Font size: +
8 minutes reading time (1505 words)

የቤት ኪራይ ግብር

-   በዓመት ከ1800 ብር በላይ ቤት የሚያከራይ አከራዮች ሁሉ የኪራይ ግብር ገቢ የመክፈል ግዴታ አለባቸው።

-   ግብር የማይከፍል ወይም አሳንሶ ገቢውን የማያሳውቅ አከራይን ለገቢዎች በማስረጃ የጠቆመ ተከራይም ሆነ ሌላ ሰው የማበረታቻ ሽልማት አለው።

-   ከአከራዮች የሚፈለገው የኪራይ ግብር አሰላልና መጠኑ ምን ይመስላል?

-   የቤት ኪራይ ግብርን አለመክፈል የሚያስከትለው የወንጀል ኃላፊነት ተከራዮች በወንጀል የሚጠየቁበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

እንዴት ናችሁ ሰላም ነው? የዛሬ ወጋችን የሚያጠነጥነው የቤት ኪራይ ግብር ላይ ነው። ለመሆኑ ምን ያህሎቻችን ተከራዮች ነን፤ አከራዮቻችንን በኪራይ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ግብር የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው የምናውቀው? ከአከራዮች መካከል ምን ያህሉ ናቸው፤ በሕግ የተጣለባቸውን የኪራይ ግዴታ እየተወጡ የሚገኙት። መንግስት በተደጋጋሚ ከአጠቃላይ ዓመታዊ የሀገሪቱ ገቢ የግብር ገቢው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አነስተኛ ነው። ስለዚህ የግብር አሰባሰቡን ውጤታማና ቀልጣፋ ለማድረግ እየጣርኩኝ ነው ቢልም ከቤቶች ኪራይ የሚሰበሰበው ገቢ ላይ ግን ጠንክሮ እየሰራ አይመስልም። እኔ ራሱ በተከራይነት የኖርኩባቸው ቤቶች የማውቃቸው ወዳጆቼ ጎረቤቶች በሙሉ አከራዮቸው የኪራይ ግብር የተጠየቁበት አጋጣሚ አላየሁም። እስቲ ለማንኛውም የተወሰኑ ቤት ኪራይ ግብርን የሚመለከቱ እስከ ፌ/ጠ/ፍ/በት የደረሱ ክርክሮችን እናንሳና ሕጎቹ ምን እንደሚሉ እናያለን።

የኪራይ ግብርን ማን ይቀንስ

ዘመን ዮሐንስ ኃ/የተ/የግል ማህበር እና አቶ ዳውድ ኢብራሂም አንድ ጉዳይ አገናኛቸው። የአቶ ዳውድን መጋዘን ዘመነ ዮሐንስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በወር 13ሺ ብር ተከራይቶ ሲጠቀም ቆየ። ሆኖም የ6 ወር የቤተ ኪራይ ብር 78,000 አልተከፈለኝም ያሉት አቶ ዳውድ ውዝፍ የቤት ኪራዩን እንዲከፈላቸው ዘመነ ዮሐንስ ላይ ክስ መሰረተ። ተከሳሽ ይህን ኪራይ የምከፍለው የመንግስት ግብር ቀንሼ ነው አለ። ከሳሽ ደግሞ የለም ሳይቀንስ ይከፈለኝ ብለው ተከራከሩ። የፌ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ተከሳሽ ግብር ሳይቀንስ 78,000 ብር ለአቶ ዳውድ እንዲከፍላቸው ወሰነ። ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ውሳኔውን አፀናው። ዘመነ ዮሐንስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በገቢ ግብር አዋጁ 286/94 መሰረት በወንጀል የሚያስጠይቀኝና አስተዳደራዊ ቅጣት የሚያስከትልብኝ ነው። አዋጁንም ስለሚጥስ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል፤ ይታረም ሲል ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አመለከተ።

አቶ ዳውድ ተጠርተው ከሰጡት መልስ የግብር እዳውን ከፍያለሁ። የመጋዘን ኪራይ ውሉን አስመዝግቢያለሁ። በመሆኑም ከሚከፈለኝ ኪራይ ላይ የሚቀነስበት ምክንያት የለም ብለው መልስ ሰጡ። ተሟጋቻቸውም በሰጠው የመልስመልስ የኪራይ ገቢ ግብር መክፈላቸው እኔን ከምከፍለው ክፍያ ላይ ግብር ቀንሼ እንዳስቀር በሕግ የተጣለብኝን ግዴታ አያስቀርም አለ።

ሰበር ጉዳዩን መርምሮ ዘመነ ዮሐንስ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ማናቸውንም የአገልግሎት ግዥ ሲፈፀም (ቤቱን ሲከራይ) ሻጭ (አከራዩ) የግብር መለያ ቁጥር ካለው 2 በመቶ ለሌለው 30 በመቶ ቀንሶ ለገቢ ሰብሳቢው አካል የመክፈል ግዴታ እንዳለበት በአዋጅ ቁ 286/94 አንቀጽ 83 እና 91 ላይ ተደንግጓል። አቶ ዳውድ ካደረግነው የኪራይ ውል ግብር የመክፈል ኃላፊነት ያለበት አከራዩ መሆኑ በግልጽ ተመልክቷል ቢሉም በሕግ በአስገዳጅነት የተቀመጠውን የተከራዩን ግዴታ የሚቃረን ውል ቢዋዋሉ ውሉ ፈራሽና ውጤት የሌለው መሆኑን አዋጁ አንቀጽ 56 እና 91 ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 716 ድንጋጌዎች መረዳት ይቻላል።

ስለዚህ አቶ ዳውድ ግብር ሳይቀንስ የኪራይ ገንዘብ ይከፈለኝ በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ፍ/ቤቶች በተጠቀሱት ድንጋጌዎች መሠረት ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው ግብር ሳይቀንስ 78,000 ይከፈል ማለታቸው መሠረታዊ የህግ ስህተት በመሆኑ አቶ ዳውድ የግብርከፋይ መለያ ካላቸው 2 መቶ፣ ከሌላቸው 30 በመቶ ቀንሶ ይክፈላቸው በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ አሻሽሎታል (ይህ ክርክር የተከፋይ ገቢ ግብርን የሚመለከት ሲሆን የኪራይ ገቢን በተመለከተ ግን ገቢውን ያገኘው አከራይ የመክፈል ግዴታ አለበት) ውሳኔው ቅጽ 13 ላይ ታትሞ የወጣና በሰ/መ/ቁ 65361 ሚያዝያ 9 ቀን 2004 ዓ.ም የተወሰነ ነው።

የቤት ኪራይ ገቢ ግብር

ሰኔ 27 ቀን 1994 ዓ.ም የወጣው የገቢ ግብር አዋጅ ነባሩን የገቢ ግብር ስርዓት በመለወጥና በማስተካከል በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ የተለያየ የገቢ ምንጮች ከሚሰራባቸው የገንዘብ ነክ መርሆዎች ጋር እንዲዋሃድ አስፈላጊ በመሆኑና የግብር ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግና የግብር መሠረቱን በማስፋት ቁጠባንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የሚያግዝ መሆኑ ስለታመነበት እንደሆነ በአዋጁ መግቢያ ላይ ተገልጿል። አዋጁ የገቢን ምንነት አስመልክቶ በሰጠው ትርጓሜ በአንቀፅ 2(10) ስር ገቢ ማለት ማናቸውን የኢኮኖሚ ጥቅም ሲሆን፣ በመደበኛነት የተገኘ ባይሆንም ከማናቸውም ምንጭ በጥሬ ገንዘብ ወይም በዓይነት በማናቸውም መልክ ለግብር ከፋዩ የተከፈለው በስሙ የተያዘለት ወይም የተቀበለውን ጥቅም ሁሉ ያካትታል። ግብር የሚከፈልበት የትኛው ገቢ ነው የሚለውን አዋጁ በአንቀጽ 6 ስር በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ከንግድ ሥራ፣ ከመዝናናት፣ ከሙዚቀኛ፣ ስፖርተኛ በግል ካከናወኑት የሚያገኙ፣ ከተንቀሳቃሽ ንብረት፣ ከማይንቀሳቀሱ ንብረት መብቶች የሚገኝ ገቢ፣ የአክሲዮን የሽርክና ማህበር የትርፍ ክፍፍል እና ሌሎችም በአዋጅ የተጠቀሰ የገቢ ምንጮች እንደሆኑ ይደነግጋል።

በአዋጁ አንቀፅ 8 ላይ የግብር አይነቶችን ከሀ-መ በአራት መደቦች የከፋፈላቸው ሲሆን ሀ. ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ፣ ለ. ከቤት ኪራይ የሚገኝ ገቢ፣ ሐ. ከንግድ ስራዎች የሚገኝ ገቢ እና መ. ሌሎች ገቢዎች የፈጠራ ስራ ማከራየት፣ ከኢትዮጵያ ውጭ አገልግሎት በመስጠት፣ በዕድል ሙከራ ውድድርአሸናፊነት፣ በአክሲዮን ድርሻ፣ ቋሚ ባልሆነ ሁኔታ ከንብረት ኪራይ የሚገኝ ገቢ፣ የወለድ ገቢና ከንግድ ሥራ ጋር ካልተያያዘ የካፒታል ዋጋ የሚገኙ ገቢዎችና ሌሎች ገቢዎች በሚለው ሰንጠረዥ ስር ግብር የሚከፈልባቸው ናቸው።

ከቤት ኪራይ የሚገኝ ገቢ በሰንጠረዥ ለ ብር የተቀመጠ ሲሆን በሕግ የሰውነት መብት ከተሰጣቸው ድርጅቶች ቤት በማከራየት ከሚያገኙት ገቢ የማስከፈያው ልክ በጥቅል 30 በመቶ ነው። የቤት አከራዮቹ ግለሰቦች ከሆኑ ደግሞ

-   የዓመት ኪራይ ገቢያቸው ከ0 - 1800 ብር የሆነው ከግብር ነፃ ተደርገዋል።

-   በዓመት ከ1801 - 1800 ብር የቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙ 10 በመቶ

-   ከ7801 - 16800 ብር ዓመታዊ የቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙ 15 በመቶ

-   ከ16081 - 28,200 ብር ዓመታዊ የቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙ 20 በመቶ

-   ከ28,201 - 42,600 ብር ዓመታዊ የቤት ኪራይ የሚያገኙ 25 በመቶ

-   ከ42,601 - 60,000 ብር ዓመታዊ የቤት ኪራይ የሚገያገኙ 30 በመቶ

-   ከ60,000 ብር በላይ ዓመታዊ የቤት ኪራይ የሚያገኙ 35 በመቶ

የቤት ኪራይ ገቢ ግብር መክፈል እንዳለባቸው በአዋጁ አንቀፅ 15 ላይ ተደንግጓል። በአንቀፅ 14 ላይ ደግሞ በድርጅትም ሆነ በግለሰብ በማናቸውም ሁኔታ ከተከራይ ቤት ከሚገኝ ገቢ ላይ ግብር እንደሚከፈል ደንግጓል። ግብር የመክፈል ግዴታ ያለበት ገቢውን ያገኘው ሰው ወይም ድርጅት ነው። የግብሩ መጠን እንዴት ይወሰናል የሚለውን በተመለከተ በአዋጅ አንቀፅ 16(2) ስር ቤቱ ወይም ግቢው የተከራየው ከነእቃው ከሆነ የእቃው ወይም የመሳሪያው ኪራይም ከቤቱ ኪራይ ገቢ ጋር ተደምሮ ይታሰባል።

አከራዩ ቤቱን የሚያከራየው ከቤቱ ባለቤት ከሆነው አከራይ ከሚከፈለው የኪራይ ዋጋ ባላይ ለሆነ የተከራይ አከራዩ ግብር የሚከፈለው ቤቱን በተከራየበትና ለሌላ ሰው ባከራየበት ሰው ለሌላ ሰው እንዲያከራይ የሚፈቅድ የቤት ባለቤት ተከራዩ ግብሩን ሳይከፈል የቀረ እንደሆነ በተከራይ አከራዩ በመተካት ያልተከፈለውን የኪራይ ገቢ ክፍል የመክፈል ኃላፊነት አለበት።

የቤት ኪራይ ግብር አሰባስበን ውጤታማ ለማድረግ በአዋጅ አንቀፅ 15(3) ስር ለኪራይ የሚሰሩ ቤቶች ተሰርተው እንዳለቁ ወይም ገና ሳይጠናቀቁ ከተከራዩ የቤቱ ባቤትና ግንባታውን የካሄደው የሥራ ተቋራጭ የቤቱ ግንባታ መጠናቀቁን ወይም መከራየቱን ከኪራዩ ላይ በሚገኘው ገቢ ላይ የሚፈለግበትን ግብር መክፈል ያለበትን የቤቱን ባለቤት ወይም ከተከራየበት በበለጠ ዋጋ ያከራየውን የተከራይ አከራይ ስም አድራሻና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ካለው ቁጥሩን ቤቱ ለሚገኝበት ወረዳ መስተዳድር ማስታወቅ አለባቸው።

ቤቱ የሚገኝበት ወረዳ መስተዳድርም በራሱ ክትትል ወይም ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ያገኘውን መረጃ ለሚመለከተው የግብር ሰብሳቢ ባለሥልጣን የማስተላለፍ ግዴታ አለበት።

የኪራይ ገቢ ግብር ተቀናሾች

በአዋጁ አንቀፅ 15(1) (ሐ) መሠረት የቤት ኪራይ ገቢ ግብር በሚሰራበት ጊዜ ከጠቅላላ ገቢ ላይ የገቢው መጠንን ተከትሎ የሚወሰነው የግብር መጠን ግብር ከፋዩ ላይ እንዳይበዛ የሚያደርጉ ተቀናሾች ተፈቅደዋል። የመጀመሪያው ተቀናሽ ከገቢ ግብር ውጭ ያሉ ከተከራየው ቤት ጋር በተያያዘ የተከፈሉ የመሬት ግብር እና የሕንጻ ታሪክ ናቸው። ሁለተኛው ተቀናሽ የተፈቀደው የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ ለሌላቸው አከራዮች፣ (ግለሰቦች)፣ የቤቶች፣ ለቤት እቃና ለመሳሪያ ማደሻ፣ መጠገኛና፣ ለእርጅና መተኪያ (ዲናሪሺይን) የሆነ ከቤት ከቤት እቃና ከመሳሪ ከሚገኘው ጠቅላላ የኪራይ ገቢ 1 አምስተኛው ተቀናሽ ከተደረገ በኋላ ነው ግብሩ የሚሰላላቸው።

በሶስተኛው ተቀናሽ መዝገብ የሚይዙ ግብር ከፋዮችን በተመለከተ ሲሆን ወጪዎቹን በማስረጃ ማረጋገጥ እስከቻሉ ድረስ የኪራዩን ገቢ ለማግኘት፣ ለኪራዩ ንግድ ስራ ዋስትና ለመስጠት፣ እና እንቅስቃሴውን ለማስቀጠል የተደረጉ ወጪዎች ተቀናሽ ይደረጉላቸዋል።

በተጨማሪ ለመሬት ሊጉ (ኪራይ) ለቤቶች፣ ለቤት እቃና ለመሳሪያ ማደሻ፣ የባንክ ወለድ፣ የኢንሹራንስ አረቦን ወጪዎች በሚይዙት መዝገብ መሠረት ተመሳክረው ተቀናሽ ይደረጋሉ። የእርጅና እና የማስጠገኛ ቅናሽን በተመለከተ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 23 (3) መሠረት የህንጻውን ወይም የሌሎች ግንባታዎች ባለቤት ለመሆን ህንፃ ወይም ሌሎች ግንባታዎችን ለማሻሻል ለማደስ እና መልሶ ለመገንባት የተደረጉ ወጭዎች ለእያንዳንዳቸው በተናጥል በቀጥተኛ የእርጅና አቀናነስ ዘዴ 5 በመቶ የእርጅና ቅናሽ ከተደረገ በኋላ ነው።

የአከራዩ ግዴታ፡- በዓመት ከ1800 ብር በላይ የቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙ አከራዮች ወይም የተከራዩትን አትርፈው የማከራየት በልዩነቱ ገቢ የሚያገኙት ተከራዮች አከራዮች በአዋጅ አንቀጽ 66(1) (ለ) መሠረት የግብር አመቱ በተጠናቀቀ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ያገኙትን የኪራይ ገቢ ለገቢ ሰብሳቢው ባለስልጣን የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው።

በገቢ ግብር ማሳወቂያው መሰረት የተሰላው ግብር ላይ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ተቀናሽ የተደረገው እና የውጭ ሀገር የተከፈለ ግብርካለ ለማካካስ ከተቀነሰ በኋላ በሚገኘው መጠን ላይ የሚፈለግበትን ገቢ ከገቢ ማስታወቂያው ጋር በአንድ ላይ ገቢ ማድረግ አለበት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከኪራይ ያገኘው ገቢ ያላደረገ ሰው ወለድ እና ክፍያው ለዘገየበት መቀጫ እንደሚከፈል በአዋጅ አንቀጽ 74 ላይ ተደንግጓል።

የኪራይ ገቢ ግብሩን በወቅቱ ያልከፈለ አከራይ ገቢ ሰብሳቢው አካል በሚሰጠው የግብር ማስታወቂያና በሚያስቀምጠው ጊዜ መሰረት ካልከፈለ በአንቀፅ 77 መሠረት የግብር ኪራዩን ሀብት ይዞ መሸጥ፣ በባንክ በስሙ የሚገኝ ገንዘብ ወይም የሚከፈለው ሂሳብ ለእዳው መክፈያ እንዲውል የማድረግ ስልጣ አለው።

የጠቋሚዎች ማበረታቻ

በአንቀፅ 84 መሠረት ግብር የሚከፈልበትን ገቢ የደበቀ አሳንሶ ያስታወቀ ወይም ያጭበረበረ ወይም ግብር የማይከፍል አከራይ ላይ በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፎ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሪፖርት የሚያቀርብ ሰው የተደበቀውን ግብር እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ሽልማት ያገኛል። ሆኖም የግብር አለመክፈሉ ድርጊት ተከራይ ከሆነ ይህን ማድረግ የስራ ግዴታው ለሆነ ሰው የማበረታቻ ሽልማቱ አይሰጥም። ግብርን በወቅቱ አለማሳወቅ አሳንሶ ማሳወቅ፣ አዘግይቶ መክፈል የየራሳቸው የተቀመጠ የጊዜ ገደብና መቀጮ አላቸው።

የወንጀል ኃላፊነቶች፡- ከቤት ኪራይ ገቢ የሚያገኙ ሰዎች እንደማንኛውም ግብር ከፋይ በሕግ የተጣለባቸው ግዴታ አለ። ይህን ግዴታ አለመወጣትም ከመቀጮና የሚፈለገውን የግብር እዳ ለማስከፈል ከሚወሰዱ የንብረት ማሸጥና ሌሎ እርምጃዎች በተጨማሪ በወንጀለኛ መቅጫ ስነሥርዓት ሕጉ መሠረት የሚያስቀጣ የወንጀል ኃላፊነት ያስከትላል።

አዋጁ በአንቀጽ 96 መሠረት የቤት አከራይም ሆነ ማንኛውንም ሌላ ግብር አከራይ ሕጉን በመጣስ ገቢውን ካላሳወቀ ወይም የሚከፈለውን ግብር ካልከፈለ ጥፋተኛ መሆኑ በፍ/ቤት ሲረጋገጥ ከአምስት ዓመት በማያንስ እስራት ይቀጣል። አሳሳች መረጃ ለግብር ሰብሳቢው ባለስልጣን ሰራተኛ አንድን መረጃ በተመለከተ አሳሳች ወይም የሀሰት መረጃ ማቅረብ ወይም ሊያሳስት በሚችል መልኩ መከታተል የሚገባውን መረጃ አካቶ አለማቅረብ የሚከፈለውን ግብር ከ1ሺ ብር በማይበልጥ አንሶ እንዲከፈል የሚያደርግ ከሆነ ከ20ሺ ብር ማይበልጥ መቀጫና ከ1-3 ዓመት እስር ይቀጣል። ያሳነሰ ግብር ከ 1ሺ በላይ ከሆነ ከ20ሺ -1000 ሺ ብር መቀጮና ከ3-5 ዓመት እስር ይቀጣል።

በተጨማሪ ተከራይም ሆነ ማንኛውም ሰው ስራውን በማከናወን ላይ ያለ የገቢ ሰብሳቢውን ሰራተኛ ስራ ያሰናከለ ወይም ለማሰናከል የሞከረ የገቢ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳዩ ሰነዶችን እንዲያስመረምር ሲጠየቅ እምቢ ካለ፤ በግብር ሰብሳቢው ባለስልጣን ለጥያቄ ሲጠሩ ካልቀረበ፣ ወደ ግብር ከፋዩ የንግድ ስራ ቦታ ለመግባት ያለውን መብት ከገደበ፣ የወንጀል ክስ ሲፈረድበት ከ10ሺ - 100ሺ የገንዘብ መቀጫን በሁለት ዓመት እስር ይቀጣል። አከራዩ የገቢ ግብር አዋጁን እንዲጥስ ያበረታታ በሚስጥር የተባበረ ተከራይም ሆነ ሌላ ሰው በአንቀፀ 101 መሠረት በእስራትና በገንዘብ ቅጣት ይቀጣል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የረዳት አብራሪው ኃይለመድህን አበራ የወንጀል ክስ ጉዳይ በየትኛው አገር ፍ/ቤት...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 24 June 2024