09 December 2020 Written by 

የተምታታው የ"ዘር ማጥፋት ወንጀል" አረዳድ በኢትዮጵያ

 

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ.ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የኢትዮጵያን ማኅበረ-ፖለቲካ በአያሌው የነቀነቁ ትላልቅ ኹነቶች ተከስተዋል። ከክልል ባለስልጣናት እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግድያ አንስቶ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግጭቶች እና አሁን ደግሞ ጦርነት ተከስተው በዓይነት የበዙ፣ በመጠን የሰፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሁሉም የሐገሪቱ አካባቢዎች በሚባል ሁኔታ ታይተዋል። እነዚህን የመብት ጥሰቶች በጥቅሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ናቸው ከማለት ባለፈ፤ በርካቶች ዓለም አቀፍ እና ሐገር አቀፍ ሕጎችን በግርድፉ በማጣቀስ ድርጊቶቹን ብዙ ጊዜ፡- የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide)፣ አለፍ ሲል፡- በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crime against humanity)፣ አሁን አሁን ደግሞ፡- የጦር ወንጀል (War crime) በሚል ሲፈርጇቸው መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን በየጊዜው የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓለም አቀፍ ተቋማትን ብንተዋቸው፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች እና ሌሎች በጣም ጥቂት የሚባሉ የሲቪክ ማኅበራት ከሚያደርጉት ጥረት በዘለለ ድርጊቱን አጣርቶ፣ መርምሮ፣ ተንትኖ እና በሰነድ አደራጅቶ ይፋ ማድረግ ላይ ያለው ትልቅ ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ብዙኃኑ የተፈጸሙትን ድርጊቶች እንዳሻው እንዲፈርጃቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በመነሳት በዚህ ጽሁፍ፤ በዋናነት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ምንነት በአጭሩ በማየት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የተምታታ አረዳድ መነሻ ምክንያት እና መፍትሔዎቹን ለመጠቆም ጥረት አደርጋለሁ፡፡

በተለያየ ጊዜ ከተደረጉ ዓለም አቀፍ ሥምምነቶችና ከሌሎችም የዓለም አቀፍ ሕግ ምንጮች መነሻነት ገዢ የሆኑትን ዓለም አቀፍ ሕጎች በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፤ የሰው ልጅን ሁሉ ክብር የሚነኩ እና ዓለም አቀፍ የስረ-ነገር ስልጣን (Universal Jurisdiction) የሚሰጡ ናቸው የሚባሉት፡- የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide)፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (Crimes against humanity) እና የጦርነት ወንጀል (War crimes) የሚባሉት የወንጀል ድርጊቶች ናቸው፡፡

የጦርነት ወንጀሎች የሚባሉት በአራቱ የጄኔቫ ስምምነቶች፣ ተጨማሪ ፕሮቶኮሎች እና ሌሎችም አግባብነት ባላቸው ሕጎች መሠረት ጦርነት ወይም የትጥቅ ግጭት (Armed conflict) መሆኑ ብያኔ በተሰጠበት የግጭት ሁኔታ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም ወገኖች ላይ ተፈጻሚ የሚሆኑ ጦርነት የሚደረግበትን አግባብ የሚወስኑ ገደቦችና ክልከላዎችን በመጣስ፤ ባልታጠቁ (ሲቪል) ሰዎች ላይ፣ በሲቪል ንብረቶች ላይ፣ በቆሰሉ ወይም በተማረኩ ተዋጊዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡ በጦርነት ወቅት እነዚህን ዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች በመጣስ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል አንዱ ሲሆን፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች እንደየሁኔታው በአገር አቀፍ አልያም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ቀርበው ሊዳኙ ይችላሉ፡፡

በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚባሉት ደግሞ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለማቋቋም በወጣው የሮም ስምምነት አንቀጽ 1 እና 2፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ በሩዋንዳ እና በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተፈጸሙትን ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ተከትለው በኑረምበርግ፣ ሩዋንዳና ዩጎዝላቪያ የተቋቋሙትን ጊዜያዊ ችሎቶች (Ad hoc Tribunals) ለማቋቋም በወጡት ድንጋጌዎች መሠረት ትርጉም የተሰጣቸው ሲሆኑ፡-

‹‹…መግደል፣ ማጥፋት፣ ባርያ ማድረግ፣ ሕዝብን በግዳጅ ማፈናቀል፣ ከባድ የአካል ነጻነት ጉዳት ማድረስ፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ባርነት እና የመሳሰሉትን የወንጀል ድርጊቶች ጨምሮ፤ ጥቃቱን በማወቅ ስልታዊ በሆነ ወይም ብዙዎችን ሰለባ በሚያደርግ መንገድ ባልታጠቁ (ሲቪል) ሰዎች ላይ የሚፈጸም ወንጀል በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው በሚል ይገለጻል፡፡››

በመሆኑም፤ በጦርነትም ሆነ በማንኛውም ሰላማዊ ወቅት በስፋት ወይም በስልታዊና በተቀናጀ መንገድ ያልታጠቁ (ሲቪል) ሰዎችን ሰለባ የሚያደርግ ወይም ሊያደርግ የሚችል ድርጊት ሆን ብሎ እቅድና ዝግጅት ተደርጎበት የተፈጸመ ከሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጣስ የሚፈጸም ወንጀል ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎች እንደሁኔታው በአገር አቀፍ አልያም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ቀርበው በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸም የወንጀል ድርጊት በሚል ሊዳኙ ይችላሉ፡፡

 የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚባለው ደግሞ እ.አ.አ በ1948 በተደረገው የዓለም አቀፉ የሰው ዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት ስምምነት አንቀጽ 2 መሠረት ዘርን ማጥፋት ማለት በሚከተሉት ድርጊቶች አማካይነት ሆን ብሎ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የአንድን ብሔር፣ ጎሣ፣ ዘር፣ ወይም የኃይማኖት ወገን ማጥፋት ማለት ሲሆን፡- በሕግ እውቅና የተሰጣቸውን ወገኖች አባላት መግደል፣ ከፍተኛ የአካል ወይም የአዕምሮ ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረግ፣ በከፊልም ሆነ በሙሉ የአካል ህልውናቸውን በሚደመስስ አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ፣ መዋለድን የሚያግዱ እርምጃዎችን መውሰድ እና ከዚያ ወገን የተወለዱ ህጻናትን አስገድዶ ለሌላ ወገን አሳልፎ መስጠት የሚሉትን የወንጀል ድርጊቶች ያካትታል፡፡

ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሲነሳ፤ በአብዛኛው ጄኖሳይድ ዋች የተሰኘው ዓለም አቀፉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተከላካይ ድርጅት ያዘጋጃቸው አስር ያህል ደረጃዎች አብረው መነሳታቸው አይቀርም፡፡ የዘር ማጠፋት ወንጀል የአንድ ቀን ድርጊት ሳይሆን፤ በብዙ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ሒደቶች ውስጥ አልፎ የሚከሰት ሒደት ነው፡፡ በመሆኑም፤ በእያንዳንዱ ደረጃዎች የሚወሰዱ የጥንቃቄ እና የመከላከል እርምጃዎች ወንጀሉን እንዳይፈጸም ለመከላከል የሚያስችሉ ጠቃሚ መለኪያዎች መሆናቸው በዓለም አቀፍ ልማድ ተቀባይነት አላቸው፡፡ እነዚህም ደረጃዎች፡- መመደብ (Classification)፣ ወካይ ሥም/ምልክት መስጠት (Symbolization)፣ አድልዎ (Discrimination)፣ ከሰውነት ክብር ማውረድ (Dehumanization)፣ መደራጃት (Organization)፣ ጽንፍ መያዝ (Polarization)፣ ዝግጅት (Preparation)፣ ጥቃት (Persecution)፣ ማስወገድ/ማጥፋት (Extermination) እና መካድ (Denial) ናቸው፡፡ ተቋሙ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ ባለፉት ዓመታት እና በቅርብ ጊዜ ከተከሰቱት ሁኔታዎች በመነሳት ኢትዮጵያ ዘጠነኛው የማጥፋት ወይም የማስወገድ ደረጃ ላይ መሆኗን አሳውቋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምንነት በተብራራ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሕጎች አንጻር ተተንትነው ሲገለጹ አይስተዋልም፡፡ በዚህም የተነሳ፤ በበርካቶች ዘንድ የመብት ጥሰቶቹን ዓይነትና ምንነት በተመለከተ የጠራ ግንዛቤ ካለመያዝ እና/ወይም ፖለቲካዊ አቋሞች የተጫናቸው ብያኔዎች ሲሰጡ ይታያል፡፡ ለአብነት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በትግራይ ክልል የነበረውን ሁኔታ ተከትሎ በተለይም በማይካድራ ከተማ የተፈጸመውን እጅግ ዘግናኝ ግፍ ዙሪያ የነበረውን ብያኔ እንመልከት፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ህዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ዘገባ ‹‹በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ተራ ወንጀል ሳይሆን የታቀደ እና በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መሆኑን ጠቅላላ ድርጊቱ አና ውጤቱ ያመለክታል። በተለይም፤  

  • አጥፊዎቹ ሆነ ብለው፣ አቅደውና ተዘጋጅተው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የገደሉ መሆኑን፤
  • ድርጊቱ በስፋት ወይም በስልታዊና በተቀናጀ መንገድ በሲቪል ሰዎች ላይ የብሔር ማንነትን መሠረት አድርጎ ያነጣጠረ ጥቃት አካል ሆኖ መፈጸሙን፤
  • አጥፊዎቹ ድርጊታቸው በዚህ በስፋት ወይም በስልታዊና በተቀናጀ መንገድ በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት አካል መሆኑን እያወቁ ወይም ድርጊታቸው የዚሁ አካል እንዲሆን አስበው ተሳታፊ የሆኑበት መሆኑን፤
  • ድርጊቱ የተፈፀመው በወቅቱ በነበረው የጦርነት አውድ ውስጥ የአካባቢው አስተዳደርና የጸጥታ መዋቅር እንዲሁም የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ከፌዴራሉ ወታደሮች ጥቃት እየሸሹ በነበረበት ወቅት የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ በብሔር ማንነት በለዩዋቸው ሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን፤ እና
  • በጥቃቱ ወቅት በስልጣን ላይ የነበረው የከተማው የጸጥታ መዋቅር ሲቪል ሰዎችን ከአደጋና ጥቃት ከመከላከል ይልቅ፤ በተቃራኒው ሳምሪ ከሚባለው የወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ የወጣቶች ቡድን ጋር እያበረና እየተባበረ ጥቃቱን መፈጸሙና ማስፈጸሙን ጠቅሶ፤

በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች፤ በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 . እና ሌሊቱን የተፈጸመው ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል ሲሆን ምናልባትም ይህ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ነው፡፡››

እንግዲህ በመጀመሪያ ደረጃ ዘገባው እንደምንመለከተው የኮሚሽኑ መርማሪዎች ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ተገኝተው ካሰባሰቡት መረጃ እና ማስረጃ በመነሳት በወቅቱ በማይካድራ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል አመላካች መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን፤ በብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ድርጊቱን የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚል ብያኔ ሲጠቅሱት በስፋት ይስተዋላል፡፡ ይህን መሰሉ ብያኔ አልፎ አልፎም ቢሆን በብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ሳይቀር ታይቷል፡፡

ለአብነት ያህል ሰሞነኛውን የማይካድራ ክስተት አነሳሁ እንጂ፤ ከዚያም ቀደም ብለው የነበሩ በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ጥልቅ ምርመራ እና የሕግ ትንተና ሳይሰራባቸው በጥቅል አገላለጽ ብያኔ ሲሰጥባቸው ይስተዋላል፡፡ በእኔ አስተያየት፤ ይህን መሰሉ የተምታታ እይታ ከሁለት መሠረታዊ ነጥቦች የሚነሳ ይመስለኛል፡፡ እነዚህም፡- መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን መርምረው እና ተንትነው ይፋ የሚያደርጉ ተቋማት ጥረት እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ እና በብዙኃኑ ዘንድ ያለው መሰል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ከፖለቲካ አረዳድና ጥቅም ጋር አስተሳስሮ ሳይነጥሉ የማየት ልማድ የሚሉት ናቸው፡፡

ከዚህ አንጻር፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በየወቅቱ የሚፈጸሙ መሰል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በተገቢው ጥራት በመመርመር፣ በማደራጀት፣ በመሰነድ እና በመተንተን አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕ እንዲያገኙ ለማድረግ እና ወንጀል ፈጽሞ ሳይቀጡ የመቅረት ልማድ እንዳይኖር የሚያስችለውን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ሊመራ ይገባል፡፡ በእዚህ መልኩ የሚሠራው የተቀናጀ ሥራ በብዙኃኑ ዘንድ የተንሰራፋውን የተምታታ እይታ ማስተካከል ይቻላል፡፡ በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማትም ይህን ሰፊ ሥራ የማስተባበር እና ተቀናጅቶ የመሥራት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም መሰል የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በሚከሰቱበት ወቅት ተጨባጭ የምርመራ ሥራዎችና ትንተና ከመደረጉ አስቀድሞ ድርጊቶቹን ብያኔ መስጠት የሚያስከትለውን ችግር በመረዳት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፡፡

Last modified on Wednesday, 09 December 2020 13:22
Tibebu Hailu

The blogger has obtained his LLB from Hawassa University, School of Law. Currently, he is working as a Report Analyst at the Ethiopian Human Rights Council - EHRCO. He can be reached at [email protected]