የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 አፈፃፀም ላይ የሚስተዋል መሠረታዊ የአሠራር ግድፈት

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ላይ አንድ ምስክር በፖሊስ ምርመራ ወቅት የሰጠው ቃል ዓቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሹ ባመለከተ ጊዜ የተሰጠውን ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህ መብት የተሰጠው ለዓቃቤ ሕግ እና ለተከሳሽ በእኩል ደረጃ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ በሚባል አኳኋን እየተጠቀመበት ያለው ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕግ በማስረጃነት የቆጠረው ምስክር በማንኛውም ምክንያት በችሎት ቀርቦ መመስከር ባልቻለ ጊዜ ሁሉ ዓቃቤ ሕግ የሚጠቅሰው ሥነ ሥርዓት የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145ን ነው፡፡ በችሎት የቀረቡ ምስክሮች አጠራጣሪ ወይም የቀረበውን ክስ በሚገባ የማያስረዱ ሲሆን ዓቃቤ ሕግ ፊቱን ወደ 145 ያዞራል፡፡ 145 የዓቃቤ ሕግ የማስረጃ ክፍተት ማሟያ እየሆነ መጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ይህንንኑ ለፖሊስ የተሰጠ የምስክርነት ቃል በአብዛኛው ተቀብለው በማስረጃት ሲጠቀሙበት ይሰተዋላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ማጠንጠኛም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ያለአግባብ በዓቃቤ ሕግና በፍርድ ቤቶች ጥቅም ላይ ውሏል የሚለው ነጥብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ በሚከተሉት ሦስት ነጥቦች እንዴት ተገቢ እንዳልሆነ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

1.  በተከሳሹ መስቀለኛ ጥያቄ፣ በፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄ ያልቀረበለት፣ ተገቢው መኃላ ፈጽሞ ምስክርነቱን ያልተሰጠን የምስክርነት ቃል በማስረጃነት መቀበል ሕገ መንግሥታዊ ስላለመሆኑ

አንድ ተከሳሽ ጥፋተኛ እስኪባል ንፁህ ነው፡፡ ይህ ንጹህነቱ ጥፋተኛ እስኪባል ድረስ ከሚረጋገጥባቸው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ደረጃዎች አንዱ የቀረበበትን ምስክር በጥያቄዎቹ መፈተን ሲችል ነው፡፡ ተከሳሽ የቀረበበትን ምስክር ሲጠይቅ ለፍርድ ቤቱ የሚያሳየው እውነት ከመኖሩም ባላይ ፍርድ ቤቱ ስለ ምስክሩ ታማኝነት፣ ስለምስክርነቱ ክብደት እና ተገቢነት የሚረዳው እውነት ይኖራል፡፡ በተከሳሽ መስቀልያ ጥያቄ ያልቀረበለት ምስክር ምስክር ሳይሆን ቃል አቀባይ ነው፡፡ በጥያቄ የሚመሰከረው ምስክርነት እውነትና ያልተመረመረ ምስክርነት ምስክርነት ሳይሆን የአቋም መግለጫ ነው፡፡ ለዚህም ነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 ላይ የተከሰሱ ሰዎች የቀረቡላቸውን ምስክሮች የመጠየቅ መብት የተጎናጸፉት፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 136 እና ተከታዮች ድንጋጌዎችም ስለምስክርነት ሥርዓት ቁልጭ ተደርጎ ተቀምጧል፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንድ ምስክር በአንድ ተከሳሽ ላይ እንዲመሰክር ሲደረግ ስለ እውነት በሚያምንበት ነገር የመማል፣ በሚመሰክርበት ጊዜ ለተከሳሽ መስቀልያ ጥያቄዎች እንዲሁም ለፍርድ ቤቱ የማጣሪያ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ምናልባትም እንደ ክርክሩ ደረጃ ከኤግዚቢቶች፣ ቀደም ሲል ከተሰጠው ምስክርነት ከነገሮች ጋር የተዛመዱ ፈታኝ የመስቀልያ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል፡፡ በነዚህ ሂደቶች አልፎ የሰጠው ምስክርነት ከጉዳዩ ጋር ተገቢነት ያለው፣ የማስረዳት ክብደቱ ከፍተኛ የሆነ፣ እምነት የሚጣልበት ምስክርነት ሰጥቶ ከሆነ በርግጥም ተከሳሹ በዚህ ምስክር ምስክርነት ንጹህ ሆኖ የመገመት ካባው ወልቆ ጥርጣሬ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ይህን ማስተባበል ባለመቻሉም ወንጀለኛ ተብሎ ቢፈረጅ የፍትሕ ሥርዓቱ የሚፈልገው ተገቢ ሁነት ነው እና እሰይ እንጂ ለምን ሊባል አይችልም፡፡

በሕገ መንግሥቱም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተቀመጡ የመማል፣ በክስ ሂደቱ የቀድሞ ጥፈተኝነት ያለመግለፅ፣ ዋና ጥያቄ መስቀለኛ ጥያቄ እና ድጋሜ ጥያቄ የመጠየቅና የመጠየቅ፣ በተለየ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በግልፅ ችሎት የመዳኘት፣ ጉዳዮች ዓላማው በተድበሰበሰ፣ ግልፅነት በጎደለው፣ ተገቢው ጥያቄ ባልቀረበበት፣ እምነት በማይጣልበት፣ ሀሰት በሆነ ምስክርነት ንፁህ የሆኑ ሰዎች ወንጀለኛ እንዳይባሉ ለመከላከል ሕጉ ለተከሳሹ መብት ዘብ ያቆማቸው መሠረታዊ የወንጀል ክርክር መግለጫዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ሂደቶች ያላላፈን በአንድ ወቅት ፖሊስ ሲጠይቀው ለፖሊስ የሰጠው ቃል ለጠፋ ምስክር፣ ለተንሻፈፈ ማስረጃ፣ ለጎደለ ምስክርነት ማሟያ የምናደርገው ከሆነ ከፍ ሲል የተገለፀው መሠረታዊ የወንጀል ክርክር ሂደቶችን አስፈላጊነት መካድ ይሆንብናል፡፡

በአብዛኛው ዓቃቤ ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145ን የሚጠቅሰው በችሎት የተሰጠው ምስክርነት ሳያረካው ሲቀር እና በተሰጠው ምስክርነት ተከሳሹ ጥፋተኛ ላይባል ይችላል ብሎ በገመተ ጊዜ በመሆኑ ተገቢውን ሥርዓት ያላለፈ ለፖሊስ የተሰጠን ምስክርነት በማቅረብ የጎደለውን ለማሟላት ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ ፍርድ ቤቶችም ወዲያውኑ ስለሚቀበሉት ዓቃቤ ሕግ ምስክሩን ተገቢውን ጥረት አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ ወደ 145 የመሮጥ አዝማሚያ እንዲያሳይ ያደርገዋል፡፡

ባልተፈተነ፣ እውነትነቱ ባልተረጋገጠ፣ በመሃላ ሥር ሆኖ ባልተሰጠ ቃልም የጎደለው ሞልቶ የተንሻፈፈው ተቃንቶ ጥፋተኛ እስክንልህ ንጹህ ነህ ያልነውን ተከሳሽ፣ ንፁህ ሰው ከሚታሰር 10 ወንጀለኛ ነጻ ይወጣ ያልነውን ሰው፣ ሳንጠነቀቅ መብቱን ሳናከብርለት በችሎት ቀርቦ ተገቢውን ሥርዓት ሳይፈፅም በአንድ ወቅት ለፖሊስ ቃሉን በሰጠ ምስክር ምስክርነት ተከላከል ብሎም ጥፋተኛ ማለት የሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 145 ን በርዕሱ ላይ ለተገለፀው መሣርያነት ማዋል መስሎ ይሰማኛል፡፡

2.     የአንቀጹ አቀራረጽና መንፈስ በችሎት ያልቀረበ ምስክር ለፖሊስ የሰጠው ቃል በተከሳሽ ላይ ማስረጃ እንዲሆን ስላለመሆኑ

አንድ ምስክር ለፖሊስ የሰጠው ምስክርነት በችሎት ቀርቦ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከተው ማድረግ ተገቢት የሚኖረው ምስክሩ ራሱ በችሎት በቀረበ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ላይ እንደተመለከተው ከመነሻው ለፖሊስ የተሰጠው ቃል ፍርድ ቤቱ እንዲመለከተው የሚደረገው በዓቃቤ ሕግ ወይም በተከሳሹ አመልካችነት ነው፡፡ የአንቀጹ ዓላማ በችሎት ያልቀረበ ተከሳሽ የሰጠውን ምስክርነት ማስረጃ አድርጎ መውሰድ ከሆነ ተከሳሹ ምስክሩን ለፖሊስ እንዲህ ብለህ ቃል ሰጥተሃል አሁን ደግሞ ለፍርድ ቤቱ እንዲህ እያልክ ነው እያለ ካልጠየቀው በስተቀር ለፖሊስ የተሰጠው ቃል ለተከሳሹ በፍጹም ሊጠቅም አይችልም፡፡ ለዚህም ነው በአንቀጹ ንዑስ ቁጥር 2 ላይ ‹‹ከዚህ በኋላ ለትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ የሚጠቅም መስሎ ከታየው የዚህ ቃል ግልባጭ ለተከሳሹ እንዲደርሰው አድርጎ በዚሁ መሠረት ምስክሩ የሰጠውን ቃል ማስተባበል ይችላል›› ተብሎ በግልጽ የተቀመጠው፡፡ ምስክሩ በችሎት ካልቀረበ ግን በአንድ ወቅት በፖሊስ ጣቢያ ተከሳሹ ሳይኖር ሳይሰማ የተሰጠን ቃል ማስተባበል በፍጹም የሚቻል አይሆንም ምስክሩ በችሎት ከቀረበ ግን ከዚህ በፊት ከሰጠው ቃል ጋር በማነፃፀር ምስክሩ መፈተን ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ምስክሩ በችሎት ካልቀረበ በተ.ቁ 1 ላይ በተገለፁት ምክንያቶች ምስክርነቱን በማስረጃነት ከጅምሩ መቀበል ተገቢ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በችሎት ቀርቦም ግን ፍርድ ቤቱ ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ የሚረዳ ነው ብሎ ካላሰበ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ተመልክቶ ውድቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡

ሕጉ በርግጥም ለፖሊስ የተሰጠ ቃል እንደ ማስረጃ በመቁጠር በዚሁም ተከሳሽ እንዲከላከል ወይም ጥፋተኛ ነህ እንዲባል ለማድረግ ቢፈልግ ኖሮ ፍርድ ቤቱ ይመለከተዋል ከማለት ይልቅ በማስረጃነት ይቀበለዋል የሚል ግልፅ ቃል መጠቀም በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ማስረጃ የሚሆነው ራሱ ለፖሊስ የሰጠው ቃል ሳይሆን ዓቃቤ ሕግ ሆነ ተከሳሽ ለፖሊስ የተሰጠውን ቃል ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትላቸው እንዲጠይቁ ባነሳሳቸው አንዳች ምክንያት ከግራ ቀኙ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምስክር የሚሠጠው ምስክርነት ለፖሊስ የሰጠው ቃልና ለፍ/ቤት የሰጠው ቃል አንድነት ወይም ልዩነት እንዲመረመር ነው፡፡

3.  ለፖሊስ የተሰጠ ቃል በሀሰተኛ ምስክርነት የማያስጠይቅ መሆኑ ለፖሊስ የተሰጠን ቃል ሕጉ ክብደት የማይሰጠው መሆኑን አመላካች ስለመሆኑ

 በወንጀል ሕግ አንቀጽ 453 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው አንድ ምስክር ሀሰተኛ ምስክር ተብሎ የሚጠየቀው ምስክሩ ምስክርነቱን የሰጠው የዳኝነት ወይም የዳኝነት ነክ ያለው ሥርዓት በሚካሄድበት ጊዜ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚሳየው ለፖሊስ የተሰጠ ቃል በሀሰተኛ ምስክርነት የማያስጠይቅ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ምስክሩ በሀሰተኛ ምስክርነት በማይጠየቅበት በሥርዓቱ መሠረት እውነት የተናገረ መሆኑን በችሎት መሃላ ቃል ባላረጋገጠበት ሁኔታ የሰጠውን ምስክርነት መቀበል ምስክሮች ሀሰተኛ ምስክርነት እየሠጡ እንዲጠፉ የሚያበረታታ፤ በሀሰተኛ ምስክርነትም ሰዎች ጥፋተኘ እንዲባሉ እድል የሚፈጥር በመሆኑ  የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 145 በጠባቡ በአጠቃላይ የሥነ ሥርዓቱ መንፈስ ለፍትሕ ካለው ፋይዳና ከተሳሽ መሠረታዊ መብት አኳያ እየታየ ሊተረጎም ይገባዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥብቃ በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ
ስለቀዳሚ ምርመራ (Preliminary Inquiry) ፍርድ ቤት ተልዕኮ፣ ሥልጣን...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 29 March 2024