የወንጀል ክስ ማንሳት እና ማስቀጠል የሚቻለዉ መቼ ነዉ?

Aug 27 2020

 

የክስ ማንሳት የፍሬ ነገር ይዘትና ስነ ሥርዓት በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 122 ስር በአምስት ንዑስ አንቀጾች ተጠቃሎ ይገኛል፡፡ በይዘቱም፡-

  1. ከከባድ የሰው ግድያ እና ከከባድ ውንብድና ወንጀሎች ውጭ ዐ/ሕግ ከፍርድ በፊት ክስ ማንሳት ይችላል፡፡
  2. ክስ የሚነሳው በዐ/ህጉ ጥያቄ ወይም በሌላ የመንግስት  አካል ትዕዛዝ ሊሆን ይችላል፡፡
  3. ክሱ የሚነሳው በፍ/ቤት ፈቃድ ሲሆን ፍ/ቤቱ ለመከልከልም ሆነ በመፍቀድ ምክንያቱን ማስቀመጥ አለበት፡፡
  4. በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 113 መሰረት አዲስ  ክስ ካልቀረበ  ተከሳሹ  ለግዜው  ይለቀቃል፡፡
  5. የክሱ መነሳት ዐ/ሕግ ክስን ከማንቀሳቀስ  አያግደውም፡፡

 የሚል ሀሳብ ያለው ነው፡፡

 

የፍትሕና የሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲቲዩት ባዘጋጀው ረቂቅ የወንጀል  ስነ-ሥርዓት ሕግ  አንቀጽ 119 ስር ዐ/ሕግ ከፍርድ ቤት በማንኛውም ጊዜ ክስ ማንሳት  የሚችል  መሆኑን በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 122 ስር የተመለከተው የፍርድ ቤት ፈቃድና በተወሰኑ የወንጀል ክሶች ላይ የተደረገው ክልከላ ተነስቷል፡፡ አብሮ በተዘጋጀው የህጉ ሀተታ ዘምክንያትም ጉዳዩን ዐ/ሕግ ካልተከታተለው በውጤት ደረጃ ልዩነት  የሌለው በመሆኑ በተወሰኑ ወንጀሎች የተደረገው ክልከላ እና የፍ/ቤት ፈቃድ መጠየቅ  አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም በሚል አስፍሯል፡፡

የኢ.ፌ.ድሪ.  አስፈጻሚ  አካላትን  ስልጣን እና ተግባር  ለመወሰን  የወጣው አዋጅ ቁ. 691/2003 የፍትሕ ሚኒስቴርን ስልጣንና ተግባር በዘረዝረው  አንቀጽ 16 ስር በንዑስ አንቀጽ 6 “… በቂ ምክንያት ሲኖር በህጉ መሰረት ክሱን ያነሳል…” በሚል ያስቀምጣል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ዐ/ሕግ ማቋቋሚያ  አዋጅ ቁ. 947/2008  ክስ  ማንሳትን አስመልክቶ “… የፌደራል ጠ/ዐ/ሕግ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ  ሆኖ ሲያገኘው ጠ/ሚንስትሩን  በማማከር  ክስ ያነሳል፡፡ የተነሳም ክስ  እንዲቀጥል  ያደርጋል፡፡” የሚል  ድንጋጌ አካቷል፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴር በ2003 ባዘጋጀው የኢትየጲያ የወንጀል ፖሊሲ ላይ  በገጽ 37  ክስ ማንሳትን አስመልክቶ “… ዐ/ሕግ የመሰረተውን የወንጀል ክስ ክርክር  መቀጠል የህዝብና የመንግስት ጥቅምን አያስጠብቅም ብሎ  ካመነ ለፍ/ቤቱ  በማስታወቅ  ክስን ማቋረጥ  ይችላል፡፡ … በዐ/ሕግ ጥያቄ የተነሳ ክስ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የተቋረጠውን የክስ ሂደት የሚቀጥል መሆኑ…” በሚል አስቀምጧል፡፡

ከላይ  የተመለከቱት ህጎች በጥቅሉ  ክስ ማንሳት  በመቀጠል ላይ ያለ የክርክር ሂደት ለሰፊና ለተሻለ ጥቅም ሊቋረጥ የሚችልበት  ሥርዓት  መሆኑን  ያመለክታሉ፡፡ በአንዳንድ  የሕግ ስርኣቶች  የወንጀል ክስ ለማስጀመር  የግድ የጽሁፍ አቤቱታ መቅረብ ያለበት  እንደመሆኑ  መጠን (Accusatory principle) በፍ/ቤት ተቀባይነት አግኝቶ የተጀመረን ክርክር  ዐ/ሕግ  ማንሳት አይችልም፡፡ (Principle of immutability) በሌሎች የሕግ ስርዓቶች ክስን ለማንሳት አሳማኝ የሆነ ምክንያት በማቅረብ በፍ/ቤት ፈቃድ (Up on the consent of the court) ሊፈጸም ይችላል፡፡ የወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 122 በሁለቱ  የሕግ ስርዓቶች  መካከል የተቀመጠ ይመስላል፡፡ በመርህ ደረጃ  በፍ/ቤት ፈቃድ በበቂ ምክንያት  ክስ ማንሳት የሚቻል ሲሆን በከባድ ወንጀሎች  ላይ ግን ክልከላ ተደርጎበታል፡፡

በአጠቃላይ በክስ ማንሳት ወቅት የዐ/ሕግ፤ የመንግስትና የፍ/ቤት ሚና እና ሀላፊነት  ምንድን ነው? (ለማስቀጠልም-) ክስ ለማንሳትና ለማስቀጠል  ተገቢ ሊሆን የሚችልና ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባ ምክንያት  የቱ ነው? የሚሉት ነጥቦች በትኩረት  መመርመር  የሚኖርባቸው  ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ህጎች ውስጥ በአንድ በኩል ክስን ለማንሳትና ለማስቀጠል በፍ/ቤት ፍቅድ ስልጣን ላይ ወጥ አቋም ባያንጸባርቁም  ክስ ማንሳትና ማስቀጠል በቂ ምክንያት  ሊኖረው ወይም የህዝብ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ ያሰምሩበታል፡፡ የቀረበው ምክንያት ተገቢ መሆን  አለመሆኑን ደግሞ መመርመር የፍ/ቤት ስልጣን ነው፡፡ በሌላ በኩል ፍ/ቤቱ  በጉዳዩ ላይ ብይን ሲሰጥ  ምክንያቱን  ማስቀመጥ አለበት፡፡ ዐ/ሕግ አቤቱታውን ሲያቀርብም ምክንያት ማቅረብ  ያለበት  መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በዘፈቀደ ክስን  ማንሳትና ማስቀጠል  ከፍ/ቤት  ነጻነት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች ነጻነት  አንድ ጉዳይ  በፍ/ቤት  ከቀረበ በኋላ  ፍ/ቤቱ  በጉዳዩ ላይ  ባለሙሉ ስልጣን  በመሆኑ በእያንዳንዱ ጉዳይ የመወሰን  ስልጣንን ይጎናፀፋል፡፡ እንኳንስ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር በፍትሐብሔር ጉዳዮች  እንኳ ክስ በፍ/ቤቱ  ፈቃድ እና ያለፈቃድ ካነሳ በኋላ  ማስቀጠሉ ላይ ትልቅ  ልዩነት ይፈጥራል፡፡ የፍ/ቤቱን ፈቃድ  ለማግኘት ምክንያት  ማቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን ከፈቃድ ውጭ ክስን ማንሳት ደግሞ ወደ ፊት  በተመሳሳይ ጉዳይ ሌላ አዲስ ክስ ማቅረብ እንዳይችል  ያደርገዋል፡፡ (የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 278 – 279)  በወንጀል የፍትሕ አስተዳደር ውስጥ በሁሉም መልኩ ሊባል በሚችል መጠን ትኩረትና  ጥብቅ  ቁጥጥር  ያሻል፡፡

የጉዳዩን ጥቅል ይዘት  በመመልከት  ክስ ለማንሳትም ሆነ የተነሳ ክስ ለማስቀጠል ለህዝብ ጥቅም  የተደረጉ  መሆናቸውን  ፍ/ቤቶች መገምገም አለባቸው፡፡ የክስ ማንሳትና ማስቀጠል  ሥርዓት  ተገቢ  ላልሆነ አላማ  እንዳይውል  መከልከል አለበት፡፡ በወንጀል የፍትሕ አስተዳደር ላይ የአንድን ሰው የፍትሕ ሥርዓት  ግንዛቤ እና እምነት በሚቃረን መልኩ  መፈጸም  የለበትም፡፡ የህዝብ ጥቅም፤ ፍትሐዊነት  ቅንልቦና  የሕግ ሥርዓት (ሂደት) (Public interest, Fairness, Good Faith (Bonafide) & Fairness) ታሳቢ ተደርገው  የሚፈጸም ሥርዓት  ነው፡፡ የማስረጃ ማነስን (Paucity of evidence) የግዜ፤ ገንዘብ እና የውጤታማነት  ጉዳዮችን (Time ,money & chance of success) ታሳቢ ተደርጎ  ክስ  የማይነሳ  ሲሆን በነዚሁ ታሳቢነትም አይንቀሳቀስም፡፡

በእኛ ሀገር የሕግ ሥርዓት  የህዝብ ጥቅም / በቂ ምክንያት  የሚሉት  የትኞቹን  ምክንያቶች  ነው የሚለው  በግልጽ  በሕግ ወይም በፍርድ ተቀምጠው ባይገኙም በዳበሩ የሕግ ስርዓቶች ውስጥ እነዚህ ምክንያቶች በተለመደ ሁኔታ የትኞቹ  እንደሆኑ  ይታወቃል፡፡ በዚህም፡-

  1. ክሶቹ ፖለቲካዊ ወይም ግለሰባዊ በቀልን  መሰረት አድርገው ቀርበው ሲገኙ፤ (Political & personal vendetta)
  2. መንግስታዊ እና ህዝባዊ በሆነ ምክንያት ክስን ለመቀጠል የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አለመኖር፤
  3. በሁኔታዎች መቀያየር  ምክንያት  በክሱ  መቀጠል  ህዝብና  መንግስትን  የሚጎዳ ሆኖ ሲገኙ ናቸው፡፡

 

በክርክር ቀረቦ በተሰማ አንድ ጉዳይ ዐ/ሕግ የክስ ማንሳት  አቤቱታ የቀረበ ሲሆን ምክንያቱም “ተጨማሪ ማጣራት የሚገባን ጉዳይ ስላገኘን” የሚል ነበር፡፡ ፍ/ቤቱም የቀረበውን ምክንያት  ሳይመረመር  በጥቅሉ ተቀብሎት ክሱ ተቋርጧል፡፡ በሌላ ግዜ በተመሳሳይ ጉዳይ ዐ/ሕግ ክስ እንዲንቀሳቀስ  አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን የሰጠው ምክንያትም 1ኛው ምስክር  ቃሌን አቃናለሁ ያለ በመሆኑ  መዝገቡ  ይንቀሳቀስ ምስክሮች እንደ አዲስ ይሰሙልኝ  በሚል ነው፡፡

 

በመሰረቱ የቀረበው ምክንያት  አሳማኝ እና ለህዝብ ጥቅም የተደረገ  ስለመሆኑ  ከመመርመሩ በፊት ክስ ለማንሳት የቀረበው ምክንያትና ክስ ለማስቀጠል  የቀረበው ምክንያት የተለያዩ ናቸው፡፡  በሌላ በኩል  በክርክሩ ሂደት ተሰምተው የተመለሱ  ምስክሮችን ክስን  በማቋረጥ  እንደገና  ቀርበው እንዲሰሙ  ማድረግ  የክርክር አመራር  ስርኣትን  ያልተከተለ እና ህገ ወጥ ነው፡፡

 

በአጠቃላይ የክስ ማንሳትና ማንቀሳቀስ የዐ/ሕግ ያልተሸራረፈ መብት ሳይሆን በሕግ መሰረት በተቋቋሙ ፍ/ቤቶች  የሚመራ  የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡

 

 

 

 

Read 4624 times Last modified on Aug 27 2020
Anwar Mohammed

The blogger is consultant and advocate in Amhara region and federal courts. He obtained LL.B from Mekelle University in 2007 and LL.M in comparative public law and good governance from Ethiopian Civil Service University in 2015. Before being advocate, Anwar worked as high and Supreme Court judge in Amhara region. He can be reached via; aumulqura@gmail.com; 0909040404