አቶ ገብረመስቀል (Gebremeskes Gebrewahd) ወቅታዊ የሆነን ጉዳይ በማንሳትህ ላመሰግንህ እወዳለሁ፡፡ ባነሳኸው ጥያቄ ማለትም የሳይበር ክልል በሃገሮች ሉአላዊነት ላይ ምን ፋይዳ አለው? የሳይበር ክልል መተዳደር ያለበት በሃገራዊ ህግ ነው ወይስ በአለም አቀፍ ህግ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የኔ አስተያየት የሚከተለው ይመስላል። በኔ እምነት በቅድሚያ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ግልፅ መሆን ያስፍልጋል።

·        የሳይበር ክልል ምን ማለት ነው?

·        የሳይበር ክልል ራሱን የቻለ አዲስ አለም (ክልል) ነው ወይ?

·        የሳይበር ክልል እንዴት ይተዳደራል (እንዴት መተዳደር አለበት)?

በሳይበር ክልል ላይ የሚሰጡ ትርጓሜዎች ብዙ ጊዜ የተወሳሰቡ፣ የተጋነኑ አንድ አንዴም ከእውነታ የራቁ መስለው ይታያሉ። የሳይበር ክልል ብዙ ጊዜ ከነባራዊው አለም ውጭ የተፈጠረ አዲስ አለም ተደርጎ ሲቀርብም ይታያል። “የሳይበር ክልል/አለም”  የሚለው ስያሜ በራሱ አሳሳች (misleading) ሊሆን ይችላል። እውነታው ግን የሳይበር ክልል ማለት ኢንተርኔት ማለት ነው። ኢንተርኔትስ ምን ማለት ነው? ኢንተርኔት እርስበርሳቸው የተሳሰሩ ኔትዎርኮች (inter-net) ማለት ነው። ኢንተርኔት የኮምፒውተሮች፣ መሳሪያዎች ወይም ዳታዎች ትስስር ሳይሆን የኔትዎርኮች ትስስር ነው። እነዚህ ኔትዎርኮች እርስበርስ በመተሳሰር አለም አቀፍ ኔትዎርክ (ኢንተር-ኔት) ይፈጥራል በዚህም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች እና መሰል መሳሪያዎች እንዲገናኙ፣ መልእክት እንዲለዋወጡ ያስችላሉ። ስለዚህ የሳይበር ክልል = ኢንተርኔት= እርስበርስ የተሳሰሩ ብዙ ኔትዎርኮች (network of networks) ማለት ነው።

የሳይበር ክልል ራሱን የቻለ አዲስ አለም ነውን? ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ አሳሳች አባባሎች (fallacies) አሉ። ለምሳሌ የሳይበር ክልል ከመደበኛው አለም ውጭ የሆነ አዲስ ግዛት (jurisdiction) ነው በመሆኑም በመደበኛው ህግና ስርዓት፣ አሰራር ወዘተ አይገዛም፣ የሳይበር ክልል አካላዊ ህልውና የሌለው አለም (virtual) ነው፣ በሳይበር ክልል የቦታ ርቀትና ጂኦግራፊያዊ ክልል ትርጉም የላቸውም (ሉአላዊነት የሚባል የለም)፣ በሳይበር ክልል ላይ የየትኛውም ሃገር ህግ ተፈፃሚ አይሆንም፣ ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል።

እነዚህ አባባሎች የተሳሳቱ አባባሎች መሆናቸውን ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ የሳይበር ክልል (ኢንተርኔት) የሚሰጠው አገልግሎት ምንድን ነው የሚለውን እንይ።

የሳይበር ክልል (ኢንተርኔት) አገልግሎት ወይም ስራ እጅጉን ቀላል ነው። ይኸውም ዲጂታል ኢንፎርሜሽን ወይም ዳታዎችን ከአንድ ኮምፒውተር ወደሌላ ኮምውተር ማጓጓዝ (ማስተላለፍ)! በቃ! በሌላ አባባል የሳይበር ክልል (ኢንተርኔት) ከኮምኒኬሽን መሳሪያነት (መንገድ) በዘለለ ሌላ ስራ የለውም። ነገር ግን ኮሙኒኬኝን ሲባል በኮምፒውተሮች መካከል፣ በሰዎች መካከል ወይም በኮምፒውተርና በሰዎች መካከል ሊሆን ይችላል። የሚተላለፈው ዳታም በፅሁፍ (text)፣ በድምጽ፣ በቪዲዮ፣ በቁጥር ወይም በኮድ መልክ፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል። የዳታው ትርጉም መጀመሪያ ላይ ካነሳናቸው ጥያቄዎች አንፃር አግባብነት (relevancy) የለውም። እንዲሁም የዳታው መተላለፍ ውጤት የተለያየ ሊሆን ይችላል (ለምሳሌ ኮምፒውተሮች የሆነ ስራ እንዲያከናውኑ ማዘዝ)። ይህም ቢሆን ግን ከጥያቄዎቹ አንፃር አግባብነት የለውም።

ሌላው መሰረታዊ ነጥብ በኢንተርኔት ዳታ ማጓጓዝ ወይም በኮምኒኬሽን ሂደት ላይ ከላኪው (ሰው/ኮምፒውተር) እና ተቀባዩ ሰው/ኮምፒውተር በዘለለ እጅግ በርካታ አካላትና መሰረተ ልማቶች የሚሳተፉ መሆናቸው ነው። ዳታው በሚፈለገው አካል ወይም ተቀባይ እስኪደርስ ድረስም በእነዚህ አካላት (intermediaries) አማካኝነት ማለፍ የግድ ይላል። አሁንም ቢሆን ግን የእነዚህ አካላት ሚና፣ ብዛትና አሰራር እንዲሁም የመሰረተልማቶቹ (ለምሳሌ servers, routers, switches, etc) ቴክኒካዊ ይዘት፣ ውስብስብነትና አሰራር ካነሳባቸው ጥያቄዎች ጋር አግባብነት የላቸውም። ይህ እንዳለ ሆኖ የሚከተሉት እውነታዎች ግን በመካድ አይቻልም፦

·        ሁሉም የሳይበር ክልል/ኢንተርኔት ተዋናዮች የግድ በአንድ ወይም በሌላ ሉአላዊ ግዛት (jurisdiction) ውስጥ ይኖራሉ፣

·        ግንኙነቱ የሚፈፀምባቸው (ኢንተርኔት የተፈጠረባቸው) መሰረተ ልማቶችና መሳሪያዎች ሁሉም የግድ በአንድ ወይም በሌላ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ ይገኛሉ፣ እንዲሁም የግድ ባለቤትም ይኖራቸዋል፣

·        ማንኛውም ሉአላዊ ሃገር በግዛት ክልሉ ውስጥ በሚደረጉ ክንዋኔዎች (activities) ላይ ሙሉ ስልጣን አለው።

ስለዚህ የሳይበር ክልል/ኢንተርኔት ከነባራዊው አለም (real world) ተለይቶ የራሱ ህልውና ያለው ነገር አይደለም። ከዚህ በመነሳት አለም አቀፉ ኢንተርኔት/ሳይበር ክልል ማን እና እንዴት ሊተዳደር ይገባል? የሚለው ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። መጀመሪያ መገንዘብ ያለብን ነገር ቢኖር ኢንተርኔት የነባራዊው አለም አካል በመሆኑ አሁንም ቢሆን እየተዳደረ ነው የሚል ይሆናል። ትልቁ ቁም ነገር ከሌሎች ዘርፎች በተለየ መልኩ የሳይበር ክልል/ኢንተርኔት ወጥ የሆነ (single) የአስተዳደር ስርዓት የሌለው መሆኑ ነው። በመሆኑም የሳይበር ክልል/ኢንተርኔት በሃገራዊ ህግ ወይስ በአለም አቀፍ ህግ ሊተዳደር ይገባል? የሚለው ጥያቄ በራሱ ተገቢ ጥያቄ አይደለም። ምክንያቱም የሳይበር ክልል/ኢንተርኔት በህግ ብቻ (በመንግስታት ብቻ) አይተዳደርም። ከሁሉም መንግስታት በላይ ለኢንተርኔት መፈጠር፣ አስተዳደርና ቀጣይ ህልውና ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ሌሎች አካላት አሉ። ለምሳሌ የኢንተርኔት ልዩ (unique) ስሞችና የኢንተርኔት ልዩ አድራሻ (IP address) የሚያስተዳድሩ አካላት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች (google facebook,---)፣ የኢንተርኔት ስታንዳርድና ፕሮቶኮሎች አዘጋጆች፣ ስቪል ማህበራት (ለምሳሌ internet society)፣ ወዘተ። እነዚህ አካላት መንግስታት በሚያወጧቸው ህጎች ሳይሆን በዋናነት በራሳቸው ህግ፣ ፖሊሲ፣ አሰራር የሚመሩ ናቸው። ከመንግስታት ባልተናነሰ (አንድ አንዴም በበለጠ) መልኩ ህግና ፖሊሲ የማውጣትና የማስፈፀም አቅም አላቸው። ለምሳሌ የመብት ጥሰቶች ሲያጋጥሙ መንግስታት ብቻ ሳይሆን እነዚህ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎችና አስተዳዳሪዎችም ትልቅ ሚና አላቸው፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማገኘት (የሳይበር ክልል ተዋናይ ለመሆን) የመንግስታት ህግና አሰራር ብቻ ሳይሆን የእነዚህ ተቋሟት/አካላት ህግና አሰራርም መቀበልና ማክበር የግድ ይላል (ለምሳሌ የፕራይቨሲ፣ የኮፒራይት ህግና ፖሊሲ)።

ስለሆነም የሳይበር ክልል አስተዳዳሪዎች መንግስታት ብቻ አይደሉም። ይህ ማለት ግን ህግ ብቻውን የሳይበር ክልል አያስተዳድርም የሚለውም መልእክት ለማስተላለፍ እንጂ የመንግስታት ሚና ለማሳነስ አይደለም። አሁንም ቢሆን የመንግስታት ሚና እንደተጠበቀ ነው። የሉአላዊነት ስልጣናቸው በሳይበር ክልልም ቢሆን ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ይሆናል። ይህ ማለት ግን የሳይበር ክልል በሃገሮች ሉአላዊነት ላይ የደቀነው አደጋ የለም ማለት አይደለም። የሳይበር ክልል አለም አቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ እንደማንኛውም አለም አቀፍ ሚዲያ (ለምሳሌ ሳተላይት ብሮድካስቲንግ፣ ቴሌኮሙኒካሽን፣ ወዘተ) የራሱ ውስብስብ ተግዳሮቶች አሉት። ቢሆንም ግን ውስብስብ ነው ማለት ሉአላዊነትን ያጠፋል ወይም ያዳክማል ማለት አይደለም።

በመጨረሻም የሳይበር ክልል/ኢንተርኔት በሃገራዊ ወይም በአለም አቀፍ ህግ ብቻ ሳይሆን ከላይ ያነሳናቸው አካላትና የአሰራር ዜይቤዎች ባካተተ መልኩ መተዳደር አለበት፣ እየተዳደረም ነው። በሌላ አባባል ሃገራዊ ህግ ያስፈልጋል፣ አለም አቀፍ ህግም ያስፈልጋል ነገር ግን ይህ ብቻውን በቂ አይደለም።