Print this page

ስለ ሌቦች፣  ቀማኞችና ወንበዴዎች የኢፌድሪ ወንጀል ሕግ ምን ይላል?

Aug 30 2019

 

መነሻ ሀሳብ

አንድ አይነኬና ከሰው ልጅ ተፈጥሮአዊነት የሚመነጭ፣ አለምአቀፍ ተቀባይነት ያገኘ ሀገራት በየሕገ መንግስታቸው እውቅና በመስጠት በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የሚያከብሩት መብት አለ፡፡ የእኩልነት መብት፡፡ ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ የእኩልነት መርህን ያልተከተለ የክስ አቀራረብ ሂደትና ወጥነትና ተገማችነት የጎደለው የቅጣት አጣጣል ስርአት አጠቃላይ የአንድ ሀገር የወንጀል ፍትህ ስርአትን የሚያናውጥና የህጎች አላማን የሚያናጋ ነው፡፡ በግልፅ ተለይቶ የታወቀ የሕግ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ማንኛውም አጥፊ በፈፀመው የወንጀል ተግባር ልክ በሕግ መሰረት ይከሰሳል፤ ተመጣጣኝ ቅጣት ይጣልበታል፡፡ ተመሳሳይ ጥፋት የፈፀሙ ሰዎች ተመሳሳይ ክስ ሊቀርብባቸው ይገባል፡፡ ከጥፋተኝነት ውሳኔ በኃላ ታሳቢ የሚደረጉ ግላዊ ሁኔታዎችንና የሚቀርቡ የቅጣት ማቅልያዎችን እንደተጠበቁ ሆኖው ለተመሳሳይ የወንጀል ክስ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል፡፡ በፍርድቤት የሚቀርቡ ክሶች ተፈፀመ ከተባለው የወንጀል ተግባር የሚጣጣም መሆኑን ወይም የተጋነነ ልዩነት አለመኖሩን ዳኞች ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለሆነም ፍርድቤቶች የማስረጃ ምዘናን ብቻ ሳይሆን የህጋዊነትና የእኩልነት መርህንም በአግባቡ እየተፈጸሙና ስራ እየዋሉ ስለመሆናቸው የመመርመር ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

አቃቤ ሕግ በበኩሉ የሕግ መርህን ያልተከተለ፣ የተዛባና ወጥነት የሌለው ውሳኔ በፍርድቤቶች ሲሰጥ በሕግ አግባብ በማስቀየርና እንዲስተካከል በማድረግ የእኩልነትና የህጋዊነት መርህን መሰረት ያደረገ የወንጀል ሕግ ተፈፃሚነት እንዲኖር የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ አቃቤ ሕግ ለተመሳሳይ የወንጀል ተግባራት ተመሳሳይና ወጥነት ያላቸው ውሳኔዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ከመጀመርያ ጀምሮ የተስተካከለና የወንጀል ህጉን አላማ በሚያሣካ መልኩ ክስ ሲያቀርብ ወይም ሌላ አግባብነት ያለው ውሳኔ ሲሰጥ ነው፡፡ ስለሆነም የወንጀል ህጉን ከማስፈፀም ረገድ አቃቤ ሕግ መሪ ተዋናይ ነው፡፡

በወንብድና፣ በስርቆት እና በአስገድዶ መጠቀም ወንጀሎች ላይ በተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች ያለው የሕግ ግንዛቤ የተለያየ በመሆኑ ወጥነት የሌለው እና የተዘበራረቀ ክስ ሲመሰረት ማየት የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችንም ይህን ክፍተት ሲቀርፉ አይታዩም፡፡ ስለሆነም በእነዚህ ወንጀሎች መካከል ያለው የሕግ አቀራረፅና አተረጓጎም፤ የውሳኔ አሰጣጥ ጉድለቶች እና በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮችን መዳሰስ አስፈላጊ ነው ብሎ ፀሃፊው በማመኑ የግል አቋሙን ለማካፈል ወዷል፡፡

 

    ጉዳዩን ግልፅ ለማድረግ በምሳሌ ልግለፀው፡፡

“አራት ተጠርጣሪዎች በየፊናቸው ከሌሎች አራት ግለሰቦች ስልክ ነጥቀው ሲሮጡ በፖሊስ ክትትል እና በምስክሮች እርዳታ እጅ ከፍንጅ ይያዛሉ፡፡ ተጠርጣሪዎች በተለያየ ቦታ እና ጊዜ ሰዎችን እየተከታተሉ የተመቻቸ ሁኔታ ሲያገኙ ስልክን ነጥቀው መሮጥ ስራቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ይህ ተግባር የመጀመርያቸው አይደለም፡፡ ፖሊስ አራቱም ተጠርጣሪዎችን የሌላ ሰው ንብረት መቀማታቸውን በማስረጃ አረጋግጧል፡፡ በዚሁ መሰረት የወንጀል ምርመራ መዝገብ አደራጅቶ ለተለያዩ አራት አቃቤያነ ሕግ ለህጋዊ አስተያየትና ውሳኔ አቀረበላቸው፡፡ መዝገቡ ለአቃቤያነ ሕግ ከደረሰ በኃላ አንዱ በውንብድና ወንጀል ፤ ሁለተኛው በስርቆት ወንጀል፤ ሶስተኛ በአስገድዶ መጠቀም፣ አራተኛው ደግሞ በከባድ ስርቆት ወንጀል ክስ አቅርበዋል፡፡ ፍርድቤቱም ክሶቹ እንደየአመጣጣቸው አስተናግዶ አራቱን ተጠርጣሪዎች ጥፋተኞች ናቸው በማለት በቀረበባቸው ክስ መሰረት የተለያየ ቅጣት ወስኖባቸዋል፡፡”

ይህ አጋጣሚ ፀሃፊው በተለያዩ ችሎት ቁጭ ብሎ የታዘባቸው አስገራሚ ክስተቶች በመሆናቸው ፈጠራ (Hypothetical cases) አለመሆናቸው ውድ አንባብያን ትገነዘቡኝ ዘንድ አስቀድሜ እጠይቃለሁኝ፡፡

በእርግጥ ይህ አጭር ጽሁፍ ለማዘጋጀት የተገደድኩበት ዋና ምክንያት በስርቆት(ከባድ ስርቆት) ወንጀል እና በውንብድና ወንጀል ላይ ትንተና ለመስጠት ወይም ሰፊ እና ጥልቀት ያለው የንጽጽር ጽሁፍ ለማቅረብ አይደለም፡፡ ይህ ለማድረግ ጊዜ እና ቦታ ይበቃል ተብሎም ስለማይገመት፤ የዚህ ጽሁፍ ዋና አላማ እና ትኩረት በኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 ስር የተመለከተውን አስገድዶ መጠቀም የወንጀል ድንጋጌ በክስ አቀራረብ ረገድ ያለው ልምድ ከህጉ አላማ ጋር በተጣጣመ መልኩ እየተተገበረ ስለመሆኑ እንዲሁም ከስርቆት እና የውንብድና ወንጀሎችን በአግባቡ ተለይቶ በሁሉም የሕግ ባለሙያ ወጥነት ባለው ሁኔታ እየተሰራበት ስለመሆኑ/አለመሆኑ አንባብያን በማያሰለች መልኩ አጠር ያለ ጽሁፍ ለማቅረብ እና የራሴ አተረጓጎም እና አቋም ለማንፀባረቅ ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ የአስገድዶ መጠቀም ወንጀል ትርጉም፣ ይዘት፣ አላማና የድንጋጌው መንፈስ ከተቀረፀበት አግባብና የሕግ አውጪው አካል ሊያሳካው ከፈለገው ግብ አንፃር እንደሚከተለው ለማብራራት እሞክራለሁኝ፡፡

  • አስገድዶ መጠቀም ምን ማለት ነው?

አንድን ሰው በማስፈራራት ንብረቱን እንዲሰጥህ ማድረግና በቀጥታ ኃይልን በመጠቀም ንብረቱን መቀማት ልዩነታቸው ምንድን ነው? የትኛውን የንብረት አወሳሰድ ስልት ነው አደገኛ? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ከተቻለ የአስገድዶ መጠቀም ይዘትና ህጋዊ ትርጉም መረዳት ከባድ አይሆንም፡፡ በመጀመርያው ላይ ዛቻን መሰረት በማድረግ የሌላ ሰው ንብረት መውሰድ ነው፤ በሁለተኛ ላይ ደግሞ ኃይልን በመጠቀም የሌላ ሰው ንብረትን መንጠቅ ነው፡፡ ልዩነታቸው ይህ ሆኖ በውጤት ደረጃ ግን ሁለቱም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁለቱም ሕገ ወጥ ተግባራት ናቸው፡፡

ከአደገኛነትና ከከባድነት መለኪያ በአንፃራዊነት ሲታይ በቀጥታ ኃይል ተጠቅመህ የሌላ ሰው ንብረትን መውሰድ አስፈራርትህ እንዲሰጥህ ከማድረግ በላይ አደገኛና ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም ካለ ምንም አይነት ቅድመ ድርድር በጉልበትህ ተማምነህና ተመክተህ በሌላ ሰው እጅ የሚገኝ ንብረት እየቀማህ ነው፡፡

በአጠቃላይ አስገድዶ መጠቀም ማለት ከባለንብረቱ መልካም ፈቃድ ውጪ በተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎች አስገድደህ ንብረቱን ወይም ሃብቱን በሕገ ወጥ መንገድ የመውሰድ ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ይዘት ስንመለከተው በቀጥታ ኃይል ተጠቅመህ መቀማትን እንዲሁም በተዘዋዋሪ የተለያዩ ማስፈራርያዎችና ሌሎች ስነ ልቦናዊ ተፅእኖዎችን በማሳደር ግለሰቡ ንብረቱን እንዲሰጥህ ማድረግን የሚያጠቃልል የወንጀል ተግባር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው በደረሰበት ከፍ ያለ ዛቻ ወይም ስነ ልቦናዊ ተፅእኖ ምክንያት ፈርቶ ንብረቱን እንካ ብሎ ለተከሳሽ መስጠት በማስገደድ መጠቀም እንደሆነ ሁሉ ተከሳሹ ስነ ልቦናዊ ተፅእኖ ሳያሳድር በቀጥታ ኃይል ተጠቅሞ ንብረቱን ቀምቶ ወይም ነጥቆ መውሰድም አስገድዶ መጠቀም ነው፤ ምክንያቱም በሁለቱም መንገዶች በዛቻ ወይም በኃይል ንብረቱን ተገድዶ እንዲሰጥህ በማድረግ በገዛ ንብረቱ ላይ የተቆጣጣሪነትና የባለቤትነት መብቱን እንዲያጣ የማድረግ ውጤት አላቸው፡፡

  • የወንጀል ሕግ አንቀፅ 713 ይዘት ምን ይመስላል?

 በዚሁ ድንጋጌ መሰረት ጥቅም የሚያስገኝ ማንኛውም ንብረት እንዲሰጠው ማድረግ የሚለው ቃል እንዴት መተርጎም አለበት?ከወንበዴነት ውጪ በሆነ የሃይል ወይም ከፍ ያለ የዛቻ ተግባር ምን ማለት ነው?በህሊና ወይም በሰው ችግር የሚፈፀም ወንጀል ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው የአንቀፅ 713 ይዘትና አላማ እንዲሁም የሚገኝበት ምእራፍና ርእስ በአግባቡ በመመርመርና ከተቀረፀበት አላማ አንፃር በመተርጎም ነው፡፡

በመሰረቱ እንዲሰጠውበማድረግ የሚለውን ቃል የሚያመለክተው በዛቻና ማስፈራሪያ ጫና ተደርጎ ብቻ መስጠት አንድ ነገር ሆኖ ሀይል ታክሎበት ስትቀማም ቢሆን ዞሮ ዞሮ ውጤቱ መስጠት ነው፡፡ ስለዚህ በኃይል ንብረትህን የወሰደብህ ሰው ቀማኛ ሲሆን ተበዳይ ደግሞ የደረሰበትን የኃይል ተግባር ሊቋቋምና ሊከላከል ባለመቻሉ ሳይወድ በኃይል ሰጥቷል ማለት እንችላለን፡፡ በዚሁ አንቀፅ የተካተተው “ኃይል” የሚል የማስገደድ መጠቀም ወንጀል ማቋቋሚያ ፍሬ ነገር በዚሁ መልኩ ስራ ላይ ካልዋለ በሌላ መንገድ የሚተረጎምበትና ሆነ ጥቅም ላይ የሚውልበት እድል የለም፡፡ በመርህ ደረጃ ማንኛውም ሕግ በተለይም ደግሞ የወንጀል ሕግ መተርጎም ሳያስፈልገው እንደወረደ ስራ ላይ መዋል አለበት፡፡ ይህ ሕግም ግልፅና ትርጉም የማያስፈልገው በመሆኑ በዚሁ መልኩ ሊሰራበት ይገባል ብሎ ፀኃፊው ያምናል፡፡ ነገር ግን ከዚሁ አንቀፅ ጋር ተያይዞ ህጉ ግልፅነት የጎደለውና ለትርጉም አሻሚ በሆኑ ቃላት የተቀረፀ ነው ቢባልስ እንዴት ነው መተርጎም ያለበት የሚለው ጥያቄ መመለሱ አስፈላጊ ነው፡፡

አንስተህ መውሰድ፣ መንጠቅ፣ ቅምያ እና መጓተት የሚሉ ቃላት የስርቆትና የአስገድዶ መጠቀም መሰረታዊ ልዩነቶችን አንጥሮ ለማውጣት በእጅጉ ሊጠቅሙን የሚችሉ ቃላት ናቸው፡፡ አንድን ንብረት አንስቶ ወሰደ ለማለት ንብረቱ የሚወሰድበት አግባብ ተጎጂው ሊያየው ወይም በቀጥታ ሊከታተለው የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም የስርቆት ተግባር የሚፈጸመው ንብረቱ ከተቀመጠበት ቦታ አንስቶ መውሰድ ነው፡፡ ይህ ከተበዳይ ኪስ ውስጥ በድብቅ አውጥተህ ወይም አንስተህ መውሰድን ይጨምራል፡፡ በወንጀል ሀተታ ዘ ምክንያት እንደተብራራውም የስርቆት ወንጀል የሚፈጸመው አዩኝ አላዩኝ ብሎ አንድ ንብረትን ከተቀመጠበት ቦታ ላይ አንስተህ መውሰድ ነው፡፡ ይህ ማለት ተጠርጣሪው የሌላ ሰው ንብረትን በሚወስድበት ጊዜ የሚያየው ሰው ካለ ይተወዋል፤ የሚያዬው ወይም የሚከታተለው ሰው ከሌለ ደግሞ ንብረቱን ይወስዷል፡፡ “ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት” የሚል በማህበረሰባችን የተለመደው ምሳሌዊ አነጋገር የሚያሳየው ሌብነት የግል ተበዳዩ ሳያውቅ ወይም ሌላ ሰው እንደማያይ እርግጠኛ በመሆን በጥንቃቄና በድብቅ የሚፈፀም ወንጀል መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ የስርቆት ወንጀል ተፈጸመ የሚባለው ተበዳዩ ወይም ሌላ ሰው በቅርብ ሆኖ እንደማያየው ፤ እንደማይከታተለው ወይም እንደማያስቆመው በማረጋገጥ በድብቅና በጥንቃቄ የሚፈጸም የወንጀል አይነት ሲሆን ተበዳዩ በአይኑ በብረቱ እያየውና ንብረቱን ከቅሚያ ለማስቀረት ፊት ለፊት እየተጋፈጠው ወይም ሌላ ሰው እያየው ቀምቶ ወይም ነጥቆ ወይም አስፈራርቶ መውሰዱን ከተረጋገጠ ግን የስርቆት ወንጀል ሳይሆን በማስገደድ መጠቀም ነው፡፡

አስገድዶ መጠቀም ወንጀል የሚገኝበት ርእስ የህሊና ወይም የሰው ችግር (Moral and Material Intimidiation) መሰረት በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ስር የሚገኝ ሲሆን ከዚሁ ርእስ መገንዘብ የሚቻለው የሰው ችግር (Material intimidiation) የሚለው ቃል አካላዊ ድክመትና ለጥቃት ተጋለጭነት የሚያካትት በመሆኑ መንጠቅን አያካትትም ማለት አይቻልም፡፡ የሰው ችግር(Matrial Intimidiation) የሰዎች ፍርኃት፣ ራስን ያለመከላከል ችግር፣ ተሎ የመደናገጥና ንብረትን ለመከላከል በተስተካከለ ቁመና ላይ ያለመገኘት ችግሮችን የሚያካትት በመሆኑ መንጠቅ የሚል የወንጀል አይነት ከርእሱ ጋር አይጣጣምም የሚል ክርክር መሰረታዊ ስህተት ነው፡፡ ስለሆነም የአንቀፅ 713 ይዘት ከስነልቦናዊ ተፅእኖ(የህሊና ችግር) ጋር ብቻ ተያይዞ በጠባቡ መተርጎም አለበት የሚለው ክርክር የህጉን አላማና መንፈስ ያላገናዘበ ፍፁም ስህተት ነው፡፡ ስነልቦናዊ ተፅእኖ (psychological threat) መሰረት በማድረግ ብቻ የሚፈፀመው ወንጀል በአንቀፅ 714 ስር የተመለከተውን የማስፈራራት ወንጀል(blackmail) ሲሆን አስገድዶ መጠቀም ወንጀል ግን ስነልቦናዊ(psychological threat) እና ቀጥተኛ ሃይል(physical force) በመጠቀም የሚፈፀም ወንጀል ነው፡፡

ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ የሰው ንብረትን ለመንጠቅ ሀይል ተጠቅሟል ወይም ሀይል እየተጠቀመ ነው ለማለት ተጎጂው ሊከላከል ሆነ ንብረቱን ለማስቀረት የሚችልበት እድል እንደሌለ አስቀድሞ በማረጋገጥ የሌላ ሰው ንብረት ነጥቆ ከሮጠ ንብረቱን የወሰደበት መንገድ ሀይልን ተጠቅሞ እንጂ አንስቶ ወስዷል ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተጠርጣሪው አንድ ንብረትን በመንጠቅ ላይ እያለ ተጎጂው ንብረቱን አጥብቆ በመያዙ ምክንያት በመካከላቸው መጓተት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ሁለቱም የአንድ ንብረት ሁለት ጫፍ ይዘው ሲጓተቱ በመጨረሻም ተከሳሹ አሸናፊ ሆኖ ንብረቱን ወደ እጁ በማስገባት ተጎጂውን ጥሎ ሊያመልጥ ይችላል፡፡ ከዚህ ምሳሌ መረዳት የምንችለው ተጠርጣሪው የተጎጂው አካል ባይነካም ሀይል ተጠቅሟል፣ ሀይል የተጠቀመው ግን በተጎጂው አካል ላይ ሳይሆን ንብረትን በሀይል ጎትቶ መውሰድ ላይ ነው፡፡ ይህ ሀይል ለወንበዴነት አላማ የሚያገለግል የኃይል መጠንና ደረጃ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንስ በተጎጂው አካላዊ ድክመት(የሰው ችግር) ላይ ነው ኃይሉን የተጠቀመው ማለት ይቻላል፡፡ ንብረቱ ሲቀማ ተጎጂው ንብረቱን ተከላክሎና አጥብቆ ያለመያዝ የአካልና የሁኔታ ክፍተት ወይም ችግር ተጠቅሞ የሚፈጽመው ጥፋት በመሆኑ የውንብድና ወንጀል ነው ልንለው አንችልም ፡፡ ሆኖም ግን ጉዳዩ ከስርቆትም በላይ ነው፡፡ የወንጀሉ አፈጻጸም መንጠቅ ወይም ቅሚያ ነው፡፡ መንጠቅ የሚለው ቃል ደግሞ በአስገድዶ መጠቀም ወንጀል ስር የሚያርፍ ነው፡፡ “መንጠቅ” ወይም መቀማት አስገድዶ መጠቀም የወንጀል ተግባር ከሚቋቋምበት ፍሬ ነገሮች አንዱ ነው፡፡

 በአጠቃላይ የሌላ ሰው ንብረትን ለመውሰድ ማንኛውም አይነት የኃይል ተግባር ከተጨመረበት የንብረት አወሳሰዱን ስርቆት መሆኑን ቀርቶ እንደየሁኔታው በማስገደድ መጠቀም አልያም ደግሞ ውንብድና መሆን እንዳለበት ከወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች አንቀጽ 665፣ 770 እና 713 መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ እንድያውም ዋና ጥያቄ መሆን ያለበት በማስገደድ መጠቀምና በውንብድና ወንጀሎች መካከል ያለውን የኃይል መጠንና ደረጃ እንዴት መለየት ይቻላል የሚል እንጂ የኃይል ተግባር የታከለበት የትኛውንም ድርጊት ከስርቆት ወንጀል ጋር ለማስተሳሰር መሞከር ግን ትክክል አይደለም፡፡

በወንብድና እና አስገድዶ መጠቀም ወንጀሎች ወንጀሎች ላይ ሀይል አለ፤ ዛቻም አለ፡፡ በውንብድና ላይ የሚያስፈልገው ዛቻ ንብረቱን በሚወሰድበት ወይም ከተወሰደ በኃላ በባለንብረቱ ወይም ንብረቱን ለመከላከል በሚሞክር ማንኛውም ሰው ላይ በቀጥታ የሚሰነዘር ነው፡፡ በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ላይ ደግሞ ንብረቱን ከመወሰዱ በፊት በማንኛውም ጊዜ ተጎጂውን በቀጥታ በማስፈራራት ሳይፈልግ እንደፈለገ ተደርጎ ንብረቱን እንዲሰጠው ማድረግ አንደኛው የወንጀሉ መቋቋሚያ ሲሆን ቀጥተኛ የሆነ ጉልበት ወይም ኃይል በመጠቀም የተጎጂውን ንብረት መቀማት ደግሞ ሁለተኛው የወንጀሉ ማቋቋሚያ ፍሬ ነገር ነው፡፡ በውንብድና ወንጀል ላይ ተጎጂው ንብረቱን ፈልጎ አያስረክብም፡፡ በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ላይ ግን በተፅእኖ ንብረቱን ፈልጎ ያስረክባል፤ ይህ ግን ስነ ልቦናዊ ጫናውን ብቻ ይመለከታል፡፡ በሁለቱም ወንጀሎች ላይ የሚያስፈልገው ዛቻ በዚሁ መልኩ መለየት የሚቻል ሲሆን ኃይልን በተመለከተ ግን ሁለቱም ወንጀሎች የሚለዩበት መለኪያ ከባድ ያደርጓል፡፡

 የውንብድና ወንጀል ተፈፅሟል የሚባለው ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ የሌላ ሰው ንብረትን ለመውሰድ በተጎጂው ላይ ቀጥተኛ የሆነ የኃይል ተግባር ወይም ከባድ የሆነ የማንገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ የፈፀመ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው እንዳይከላከል ያደረገ እንደሆነ ነው በማለት የወንጀል ህጉ አንቀፅ 670 ይደነግጋል፡፡ በሰው አካል ላይ በቀጥታ ማናቸውም አይነት የኃይል ተግባር ተጠቅሞ ንብረት መውሰድ ውንብድና ነው፡፡ በተጎጂው አካል ላይ ቀጥተኛ ኃይል ሳይጠቀም ንብረቱን ብቻ ለመቀማት፣ ለመመንተፍ ወይም ለመንጠቅ ኃይል የተጠቀመ እንደሆነ ግን ወንጀሉ ውንብድና መሆኑን ቀርቶ አስገድዶ መጠቀም ይሆናል፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 ስር “ከውንብድና ውጪ ያለው ኃይል” እየተባለ ያለውም ይህን ነው፡፡ በውንብድና ወንጀል ላይ የሚያስፈልገው የኃይል መጠን ንብረትን ለመውሰድ በተበዳይ ላይ የሚጠቀመው ኃይል አለ፤ በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ላይ የሚያስፈልገው ኃይል ግን ንብረቱን በቀጥታ ቀምቶ በመውሰድ ላይ ብቻ የተገደበና የተበዳይ አካልን የማይጎዳ ሀይል ነው፡፡ ለውንብድና ወንጀል የሚያስፈልገው ኃይልና ለአስገድዶ መጠቀም ወንጀል የሚያስፈልገው ኃይል ወይም ጉልበት በዚሁ መልኩ እየለያየን ከልተጠቀምንበት ህጎቹ በሚፈለጉበት አግባብ ስራ ላይ ማዋል አይቻልም፡፡ በማስገደድ መጠቀም ወንጀል ላይ ኃይልን መጠቀም የሚቻለው ንብረቱን በሚወሰድበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በውንብድና ወንጀል ላይ ግን ኃይል መጠቀም የሚቻለው ንብረቱን በሚወሰድበት ጊዜም ንብረቱን ከተወሰደ በኃልም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ በአስገድዶ መጠቀም ወንጀል ላይ ኃይል የሚያስፈልገው ንብረቱን ለመቀማት ብቻ መሆኑና፤ ለውንብድና ወንጀል የሚያስፈልገው ኃይል ደግሞ በሰው አካል ላይ ጉዳት ማድረስ ወይም ጉዳት ለማድረስ ከባድ የማንገላታት ተግባርና ከባድ ዛቻን መጠቀምን ጭምር መሆኑን ግልፅ ነው፡፡

  • የሕግ አውጪው ሃሳብ

ትርጉም የሚያስፈልገው አንድ የሕግ ቃል ሕግ አውጪው ለምን እንደተጠቀመበት ለማወቅ ለህጉ መውጣት ምክንያት የሆኑት ማህበራዊ ጉዳዮች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ከታሪክ፣ ከልምድ እና ከሕግ አወጣጥ ሂደት መመርመር አስፈላጊ መሆኑ የሕግ ምሁሩ ፀሀይ ወዳ የወንጀል ሕግ መሰረታዊ መርሆዎች በሚል መፅሃፋቸው ላይ ገልፀውታል፡፡ በተጨማሪም የሕግ አውጪው ሃሳብ ለማወቅ ህጉን ለምን ወጣ፣ ምን አይነት ጉዳዮችን ለማጠናከር ወይም ለማስወገድ ወጣ ወዘተ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ መሆን እንዳለበት በሕግ ዙርያ የካበተ ልምድ እና እውቀት ያላቸው አለም አቀፍ እና ሃገር በቀል ምሁሩን የሚስማሙበትና ተቀባይነት ያገኘ የሕግ አተረጓጎም መርህ ነው፡፡

ህጉ ሊያጠናክራቸው ወይም ሊከለክላቸው የፈለጋቸው ጉዳዮች ህጉ በወጣበት ዘመን ከነበረው የአንድ ሃገር ልምድ ፣ የህብረተሰቡ እምነት ወይም አመለካከት የሚታወቅ ነው፡፡ መንጠቅ የሚል ቃል መውሰድ በሚል ቃል ውስጥ ተካቶ የሕግ ትርጉም ሊሰጥበት ይቅርና በአማርኛ ጠቅላላ መዝገበ ቃላትም በዚህ መልኩ የማይተረጎም ነው፡፡ መንጠቅ/መቀማት የሚል ቃል መውሰድ ከሚለው ተራ የሆነ የንብረት አወሳሰድ ለመግለፅ የሚያገለግል ቃል ሳይሆን ሀይል ከመጠቀም ጋር በእጅጉ የሚተሳሰር ነው፡፡ ማህበረሰባዊ ቅቡልነት ያለው አተረጓጎምም ይህ ነው፡፡

“የአገሬ ሰው” እንዲህ አይነት ክስተት ሲገጥመው ተሰረቅኩኝ፣ ንብረቴን ተወሰደብኝ አይልም ይልቁንስ ተዘረፍኩኝ ፣ ተነጠኩኝ፣ ጉልበተኞች ቀሙኝ ይላል፡፡ የስርቆት ወንጀልን ለመፈፀም ጉልበተኛ መሆን አያስፈልግም፤ ኃይልን ወይም ዛቻን መጠቀም አይጠይቅም፡፡ ቀማኛ፣ ነጣቂ ወይም መንታፊ ግን እንደቀማ ወድያውኑ የመሮጥ አቅምና ጉልበት የሚያስፈልገው ከመሆኑ በላይ አንስቶ እንደመውሰድም ጉዳዩ ቀላል አይሆንለትም፡፡ ምክንያቱም መጓተት፣ አልሰጥ ባይነት፣ ተቋውሞና ንብረትን የማስቀረት ትግል እንደሚገጥመው ያውቃል ወይም ይገምታል፡፡ ስለሆነም በመርህ ደረጃ እንዲህ አይነት ቀማኛ ወይም ነጣቂ በጉልበቱ የሚተማመንና የሚመካ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሕግ የማህበረሰብ ነጸብራቅ ነው፡፡ ሕግ የአንድ ማህበረሰብ ጸጥታ፣  ሰላምና ደህንነት የሚያስጠብቅ ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ህጉ ከማህበረሰቡ እምነት እና እሴት ተነስቶ ሌባን፣ ቀማኛን እና ወንበዴን የተለያዩ ቅጣቶች እንዲጣልባቸው ይፈልጋል፡፡ አንድ ሕግ መፈፀም ያለበት ደግሞ ማህበረሰቡ ከሚፈልገው አንፃር ተለክቶ እና ተሰፍሮ መሆን አለበት፡፡

 በተጨማሪም ሕግ አውጪው ህጉን ሲያወጣ በረቂቁ ላይ ያካሄዳቸው ክርክሮችና ህጉን ከመውጣቱ በፊት የነበረው የቀድሞ ሕግ የተሻሻለበት/የተሻረበት መንገድ፣ የተጨመረበት እና የተቀነሰበት ቃል ከሃተታ ዘ ምክንያት ላይ በመገንዘብ የሕግ አውጪው ሃሳብ ማወቅ ይቻላል፡፡ በዚሁ መሰረት የቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣  የወንጀል ሃተታ ዘ ምክንያት እንዲሁም አግባብነት ያላቸው የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች ስለ አስገድዶ መጠቀም ወንጀል እንዴት ይገልጹታል? በህጉ አተረጓጎም ዙርያሰ ምን አይነት አስተዋጽኦ ይኖራችዋል? የሚሉትን ጉዳዮች እንመለከታቸዋለን፡፡

  • አስገድዶ መጠቀም ወንጀል በ1949 ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ

አንቀጽ 668- ስለ መንጠቅ 

ማንም ሰው ከዚህ በላይ ከተመለከተው ከወንበዴነት ስራ ውጭ በሆነ አድራጎት የኃይል ወይም ከፍ ያለ የዛቻ ስራ በሌላው ሰው ላይ በመፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ ዓይነት አድራጎት እንዳይከላከል በማድረግ የማይገባውን የንብረት ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ሲል ገንዘቦችን ወይም ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ወይም ሰነዶች ወይም ግዴታ ያለባቸውን መብቶችን የሚሰጡ ወይም ዕዳ የሚያስቀሩትን ወይም ማናቸውንም ይህን የመሳሰለ ጥቅም ያለበትን ነገር እንዲሰጠው ያስገደደ እንደሆነ በስርቆት ወንጀል መሰረት እጅግ ቢያንስ በሶስት ወር እስራት ወይም እንደ ወንጀሉ ክበደት መጠን እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡

የቀድሞው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 668 ስር “መንጠቅ” የሚል የድንጋጌው ርዕስ የነበረ ሲሆን ይህንን የአንቀፁ ርዕስ በግርድፉ እና በመደበኛው የአማርኛ አነጋገር ስንተርጉመው አንድን ንብረት ከአንድ ሌላ ግለሰብ እጅ ላይ ነጥቀህ/መንትፈህ መውሰድ የሚያመላክት ቃል ነው፡፡ ወደ ዝርዝር ይዘቱ ስንገባ ግን በአንቀፁ ርእስ ያልታቀፈ ወይም ሊካተት የማይችል ይዘት እናገኝበታለን፡፡ ይኸውም አንድን ግለሰብ በተለያዩ ዘዴዎች አስፈራርተህ ወይም ስነልቦናዊ ጫና አሳድረህ ንብረቱን ተገድዶ ወይም በፍርሃት ውስጥ ሆኖ እንዲሰጥህ በማድረግ  ንብረትን መውሰድ እንደሚያጠቃልል ህጉ በግልፅ ያሳያል፡፡ ይህ የሚያሳየው የአንቀፁ ርእስ እና ዝርዝር ይዘቱ ተጣጥሞ አልተቀረጸም ነበር የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሳል፡፡ የቀድሞው ሕግ የእንግሊዘኛ ቅጂ ይህን ችግር አይታይበትም ነበር፤ ምክንያቱም መንጠቅ የሚል የአንቀፁ ርእስ “Extortion” በሚል ቃል ተተርጉሞ የነበረና ይህ ቃል አሁንም በአንቀፅ 713 ስር ተቀምጦ የሚገኝ ነው፡፡ የአሁኑ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 ሲቀርጽ ይሄንን ጉድለት ታሳቢ በማድረግ ሁለቱም ማለትም አካላዊ ሀይልና ስነልቦናዊ ማስፈራሪያን (Physical force and psychological threat) ለማጠቃለል በማሰብ በማስገደድ መጠቀም የሚል ለሁሉም የአንቀፁን ይዘት እና አላማ የሚያካትት አቃፊ ቃል ተፈልጎ በሕግ አውጪው ታስቦበት የተቀመጠ የተሻለና የተጣጣመ አቀራረጽ ነው፡፡

  • የወንጀል ሕግ ሃተታ ምክንያት ምን ማብራርያ ሰጠ?

የወንጀል ሃተታ ዘ ምክንያትም የወንጀል ህጉ አንቀጽ 713 ከወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 668 አንጻር ያስቀመጠውን ሃተታ እና ምክንያት ሲታይ አንቀፁ ከርእሱ ጀምሮ አንዳንድ የቃላት ማስተካከያ እንደተደረገበት ሲገልፅ መሰረታዊ የሆነ የይዘት ሆነ የአላማ ለውጥ እንደተደረገበት ግን ያስቀመጠው ነገር የለም፡፡

ስለሆነም ከተሻሻለው የወንጀል ሕግ ሀተታ ዘ ምክንያት በማንበብ መረዳት እንደሚቻለው የቃላት አወቃቀር እና አቀማመጥ ለማስተካከል ተብሎ መንጠቅ የሚለው ቃል አስገድዶ መጠቀም ወደሚለው ቃል እንደተቀየረ እንጂ መሰረታዊ ይዘቱና አላማው ለመቀየር ተብሎ አይደለም፡፡

በሌላ አነጋገር አሁን በስራ ላይ ያለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 የቀድሞው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 668 ስር የነበረውን መንጠቅ የሚል የወንጀሉ ርዕስ በማስገደድ መጠቀም የተካበት ዋና ምክንያት ስነልቦናዊ ጫና/ዛቻ ለማጠቃለል በማሰብ እንጂ “መንጠቅን” ከአንቀፁ ለማስወገድ አለመሆኑን ግለጽና የማያከራክር ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም መንጠቅ የሚል ቃል አካላዊ/ቁስአካላዊ ጥቃት(ቀጥተኛ ኃይልን) ብቻ እንጂ ስነልቦናዊ ጥቃትን(ዛቻ፣ ማስፈራርያዎች፣  ሌሎች ተፅእኖዎችና መሰል ተግባራትን) የሚያቅፍ አልነበረም፡፡ አስገድዶ መጠቀም ግን አቃፊ ቃል ነው፤ የወንጀሉ ርእስና የወንጀሉ ዝርዝር የአፈጻፀም መንገዶችን አጣጥሞ የሚያስቀምጥ ግልፅ የሆነ የሕግ አቀራረፅ በማስፈለጉ መንጠቅን በማስገደድ መጠቀም መተካት አስፈላጊ ነበር፡፡ ለምሳሌ አዲሱ የወንጀል ሕግ ከመውጣቱ በፊት ተጠርጠሪ ስልክ ነጥቆ ቢሮጥ አቃቤ ሕግ ክስ መመስረት ያለበት በየትኛውን ድንጋጌ ነው የሚለው ጥያቄ አሁን ከያዝነው ጉዳይ የበለጠ አወዛጋቢ ጉዳይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም ርእሱ መንጠቅ ቢልም ውስጡ ወይም የአንቀጹ ይዘት ካየነው ግን ተከሳሽ በተለያዩ ምክንያቶችና መንገዶች ተጎጂው ንብረቱን እንዲሰጠው ማድረግ የሚል ይዘት አለው፤ ነገር ግን ይህ ሕግ ስራ ላይ በነበረበት ጊዜ የሌላ ሰው ንብረት ነጥቆ የወሰደ ሆነ አስፈራርቶ እንዲሰጠው ያደረገ ተጠርጣሪን ሁለቱንም መንጠቅ በሚል የወንጀል ክስ ይቀርብበት እንደነበር ያለፉት የአቃቤ ሕግ ስራዎችንና የፍርድቤቶች ውሳኔዎችን በማየት መገንዘብ ይቻላል፤ መሆን የነበረበትና ያለበትም ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እንዲሰጠው ያደረገ የሚል ቃል በቀድሞው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 668 ስር ስላልነበረ አይደለም፡፡ ይህ ቃል ያኔም ነበር፡፡

 

  • የ1996 የወንጀል ሕግ የእንግሊዘኛ ቨርዝን ምን ይላል?

Article 713 -Extortion

Whoever, in cases not amounting to robbery(art.670),uses violence or grave threats against a person,or in any other manner renders such person unable to resist,in order to obtain himself or to procure to a third person an unjustifiable benefit in property,whether by an assignment of funds or securities,documents or writings,executing or evidencing the transaction,disposion or discharge,or any other similar benefit, Shall be punishable.(ቅጣት ተቀምጧል)

 በቀድሞ ሕግ ሆነ በአዲሱ ሕግ የእንግሊዘኛው ቨርዢን ኤክስቶርሽን (extortion) የሚል ርእስ እና አጠቃላይ የአንቀፁ ዝርዝር ይዘት እንደወረደ በተመሳሳይ መልኩ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ይህ ደግሞ የሕግ አውጪው ሃሳብ እና አጠቃላይ የህጉን አላማ በመገንዘብ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እሙን ነው፡፡ መጠነኛ የቃላት አቀማመጥና አቀራረፅ ለውጥ የተደረገው በአማርኛ ቅጂ ላይ እንጂ በእንግሊዘኛው ላይ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 668 የነበረውን ይዘት (ርእሱን ጨምሮ) እንደወረደ በአዲሱ የተሻሻለው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 713 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡  

በተጨማሪም በእንግሊዘኛው ቅጂ ላይ እንዲሰጠው ለማድረግ የሚል የአማርኛ ትርጉም የሚሰጥ አንድም የእንግሊዘኛ ቃል አልተቀመጠም፡፡ ይህ የሚያሳያው የሕግ አውጪ ሃሳብ መስጠት በሚል የአማርኛ ቃል ላይ በመንጠልጠል የህጉን አጠቃላይ መንፈስ፣  አላማና ሊያሳካው የፈለገውን ግብ በማዛባት ቀማኞችና ነጣቂዎች በስርቆት እንዲከሰሱ እና እንዲቀጡ በመፈለግ ሳይሆን አጥፊዎች የሌላ ሰው ንብረት ለመውሰድ በመደበኛ የስርቆት አፈፃፀም ዘዴ ሳይሆን ለውንብድና ከሚያስፈልገው ሀይል በታች በሆነ ሀይል ወይም መጠነኛ የሆነው የንብረት መጓተት ወይም መንጠቅ መሰል የአወሳሰድ ስልቶችን ተጠቅመው የሚቀሙ ሰዎችን ለመቅጣት የተቀረፀ የሕግ ማእቀፍ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 የአማርኛ ቅጂው ላይ የሰፈረው መስጠት የሚል ቃል በተለያዩ ጫናዎችና ተፅእኖዎች ምክንያት እንካ ውሰድ ብለህ ንብረትህን መስጠት ብቻ ቢሆን ኖሮ በእንግሊዝኛው ቨርዥን ላይ ይህን ቃል በጥንቃቄ ተተርጉሞ አቻ ፍቺ ይቀመጥለት ነበር፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ/ም በሰበር መዝገብ ቁጥር 159407 መሰረት የሰጠውን ውሳኔ ማየት ይጠቅማል፡፡ ይዘቱ በተመለከተ በአጭሩ ለማቅረብ ተከሳሽ የግል ተበዳይ በእጇ ይዛው የነበረውን ቦርሳ ለመቀማት እንዲመቸው እጇን አጥብቆ በመያዝ ሲታገላት ቦርሷን መሬት ላይ እንድትጥል ያደረገና እሷን መሬት ላይ በመጣል ንብረቷን መውሰዱ በፍሬ ነገር ደረጃ ተረጋግጧል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጥፋተኛው የግል ተበዳይን እጅ በመያዝ የያዘችው ንብረት እንድትሰጠው ወይም እንድትጥለው በማድረግ ወይም ለመቀማት በሚመቸው መልኩ ተዘጋጅቶ ንብረቱን በመውሰዱ ወንጀሉ የሚቋቋመው በወንጀል ሕግ አንቀፅ 670 በተመለከተው የውንብድና ወንጀል ሳይሆን በአንቀፅ 713 መሰረት በአስገድዶ መጠቀም ወንጀል ነው በማለት ግልፅ የሆነ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ውሳኔ መረዳት የሚቻለው ምንም እንኳን ተከሳሹ የተጠቀመው ኃይል የውንብድና ማቋቋሚያ ፍሬ ነገር የሚያሟላ መሆኑን ፀኃፊው ቢያምንም በሌላ በኩል ግን አስገድዶ መጠቀም ወንጀል የሚፈፀመው የግል ተበዳዩ በደረሰበት ዛቻና የኃይል ተግባር ምክንያት ንብረቱን ፈልጎ መስጠት ብቻ ሳይሆን በኃይል ሲወሰድበትና ሲቀማ እንደሚያጠቃልልም ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከሰጠው ውሳኔ መገንዘብ የሚቻል ነው፡፡

  • ሌሎች አንቀፆች ስለ አስገድዶ መጠቀም /መንጠቅ የሚሰጡት ፍንጭ አለ ወይ?

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ሕግ መተርጎም ያለበት ድንጋጌው ሊያሳካው ከፈለገው ውጤትና ከአጠቃላይ የህጉን ዓላማ ታሳቢ በማድረግ እንጂ ከአረፍተ ነገሩ አንድ ቃል እየተቀነጨበ በመውሰድ መሆን የለበትም፡፡ በሌላ አገላለጽ የአንድ ቃል ትርጉም እና በድንጋጌው ላይ የገባበት አላማ ለማወቅ ከቃሉ በፊት ወይም ከቃሉ በኃላ ባሉ ቃላት እና ቃሉ በአረፍተ ነገሩ ውስጥ ካለው ቦታ አያይዘን መተርጎም ይጠበቅብናል፡፡ እውቁ የሕግ ሙሁር ጸሃይ ወዳ የወንጀል ሕግ መሰረታዊ መርሆዎች በሚል መጽሃፋቸው ላይ እንዳሰፈሩትም ትርጉም የሚያስፈልገው የሕግ ቃል መኖሩን ከታወቀ የቃሉ ትርጉም አብሮውት ካሉት ቃላት እና አረፍተ ነገር መፈለግ ይኖርበታል ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ቃሉ በህጉ ሌሎች አንቀፆች የሚገኝ ከሆነ ይኸው ቃል በነዚህ ሌሎች አንቀጾች እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ በማመሳከር የቃሉ ፍቺ ማወቅ እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ አይነት የአተረጓጎም ስልት በማመሰካከር መተርጎም ይባላል፡፡

 ስለሆነም በወንጀል ህጋችን የእንግሊዘኛው እና የአማርኛው ቨርዥን ላይ የተደነገጉ የተለያዩ አንቀጾችን ማንሳትና ማየት የወንጀል ህጉን አንቀፅ 713 ን በተገቢው ሁኔታ በመተርጎም ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አላቸው ብዪ ስለማምን እንደሚከተለው ይዳሰሳሉ፡፡ ይኸውም በኢፌድሪ የወንጀል ሕግ የእንግሊዘኛው ቨርዥን ከአንቀፅ 713 ውጭ በሁለት ቦታዎች ላይ Extortion የሚል ቃል የሚገኝ ሲሆን ይህ ቃል በአማርኛው ቨርዥን ላይ ሁለት የተለያዩ ትርጉሞች ሰጥቶት እናገኘዋለን፡፡ እነሱንም መንጠቅ እና ቅሚያ የሚሉ ናቸው፡፡

) አንቀፅ 664(መንጠቅ የሚል ቃል ይገኛል)

አንቀፅ- 664(አማርኛ ቨርዥን)

  • እንደ ውንብድና ፣ መንጠቅ ወይም ማስፈራራት ከመሳሰሉ በኃይል ወይም በማስገደድ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች በስተቀር ሌሎች ወንጀሎች የተደረጉት በቤተዘመድ መካከል እንደሆነ ክሱ የሚታየው በግል አቤቱታ አቅራቡነት ብቻ ይሆናል( ቤተዘመድ ምን ያካትታል የሚል በንኡስ አንቀፅ ‘ሀ’ እና ‘ለ’ በዝርዝር ተቀምጠዋል)

Article-664 (English version)

  • Except in the cases of crimes involving violence or coercion,such as robbery, extortion, or blackmail, where a crime has been committed between relatives. (people who are considered as relatives are described in sub article ‘A’ and ‘B’)

Proccedings may only be taken upon the complaint of the victim.

በዚሁ አንቀፅ መሰረት መደበኛ የሆነ የስርቆት ተግባሩ የተፈፀመው በቤተ ዘመድ መካከል እንደሆነ በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ ያስቀጣል፡፡ በቤተዘመድ መካካል ሆኖ ወንጀሉ ውንብድና፣ መንጠቅ ወይም መስፈራራት እና መሰል ወንጀሎች ከሆኑ የመንግስት ክስ ነው፡፡ ውንብድና( Robbery) የሚለው አንቀፅ 670 ን ሲያመለክት ማስፈራራት(Blackmail) የሚለውም አንቀፅ 714 ን እያሳየ መሆኑን ግልፅ ነው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ መሰረት መንጠቅ ወይም “extortion” የሚል ቃል የትኛውን ድንጋጌ እየጠቆመ ነው የሚለው ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ይህ ድንጋጌ ከወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 ውጪ በሌላ ቦታ ፈፅሞ ሊገኝ አይችልም፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 664 ይዘትና መንፈስ በቀላሉ መረዳት ይቻል ዘንድ አንድ ምሳሌ ልጠቀም፡፡ ልጅ ከእናቱ ሞባይል ስልክ ቢቀማ ይህ ተግባር ስርቆት ሳይሆን አስገድዶ መጠቀም(Extortion) ነው፤ ይህን ድርጊት ደግሞ በአንቀፅ 665 ሳይሆን አስገድዶ መጠቀም በሚል በአንቀፅ 713 ነው የሚሸፈነው የሚል መልእክት እያሰተላለፈ ነው፡፡ በዚሁ አንቀፅና ምሳሌ መሰረት ልጅ ከእናቱ ሞባይል ስልክ የወሰደው ከተቀመጠበት ቦታ አንስቶ ከሆነ እናት ክስ ከመሰረተች በኃላ ከልጇ ጋር እርቅ ብትፈልግ ክሱን ማንሳት ትችላለች፤ ምክንያቱም ክሱ የሚቀጥለው በእናትዬው የግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ መሆኑን በወንጀል ህጉ አንቀፅ 664 ስር በግልፅ ተመልክቷልና፡፡ ልጅ የእናቱን ስልክ የወሰደው ቀምቶ ወይም ነጥቆ ከሆነ ግን ክሱን የሚቀጥለው በግል አቤቱታ አቅራቢነት ወይም በእናትዬው መልካም ፈቃድ መሆኑን ቀርቶ በመንግስት ወይም በወንጀል ክስ አቅራቢነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእርቅ መነሳት የማይችል የወንጀል ተግባር መሆኑን ይኸው በአንቀፅ 664 በልዩ ሁኔታ በግልፅ ተደንግጓል( በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ የወንጀል ድርጊቶች ሁሉም በእርቅ መነሳት ይችላሉ፣ በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስከስሱ የወንጀል ተግባራት ግን በእርቅ መነሳት አይችሉም የሚል መርህ እናስታውስ)፡፡ ክሱን የሚቀርበውም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 665 መሰረት በስርቆት ወንጀል ሳይሆን በወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 መሰረት በአስገድዶ መጠቀም ወይም በ Extortion ወንጀል ነው፡፡ (አንቀፅ 664 የአማርኛውና የእንግሊዘኛው ቅጂ ከአንቀፅ 713 አንፃር በደንብ ይመልከቱ)

) አንቀጽ 683(3) (ቅሚያ የሚል ቃል ይገኛል)

አንቀፅ 683- አማርኛ ቨርዠን

ቅጣቱ የሚከብደው(ቅጣት ተቀምጧል) ተከሳሹ ንብረቱን የሸሸገው የውንብድና፣ የዘረፋ፣ የባህር ውንብድና፣  የቅሚያ፣ የማስፈራራት ፍሬ መሆኑን ወይም እቃው የተገኘው ከመከላኪያ ሰራዊት ንብረት ወይም በጠቅላላው ከመንግስት ሀብት ውስጥ መሆኑን እወቀ እንደሆነ ነው፡፡

Article 683- English version

Punishment will be aggravated, (ቅጣት ተቀምጧል) Where the criminal

(C) Receives objects which he knows come from acts of robbery, looting, piracy, extortion, blackmail, or objects taken from the defence forces or from state property in general.

በዚሁ አንቀፅ መሰረት የውንብድና ወንጀል(Robbery)፣ የዘረፋ ወንጀል(looting)፣ የባህር ውንብድና ወንጀል(piracy)፣  የማስፈራራት ወንጀል(blackmail) እየጠቆሙት ያሉት አንቀፆችን በተከታታይ አንቀፅ 670፣ 672፣ 673 እና 714 መሆኑን ግልፅና ምንም አይነት ክርክር የማያስነሳ ነው፡፡ ታድያ በዚሁ አንቀፅ መሰረት ቅሚያ(Extortion) የሚል ቃልስ የትኛውን የወንጀል ሕግ ድንጋጌ ነው እያሳየ ያለው የሚለውን ጥያቄ በግልጽ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት “Extortion” የሚል ቃል ከወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 ውጪ በሌላ ድንጋጌ አይገኝም፡፡ ቅሚያ የሚል ቃልም አስገድዶ መጠቀም ከሚል ቃል ጋር በተቀያያሪነት የሚያገለግል ይመስላል፡፡ ስለሆነም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 683(ሐ) ስር የሰፈረው ቅሚያ ወይም “Extortion”የሚል ቃል የወንጀል ህጉ አንቀፅ 713 ን እየጠቆመ መሆኑን ግልፅ ነው፡፡

መደምደሚያ

ስርቆት፣ በማስገደድ መጠቀምና የወንብድና ወንጀሎች የሚመሳሰሉበት ምክንያት ሁሉም ከተጎጂው መልካም ፈቃድና ፍላጎት ውጪ በንብረት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሲሆኑ የሚፈጸሙበት መንገድ ግን የተለያየና የየራሳቸውን ባህርይና የአፈፃፀም ዘዴ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ቅሚያ፣ መንጠቅ ወይም “Extortion” ራሱን የቻለ ወንጀል እንጂ ስርቆትም ውንብድናም ሊሆን እንደማይችል ከወንጀል ህጉ አንቀፅ 664፣ 683፣ 670፣ 665 እና 713 ድንጋጌዎች ይዘት፣ መንፈስ እና አላማ በማገናዘብ መረዳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም አንድ አሻሚ ትርጉም ያለውን ቃል በአውዱ ውስጥና በህጉ ሌሎች ድንጋጌዎች ላይ ጥቅም ላይ የዋለበትን አግባብ እና ያለውን ትርጉም መሰረት በማድረግ መተርጎም የሕግ አተረጓጎም አንድ ዘዴ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ በማስገደድ መጠቀም የሚል ቃል በተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎች በአማርኛ የተጻፈበትና በእንግሊዝኛ የተተረጎመበት መንገድ በማገናዘብ የአንቀጽ 713 ትርጉም መወሰን አግባብነት ያለው የሕግ ትርጉም ዘዴ ነው፡፡

Read 8519 times Last modified on Aug 31 2019
ገብረእግዚአብሔር ወልደገብርኤል

ጸሐፊው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ በስልክ ቁጥር -0914505008, 0947931110 ወይም ኢ-ሜይል wgebregziher@gmail.com ሊያገኟቸው ይችላሉ፡፡