Print this page

ግዴታን ባለመወጣት የሚመጣ የወንጀል ሀላፊነት ከወንጀል ሕጉ አንቀፅ 575 አንፃር

May 14 2020

 

በወንጀል ሕግ መሠረት የሚያስጠይቁ የወንጀል ተግባራትን በጥቅሉ በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው አታድርግ የተባለን ነገር በማድረግ የሚመጣ የወንጀል ሀላፊነት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አድርግ በሚል በሕግ የሚጣልን ግዴታ ባለማድረግ የሚመጣ ሀላፊነት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና አለማም አድርግ ተብሎ በሕግ ግዴታ ተጥሎ ባለማድረግ የሚመጣን የወንጀል ሀላፊነት የሚመለከት በመሆኑ የተነሳ በዚሁ ላይ ብቻ የምናቶክር ይሆናል፡፡ አድርግ ተብሎ ባለማድረግ የሚመጣን የወንጀል ሀላፊነት ለማቋቋም በጥቅሉ በመሰረታዊነት መሟላት ያለበት በመጀመሪያ ደረጃ በሕግ አድርግ የመባል ግዴታ መኖር፣ በሕግ ግዴታ  የተጣለ መሆኑን ማወቅ ፣ ይህንን ግዴታ ለመወጣት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ መገኘት፣ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችል አካላዊ ቁመና መኖር፣ ግዴታውን በምንወጣ ጊዜ ግዴታውን በሚወጣው ሰውና በሌሎች ሶስተኛ ወገኖች ጥቅም ላይ ጉዳትና አደጋ የማይደርስ መሆን ዋና ዋና ጥቅል መስፈርት ሲሆን ይህን መስፈርት እንደመነሻ በመያዝ የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 575 በቀጣይ የፅሁፉ ክፍሎች ላይ የምንመለከተው ይሆናል፡፡

በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 575 መሠረት በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳትን በወንጀልነት ለማቋቋም በዋናነት የወንጀሉ ማቋቋሚያዎች  

1ኛ) በሆን ብሎ የሀሳብ ክፍል የሚፈፀም መሆን (INTENTION)

የመነሻው መስፈርት ሆኖ በሕጉ የተቀመጠው በዚህ ወንጀል ሰውን ለመጠየቅ ግለሰቡ ግዴታ ያለበት መሆኑን እያወቀና እና የመርዳቱን ግዴታ መፈፀም እያለበት አለመፈፀም ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ ማንም ሰው በአደጋ ላይ የሚገኝን ሰው የመርዳት ግዴታ አንዳለበት ያውቃል ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ ይህ ግምት የሚገመተው ሕጉ በሁሉም ሰው ላይ ግዴታ ከመጣሉና ሕግን አለማወቅ ከተጠያቂነት የማያድን መሆኑን ከወንጀል ሕጉ አንቀፅ 81 ከመቀመጡ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ሌላን ሰው መርዳት እንዳለበት እያወቀ አለመርዳት በሕጉ ግምት ተወስዶበት የሀሳብ ክፍል መኖሩ ቢታወቅም ነገር ግን ሌላው ሰው በአደጋ ላይ ስለመሆኑ ማወቅ ግን በሕግ የሚገመት ሳይሆን በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚገባው መሰረታዊ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ህፃን ውሀ ውስጥ እየገባ ያየ ሰው የመርዳት ግዴታ ያለበት ሲሆን አደጋ ላይ የሚገኘውን ሰው ካልረዳው የመርዳት ግዴታ እንዳለብኝ ስለማላውቅ ነው ያልረዳሁት ብሎ መከራከር የማይችል ሲሆን ነገር ግን ህፃኑ ከመነሻው ወደ ውሀ ውስጥ እየገባ መሆኑን የማያውቅ ሰው ውሀ ውስጥ ሰምጦ ለሚሞት ህፃን ሀላፊነት አይኖርበትም፡፡

2ኛ) የሚደርሰው አደጋ ቅርበትና ከባድ መሆን (IMMINNENCE AND GRAVITY)

በአደጋ ላይ ያለን ሰው የመርዳት በሕግ የሚጣል ግዴታና ባለመወጣት የሚመጣ የወንጀል ሀላፊነት በሚደርሰው የአደጋ መጠን ክብደትና ቅርበት ላይ የሚመሠረት ነው፡፡ አደጋ የሚደርስበት ሰው የተጋረጠበት አደጋ በመጠኑ ከባድ የሆነን ፤የመድረሱ ቅርበትም

ቅፅበታዊ መሆን መቻል አለበት፡፡ የሚደርሰው አደጋ ከባድ ካልሆነና የሚረዳው ሰው ወዲያው ካልረዳው አደጋው የሚደርስ ቢሆን ወይም ደግሞ የሚደርሰው ጉዳት ከባድ ሆኖ የሚረዳው ሰው ባይረዳው ወዲያው ጉዳቱ ባይደርስ ወይም ደግሞ ጉዳቱ ወዲያው የሚደርስ ሆኖ በህይወቱ፣ በአካሉና በጤንነቱ የሚደርሰው ጉዳት ቀላል ከሆነ፣ በሕግ የመርዳት ግዴታ ያለበት ሰው ጉዳት የሚደርስበትን ሰው ባይረዳው በወንጀል የሚያስጠይቅ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ከባድ የሆነ አደጋና ሊደርስ የተቃረበ መሆን ወንጀሉን ለማቋቋም በጣምራ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ናቸው፡፡ የሚደርሰውም አደጋ በሰው ህይወት፣ ጤንነትና፣ አካል ላይ ከመሆን ባለፈ በንብረትና በመሰል ጥቅም ላይ የተጋረጠን አደጋ የሚመለከት አይሆንም፡፡

3ኛ) ግዴታ የሚጣልበት ሰው ጉዳቱን ለመከላከል የሚያስቸል አካላዊ ብቃት መኖር (Physical possibility)

በአንቀፅ 575 መሠረት የመርዳት ግዴታ ያለበት ሰው ሌላውን ሰው ለመርዳት የሚያስችል አካላዊ ቁመና ኖሮት ይህን በሕግ የተጣለበትን ግድታ ሳይወጣ ሲቀር የሚመጣ ሀላፊነት ነው፡፡ ሌላን ሰው ለመርዳት በማያስችል ሁኔታ ውስጥ ያለ ሰው ምንም አንኳን የሀሳብ ክፍሉ ተሟልቶ ቢገኝም በወንጀል ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ነገር ግን እዚህ ጋርም ቢሆን በጥንቃቄ መታየት ያለበት ግዴታ የሚጣልበት ሰው ያለበት ሀላፊነት አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው በቀጥታ ራሱ ከመርዳት ባለፈ በተዘዋዋሪም ቢሆን የመርዳት ግዴታ ያለበት መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በተዛዋዋሪ መንገድ መርዳት እየቻለ ይህን ካለደረገ በወንጀል ከመጠየቅ አይድንም፡፡ ለምሳሌ በዊልቸር ላይ ሆኖ በመንገድ የሚሔድ ሰው አንድ ህፃን ልጅ ወደ ኩሬ ውስጥ እየሰጠመ መሆኑን ቢመለከትና ምንም እንኳን ይህ ሰው ህፃኑን በራሱ ማዳን ባይችልም ነገር ግን በሰአቱ በአቅራቢያው ለምትገኘው ለህፃኑ እናት በስልክ ወይም በሌላ መንገድ መንገር እየቻለ ይህንን ባያደርግ በሕጉ የተመለከተውን በተዘዋዋሪ መንገድ በአዳጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት ግዴታ ያልተወጣ ስለሆነ በወንጀል ከመጠየቅ አይድንም፡፡

4ኛ) አደጋ አለመኖር (Absence of risk)

ሌላው በሕጉ የተመለከተው ማቋቋሚያ እርዳታውን የመስጠት ግዴታ ያለበት ሰው እርዳታውን በመስጠቱ በራሱና በሶስተኛ ወገኖች አደጋ የማይደርስ ሆኖ ሳለ አደጋ ላይ ያለን ሰው ካልረዳ በወንጀል ሀላፊነት ይኖራል፡፡ ነገር ግን እርዳታውን በመስጠቱ የተነሳ እርዳታውን በሚሰጠውና በሶስተኛ ወገኖች ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት በወንጀል አያስጠይቅም፡፡ ነገር ግን ይህ መስፈርት ግልፅነት በጎደለው መልኩ ነው በድንጋጌው የተመለከተው፡፡ ለአብነትም በራስ ላይና በሶስተኛ ወገን ላይ አደጋ የማይደርስ ከሆነ ቢልም በራስና በሶስተኛ ወገን ላይ የሚደርሰው አደጋ ምን አይነት አደጋ መሆኑ በግልፅ አልተመለከተም፡፡ በራስና በሶስተኛ ወገን የህይወት፣ የአካል፣ የጤንነነት ወይም የንብረት መብት ላይ የሚደርስ ጉዳት ብሎ በግልፅ አላመለከተም፡፡ ሕጉ የሌላን ሰው ጉዳት ለማዳን (በህይወት፣ በጤናና በአካል) ተመሳሳዩ አደጋ እርዳታ በሚሰጠው ሰው ላይ ሳይደርስ የሚደረግ ግደታ አለመወጣትን አንደመከላከያ ይቀበላል ተብሎ መገመት ቢቻልም እርዳታ በሚሰጠው ሰው ንብረት ላይ የሚኖር ጉዳትን ግን ጉዳት ከሚደርስበት ሰው አካል፣ ህይወትና ጤንነት የማይበልጥ በመሆኑ የተነሳ በጠንካራ የሕግ ምክንያት ሕጉ ከግምት የሚያስገባው አይመስልም፡፡ በመሆኑም ሀብታም የሆነ ሰው በርሀብ ጠኔ ላይ ያለን አንዲት ደሀ ቢያገኝ ካለው ገንዘብ የመስጠት ግዴታ አለበት ማለት ነው፡፡ በገንዘብ ጥቅሜ ላይ ጉዳት ይደርሳል ብሎ በሞት አደጋ ላይ የሚገኝን ሰው አለመርዳት እንደመከላከያ የሚቀርብ አይመስልም፡የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 575 በዋናነት ግዴታ የሚጥለው በሁሉም ሰው ላይ ሲሆን ነገር ግን አንዳንድ የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች በልዩነት በውስን ሰዎች ላይ ግዴታ የሚጥሉና እነዚህን ግዴታዎች አለመወጣትን በወንጀል የሚቀጡ ናቸው፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 658 የቀለብ ግዴታ መወጣት ያለባቸው ሰዎች ቀለብ ካልሰጡ የሚመጣ የወንጀል አላፊነት ነው፡፡ በመሆኑም በቤተሰብ ሕጉ መሠረት ቀለብ የመስጠት ግዴታ ባለበት ሰው ላይ ብቻ ተለይቶ የሚመጣ የወንጀል ሀላፊነት ነው፡፡ በወንጀል ሕጉ አንቀፅ አንቀፅ 659 ስር ያለው የልጅ ማሳደግ ግዳታን ባለመወጣት የሚፈፀመው ወንጀልም አባት፣ አሳዳሪ ወይም ሞግዚት መሆንን ይጠይቃል፡፡

Read 4020 times Last modified on May 14 2020
Sesay Goa

ጸሐፊው በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአቃቂ ቃሊቲ ምድብ ፅ/ቤት ምክትል ሀላፊ ነው፡፡ ጸሐፊው የመጀመሪያ ድግሪና በሀዋሳ ዩንቨርሲቲ በንግድ ሕግ የሁለተኛ ዓመት የሁለተኛ ድግሪ ተማሪ ነው፡፡ ሀሳብ አስተያየቶን በዚህ አድራሻ temamosisay@gmail.com ለመስጠት ይችላሉ፡፡