ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አንደኛው መገለጫ ነው፡፡  ሀሳብን የመግለፅ መብት ከመንግሥት ገደብ (Limitation) ሊጣልበት የሚችለውም ውስን በሆነ ምክንያት እንደሆነ ይሄ ሕግ መንግሥት የሚያስቀምጠው ጉዳይ ነው (አንቀጽ 29/6ን መመልከት ይቻላል)፡፡ አዋጅ ቁጥር 533/2007 እና ከዛ በፊት የወጡ ሕጎችም ትልቅ ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባውን ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሊገደብ የሚችልበትን አግባብ ያስቀምጣሉ፡፡ ሀሳብን የመግለፅ መብት በሕግ የሚገደበውም ሦስት መሠረታዊ ፍላጎቶችን (Interests) ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ነው፡፡ እነዚህም፡-

1.     የሰዎችን ክብርና መልካም ስም፣

2.    የሕዝብን ሞራልና የወጣቶችን ደህንነት እና

3.    የሕዝብን ሰላም፣ ደህንነትና ሥርዓት ለማስከበር ሲባል ብቻ ነው ገደብ የሚጣለው፡፡

በፊልም ላይ የአንድን ሕግ ፅንሰ ሀሳብ በተሳሰተ መንገድ ስሎ ማሳየት ከነዚህ ፍላጎቶች የትኛውንም ለማስጠበቅ ገደብ ሊጣል ይገባል ለማለት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዓይነት የሕግ ፅንሰ ሀሳብ ስህተቶች በፊልሞች ውስጥ መኖራቸው ለገደብ ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉና ነገር ግን ሦስቱን ፍላጎቶች ከማስጠበቅ አንፃር ሊጣሉ የሚችሉ ገደቦችም በሕግ ላይ በግልፅ የሰፈሩና የተደነገጉ በትክክል እነኚህን ፍላጎቶች ለመጠበቅ የተደረጉ ስለመሆናቸው በደንብ መጠናት ይኖርበታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ይህ ሳይሆን በፊልሞቹ ላይ የሚታዩትን የሕግ ግንዛቤ ክፍተቶች ማሳየት ነው፡፡ ከላይ በተነሳው ጉዳይ ላይ ግን ጥናቶች ሊደረጉ እንደሚችሉ ጠቋሚ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ ፊልሞች ከግዜ ወደ ግዜ በቁጥር እየጨመሩ መምጣታቸው በተለያየ ሜዲያ ሲነገር ይሰማል፡፡ የሚሰሩት ፊልሞችም ከማዝናናት በዘለለ ማህበራዊ ግዴታ የሆነውን የማስተማር ተልዕኮም ሊኖራቸው እንደሚገባም ይታመናል፡፡ እየወጡ ከሚገኙ ፊልሞች መካከልም የችሎት ሥራን እንዲሁም የሕግ ጉዳይን በተመለከተ ጭብጥ በማንሳት ለዕይታ የሚቀርቡ ይገኙበታል፡፡ ብዙው የህብረተሰብ ክፍል የሕግ ዕውቀቱ አናሳ በሆነበት ሀገር ላይ ከተመልካቹ ወገን ተኩኖ ሲታይ በፊልሞቹ ላይ የሚስተዋለው የችሎት አካሔድና የሕግ ጉዳዮች ይዘት በትክክለኛው የሕግ ሥርዓት ውስጥ ይኸው በፊልሙ ላይ የሚስተዋለው ሂደት ትክክለኛ መገለጫ አንድና ያው አድርጎ ሊያስብ ይችላል፡፡ እንደ ሕግ ባለሙያ ሆኖ ሲታይ ደግሞ ስህተቶቹ ትኩረት ተደርጎባቸው ሊስተካከሉ የሚገቡ መሆናቸውን ያሳስባል፡፡ በተለይም በሕግ ላይ በግልፅ የተቀመጠን ጉዳይ ከሕግ ግንዛቤ ጉድለት በተሳሳተው መንገድ ስሎ ለዕይታ ማቅረብ ቀላል የማይባለውን የፊልሙን ተመልካች የተሳሳተ ግንዛቤ ሊያሲዝ ይችላል፡፡

በሌሎች ሀገሮች ለምሳሌም በአሜሪካ የዚህን ዓይነት በፊልሞች ላይ የሚታይ የሕግ ይዘት መዛባቶች ችግር ሲኖር የሕግ ጦማሪያን (Legal Bloggers) ጉዳዮቹን በጥልቀት እየመረመሩ ሲተቹ ይስተዋላል፡፡ በእኛ ሀገር ላይ ግን የዚህን ዓይነት ነገር ሲሠራ አይስተዋልም፡፡ የዚህን ዓይነት ትችት መስጠቱ ቢለመድና ቢኖር ኖሮ ለሎችም ፊልም ሰሪዎች በጉዳዩ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያደርጋቸው ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር በዚሁ በአሜሪካን ሀገር የሕግ ጉዳይ የሚያነሱ የተወሰኑ ፊልሞች በሕግ ትምህርት ቤቶች (Law Schools) ውስጥ በመማሪያነት ያገለግላሉ፡፡ ለዚህ ደረጃ የሚያበቃቸውም የሀገሪቱን ሕግና የሕግ አካሔድ በአግባቡ ተገንዝበው አስፈላጊ ሲሆንም የሕግ ባለሙያ አማክረው ትክክለኛውን የሕግ ሥራ በፊልማቸው ውስጥ ስለሚያካትቱ ነው፡፡ የእኛ ሀገር ፊልሞች ለዛ ደረጃ እንኳን ባይደርሱ የተሳሳተ የሕግ ግንዛቤ ባያሲዙ ይመረጣል፡፡ ቢሆን ቢሆን ደግሞ የሕግ ሥነ ሥርዓት ማስተማሪያም ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ በትያትር በኩል ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የተሠራው 3ኛው ችሎት የሚለው ቲያትር በማስተማሪያነት ለመቅረብ እጅጉን የቀረበ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በዚህ ቲያትር ላይ የምንመለከታቸው ሁነቶች ሕግና ፍትሕ እንዴት በተዛባ መንገድ ሊሄዱ እንደሚችሉና በጥንቃቄ ጉዳዮች ካልታዩ ከፍተኛ የሆነ የፍትሕ መጓደል (Miscarriage Of Justice) ሊከሰት እንደሚችልና በሰው ህይወትና ነፃነት ላይ ጭምር የተሳሳተ ውሳኔ በምን አግባብ ሊሰጥ እንደሚችል ለሕግ ባለሙያውም ለሌላውም ተመልካች ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ፊልሞቻችን ላይ የሕግ ጉዳይን አንስተን ለዕይታ ከማቅረባችን በፊት ደጋግሞ ማሰብና አስፈላጊ ከሆነም ተገቢውን የሕግ ባለሙያ ማነጋገር ከላይ የተጠቀሰው ውጤት እንዳይመጣ ይረዳል፡፡ የሕግ ጉዳዮችን በዘፈቀደና እንደፈለጉ የሚቀርፁትና ለዕይታም የሚያቀርቡት ከሆነ አልፎ አልፎ እየተመለከትን እንዳለነው የፍርድ ቤቶችን ወይም የችሎት አካሄድን፣ የሕጉን ይዘት እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎቹን ሁኔታ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረጉ አይቀርም፡፡ ይህም ጽሑፍ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥንና ማሳያ የሚያቀርብ ሲሆን የወንጀል ሕግ እና ችሎት አካሔዶች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይሆናል፡፡

በወንጀል ጉዳይ የችሎት አካሄድ የሚመራበት አግባብ

የወንጀል ችሎት አካሄድ የሚመራው በ1954 በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ በተቀመጠው አግባብ እና አልፎ አልፎም ልዩ ጉዳዮችን በተመለከተ ብቻ ተፈፃሚ የሚሆኑ አንድ አንድ አዋጆችን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ የወንጀል ጉዳይ ክርክር እያንዳንዱ አካሄድ የሚመራውም በዋናነት በዚሁ ሕግ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ይህ የሥነ ሥርዓት ሕግም ከሚመራቸው ጉዳዮች መካከል የክስ መዝገቡ ለችሎቱ ከቀረበበት ግዜ አንስቶ አስከ ብይን (የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ ቁጥር 141 መሠረት)፤ ወይም አስከ ፍርድ (የዚሁ ሕግ አንቀጽ 149 መሠረት) እንደሁኔታውም እስከ ቅጣት ውሳኔ ድረስ ያለውን አካሔድ የሚመራው ይኸው ሕግ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ አንድ ፊልሞች (ከታች በማሳያነት የምናቀርበውን ጨምሮ) በሥነ ሥርዓት ሕጉ የተቀመጠውን አሠራርና አካሄድ ያዛባ ብቻም ሳይሆን የባለሙያዎችንና የተቋማትን ድርሻ (በተለይም የዐቃቤ ሕግን) ያዛባና በተመልካች ዕይታ የሕጉን አካሔድና የባለሙያዎችን ድርሻ የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያሲዝ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ማሳያ

ሄሮሺማ

በዚህ ፊልም ላይ የወንጀል የችሎት ክርክር ትዕይንት ያለ ሲሆን 3 ዳኞች፤ የዐቃቤ ሕግ ገዋን የለበሰ ምናልባትም ዐቃቤ ሕግ፤ ተከሳሽ እንዲሁም የችሎት ታዳሚዎች ይገኛሉ፡፡ ተዕይንቱም ተከሳሹ ስለድርጊቱ ሲያስረዳ ወይም በከፊል ሲያምንና ቀሪውን በተመለከተ ግን አጣርታችሁ ድረሱበት ብሎ ሲል ያስመለክታል፡፡ ከዛም ከችሎቱ ታዳሚዎች አንዷ ትነሳና “ክቡር ፍርድ ቤት ይህን ጉዳይ የሚያውቅ ምስክር ስላለኝ ምስክር እንዳቀርብ ይፈቀድልኝ” ትላለች፡፡ የመኃል ዳኛም “ተፈቅዷል” በማለት ለችሎት ታዳሚዋ መልስ ይሰጣል፡፡ የዐቃቤ ሕግ ገዋን የለበሰ ግለሰብ ይታያል ነገር ግን ምንም አይናገርም፡፡ አንድ ምስክር ይገባና( በችሎት ታዳሚዋ ግለሰብ አስፈቃጅነት) ስለ ወንጀል ጉዳዩ ማስረዳት ይጀምራል፡፡ በኋላም ጉዳዩ ለሌላ ግዜ መቀጠሩን ፍርድ ቤቱ ይጠቅስና ታዳሚውም ዐቃቤ ሕጉም (ምንም ዓይነት ድርሻ ሳይኖረው ማለት ነው) ችሎቱን ለቀው ሲወጡ ያሳያል፡፡

በዚሁ ትዕይንት ላይ ተከሳሹ የተከሰሰባቸው የሕግ አንቀፆች ባይጠቀሱም ተከሳሹ የተከሰሰበት ጉዳይ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስስ አይደለም፡፡ ምክንያት አንደኛ በ3 ዳኛ የሚታይ ጉዳይ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከፊልሙ ትዕይንቶች መረዳት እንደሚቻለው ተከሳሹ የመግደል ሙከራ ወንጀል የፈፀመና በሌሎችም ወንጀሎች ሊከሰስ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ በትይንቱ ላይ በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስስ ወንጀል ተከሳሹ ሲፈፅምም አይታይም፡፡ የበለጠ ለማጠናከርም በችሎት ታዳሚዋ የተጠራው ምስክር በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስስን ጉዳይ አልመሰከረም፡፡

ከሕጉ አንፃር በፊልሙ ላይ የተፈፀሙ ዋና ዋና ስህተቶች

በፊልሙ ትዕይንት ላይ የተያያዙ ነገር ግን መሠረታዊ የሆኑ ሁለት ዋና ዋና ስህተቶች ይስተዋላሉ፡፡ አንደኛው በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት የወንጀል ችሎት አካሄድን በሚመለከት ያስቀመጠውን አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌ ያልተከተለ መሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የዐቃቤ ሕግን የሥራ ድርሻ እና ኃላፊነት በተዛባ መልኩ መቅረፁ ነው፡፡  

የመጀመሪያውን ስህተት በተመለከተ የወንጀል ክርክር ባለቤት ወይም ከሳሽ በዋናነት መንግሥት(ፍትህ ሚኒስቴር - ለሌሎች የመንግሥት አካላት ከተሰጠው ሥልጣን ውጭ) ሲሆን በዐቃቤ ሕግ በኩል ክስና ክርክሩ ይካሄዳል (አዋጅ ቁጥር 691/2003 ወይም የፍትህ ሚኒስቴርን ሥልጣንና ኃላፊነት የሚደነግግ አዲስ ሊወጣ የሚችል አዋጅን መመልከት ይቻላል)፡፡ የሙስና፣ የጉምሩክና የሸማቾች አዋጅን በተመለከተ ሌሎች የመንግሥት አካላት በባለቤትነት ይዘውት ይሰራሉ፡፡ የወንጀል ዓይነቶችን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስከስስ ሲሆን ሌላኛው ዓይነት ደግሞ የግል አቤቱታ መቅረቡ ሳያስፈልግ የሚያስከስስ (በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስከስሱ) ናቸው፡፡ ግለሰቦች በእራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት የወንጀል ክስ እንዲመሰርቱና የችሎት ክርክር እንዲያደርጉ የሚያስችል አንድ ብቸኛ ሁኔታ ብቻ አለ፡፡ ያ ቅድመ ሁኔታ ተሟልቶ ግለሰቦች ወይም የግል ክስ አቤቱታ አቅራቢዎች ክስ እንዲመሰርቱ ከቻሉ ምስክር የሚያቀርቡት ግለሰቦቹ በእራሳቸው ይሆናሉ፡፡ ከዛ ውጭ ባለው ሁኔታ ግን የማንኛውም የወንጀል ጉዳይ ከሳሽም ሆነ ክርክር አድራጊ መንግሥት (በዐቃቤ ሕጎቹ አማካይነት) ይሆናል፡፡ ይህም ግለሰቦችን የወንጀል ክስ እንዲመሰርቱና ክርክር እንዲያደርጉ የሚፈቅደው የሕግ አንቀጽ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት (ከዚህ በኃላ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ተብሎ የሚገለፅ) ቁጥር 44(1) ነው፡፡ ይህም የሕግ ድንጋጌ  የክስ አቤቱታ በማቅረብ ብቻ በሚያስቀጣ የወንጀል ነገር በዚሁ የሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 42/1/ሀ/ መሠረት ክስ አይቀርብም በማለት ውሳኔ ዓቃቤ ሕጉ የሰጠ እንደሆነ በዚሁ የሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 47 መሠረት የተቀመጡትና ክስ ለማቅረብ መብት ለተሰጣቸው ግለሰቦች የግል ክስ እንዲያቀርቡ ዓቃቤ ሕግ በጽሑፍ ሊፈቅድላቸው ይችላል ብሎ ያስቀምጣል፡፡ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 44/2/ ላይ ደግሞ የክስ አቤቱታ በማቅረብ ብቻ የማያስቀጡ (በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስቀጡ) በተመለከተ ግን ዓቃቤ ሕጉ በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 42/1/ሀ/ መሠረት ክስ አይቀርብም በማለት ውሳኔ ቢሰጥ እንኳን ተበዳዩ ወይም የግል አቤቱታ ለማቅረብ መብቱ ያለው ግለሰብ በ30 ቀን ውስጥ ዓቃቤ ሕግ በትዕዛዝ ክስ እንዲመሰርትለት ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሊያመለክት ይችላል እንጂ በነዚህ ጉዳዮች ክስ የመመሥረትም ሆነ የችሎት ክርክር የማድረግ ዓቃቤ ሕግ ብቻ ሥልጣን ያለው መሆኑን ያመላክታል፡፡ ስለሆነም የግል አቤቱታ የማቅረብ መብት የተሰጣቸው ግለሰቦች የግል የወንጀል ክስ ለማቅረብ የሚችሉት በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ በሚያስቀጡ (Crimes Punishable Up On Complaint) ወንጀሎች ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ግዜም በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ ቁጥር 153/1/ ላይ እንደተቀመጠው ተከራካሪዎቹም (የግል ክስ አቅራቢና ተከሳሽ) በዓቃቤ ሕግ በኩል የሚቀርበውን ክስ ዓይነት መብትና ግዴታ ይኖራቸዋል፡፡ የዓቃቤ ሕግን ድርሻ ተክተው በወንጀል ጉዳይ ምስክር ሊያቀርቡ የሚችሉትም በዚህና በዚህ አግባብ ብቻ ነው፡፡ በክስ አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስከስሱ ወንጀሎች (Crimes Punishable Up On Complaint) የሚባሉትም በወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ላይ በተበዳይ ወይም ስለ ተበዳዩ ባለመብት በሆኑ ሰዎች ክስ አቅራቢነት ብቻ የሚያስከስሱና የሚያስቀጡ ተብለው የተቀመጡ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ማለት ናቸው (የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 13ን መመልከት ይቻላል)፡፡  በተለምዶም በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙ በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስከስሱ ወንጀሎች መኃል: በ1996 ዓ/ም የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 556/1/ ላይ የተደነገገው ታስቦ የሚፈፀም ቀላል የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል፣ አንቀጽ 560/1/ ላይ የተደነገገው የእጅ እልፊት ወንጀል፣ አንቀጽ 580 ላይ የተቀመጠው የዛቻ ወንጀል፣ አንቀጽ 612 ላይ የተደነገገው የስም ማጥፋት ወንጀል፣ አንቀጽ 615 ላይ የተቀመጠው የስድብና ማዋረድ ወንጀል፣ በአንቀጽ 689 ላይ የተደነገገው ታስቦ የሚፈፀም በሌላ ሰው ንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ ወንጀል በዋናነት ይገኙበታል፡፡ እነኚህን ወንጀሎች በተመለከተ ምንም እንኳን በተግባር እየተሰራበት ያለ ባይሆንም ዓቃቤ ሕግ ክስ አላቀርብም በማለት ውሳኔ በሚሰጥበት ግዜ የግል አቤቱታ ለማቅረብ መብቱ የተሰጠው ግለሰብ በእራሱ ክስ እንዲመሠርት በጽሑፍ እንዲፈቅድለት ለመጠየቅ በሕጉ የተቀመጠ መብት አለው፡፡ በዚህ አካሄድ መሠረትም የተፈቀደለት የግል ክስ አቅራቢ ክስ ይመሰርታል፣ ለተከሳሽና ምስክሮች መጥሪያ ያደርሳል፣ ምስክሮቹን ለፍርድ ቤት አቅርቦ ያሰማል-ልክ ዐቃቤ ሕግ የሚያድረጋቸውን አጠቃላይ ኃላፊነቶች ይወስዳል ማለት ነው (የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 153/1/ን መመልከት ይቻላል)፡፡ በዚሁም አጋጣሚ በሕጉ የዚህን ዓይነት አሠራርና መብት ተቀምጦ ሳለ ለምን በተግባር እንደማይሰራበት እራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ የግል አቤቱታ ለማቅረብ መብት የተሰጣቸው ግለሰቦች ይህንን ጥያቄ ይጠይቃሉ ወይ? ቢጠይቁ በዐቃቤ ሕግ በኩል በጽሑፍ ፈቃዱን ለመስጠት ዝግጁነቱስ እንዲሁም የአሠራር ሥርዓቱ አለ ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሚያሻቸው ይመስለኛል፡፡ የሚመለከታቸው ሁሉም አካላትም በዚህ ዙሪያ ተገቢውን መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡

ወደ ፊልሙ ስንመለስ ከላይ እንደተገለፀው በወንጀል የችሎት ክርክር ጉዳይ ጉዳዩ ይመለከተኛል ያለች አንድ ግለሰብ ምስክር ለማቅረብ ጠይቃ ሲፈቀድላት የሚያስመለክተው ትዕይንት ጉዳዩ በግል ክስ አቅራቢነት የሚያስከስስ አለመሆኑን ከላይ ከቀረበው ማብራሪያ መረዳት ይቻላል፡፡ እስከ አሁን ባነሳናቸው የሕግ ድንጋጌዎችና በተጨማሪነትም በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 124 መሠረት ዓቃቤ ሕጉ ምስክሩን ስለመጥራቱ እንጂ ሌላ ግለሰብ ምስክሩን ያቀርብለታል ተብሎ አልተደነገገም፡፡ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 136/2/ መሠረትም ዓቃቤ ሕጉ ምስክሮቹንና በምስክርነት የሚቀርቡ ልዩ ዕውቀት ያላቸውን እንዳሉ መጥራት አለበት ነው የሚለው፡፡ ስለዚህም በፊልሙ ትዕይንት ላይ የችሎት ታዳሚዋ በዛ ዓይነት ጉዳይ ምስክር ለመጥራት የምታስፈቅድበትና ምስክር የምትጠራበት የሕግ አግባብ የሌለ እና በፊልሙ ተመልካች ዘንድ የተዛባ የሕግ ግንዛቤ ያሲዛል ብዬ አስባለሁ፡፡

ከዚሁ ከላይ ከዘረዘርነው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ነገር ግን የዓቃቤ ሕግን የሥራ ድርሻ በተመለከተ ከፊልሙ ተዕይንት እንደተመለከትነው በሕጉ አግባብ የዚህን ዓይነት አካሄድ በዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የሌለ ቢሆንም የችሎት ታዳሚዋ ምስክር ለማቅረብ ስትጠይቅም ሆነ ምስክር ስትጠራ ዓቃቤ ሕግ (የተለመደውን የዓቃቤ ሕግ ገዋን በመልበሱ) ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ አንዳንዴም ተነስቶ ያሳያል፡፡ የሥራ ኃላፊነቱና ሥልጣኑ የዓቃቤ ሕግ እና የዓቃቤ ሥልጣን ሆኖ ሳለ እና በሕግም ኃላፊነት የተጣለበት ሆኖ እያለ ዝምብሎ ቁጭ ብሎ ተመልካች እንዲሆን አድርጎ መሳል ተመልካቹ ቀይ ሪቫን ያለውን ገዋን የሚለብስ ዓቃቤ ሕግ ስለሚሰራው ሥራ የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት ውስጥ ይጥላል፡፡

የመፍትሔ ሃሳብ

እንግዲህ ከላይ ባቀረብነው ሁኔታ መሠረታዊ የሕግ ዕውቀት ክፍትት በፊልም ሥራዎቻችን ላይ እንደሚስተዋል ማየት ችለናል፡፡ ይህንን ዓይነት ክፍተት ከመፍጠር የተሻለው አማራጭ የሕግ ጉዳዮችን በተለይም ጉዳዩ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመና ጉዳዩም እየታየ እንደ ሆነ እየገለፅን ነገር ግን ሕጉ የማይለውንና የተሳሳተ ግንዛቤ ሊያሲዝ የሚቸለውን ጉዳይ ስለን ከምናስመለክት በቀላሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የሕግ ባለሙያዎች ስለ ሕጉ ይዘት ማብራሪያ መጠየቁ ከዚህ ዓይነት መሠረታዊ የሕግ ዕውቀት ክፍተት ያድናል፡፡ የሕግን ጉዳይ የተለየ ትኩረት አድርጎ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው በሕግ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ማስተማሪያ እስከመሆን ድረስ መድረስ የሚቻለው የዚህን ዓይነት አካሄድ የመከተል ዝንባሌ ሲኖረን ነው፡፡ አንድ አንድ ድራማዎች ላይ ህክምናንና ሥነ ልቦናን በተመለከተ የህክምናና ሥነ ልቦና አማካሪ በሚል የተለየ ሰው አዘጋጅተው ትክክለኛውን ነገር ሳይዛባ ለማቅረብ እንደሚሞክሩት ሁሉ በሕግም መስክ ይኸው ተግባር ሊለመድ የሚገባው ነው፡፡ የተለየና ሌላ ምዕናባዊ (imaginary)ነገሮችን መፍጠር ከታሰበም ይኸው በግልፅ በፊልሙ ላይ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የሕግ ባለሙያዎችም የእዚህን ዓይነት ጉዳይ ሲመለከቱ የተፈፀመውን የሕግ ስህተት ቁልጭ አድርገው ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ለሌሎች ማረሚያ መንገድ በመሆን ስህተቶቹ እንዳይደገሙ ለማድረግም ስለሚያስችሉ፡፡

ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ አንድ አንድ ፊልሞች ከሕግ ግንዛቤ ክፍተት የተነሳ የሕጉን አካሔድ አዛብተው በመሳላቸው በተመልካች ዘንድ የተሳሳተ የሕግ ግንዛቤ ሊያሲዙ ይችላሉ፡፡ በማሳያነት አንድ ፊልም ብቻ አቀረብን እንጂ አንባቢ የተመለከታቸው በፊልሞቻችን ላይ እንዲሁም በቴሌቭዥን ድራማዎችም ላይ ጭምር የሚስተዋሉ መሠረታዊ የሕግ ግንዛቤ ክፍተቶች ሲንፀባረቁ ተመልክተው ይሆናል፡፡ ይህን ዓይነት ስህተቶች ሲፈፀሙ በዝምታ የሚታለፉ ከሆነ ስህተቱን የሠራው አካልም እንዲሁም የሕግ ግንዛቤው የሌለው የፊልሙ ተመልካች የሆነው ነገር ትክክለኛው የሕጉ ይዘት ይኸው ነው ብለው እንዲያምኑ እድል ይከፍታል፡፡ ስለዚህም የፊልም ሰሪዎቹ ጥንቃቄ ቢያደርጉ፣ የሕግ ባለሙያውም ስህተቶችን ሲመለከት ግልፅ ትችት መስጠት ቢለመድ ነገሮች ተሻሽለው ለማየት እድሉ ይኖራል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በወንጀል ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔን እንደገና ስለማየትና በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ
(Non) retroactivity of Ethiopian Criminal Law
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024