የሚራንዳ መብት (Miranda Right) እና ያለመናገር መብት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ: ሕጉና ተፈፃሚነቱ

Dec 06 2018

 

መግቢያ

በአንድ ወንጀል የተጠረጠረ ከዛም የተከሰስ ግለሰብ በሕግ ከለላ ሥር ከዋለበት ግዜ ጀምሮ ሊገለገልበት የሚጋባው የተለያዩ መብቶች አሉት። ያለ መናገር መብት፣ በእራስ ላይ ምስክር ሆኖ እራስን ያለመወንጀል መብት እና የሕግ አማካሪ ጠበቃ የማግኘት መብት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

አንድ ተርጠርጣሪ ያለመናገር መብት እንዳለውና የሚሰጠው ቃልም እንደማስረጃነት ሊቀርብበት እንደሚችል በሚገባው ቋንቋ የማሳወቅ ግዴታ በሕግ ከለላ ሥር የሚያውለው አካል ሲሆን፣ ይህ መብት በሌሎች ሃገር የሕግ ማዕቀፍ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ፅንሰ ሃሳብ ነው። ይህ በተለምዶው የMiranda  Warning በመባል የሚታወቀው መብት መብቱ እንደ አግባብነቱ በሥራ ላይ ካልዋለ በፍርድ ቤት የሚቀርበውን የተጠርጣሪ ቃል ማስረጃ ውድቅ የማድረግ አቅም አለው።

ይህ መብት በሃገራችን የወንጀል ሕግ ማዕቀፍ አለ? መችና እንዴት ተፈፃሚ ይሆናል ? መብቱ በአግባቡ ተፈፃሚ መሆኑንስ ማን ክትትል ይደርጋል? የMiranda መብት በኢትዮጵያ ሕግ ምን ይመስላል? ተፈፃሚነቱና አተገባበሩስ?

1. ያለ መናገር መብት (The right to remain silent)

አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ካሉት ወሳኝ መሠረታዊ መብቶች ውስጥ ያለመናገር መብት ቀዳሚው ነው።

ያለመናገር መብት ወይም the right to remain silent የምንለው አንድ ግለሰብ  በተጠረጠረበት የወንጀል ጉዳይ ቃል ወይም መልስ ያለመስጠት መብቱ የሚከበርበትና በጉዳዩ ላይ ቃል እንዲሰጥ በማናቸውም ሁኔታ የማይገደድበት ሁኔታ ነው። ይህ መብት "እራስን ያለመወንጀል" ከሚለው ሌላኛው የተጠርጣሪ መሠረታዊ መብት ጋር ሳይነጣጠል ሊታይ የሚገባ ሲሆን፣ አንድ ተጠርጣሪ በማናቸውም ሁኔታ በማወቅ ወይም ባለማወቅ ያለ ፈቃዱ እራሱን እንዲወነጅል ሊደረግ ወይም ሊገደድ እንዳማይገባ የሚከለክል የሕግ ድንጋጌ ነው። ይህ መብት በመሠረታዊ ደረጃ ተጠርጣሪውን በማስፈራራት፣ አካል ላይ ጉዳት በማድረስ አልያም ሕግን ካልተከተለ የምርመራ ሂደት የሚገኝ የተጠርጣሪ ቃልን ውድቅ የማድረግ ትልቅ አቅም አለው።

በአሜሪካው ሕገ መንግሥት ላይ የተደረገውን 5ኛ ማሻሻያ የያዘው ይህ ፅንሰ ሃሳብ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ተጠርጣሪ በተጠረጠረበት የወንጀል ጉዳይ ላይ እራሱን መወንጀል ወይም ደግሞ በራሱ ላይ እንዲመሰክር ማስገደድ እንደማይቻል ( No person shall be compelled in any criminal case to be witness against himself) የሚያሳሳብ ነው። ይህም ከሳሽ አቃቢ ሕግ የተጠርጣሪን ፍላጎት መሠረት ካላደረገ ማስረጃዎች ተላቆ ክሱን ሊደግፍ በሚችል ሌላ ማስረጃ ላይ ብቻ በመመርኮዝ ተጠርጣሪው ወንጀለኛ መሆኑን ማስረዳት እንደሚጠበቅበት የሚያስረዳ በምርመራ ሂደት ውስጥ አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ እጅግ አስፈላጊ የሆነ መብት ነው።

ይህ መብት በዋናነት አንድ ተጠርጣሪ በሕግ ከለላ ሥር ከዋለበት ስዓት ጀምሮ ተፈፃሚ የሚሆኑ ሲሆን፣ ተፈፀመ የተባለው ወንጀል በምርመራ ሂደት ውስጥ ፍርድ ቤት እስኪደርስ ድረስ ያለውን የምርመራ ሂደት (Pre trial) የሚያጠቃልል ነው።

በሃገራችን ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ በሕግ ከለላ ሥር ከዋለበት ሰዓት ጀምሮ ያለመናገር መብት እንዳላው የሰብዓዊ መብቶችን ዝርዝር ባቀፈው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ምዕራፍ 3፤ አንቀፅ 19(2) በግልፅ ተደንግጔል። ይህ መብት አንድ ሰው በወንጀል ከተጠረጠረበትና በቁጥጥር ሥር ከዋለበት ግዜ ጀምሮ ሊከበርለትና ይህ መብቱ በሚገባው ቋንቋ እንዲረዳ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አንቀፁ ያሳስባል። ከዚህ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 20(3) ላይ ከተቀመጠው አንድ ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ እራሱን ያለመወንጀል መብት ጋር በእጅጉ የሚዛመድና የማይነጣጠል መብት ነው።

2. የሚራንዳ መብት (Miranda Right)

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው የMiranda መብት በመባል የሚጣራው በMiranda Vs Arizona State ጉዳይ ላይ የአሜሪካው ፍርድ ቤት ውሳኔ ካስለፈበት ውሳኔ በመነሳት የተጀመረ ሲሆን ተጠርጣሪ ግለሰብ ያለመናገር መብት ያለውና በቁጥጥር ሥር ከዋለበት ግዜ ጀምሮ በሕግ ከለላ ሥራ ባለበት ወቅት የሚናገረው ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮች እንደ ተጠርጣሪ ቃል በማስረጃነት ተመዝግቦ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብበት አስቀድሞ ሊነገር እንደየሚገባው የሚያሳስብ መሠረታዊ መብት ነው። ይህ መብት በዋናነት ፓሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ሲያውለው ከዛም አልፎ በምርመራ ወቅት የተጠርጣሪውን ቃል ከመመዝገቡ በፊት አስቀድሞ ባለመብቱን ተጠርጣሪ በሚገባው ሁኔታ ሊያስረዳው እንደሚገባና ተጠርጣሪውም የሚናገረው ነገር እንደ ቃል ተመዝግቦ ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብበት እንደሚችል በመገንዘብ እራሱን ወንጀለኛ ሊያደርግ ከሚችሉ የትኛውም ዓይነት ሁኔታዎች እንዲቆጠብ ይረዳዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ልብ ሊባል የሚገባው ይህን መሸረታዊ መርህ ያልተከተለ የምርመራ ውጤት ዋጋ ቢስና ማስረጃው በሕግ አግባብነት ውጭ የተገኘ እንደመሆኑ መጠን በፍርድ ቤት ተቀባይነት የሌለውና ውድቅ  ( Inadmissible ) ይሆናል። ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ ግለሰቡን ደግሞ መክሰስ ስለማይቻልና Double Jeopardy ስለሚሆን በሌላ መንገድ በዚህ መንገድ በተፈፀመ ስህተት ወንጀል ፈፃሚዎች ከሕግ ተጠያቂነት የሚያስመልጥ ጥፋትም ይሆናል።

3. የሚራንዳ መብት እና ያለመናገር መብት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ (The legal frame work)

ይህ መብት በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በግልፅ ተደንግጎ የተቀመጠ ሲሆን ከሌሎች መሸረታዊ እላይ ከተጠቀሱ በሕግ ከለላ ሥር ካለ የተጠርጣሪ መብቶች ጋር የማይነጣጠል በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉት አንቀፆች መረዳት ይቻላል።

መሠረታዊ መብቶችን እና ነፃነቶችን ባቀፈው የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ 3 አንቀፅ 19(1) ማንኛውም የተያዘ ሰው ያለመናገር መብት ያለው እና የሚሰጠው ማንኛውም ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል መረዳት በሚችለው ቋንቋ በቁጥጥር ሥር እንደዋለ ሊነገረው እንደሚገባ ይደነግጋል። 

ይህ አንቀፅ እላይ ካነሳናቸው መብቶች በተጨማሪ በአንቀፅ 20(3) ተጠርጣሪው በወንጀለኛነት  እራሱ ላይ ምስክር ያለመሆን መብቱን በአፅንዖት የሚያስገነዝብ ነው።

ከዚህ ከተጨማሪ ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ እንደሚያስቀምጠው ተጠርጣሪው በሕግ ከለላ በዋለበት ወቅት ያለመናገር መብት እንዳለውና የሚሰጠው ማንውኛም ቃል እንደ ማስረጃትነ እንደሚቀርብበት ቢደነግግም የወንጀል ሕጉ ስነሥርዓት አንቀፅ 27(2) በምርመራ ወቅት ብቻ የሚመለከት እንደሆነ ነው ሚያስቀምጠው።

4. የሕጉ አተገባበር (The practice)

የMiranda መብት መከበሩን ሊከታቱሉ የሚገቡት በዋናነት መርማሪ ፓሊሱና አቃቢ ሕግ ሲሆኑ ተጠርጣሪው በሕግ ከለላ ሥር ከዋለበት ግዜ ጀምሮ ይህ መብት መጠብቁን የመከታተል ግዴታ እንዳለባቸው ሕገ መንግሥቱ ያሳስባል።

ይሁን እንጂ በሃገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ የተካተተው ይህ ዋና መብት ባብዛኛው ሲተገበር አይስተዋልም። ፓሊስ ተጠርጣሪን ከያዘበት ግዜ አንስቶ ይህ መብት ተጠርጣሪው እንዳለው ካለማሳሰብ በተጨማሪ ፓሊስ ጋር የዚህ መብት ግንዛቤ በጥልቀት ስለመኖሩ አጠራጣሪ ነው።

ግለሰቦች በሕግ ከለላ ሥር ከዋሉ በኋላ በምርመራ ሂደት የሚሰጡት ቃል በማስረጃነት እንደሚቀርብባቸው በምርመራ ወቅት የማስገንዘቡም ሁኔታ እዚህ ግባ የማይባል ስለመሆኑ ፍርድ ቤት ላይ ከሚቀርቡ ተደግጋሚ የተከሳሽ ቅሬታዎች መረዳት ይቻላል። የMiranda መብት በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 19(2) በሕግ ከለላ የሚያውለው አካል ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር በሚያውለው ወቅት ያለመናገር መብት እንዳለውና የሚሰጠው ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት እንደሚቀርብበት ሊረዳው በሚችለው ቋንቋ እንዲያስገነዝበው ቢደነግግም ፓሊስ እኚህ ነገሮች ሲተላለፍ ማየት የተለመደ ነው።

5. መደምደሚያ

የMiranda መብት መሠረታዊና የተጠረጠረን ግለሰብ ካለው ያለ መናገርና እራስን ያለመወንጀል መብት ጋር ተለይቶ ሊታይ የማይችል መብት ከመሆኑ አንፃር ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ይህ መብት ግለሰቡ መብቱን እንዲጠቀም የሚያደርግና የወንጀል ምርመራውም የሕግ አግባብ በተከተለ ማስረጃ የሚደገፍ ስለሚሆን ይህን መብት መሠረት ካደረገ ምርምራ የሚገኝ ማስረጃ የተሳካ የፍትሕ አስጠጣን የሚያሰፍን ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የወንጀለ ምርመራ የሰው ኃይልና የማይናቅ ኃብት የሚያስወጣ ከመሆኑ አንፃር ይህን መርህ ባልተከተለ የምርመራ ውጤት የሚባክነውን የሰው ሃይልና የሃብት ብክነት የሚቀነስ ከመሆኑ አንፃር በሕጉ አተገባበር ዙርያ ሊሠራበት ይገባል።    

 

 

 

Read 8560 times Last modified on Dec 06 2018
Yonas Alemayehu

The blogger is currently working as a Deputy General Director at Addis Ababa City Government Vital Events Registration Agency and as a Par-time Business Law Lecturer, Rift Valley University, Addis Ababa, Ethiopia. He can be reached at yalemayehuson@gmail.com.