የውጪ ሀገር ገንዘብ ትርጓሜና የወንጀል ኃላፊነቱ - ሕግና ትግበራ አጭር ዳሰሳ

Apr 08 2022

 

 “Individual rights are the means of subordinating society to moral law” Ayn Rand

     “የግለሰቦች መብት ማህበረሰብን ለሞራል ህግ ተገዢ የምናደርግበት መሳሪያ ነው”

“ይህቺ አጭር ዳሰሳ በሀገራችን የህግ ታሪክ ትምህርት መስክ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ላደረጉትና  ህያው መታሰቢያ ለገነቡት የማይተኩት አቶ አበራ ጀምበሬ ትንሽ ምስጋና ትሁንልኝ”

ወዳጄ! በኪስህ እንደ ልማድም (hobby) እንደ ቅንጦትም በዋሌትህ ወይም በእጅሽ ቦርሳ የያዝሻት 1(አንድ የአሜሪካን ዶላር) እስከ 10(አስር ዓመታት) ሊያሳስርህ እና እስከ ብር 50,000(ሀምሳ ሺ) ሊያስቀጣህ እንደሚችል ብነግርህ ምላሽህ/ሽ ምን ይሆን? ነገሩ ወዲህ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት ለውጪ ሀገር ኢንቨስተሮች ያቀረበውን ጥሪ ተቀብላ በሆቴል የሥራ መስክ የተሠማራችው የውጪ ሀገር ዜጋ የሆነችው ደንበኛዬ በሆቴሏ ላይ በተደረገ ብርበራ 1 (አንድ) የአሜሪካን ዶላር፣ 1 (አንድ) የቻይና የን፣ እና 1000 (አንድ ሺ) የጂቡቲ ፍራንክ ተገኝቷል ተብሎ በደንበኛዬ ላይ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ-ህግ ‘የውጪ ሀገር ገንዘቦችን የማስቀመጥ ወንጀል’ ክስ መቅረቡ ነው የዚህ አጭር ጽሑፍ መነሻ ምክንያት ...በንባብ ተከተሉኝ በአስተያየታችሁ አርሙኝ፡፡

1.ትርጓሜ

በሀገራችን ህግና ስርዓትን የማስከበር ዓላማን ይዞ ወንጀለኛን በመቅጣትና በማረም እንደዚሁም ህብረተሰቡን ደግሞ አስቀድሞ ከወንጀል ድርጊት እንዲቆጠብ ለማሳሰብ በ1996ዓ.ም የጸደቀው የኢፌዲሪ የወንጀል ህጋችን አጠቃላይ(General) የወንጀል መርህዎችንና እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ተግባራትን ዘርዝሮ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የወንጀል ህጋችን ስለውጪ ሀገር ገንዘብ በሚደነግገው አ.ቁ 346 ላይ

“የውጪ ሀገር ገንዘብን ፍቃድ ሳኖረው ወይም ህግን በመጣስ ከውጪ ሀገር ያስመጣ ወይም ወደ ውጪ ሀገር የላከ በአደራ አስቀማጭነት የተቀበለ ያስቀመጠ የመነዘረ የሸጠ ወይም ለሽያጭ ማቅረብ ከ10ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከ50,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል”

 ወንጀል ስለመሆኑ ከመግለጽ ባለፈ የውጪ ሀገር ገንዘብ  ማለት ምን ማለት ስለመሆኑ ትርጓሜ ከመስጠት ታቅቧል፡፡

ይህን ክፍተት ለመሙላት የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በአንቀጽ ቁጥር 2(5) እና የብሄራዊ ባንክ መመሪያ የሆነው Transparency in Foreign Currency Allocation and Foreign Exchange Management Directive No. FXD/77/2021 በአንቀጽ ቁጥር 2(5)ስር እንደሚከተለው ትርጉም ሰጥቷበታል፡፡ የውጪ ሀገር ገንዘብ ማለት

ከኢትዮጵያ ገንዘብ መስተቀር ከኢትዮጵያ ውጪ በማናቸውም ሀገር ህጋዊ ገንዘብ የሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደረግ ክፍያ ተቀባይነት እንዳለው ብሔራዊ ባንክ ያሳወቀው ማናቸውም ገንዘብ ነው” በማለት ትርጉም ሰጥቷበታል፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ገንዘብ የውጪ ሀገር ገንዘብ ለመባል ሁለት ቅድመ-ሁናቴዎችን ማሟለት ያለበት ሲሆን እነርሱም፡-

1ኛ/ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሀገሮች ህጋዊ ገንዘብ መሆን እና

2ኛ/ ይህን የውጪ ህጋዊ ገንዘብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለክፍያ/ግብይት መዋል መቻል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለግብይትና ለምንዛሬ መዋል የሚችሉትን የውጪ ሀገር ገንዘቦች ለመለየት ስልጣን የተሰጠው ይሄው ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው ለባንኮች በሚለከው ሰርኩላር ደብዳቤ ላይ በሀገራችን ለክፍያና ለምንዛሬ መዋል የሚችሉት 17  የውጪ ሀገር ገንዘቦችን(ይህ ጽሁፍ በተጻፈ ጊዜ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የመጨረሻው ሰርኩላር) የለየ ሲሆን በምክንያትነትም የሀሪቷን ውስን አቅም፣ በተመረጡት ገንዘቦች በዓለም ዓቀፍ ገበያ በቀላሉ ለመመንዘር መቻላቸው፣ የተመረጡት ገንዘቦች ምንዛሬ በቀላሉ የማይዋዥቅ መሆን፣ ከሀገራቱ ጋር ኢትዮጵያ ያላት የንግድ ትስስር፣ የሀገራቱ የኢኮኖሚ አቅምና የገንዘባቸው ጥንካሬ እና ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶችን ዘርዝሯል፡፡ እነዚህ 17 የውጪ ሀገራት ገንዘቦች ሲሆኑ እነርሱም፡-

 1. የአሜሪካን ዶላር
 2. የእንግሊዝ ፓውንድ
 3. የሰውዲ ክሮነር
 4. የስዊዝ ፍራንክ
 5. የኖርዌይ ክሮነር
 6. የዳኒሽ ክሮነር
 7. የጃፓን የን
 8. የካናዳ ዶላር
 9. የሳውዲ ሪያድ
 10. የተባበሩት ዐረብ ኢምሬት ድርሀም እና
 11. የአውሮፓ ዩሮ
 12. የህንድ ሩፒ
 13. የቻይና የን
 14. የኬንያ ሽልንግ
 15. የአውስትራሊያ ዶላር
 16. የደበብ አፍሪካ ራንድ እና
 17. የኩዌይት ዲናር

ብቻ ናቸው፡፡

ስለሆነም ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት የውጪ ሀገራት ገንዘቦች ውጪ በሌሎች የዓለማችን ክፍል በሆኑት ሀገራት ላይ ያሉት የውጪ ሀገር ገንዘቦች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ውጪ ሀገር የማይቆጠሩ ናቸው፡፡

 1. የወንጀል ኃላፊነቱ

  በሀገራችን አንድ ድርጊት ህገ-ወጥነቱና አስቀጪነቱ በህግ እስካልተደነገገ ድረስ ማንም ሰው ለፈጸመው ድርጊት የወንጀል ኃላፊነት ማይኖርበት ስለመሆኑ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 23(1) የሚደነግግ በመሆኑ ከላይ ከተመለከቱት ውጪ የውጪ ሀገር ገንዘቦችን መያዝም ሆነ ማስቀመጥ የወንጀል ኃላፊነት የሚያመጣ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከላይ በዝርዝር ከተመለከቱት ውጪ የውጪ ሀገራት ገንዘቦችን በመያዙ ወይም በማስቀመጡ ማንም ሊከሰስም ሆነ ሊቀጣ አይገባም፡፡

 ነገር ግን ከላይ ከተመለከቱት 17ቱ የውጪ ሀገራት ገንዘቦች ውስጥ መያዝና ማስቀመጥ የማይቻልበት የገንዘብ መጠን አለ? ወይስ የለም? በተለይም ደግሞ ብዙ ሰው እንደ ልዩ ልማድ(hobby) የውጪ ሀገር ገንዘቦችን የማስቀመጥና የመያዝ ባህል በዳበረበት ሁናቴ (የዚህ ልማድ ያላቸው ሰዎች Notaphilist ይባላሉ) ህጉ ይህን ግንዛቤ ውስጥ አድርጓል ወይስ አላደረገም? የሚለውን በአጭሩ እንደሚለከተው እዳስሳለሁ፡-

2.1 የሚያስቀጣው የገንዘብ መጠን ልክ ስንት ነው?

  የወንጀል ህጋችንም ሆነ የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅና መመሪያ የውጪ ሀገር ገንዘብ ማለት የሚለውን ትርጉም በመስጠት እንዚህን ገንዘቦችን የያዘና ያስቀመጠ ማንኛውም ሰው በወንጀል እንደሚቀጣ ከመደንገግ ባለፈ በሀገራችን ለክፍያ መዋል የሚችሉ የውጪ ሀገራት ገንዘቦች አስቀጪ የሚሆኑት መጠናቸው ምን ያህል ሲሆን ነው የሚለውን መልስ አልሰጡበትም፡፡ በመሆኑም የገንዘብ መጠኑ ልዩነት ሳይኖረው ከላይ ከተመለከቱት 17 የውጪ ሀገር ገንዘቦችን1( አንድ)ም ይሁን 1,000(አንድ ሺ) ፍቃድ ሳይኖረው መያዝና ማስቀመጥ ከ10ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከ50,000 ብር በማይበልጥ መቀጮ የሚቀጣ ስለመሆኑ የወንጀል ህጉ ይደነግጋል፡፡

     2.1.1 ልዩ ድንጋጌዎች( exceptional provisions)

ሀ/ የብሔራዊ ባንክ ደንቦች

ይሁን እንጂ እነዚህን ገንዘቦች በህጋዊ መንገድ መያዝ የምንችለበትን ልዩ ድንጋጌዎች(exceptional conditions) አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ Directive NO. FXD /49/2017 Limits on the Birr and Foreign Currency Holding in the territory of Ethiopia የተባለ ደንብ ያወጣ ሲሆን ይህ ደንብ በአንቀጽ ቁጥር 3 ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሰው የውጪ ሀገር ገንዘብን ከ30 ቀናት በላይ ለመያዝ አይችልም በማለት ይደነግጋል፡፡ ይህም ማለት ከውጪ ሀገር ሲገቡ ወይም ከሀገር ውጪ ለሚያደርጉት ጉዞ በባንክ ተፈቅዶ የውጪ ሀገር ገንዘቡን ከያዙበት ቀን ጀምሮ ላሉት 30 ቀናት እነዚህን 17 የውጪ ሀገር ገንዘቦችን መያዝ የሚችሉና በዚህም ድርጊት በወንጀል የማይጠየቁ ስለመሆኑ ይደነግጋል፡፡

እንደዚሁም ብሔራዊ ባንክ Issuance, Use and Acceptance of International Credit/Debit Card, Foreign Cuurency Cash Notes and Travellers Cheques International Payme Instruments (As Amended)Directive No. FXD/56/2018 በሚል ባወጣው የተሻሻለው ደንብ አንቀጽ 9 ላይ እነዚህን 17 የውጪ ሀገር ገንዘቦችን ለክፍያ እና ለመገበያያ እንዲቀበሉ የተፈቀደላቸው ተቋሞች የውጪ ሀገራት ገንዘቦችን ይዘው በመገኘታቸው ወይም በማስቀመጣቸው የወንጀል ኃላፊነት አይኖርባቸውም፡፡

ከዚህ ልዩ ሁናቴ ውጪ እነዚህን 17 የውጪ ሀገር ገንዘቦች መያዝ አስቀጪ ስለመሆኑ በወንጀል ህጉ የተደነገገ ሲሆን የገንዘቡን መጠን ማነስና መብዛት በቅጣት አወሳሰን ላይ ከመጠቀም ባለፈ ከድርጊቱ አስቀጪነት ነጻ አያወጣም፡፡ እንደዚሁም እንደ ልማድ(hobby) ገንዘብ የምትሰበስብ ሰው መሆንህን ህጉ ለይቅርታ ምክንያት አድርጎ አላስቀመጠውም፡፡

 በዚህም ህግ አውጪውና የብሔራዊ ባንክ ገዢዎች የህግ መሰረታዊ ባህሪ የሆነውን የህብረተሰብን መልካምና ጤነኛ ባህልና ልማድን ዕውቅና መስጠት ማስከበርና መጠበቅ ያላገነዛበ ድንጋጌዎችን በማውጣት የግለሰብን መብት ባለማክበር ማህበረሰብ ለሞራል ህግ ተገዢ እንዳይሆን ዱላ እያቃበሉ ነው፡፡

 ለ/ የፍትህ ሚኒስትር ሰሩኩላር

ነገር ግን የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር(ጠቅላይ ዐቃቤ-ህግ) ይህ ከላይ የተመለከተው አዋጅና መመሪያ መሰረታዊ የግለሰቦች መብት ላይ ጥሰት የሚያስከትል መሆኑን ዕውቅና በመስጠት በ2011ዓ.ም ባወጣው ሰርኩላር (ይህን ለማግኘት ያደረኩት ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም) በኢትዮጵያ ሲመነዘሩ የገንዘብ መጠናቸው ከብር 1,000(አንድ ሺ) በታች የሆኑ በኢትዮጵያ ለክፍያ መዋል የሚችሉ ማንኛውም የውጪ ሀገር ገንዘቦችን በያዙና ባስቀመጡ ሰዎች ላይ ክስ እንዳይቀርብና ፣የቀረበ ክስ ካለም እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡ ይህን ጽሁፍ በማገባደድ ላይ እንዳለሁ የፍትህ ሚኒስቴር ይህን ሰርኩላር በማሻሻል መጋቢት 15 ቀን 2014ዓ.ም በቁጥር ፍ/ሚ 01ደማ3066 በተጻፈ ሰርኩላር  ይህን የገንብ መጠን ልክ ወደ 100(አንድ መቶ ) የአሜሪካን ዶላር ከፍ ወይም አሁን ባለው የባክ ምንዛሬ ሲመነዘር ከ5,200(አምስት ሺ ሁለት መቶ) በታች ከሆነ ገንዘቡ እንዲወረስ ክስ ግን እንዳይቀርብ አሳውቋል፡፡ ልብ አድርግ ክስ እንዳይቀርብ እንጂ ድርጊቱ ወንጀል አይደለም አልተባለም፡፡ በዚህም ተግባሩ የግለሰቦች ጤናኛ ልማድን አክብሮ ጤናኛ ማህበረሰብ እንዲገነባ ፍትህ ሚኒስቴር መሰረት ጥሏል፡፡

 1. ትግበራ

ህጉ በተለይም ደግሞ የፍትህ ሚኒስቴር ሰርኩላር ደብዳቤ ተፈጻሚ እየሆነ ባለበት ሁናቴ የራሱ የተቋሙ ሰራተኞች ከላይ ለዚህ ጽሁፍ ምክንያት የሆነውን ክስ ማቅረባቸው ተቋሙና ሰራተኞቹ የትና የት ናቸው? የሚያሰብል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እኔም የተቋሙን ሰርኩላር መሰረት በማድረግ ጉዳዩን ለበላይ አካል በማሳወቅ ከ8ወራት የፍርድ ቤት ምልልስ በኃላ ክሱ ተቋርጦ መዝገቡ ተዘግቶ ተሸኘን፡፡ ይህ አንድ ጉዳይ የትግበራው ሙሉ ሂደትን ለማስቃኘት በቂ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ቢሆንም ሀሳቤ እንደ ሁልጊዜው የገጠማችሁን እንድታካፍሉንና ልማድን በዕውቀት እንድንሽር ነውና ዝምታቹን ስበሩ፡፡

Read 1813 times Last modified on Apr 08 2022
Dagim Assefa

ጦማሪው በሕግ የመጀመሪያ ድግሪውን (LLB) ከቅ/ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በ1999 ዓ.ም ያገኘ ሲሆን ሁለተኛ ድግሪውን (LLM) ደግሞ ከባህር ዳር የኒቨርስቲ በ2005ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በአቃቤ-ሕግነት፣ በመምህርነትና በነገረ-ፈጅነት ያገለገለ ሲሆን አሁን ደግሞ ጠበቃና የሕግ አማካሪ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡