Print this page

አራጣ /Usury/ እና መዘዙ

Dec 31 2018

 

አራጣ የሰዉ ልጅን የግብይት ታርክ በቅርበት ተከትሎ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በዘርፉ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፍ ያበረከቱ ምሁራንም ቢሆኑ አራጣ ከአራት ሺህ አመት ያላነሰ ታርክ እንዳለዉ በመግለጽ የቅርብ ግዜ ክስተት እንዳልሆነ ደጋፊ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ ስለ ታርካዊ አመጣጡ ይህንን ካልኩኝ ወደ ዋናዉ የጽሁፉ አላማ ማለትም የአራጣን ምንነት፣ የሚያስከትለዉን የወንጀል ሃላፊነት/ተጠያቂነት፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ አንዲሁም በሀገር እኮኖሚ ላይ የሚያስከትለዉን ጉዳት ለአንባቢያን ግንዛቤ ማስጨበጥ በመሆኑ ያንኑን እንደሚከተለዉ በዝርዝር እናያለን፡፡

አራጣ በተለያዩ ሀገራት ሕግጋት እና በተለያዩ የሙያ መስክ ባሉ ምሁራን በተጻፉ መጻህፍት ላይ የተለያዩ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በሀገራችን ሕግ አራጣ ያለዉን ቦታ ከስር በጥልቀት የሚናየዉ ቢሆንም በመደበኛዉ አረዳድ ግን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባሳተመዉ የአማርኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት በገጽ 312 ላይ አራጣ ማለት ‘’ከፍተኛ የገንዘብ ብድር ወለድ’’ ነዉ በማለት ጠቅለል ያለ ትርጉም መስጠቱን እንመለከታለን፡፡ 

የሆነዉ ሆኖ ለዚህ ጽሁፍ አላማ ብቻ ሲባል አብዛኛዎቹ የአራጣ ትርጉሞች በዉስጣቸዉ ከያዙዋቸዉ ፍሬ ነገሮች በመነሳት ተግባሩን ‘’በህግ ወይም ተቀባይነት ባለዉ ልማድ ከተፈቀደዉ በላይ በሆነ የወለድ ምጣኔ ገንዘብ ማበደር ነዉ’’ ብለን በአጭሩ መተርጎም እንችላለን፡፡

 

እዉን የአራጣ ተግባር የተወገዘ ነዉን ?

ለአንድ ተግባር ተቀባይነት ወይም ዉጉዝ መሆን በርካታ ግላዊ /Subjective Standard/ እና ዉጪያዊ /Objective Standard/ መመዘኛዎች ያሉ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ከሞራላዊ፣ አመክንዮአዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ሕጋዊ መመዘኛዎች የሚያልፉ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአራጣ ተግባር በበርካታ አከባቢዎች በተለይም በገጠራማዉ አከባቢ የተስፋፋ ቢሆንም ከላይ በተዘረዘሩት መስፈርቶች በአብዛኛዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸዉ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

በአለማችን ላይ በርካታ ተከታይ እና ታርክ ካሉዋቸዉ ሀይማኖቶች ዉስጥ በአይሁዳዉያን እምነት አራጣ ማበደር ከአይሁዳዊያን ወገኖቻቸዉ ዉጪ ላሉት ባዕዳን ከሚፈቅደዉ ዉጪ ሌሎቹ ታላላቅ ሀይማኖቶች ማለትም በክርስትና፣ በእስልምና፣ በቡዲዚም እና በሕንዱይዝም የሐይማኖት ተቋማት አስተምሮ አራጣ ማበደር የተከለከለ ነዉ፡፡ በክርስትናዉ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሐይማኖት ምንጭ በሆነዉ በቅዱሱ መጽሀፍ ከስልሳ ጊዜ በላይ የአራጣ ተግባር ተኮንኗል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በእስልምናዉ ሀይማኖት ጭራሹኑን የወለድ ምጣኔዉ ከግምት ሳይገባ ከተቀማጭ ገንዘብ ትርፍ/ወለድ መቀበል የተከለከለ እንደሆነ እናዉቃለን፡፡

ከሞራል አንጻርም ጉዳዩን ብንመዝነዉ አብዛኛዉን ግዜ የአራጣ ብድር ሰለባ የሆኑት በአስቸኳይ ሁኔታ የሚደርስላቸዉን ገንዘብ የሚፈልጉ እና በከፍተኛ ሁኔታ የገንዘብ ችግር ላይ ያሉ ሰዎች በመሆናቸዉ ማናቸዉን ዋጋ ከፍለዉ ገንዘብ ከማግኘት ወደኋላ የማይመለሱ ግለሰቦች ናቸዉ፡፡ በመሆኑም ገንዘብ አቅራቢ/አራጣ አበዳሪዎች የሚወስኑትን የወለድ ምጣኔ ላይ ድርድር በማድረግ ለማስቀነስ ሁኔታዉ የማይፈቅድላቸዉ በመሆኑ ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለተወሰነ የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብሎ የሌላዉን ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ህይወት፣ የቤተሰብ ህልዉና አደጋ ላይ መጣል በየትኛዉም የሞራል መመዘኛ ቢታይ ተቀባይነት ያለዉ ተግባር አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ እርዳታ የሚፈልገዉን ሰዉ ለመጠቀሚያነት ማመቻቸት በተገለጸዉ ሁኔታ የሞራል ልዕልናን የሚጋፋ ተግባር መሆኑ እሙን ነዉ፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ አራጣን ከአመክንዮአዊ /Logical/ አሰራር ሆነ አስተሳሰብ አንጻር ብናየዉ ድጋፍ ያለዉ ተግባር አይደለም፡፡ ምክንያቱም የወለድ ፅንሰ ሀሳብ አበዳሪው ገንዘቡን ቢጠቀምበት ሊያገኝ የሚችለውን የኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ከዚያ ዉጪ ሰርቶ ሊያገኝ ከሚችለዉ በላይ መጠየቅ አመክንዮአዊ ትርፍ አይሆንም፡፡ ከአራጣ የሚገኝ ትርፍ ያልተደከመበት፣ ፍትሀዊ ያልሆነ እንዲሁም በሌላ ግለሰብ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ የሚያሳድር በመሆኑ አራጣ አበዳሪዉን የሚያኮራ እና የድካሙን ዋጋ እንዳገኘ የሚያስቆጥር ትርፍ አይደለም፡፡

በመጨረሻም አራጣ ብድር ከወንጀል ሕጋችን አንጻር ሲታይ እንደአብዛኛዎቹ ሀገራት የአራጣ አበዳሪነት ተግባር የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በወንጀል ሕጋችን አንቀጽ 712 ላይ “ማንም ሰዉ የተበዳዩን ችግረኛነት፣ የበታችነቱን፣ ወይም የገንዘብ ችግሩን ወይም መንፈሰ ደካማነቱን ወይም ልምድ ወይም ችሎታ የሌለዉ መሆኑን መሰረት በማድረግ በሕግ ከተፈቀደዉ ወለድ በላይ ገንዘብ ያበደረዉ እንደሆነ ወይም ካበደረዉ ገንዘብ ጋር በግልጽ ተመጣጣኝነት የሌለዉን ንብረት በምትኩ እንዲሰጠዉ ያደረገ ወይም ቃል ያስገባዉ እንደሆነ ……. በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና በመቀጮ ይቀጣል፡፡” በማለት ይደነግጋል፡፡

ከወንጀል ሕጉ ድንጋጌ አንጻር አበዳሪዉን በወንጀል ለማስቀጣት መሟላት ያለባቸዉ ሁለት አበይት ፍሬ ነገሮችን /Elements of the Provision/ አሉ፡፡ የመጀመርያዉ የተበዳሪዉ የገንዘብ ችግር፣ የግንዛቤ ደረጃ እና መሰል የመደራደር አቅሙን የሚያሳጡ ዉስጣዊና/ዉጪያዊ ምክንያቶች ሲሆኑ ሌላኛዉ ደግሞ በሕግ ከተፈቀደዉ የወለድ ምጣኔ በላይ ተቀብሎ ማበደር ናቸዉ፡፡ በሕግ የተፈቀደዉ የወለድ ምጣኔ ማለት በወንጀል ሕጉ ላይ ባይቀመጥም በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2479 ላይ እንደዉሉ ሁኔታ በአመት ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለት በመቶ የሚደርስ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከላይ የተገለጸዉ የድንጋገዉ የመጀመሪያዉ ፍሬ ጉዳይ ማለትም በወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 712 (1) የተገለጸዉ የተበዳሪዉ የግል እና ዉስጣዊ ምክንያት ሀሳቡ ግልጽ ቢሆንም በአብዛኛዉ የፍርድ ቤት ዉሳኔዎች ላይ የምንመለከተዉ ግን ሕጉ በተገቢዉ ሁኔታ እየተተረጎመ ነዉ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡

ምክንያቱም የሕጉ አቀራረጽ በግልጽ የሚያሳየዉ በሕግ ከተቀመጠዉ የወለድ ምጣኔ በላይ በመቀበል ገንዘብ ማበደር ብቻዉን የአራጣ ተግባር እንደተፈጸመ የማያስቆጥር እና በተጨማሪነት አበዳሪዉ የተበዳሪዉን የገንዘብ ችግር፣ የመንፈስ ደካማነት፣ የልምድ እና አነስተኛ ግንዛቤዉን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ተግባሩን የፈጸመ መሆኑ መረጋገጥ ያለበት መሆኑን ነዉ፡፡

ሆኖም ግን በአሁኑ ሰዓት በፍርድ ቤቶቻችን በተጨማጭ እየታየ ያለዉ የአበዳሪዉ ከላይ የተገለጹት ዉስጣዊ ምክንያቶች ከግምት ሳይገቡ የወለድ ምጣኔዉ በሕግ ከተቀመጠዉ በላይ ብቻ መሆኑን ካረጋገጡ አበዳሪዉን በአራጣ አበዳሪነት ከመቅጣት ወደ ኋላ የማይሉ መሆኑን ጸሃፊዉ ለዚህ ጽሁፍ ሲል ባደረገዉ መጠነኛ ጥናት አረጋግጧል፡፡ ይህ ሁኔታ በአፋጣኝ ማስተካከያ ካልተደረገበት የሕግ ክልከላዉን አላማ ከግብ እንዳይደርስ ከማሰናከሉም ባሻገር በተደጋጋሚ ጊዜ በፍርድ ቤቶቻችን የሚሰጡ የሕግ ትርጉሞች ተቀባይነት እና ተአማኒነት እንዳይኖራቸዉ አሉታዊ ሚና የሚኖረዉ መሆኑን በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡

ከላይ የተገለጸዉ በፍርድ ቤቶቻችን የሚታየዉ የሕግ አተረጓጎም እንዳለ ሆኖ የአራጣ ማበደሪያ መንገዶች ሕጋዊዉን ተግባራት በማስመሰል የሚፈጸሙ እና ተበዳሪዎቹም አብዛኛዉን ግዜ ጉዳዩን በተለያዩ ምክንያት የማያጋልጡ በመሆኑ ከሚፈጸመዉ ወንጀል አንጻር ጥፋተኞቹን ለሕግ በማቅረብ እና በወንጀል በማስቀጣት የተገኘ ዉጤት እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ አብዛኛዉን ጊዜ አራጣ አበዳሪዎች ተግባሩን ለመፈጸም ከሚጠቀሙት መንገዶች ዉስጥ ተግባሩ በብድር መልክ ሆኖ አራጣ አበዳሪዉ ለተበዳሪዉ ከሰጠዉ የገንዘብ መጠን በላይ እንዳበደረ አድርጎ ማስፈረም፣ አበዳሪዉ በብድር ከሰጠዉ የገንዘብ መጠን በላይ የሆነ የገንዘብ መጠን በቼክ ላይ አስጽፎ መቀበል እና ከብድር ገንዘብ በላይ ዋጋ ያለዉን ንብረት በመረከብ ገንዘቡ በወቅቱ ባይመለስና ቢዘገይ በአዳሪዉ የንብረቱን ስሜ ሀብት በራሱ ስም ማዛወር እንዲችል በማድረግ መዋዋል እና የመሳሰሉት የሚዘወተሩ ዘዴዎቻቸዉ ናቸዉ፡፡ አበዳሪዎች እነዚህን የማበደር ዘዴዎችን በልምድ እና በንባብ ባዳበሩት እዉቀት በመጠቀም የሚከዉኑት በመሆኑ ከህግ ተጠያቅነት የማምለጥ ዕድላቸዉ በጣም ከፍተኛ ነዉ፡፡ በመሆኑም የአራጣ ተግባር ዉስጥ ለዉስጥ እየተስፋፋ ከፍተኛ ጉዳት እደረሰ መሆኑን ጸሃፊዉ ያምናል፡፡ ጉዳቱን ከአባዳሪዉ አንጻር ስናየዉ ተግባሩ ወንጀል በመሆኑ ጥፋተኝነቱ ሲረጋጥ አበዳሪዉ ከመደበኛዉ ስራዉ እና ህይወቱ ተገልሎ በርካታ አመታትን በእስር ለማሳልፍ የሚገደድ በመሆኑ ዉጤቱ በቤተሰቡ፣ በራሱ እና በጥገኞቹ እና በእርሱ በሚረዱት ሰዎች ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ከተበዳሪም አንጻር ስንመለከት አራጣ በሚበደርበት ወቅት በአፋጣኝ ገንዘቡን ለማግኘት የሚፈልግ በመሆኑ ከፍተኛዉን የወለድ ሚጣኔ ተደራድሮ ለማስቀነስ የሚያዳግተዉ በመሆኑ ሰርቶበት ሆነ ችግሩን ተወጥቶ ብድሩን መመለስ የሚያዳግተዉ በመሆኑ ቋሚ ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረቱን/ጥሪቱን ሰብስቦ ለአበዳሪዉ በመስጠት ጎዳና ላይ የመዉጣት እድሉ ሰፊ ነዉ፡፡ በስራ ላይም ቢሆን አራጣ በአዳሪዎች አብዛኛዉን ጊዜ የሚሰሩት ትርፋቸዉን ሰብስበዉ ንብረት ለማፍራት ሳይሆን ዕዳቸዉን ለመክፈል መሆኑን በብዙ አጋጣሚዎች ታዝበናል፡፡ ከላይ በአበዳሪዉ ላይ እናዳየዉ የአራጣ ተግባር ዉጤቱ በሌሎች ሰዎች ላይ ጭምር አሉታዊ ተጽእኖ የሚኖረዉ መሆኑ ግልጽ ነዉ፡፡ በዚህ ሁኔታ በአራጣ አበዳሪ እና ተበዳሪ ላይ የሚደርሰዉ ጉዳት በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁኔታ በጠቅላላዉ ማህበረሰቡ ላይ ከሚያደርሰዉ ተጽእኖ አልፎ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ በመሆኑም ማንም ሰዉ ከአራጣ ተግባር እንዲታቀብ ጸሀፊዉ ምክሩን ይለግሳል፡፡

ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀዉ ለሕግ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን በሳምንታዊዉ የስንቅ መጽሔት ላይ የሁሉንም አንባቢ የሕግ እዉቀት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

 

Read 8485 times Last modified on Dec 31 2018
Melkamu Ogo

ጸሐፊዉ በፌዴራል ማናቸዉም ደረጃ ፍርድ ቤት የሕግ አማካሪ  እና ጠበቃ  በመሆን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡  ጸሐፊን በስልክ +251 911 02 71 03 ወይም በኢ.ሜይል E-Mail - andiracha16@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡