Print this page

የጊዜ ቀጠሮ - በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት

Jun 26 2020

 

 

መግቢያ

የወንጀል ተግባራት ዝቅ ሲል የግለሰቦችን ደህንነት፣ ነጻነትና የንብረት መብቶች የሚጋፉ ሲሆኑ ከፍ ሲል ደግሞ የማህበረሰብን ሁለንተናዊ ደህንነትና ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ማህበራዊ ክስተቶች እንደመሆናቸው መጠን የወንጀል ተግባራት እንዳይፈጸሙ መከላለል፤ተፈጽመው ሲገኙ ደግሞ ተገቢውን የወንጀል የምርመራ ስራ በማከናወን አጥፊዎችን በሕግ ፊት አቅርቦ የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙና ከጥፋታቸው ታርመው ወደ ማህበረሰቡ እንዲመለሱ ማድረግ የወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ነው በወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ ወሳኝ ከሆኑ ተግባራት መካከል የወንጀል ምርመራ አንዱና ቀዳሚው ነው የሚባለው፡፡ የወንጀል ምርመራ ሂደት መሠረታዊ ከሆኑ የዜጎችና የህዝብ መብቶች፣ ነጻነቶችና ጥቅሞች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ሂደቱ ሲከናወን በጥንቃቄ ማለትም ሕግን ባከበረና ባስከበረ ሁኔታ መሆን እንዳለበት ይታወቃል፡፡ በዚች አጪር ጽሑፍ (article) ላነሳው የፈለግሁት ነጥብ ግን በውስጡ ሰፊና ዝርዝር ይዘቶችን ካካተተው የወንጀል ምርመራ ተግባር ውስጥ አንዱ ስለሆነው የ‹‹ጊዜ ቀጠሮ›› ጉዳይና ተያያዥ ፍሬ ነገሮች ነው፡፡ የጊዜ ቀጠሮ ምንነት፣ አስፈላጊነት፣ የጊዜ ቀጠሮ ለመጠየቅ ምክንያት ስለሚሆኑ ጉዳዮችና ከጊዜ ቀጠሮ መዝገብ (ፋይል) መዘጋት ጋር ተያይዞ የሚነሱትን የተጠርጣሪ መሠረታዊ መብቶች (የህዝብ ጥቅምም ጭምር) በምን ሁኔታ ይከበራሉ የሚሉትን ዝርዝር ጉዳዮች አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ከተመለከትን በኋላ ከጊዜ ቀጠሮ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችንና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ (ማስታዎሻ ይህ ጽሑፍ ከሙስና በተለይም ከከባድ የሙስና ወንጀሎች ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ አይመከትም)፡፡   

 

1. ትርጓሜ

 

‹‹የጊዜ ቀጠሮ›› የሚለው የአማርኛ ስማዊ ሀረግ በአማርኛ በተዘጋጁ የተለያዬ መዝገበ-ቃላት በግለጽ ያልተቀመጠ ከመሆኑም ባሻገር ይህ ስም በወንጀል የፍርድ ሂደት ውስጥ ሊተካ የተፈለገውን ፍሬ ነገር በትክክል የሚወክል ገላጪ ስያሜ እንዳልሆነ በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው፡፡ በተለይም በእንግሊዝኛ የተቀመጠው የቃሉ አቻ ስያሜ ‹‹Remand›› የሚለው ስም ከአማርኛው ስያሜ ጋር የማይጣጣም ነው፡፡


ታወቂው የሕግ መዝገበ-ቃል ብላክስሎው ዲክሽነሪ[1] ‹‹Remand›› የሚለውን ቃል እንደሚከተለው ይተረጉመዋል፡፡

Remand – 1. [t]he act or an instance of sending back something (such as a case, claim or person) for further action.
               2. [a]n order remanding  a case, a claim or person.

‹‹ለተጨማሪ (ለሌላ) አድራጎት አንድን ጉዳይ ለምሳሌ፡-ጉዳይን (ክርክርን)፣ የክስ አቤቱታን ወይም ሰውን መልሶ የመላክ ተግባር ወይም የሚላክበት ሁኔታ ነው፡፡ አንድን ክርክር (ጉዳይ)፣ ክስ ወይም ሰው መልሶ የመላክ ትዕዛዝ ነው፡፡›› ይህ መዝገበ-ቃል ‹‹remand›› ለሚለው ቃል የሰጠው ትርጓሜ እንዲሁ ሲታይ ጥቅል ከመሆኑም በላይ  ተመልሶ የሚላከው ክርክር፣ የክስ አቤቱታ ወይም ሰው የሚላከው ወይም የሚመለሰው ለምንና ወደ የት ነው የሚሉትን ጥያቄዎች በግልጽ የማያብራራ ነው፡፡

ሌላውና ከቃሉ አገባብ አንጻር የተሻለ ትርጓሜ የሰጠው የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃል (English 2.4) የቃሉን ብያኔ በሁለት ከፍሎ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡

1. The act of sending an accused person back into custody whilst awaiting trail.
2. The act an appellate court sending a matter back to a lower court for review or disposal.

ከነዚህ ሁለት ክፍል ያላቸው አገላለጾች ውስጥ ከያዝነው ጉዳይ ጋር የሚገናኘውን ገለጻ ለይተን ስንመለከት (ቁጥር 1) መዝገበ ቃሉ ‹‹ተከሳሽ ክርክሩ ወይም ሙግቱ እስኪደረግ ድረስ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ የማድረግ ተግባር ነው›› የሚለው በእኛ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ የጊዜ ቀጠሮ በሚል ከሚታወቀው የምርመራ ሂደት ጋር የሚቀራረብ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ አገላለጽ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ የሚወሰንበትን ሰው ‹‹ተከሳሽ›› በማለት የገለጸበትና የሚቆይበትንም ምክንያት ‹‹ክርክሩን ለማድረግ›› በሚል ያስቀመጠበት ሁኔታ በእኛ ሀገር የወንጀል ፍትህ ስርዓት ውስጥ ከተቀመጠው የጊዜ ቀጠሮ ገለጻ ጋር ልዬነት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ በርግጥ ይህ ገለጻ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ[2] ከተቀመጠው በእስር የማቆያ ትዕዛዝ ምክንያቶች ጋር በተለይም በሕጉ አንቀጽ 20(5) ሥር ከተደነገገው ጋር የሚጣጣም ገለጻ አንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡

በሕግ ት/ቤት ጥልቅ ስለሆነው የወንጀል ፍትህ አስተዳደር በተለይም የወንጀል ፍትህን ስለሚመራው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ[3] እጅግ በሚገርም ሁኔታ ያስተማረኝ መምህሬ ረ/ፕሮፌሰር (ማዕረጉ ተለውጦ ከሆነ ከወዲሁ ይቅርታን አጠይቃለሁ) ወርቁ ያዜ ደግሞ ‹‹የጊዜ ቀጠሮ በአንድ የወንጀል የምርመራ ተግባር ውስጥ ተጠርጣሪን በፍ/ቤት ፈቃድ አስረን የምናቆይበት ሂደት ነው›› በማለት ይገልጸዋል፡፡


በ1954 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ በሁለተኛው መጽሐፍ፣ ሁለተኛው ርዕስ ‹‹ምርመራው እስኪደረግ ድረስ ስለሚደረገው ጥንቃቄ›› በሚል ከተቀመጡት ሦስት ምዕራፎች ውስጥ በአንደኛውና በሁለተኛው ምዕራፎች ስር ባሉት ከአራት ያልበለጡ ድንጋጌዎች[4] ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት ስለሚቆይበት ሁኔታና ከዚያ ቀጥሎ ስለሚደረገው ሥነ ሥርዓት ጥቅል በሆነ ሁኔታ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በተለይም አንቀጽ 59(1) መርማሪ ፖሊስ በሕግ አግባብ የያዘውን ተጠርጣሪ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውስጥ[5] ፍ/ቤት ካቀረበው በኋላ ፍ/ቤቱ ‹‹…የተያዘው ሰው በማረፊያ ቤት ይቆይ ወይም በዋስትና [ግዴታ] ይለቀቅ በማለት መወሰን አለበት›› በማለት ይደነግጋል፡፡ በዚህ ድንጋጌ ንኡስ ቁጥር ሁለትና ሶስት ደግሞ ምርመራው ያልተፈጸመ እንደሆነ ‹‹መርማሪው ፖሊስ ምርመራውን የሚፈጽምበት በቂ ጊዜ እንዲሰጠውና ተጠርጣሪውም በማረፊያ ቤት እንዲቆይለት አቤቱታውን በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚገባው ተገልጧል፡፡

በ2001 ዓ.ም የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ[6] ደግሞ በአንቀጽ 20 ድንጋጌው ሥር ‹‹በእስር የማቆያ ትዕዛዝ (Dtention and Remand Order) ›› በማለት ርዕሰ-አንቀጽ የሰጠው ሲሆን በስሩም ከጉዳዬ ጋር የተያያዙ በርካታ ጉዳዮች ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ አንድ መሠረት በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥሮ ‹‹የተያዘ ሰው የቀረበለት ፍርድ ቤት ለምርመራ ወይም ወይም ክሱን በፍርድ ቤት ለማሰማት  የተያዘው ሰው በማረፊያ ቤት አንዲቆይ ሊወስን ይችላል›› በማለት ሲደነግግ፤ የአንቀጹ ንኡስ ቁጥር ሁለት ደግሞ ‹‹ምርመራው ያልተጠናቀቀ እንደሆነ መርማሪው ፖሊስ ምርመራውን የሚፈጽምበትን በቂ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን መጠየቅ ይችላል›› በማለት ተደንግጎ ይገኛል [አጽንኦት የተጨመረ]፡፡ ሌላውና ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የድንጋጌውን ንኡስ ቁጥር አንድ በአብራራ ሁኔታ የተቀመጠው ንኡስ ቁጥር አምስት ሲሆን ይህም በሽብርተኝነት አዋጁ ‹‹መሠረት በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የቀረበ እንደሆነ ፍ/ቤቱ ክሱን ሰምቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ተከሳሹ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ያዛል›› የሚል ነው [አጽንኦት የተጨመረ]፡፡


ከዚህ የአዋጁ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው የጊዜ ቀጠሮ ወይም ‹‹በእስር የማቆያ ትዕዛዝ›› በሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ሊሰጥ እንደሚችል ነው፡፡ እነዚህም፡-

1ኛ) ምርመራው ያልተጠናቀቀ በሚሆንበት ጊዜ ተጠርጣሪው ታስሮ ለምርመራው ማከናወኛ ጊዜ እንዲሰጥ ለማድረግና፣


2ኛ) ምርመራው ተጠናቆ በአዋጁ መሠረት የወንጀል ክስ ሲቀርብበት ደግሞ ፍርድ ቤቱ ክሱን ሰምቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ተጠርጣሪው በማረፊያ ቤት ተይዞ እንዲቆይ ለማድረግ የሚሉ ናቸው፡፡

ስለሆነም እስካሁን ካየናቸው ማብራሪያዎችና የህጎቹ ድንጋጌዎች መንፈስ ለመረዳት እንደሚቻለው በሀገራችን በተለምዶ ‹‹የጊዜ ቀጠሮ›› እየተባለ የሚጠራው ጉዳይ ትርጓሜ በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ ፖሊስ የምርመራ ሥራውን  አጠናቆ እስኪጨርስ ድረስ (እና ወይም ተጠርጣሪው በጸረ ሽብር አዋጁ ክስ ተመስርቶበት ከሆነ ፍርድ ቤቱ ክሱን ሰምቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ) በፍ/ቤት ይሁንታ ተይዞ ወይም ታስሮ እንዲቆይ የሚደረግበት ሥነ-ሥርዓት ነው ማለት ይቻላል፡፡

 

2. የጊዜ ቀጠሮ አስፈላጊነትና መጠየቂያ ምክንያቶች

ከላይ ባየናቸው የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 59ም ሆነ በቀሪዎቹ የሕጉ አንቀጾችና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አንቀጽ 20 ድንጋጌ መሠረት የጊዜ ቀጠሮን አስመልክቶ የተቀመጡት ነጥቦች ተጠርጣሪው በጊዜ ቀጠሮ የሚቆይበት ምክንያት ‹‹የምርመራው አለመፈጸም›› ወይም ‹‹በተከሳሹ ላይ በቀረበበት ክስ ላይ ፍ/ቤቱ ውሳኔ እሰኪሰጥ›› መሆኑን፣ ተጠርጣሪውን በማረፊያ ቤት ለማቆየት የሚሰጠውም ተጨማሪ ጊዜ በጽሑፍ መቅረብ እንዳለበት፣ በየጊዜው የሚጠየቀው የቀን ብዛትም ከአስራ አራት ቀን መብለጥ እንደሌለበት፣[7] የተጠርጣሪው አቆያየትም ልክ እንደማንኛውም እስረኛ የእስረኛ ሕጉ በሚያዘው አኳኋን እንደሆነ፣ ተጠርጣሪው በቆይታውም ከጠበቃው ጋር የመገናኘት መብት እንዳለውና በመጨረሻም በማረፊያ ቤት ተይዞ የቆየው ሰው በዋስትና የሚለቀቅ የሆነ እንደሆነ ዋስ ፈልጎ እንዲያገኝ ርዳታ ማግኘት እንደሚገባው፣ አቃቤ ሕግ በዋስትና ጉዳይ ላይ ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳለው የሚሉት ፍረ ነገሮች ቢጠቀሱም በመሠረታዊነት ስለጊዜ ቀጠሮ አስፈላጊነትና ከሁሉም በላይ ደግሞ መርማሪ ፖሊስ በያዘው ተጠርጣሪ ላይ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ በማመልከቻው ውስጥ በምክንያትነት ስለሚዘረዝራቸው ነጥቦች ሕጉ ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡   

እንደወንጀሎቹ ውብስብነት አንዳንድ የወንጀል የምርመራ መዛግብትን በሚገባው ደረጃ መርምሮ ለውሳኔ ለማብቃት ሂደቱ ሰፋ ያለ ምርመራ ማድረግ ሊፈልግ ይችላል፡፡ በዚህ ሂደትም እንደሁኔታው ተጠርጣሪውን ወይም ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ወይም በማሰር ጭምር ሊከናወን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከፍ ሲል እንደተገጸው ፖሊስ ተጠርጣሪውን ወይም ተጠርጣሪዎችን በመያዝ ወይም በማሰር የምርመራ ተግባሩን ማከናወን የሚችል ቢሆንም ይህን የመሰለው ሰዎችን የመያዝ ወይም የማሰር ድርጊት መሠረታዊ የሆነውን የሰዎችን የነጻነት መብት[8] የሚጋፋ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ፖሊስ ተጠርጣሪውን ሲይዝ ምንጊዜም ቢሆን ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ነጥቦች ውስጥ ቢያንስ አንዱን ወይም ሌላውን ለማሳካት በማሰብ መሆን አለበት፡፡[9]

1ኛ. ተጠርጣሪውን በመመርመር (በማወጣጣት) የማስረጃ ግብዓት ለማግኘት ለምሳሌ አሻራ፣ የደም ሳምፕል፣ ቃል ለመቀል፣ በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፈን ሌላ ሰው ለመለየት ወይም አንዳንዴ የተያዘው ሰው ምስከር ሆኖ ትክክለኛውን ተጠርጣሪ ለመፈለግ፣ ወይም፤


2ኛ.ፍትህን ለመጠበቅ ሲባል ተጠርጣሪው ፍ/ቤት መቅረብ ሲኖርበት ወይም ተጠርጣሪው እንዳይሸሽ ለምሳሌ ሰው በመግደል ወንጀል የተጠረጠረ ሰው በሕግ ጥላ ሥር መዋል ያለበት በመሆኑ መያዝ ይገባዋል፤ወይም

3ኛ. የተሰበሰቡ ወይም የተገኙ፣ ያልተሰበሰቡ ማስረጃዎችን ከተጠርጣሪው የጥፋት ድርጊት ለመጠበቅ ሲባል፤ለምሳሌ የሰነድና ሌሎች ቁሳዊ ማስረጃዎችን ተጠርጣሪው እንዳይሰውራቸው፣ እንዳይጎዳቸው ወይም በምስክርነት ሊቀርቡ የሚችሉ ሰዎችን ባልተገባ ሁኔታ በማስፈራራት፣ በመደለል ወይም በሌላ ማናቸውም ሁኔታ ለማስረጃነት እንዳይቀርቡ ሊያደርጋቸው የሚችል መሆኑ ከታመነ፤ወይም

4ኛ. ተጠርጣሪው ተጨማሪ ወንጀሎችን ያደርጋል ተብሎ ሲታመን ወይም

5ኛ. የተጠርጣሪውን ደህንነት ለመጠበቅ በማሰብ መሆን ይገባዋል፡፡

በመርህ ደረጃ በወንጀል የምርመራ ሂደት ውስጥ ተጠርጣሪውን የመያዝ ጉዳይ የመጨረሻ ተግባር በመሆኑ  የምርመራ ሂደት ሳይጠናቀቅ ተጠርጣሪው አስቀድሞ ሊያዝ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ ተጠርጥሮ ቢያዝም እንኳ በዋስትና የመለቀቅ መሠረታዊ መብቱ ደግሞ መጠበቅ እንዳለበት በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት የስምምነት ድንጋጌዎች፣ በህገመንግስቱና በሥነስርዓቱ ሕጉ ተገልጧል፡፡ እንግዲህ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው መርማሪ ፖሊስ በምርመራ ሂደት መካከል ተጠርጣሪውን ከያዘውና ፍ/ቤት ካቀረበው በኋላ በመርህ ደረጃ ለተጠርጣሪው እንደሚከበርለት የሚጠበቀው የዋስትና መብቱ ለጊዜው ታልፎ ተጠርጣሪው ‹‹ውስን ለሆነ ጊዜ›› በማረፊያ ቤት እንዲቆይለት የሚያስችለውን ምክንያት በበቂ ሁኔታ ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ ማስፈቀድ ይጠበቅበታል ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው በዋስትና ግዴታ ወጥቶ ምርመራውን የማያከናውንበትን አሳማኝ ሁኔታ ለፍ/ቤቱ አቅርቦ ማስረዳትና ማሳመን አለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራቀኙን ክርክር በተለይም ደግሞ ፖሊስ ተጠርጣሪው በዋስትና ቢወጣ በምርመራው ሂደትና ውጤት ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን ጣልቃ-ገብነት ወይም መሰናክል በሚገባው ሁኔታ አገናዝቦ ሲያበቃ የጊዜ ገደቡን ገልጾ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ መወሰን ይገባዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በየቀጠሮው ቀን ፖሊስ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማከናውን አስቀድሞ የዘረዘራቸውን ፍሬ ጉዳዮች በትጋት ማከናውኑን ራሱን መራማሪውን በመጠየቅ፣ ተጠርጣሪውን በመስማትና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ አስቀርቦ በመመርመር በጥብቅ መቆጣጠርና መከታተል ይገባዋል፡፡ በዚህ ሂደት መርማሪ ፖሊስ በእንዝህላልነት ወይም ከቅን ልቦና ውጪ በሆነ ሁኔታ የተፈቀደለትን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ በአግባቡ የማይጠቀም ከሆነ (የህዝብ ጥቅም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አስቀድሞ ተገቢውን ተግሳጽና ማስጠንቀቂያ በመስጠት) የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን መዝጋት ይገባዋል፡፡  

በአጠቃላይ የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ በህጎቻችን ውስጥ በጥቅል የተቀመጠና በጉዳዬ ላይ ከፍተኛና ያልተገደበ የመወሰን ስልጣን የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮውን የሚከታተለው ፍርድ ቤት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ ረ/ፕሮፌሰር ወርቁ ያዜ አገላለጽ ‹‹ለእያንዳንዷ ጉዳይ ግልጽ ገዢ ሕግ ማስቀመጥ የማይቻል በመሆኑ የሚቀርቡትን ጉዳዮች እንደየ ሁኔታው (case-by-case basis) አይቶና መርምሮ መወሰን ይገባል፡፡ በመሠረታዊነት ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪውን በዋስትና እንዳይለቀው የሚከለክለው ሕግ ካልኖረ በስተቀር እና ወይም ከምርመራው መጠናቀቅ በፊት ተጠርጣሪውን በዋስትና ግዴታ ቢለቀው በምርመራ ሂደቱና ውጤቱ ላይ መስተጓጎል የሚፈጥር መሆኑን ካላመነበት ተጠርጣሪውን በበቂ የዋስትና ግዴታ መልቀቅ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ይህን የመሰለውን ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት ውሳኔው ፖሊስ የወንጀል ምርመራውን በማድረግ ወንጀልን የመከላከልና የመቆጣጠር ህጋዊ ጥረቱን የሚጋፋበት እንዳይሆን እጅጉን መጠንቀቅ ይገባዋል›› በማለት በአጽንኦት ያስቀምጠዋል፡፡   

 

3. የጊዜ ቀጠሮ የክርክር መዝገብ (ፋይል) ከተዘጋ በኋላ ምን ይከተላል?

የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በሁለት አኳኋኖች ሊቋጭ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው መርማሪው በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ለምርመራው የሚያስፈልጉትን ጉዳዮች አጣርቶ ሲፈጽም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ፖሊስ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ የምርመራ ሥራውን በአግባቡና በቅን ልቦና ሳይፈጽም ሲቀር ፍርድ ቤቱ በሚወስደው እርምጃ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ ተቋርጦ ሊዘጋ ይችላል፡፡ ከመዝገቡ መዘጋት በኋላ [የሚመጡ የይግባኝ ክርክሮች እንደተጠበቁ ሆነው] የሚከተለው ጥያቄ በማረፊያ ቤት ተይዞ የሚገኘው የተጠርጣሪው የአቆያየት ጉዳይ ነው፡፡

ብዙ ጊዜ በተግባር እንደምናየው የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ ተዘግቷል ተብሎ ክርክሩን ሲመራው የቆየው ፍርድ ቤት ከገለጸ በኋላ በተጠርጣሪው አቆያየት ላይ ውሳኔ በመስጠት ረገድ ግራ መጋባት ይስተዋላል፡፡ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ መዘጋት በራሱ ሌላ የክርክር ሂደትን የሚፈከፍት ወይም የሚፈልግ እንጂ ለጉዳዬ ማቋጫ የሚሰጥ ባለመሆኑ ተጠርጣሪው  እንዲሁ የሚለቀቅ አይሆንም፡፡ ይሄን ጉዳይ አስመልክቶ ከላይ ባየናቸው የህጎቹ ድንጋጌዎች ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ ምላሽ ባይኖርም ከጊዜ ቀጠሮ ትርጓሜና ዓላማ፣ ከህጎቹ አጠቃላይ መንፈስና መሠረታዊ ከሆነው የዋስትና መብት አንጻር ስንመለከተው የተጠርጣሪውን አቆያየት ለመወሰን መሠረቱ በተጠርጣሪው ተጽፎ የሚቀርበው የዋስትና አቤቱታ፣ በዚያ መነሻነት የሚደረገው ክርክርና ያን ተከትሎ የሚሰጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ ነው፡፡[10]

በግልጽ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እንደተቀመጠውተጠርጣሪው የተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት በሕጉ አንቀጽ 63 መሠረት ዋስትና የማያሰጠው ካልሆነ ወይም ደግሞ በሕጉ አንቀጽ 67 መሠረት ተጠርጣሪው የዋስትና ግዴታውን አያከብርም የሚያስብሉ ሁኔታዎች በበቂ ማሳያዎች ተደግፈው ካልቀረቡ በስተቀር የተጠርጣሪው የዋስትና መብት ሊከበር ይገባዋል፡፡ በዚህ አካሄድ መሠረት ፍ/ቤቱ የተጠርጣሪውን የዋስትና መብት ካከበረለት ወዲያዉኑ ከእስር የሚፈታ ሲሆን፤ተጠርጣሪው ያቀረበው የዋስትና አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት ካጣ ደግሞ ለቆይታው አስፈላጊ የሆኑትን የቀለብና የህክምና አገልግሎቶችን በሚያገኝበት ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ይታዘዛል፡፡[11]

 

4. ከጊዜ ቀጠሮ ጋር ተያይዞ ምን ምን ችግሮች ይስተዋላሉ?በዐ/ሕግነት በሰራሁባቸው ባለፉት አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከመርማሪ ፖሊስ ጋር በቅርብ የመስራት ዕድሉንና አጋጣሚውን ስላገኘሁ የጊዜ ቀጠሮን አተገባበር አስመልክቶ ከተለያዬ መርማሪ ፖሊሶች ያየሁት፣ ከፍ ባሉ የወንጀል የምርመራ መዛግብት ላይ የሚደረጉ የጊዜ ቀጠሮ ክርክሮችን በብዙ ችሎቶች ውስጥ ስከታተል ካስተዋልሁኋቸው ትዝብቶችና በስራ አጋጣሚ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ከማደርገው ውይይት እንደታዘብዙት ብዙዎቹ የጊዜ ቀጠሮ ክርክሮች ዓላማቸውን የማያሳኩና በተጠርጣሪ ግለሰቦች ላይም ያልተገባ መጉላላትና የመብት ጥሰትን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡

በፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻዎች ውስጥ ተደጋግመው ከሚቀርቡት ምክንያቶች ውስጥ ‹‹የምስክር ቃልን ጨምሮ ሌሎች ማስረጃዎችን እስክንሰበስብ፣ የተጠርጣሪውን ቃል እስክንቀበልና ከተጠርጣሪው አሻራ እስክንወስድ፣ የምርመራ መዝገቡን ለክፍሉ ዐ/ሕግ እስክናቀርብ ድረስ፣ በዋስትና ቢወጣ ተጠርጣሪው ሊጠፋ ስለሚችል›› የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ ምክያቶች ውስጥ ምናልባትም ‹‹የተጠርጣሪውን ቃል እስክንቀበልና ከተጠርጣሪው አሻራ እስክንወስድ›› ከሚለው ውጪ ሌሎች ምክንያቶች የጊዜ ቀጠሮ ለመጠየቅ የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች አይደሉም፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ፍርድ ቤቶችም ከላይ የቀረቡት አሳማኝነት የሌላቸውን ምክንያቶችን በመቀበል በተደጋጋሚ ተገቢነት የሌላቸውን የጊዜ ቀጠሮዎችን ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ይህ የፍርድ ቤቶች በተግባር የዳበረ አሰራር ልዬ የወንጀል ምርመራ ሥነ ሥርዓት የሆነውን ‹‹ተጠርጣሪን አስሮ ምርመራ የማከናወን›› ሂደት ወደ መደበኛ ሁኔታ ቀይሮታል፡፡ ችግሩ የሂደቱ መለወጥ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ያለበቂ ምክንያትና ለተራዘሙ ጊዚያት የሚፈቀዱ የጊዜ ቀጠሮዎች በወንጀል ተግባራት በተለይም (ከፍ ባሉ የወንጀል ድርጊቶች) ተጠርጥረው በሚያዙ ግለሰቦች ህይወትና መብት ላይ ቀላል የማይባሉ ምስቅልቅሎችን የሚያስከትል ነው፡፡ በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ ሥራውን በትጋት እንዳያከናውን ሊያደርገውም ይችላል፡፡

እንደ እኔ ምልከታ ከጊዜ ቀጠሮ አተገባበር ጋር ተያይዞ ለሚስተዋሉት ችግሮች መከሰት ሶስት ዓበይት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላል፡፡ እነዚህም፡-


1ኛ) የወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ ለረዥም ዘመናት ሲከተለው የቆየው ‹‹ተጠርጣሪን አስሮ የመመርመር›› ልማድ የጊዜ ቀጠሮን እንደመደበኛ የወንጀል ምርመራ ማከናወኛ ሂደት እንዲቆጠርና እንዲለመድ ማድረጉ፤

2ኛ) የጊዜ ቀጠሮን አስፈላጊነትና ዓላማና በቅጡ ተገንዝቦ ያሉትን ህጎች (ክፍቶችን ለመሙላት ከህገ-ፍልስፍና ጋር የማይጋጩና በተግባር የዳበሩ አሰራሮችን በመጠቀም) በአግባቡ የማስፈጸም ችግር፤

3ኛ) የጊዜ ቀጠሮን የክርክር አመራር አስመልከቶ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉም ሆነ በሌሎች ህጎች የተቀመጡት ድንጋጌዎች ዝርዝርና ግለጽ አለመሆናቸውና ይህም ሂደቱን በትክክል በመምራት ረገድ ሰፊ ክፍተትን እየፈጠረ ይገኛል፡፡   

   

5.ማጠቃለያ

ቀደም ባሉት አንቀጾች ስለጊዜ ቀጠሮ ትርጓሜ፣ የጊዜ ቀጠሮን አስመልክቶ ያሉት የሕግ ማዕቀፎችና ተግባራዊ አፈጻጸማቸው፣ የጊዜ ቀጠሮ ለመጠየቅ በቂ ምክንያት ስለሚሆኑ ምክንያቶችና በክርክር ወቅት ስለሚስተዋሉ ችግሮች(ምንጮቻቸውን ጭምር) ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ሥርዓት ውስጥ በተለምዶ የጊዜ ቀጠሮ እየተባለ የሚጠራው ተጠርጣሪን አስሮ የመመርመር ሥነ ሥርዓት እጅግ ትቂትና ጥቅል በሆኑ የሕግ ድንጋጌዎች የተቀመጠ ሲሆን በአተገባበር ሂደቱም ከመሠረታዊ ዓላማው ያፈነገጡ የአፈጻጸም ችግሮች መኖራቸውንም ለመረዳት ይቻላል፡፡

 

6. የመፍትሔ ሃሳቦች

ለወንጀል ምርመራ ተብሎ ከሚሰጥ የጊዜ ቀጠሮ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ያሉ መሆናቸውን ከላይ ለመገለጽ የተሞከረ ሲሆን አሁን ደግሞ በወንጀል ምርመራ ሂደት ውስጥ ልዬ ሥነ ሥርዓት የሆነውን  ‹‹ተጠርጣሪን አስሮ የመመርመር›› ሂደት ሕጉ ሊያሳካው የሚፈልገውን ዓላማ በጠበቀ ሁኔታ እንዲፈጸም የሚያስችሉ ትቂት የመፍትሄ ሃሳቦችን ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ሃሳቦች ከላይ በተራ ቁጥር አራት ከጊዜ ቀጠሮ አተገባበር ጋር ተያይዞ ለሚስተዋሉት ችግሮች ያነሳናቸው ምክንያቶች ግልባጮች ናቸው፡፡


1ኛ) የወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ ለረዥም ዘመናት ሲከተለው የቆየው ‹‹ተጠርጣሪን አስሮ የመመርመር›› ልማድ የጊዜ ቀጠሮን እንደመደበኛ የወንጀል ምርመራ ማከናወኛ ሂደት እንዲቆጠርና እንዲለመድ የሆነውን ልማድ ለመቀየር መትጋት፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ዐቃቤ ሕግ መር››[12] የሆነው የወንጀል ምርመራ ሂደት ይሄን ልማድ ለመቀየር የወንጀል ምርመራዎችን በቅርብ በመከታተል፣ አስፈላጊ ስልጠናዎችን ለመርማሪ ፖሊሶች በመስጠት የጊዜ ቀጠሮን ዓላማ በሚገባ ለማስፈጸም እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡


2ኛ) የጊዜ ቀጠሮን አስፈላጊነትና ዓላማና በቅጡ ተገንዝቦ ያሉትን ህጎች (ክፍቶችን ለመሙላት ከህገ-ፍልስፍና ጋር የማይጋጩና በተግባር የዳበሩ አሰራሮችን በመጠቀም) በአግባቡ ለመፈጸም መትጋት፤


3ኛ) ከችግሮቹ ጋር ተያይዞ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ደግሞ የጊዜ ቀጠሮን የክርክር አመራር አስመልከቶ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉም ሆነ በሌሎች ህጎች የተቀመጡት ድንጋጌዎች ዝርዝርና ግለጽ እንዲሆኑ ለማድረግ የሕግ ማሻሻያ ተግባራትን ማከናወን በመፍትሄነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

 

የግርጌ ማስታወሻ

[1] Black’s Law Dictionary, edition.

[2] Article 20(5) of proclamation on anti-terrorism proclamation says that << [i]f a terrorism charge is filed in accordance with this proclamation, the court shall order the [accused] to be remanded for trial until the court hears and gives decision on the case.>> ከዚህ በኋላ የጸረ ሽብር ህጉ እየተባለ የሚጠቀስ፡፡

[3] የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህግ አዋጅ ቁጥር 185/1954፡፡ ከዚህ በኋላ የወንጀለኛ ሥነ ሥርዓት ህግ እየተባለ የሚጠቀስ፡፡

[4] ዝኒ ከማሁ (አንቀጽ 59፣ 60፣ 61 እና 62)፡፡

[5] ዝኒ ከማሁ (አንቀጽ 29)፣ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አዋጅ ቁጥር 1/1987 አንቀጽ 19(3)፡፡

[6] ዝኒ ከማሁ (ማጣ.ቁጥር 3ን ይጠቅሳል)፡፡

[7]  ይህ ጊዜ በጸረ ሽብር ህጉአንቀጽ 20(3) እስከ አንድ ወር የሚጠጋ (28 ቀናት) ሆኖ ተለጥጦ ተቀምጧል፡፡

[8] የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 17፡፡

[9] ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ የተወሰኑት በአንቀጽ 27 ሲገኙ የተወሰኑት ደግሞ የስነስርዓት ህጉ በአንቀጽ 67 መሰረት የዋስትና መብትን ለመከልከል የተቀመጡ ሲሆኑ፣ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ በብዙ የሀገራችን ፍ/ቤቶች በተለይም በፌደራል ፍ/ቤቶች በሚቀርቡ የጊዜ ቀጠሮ ክርክሮች ወቅት በተግባር የዳበሩና ተደጋግመው የሚነሱ ናቸው፡፡ በርግጥም ምክንያቶቹ አሳማኝ ናቸው፡፡

[10] የጊዜ ቀጠሮ የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ፋይሉ ከተዘጋ በኋላ ተጠርጣሪው የተጠረጠበት የወንጀል ድርጊት በህጉ አንቀጽ 63 መሰረት ዋስትና የማያሰጠው ከሆነ ወይም ደግሞ በህጉአንቀጽ 67 መሰረት ተጠርጣሪው የዋስትና ግዴታውን አያከብርም የሚያስብሉ ሁኔታዎች በበቂ ማሳያ ተደግፈው በሚቀርቡበት ጊዜ የተጠርጣሪው የዋስትና መብት ሊነፈግ ይችላል፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች ውጪ ከሆነ የተጠጠርጣረው የዋስትና መብት ሊከበር ይገባዋል፡፡

[11] የወንጀል ሥነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 64-72፡፡

[12] የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 8(2)፣ የፌደራል ሚኒሰቴር መስሪያ ቤት ስልጣንና ተግባር ለመወሰኝ የወጣው አዋጅ ቁጥር(/2011)፣ የኢፌዴሪ የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ፡፡

Read 5281 times Last modified on Jun 27 2020
ስለሺ መኳንንት አንዳርጌ

ጸሐፊው በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቂ/ም/ጽ/ቤት በዓቃቤ ሕግነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ጸሐፊውን በኢሜል yeshimequanint@gmail.com አድራሻቸው ማግኘት ይችላሉ፡፡