Print this page

ፍትሕ የተነፈገው የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ገደብ - የፍርድ ቤቶች የተከሳሽን መብት የመጠበቅ ሥልጣን ሲፈተሽ

Oct 04 2018
  1. መግቢያ

በኢትዮጵያ የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የፍርድ ቤቶች ሚና የጎላ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በሕግ አውጭው አካል የሚወጡ ሕግጋትን ተረድተውና ተርጉመው ሕጉ የወጣለትን ግብ እንዲመታ የሚያስችል ውሳኔ የመስጠት ተፈጥሮዓዊ ሥልጣን አላቸው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች የተከሳሽ መብትን የሚያስጠብቁበት የተለያዩ የሕግ ሥርዓቶች ይገኛሉ፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰው በወንጀል ጉዳዮች ከሳሽ በመሆን የሚቀርበው ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ ሆኖ ከሚቀርበው ግለሰብ አንፃር የተሻለ እውቀት፤ ማስረጃ የማቅረብ ጉልበት እና በተያያዥ ነገሮች የበለጠ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ የሚፈጠረው የዓቅም አለመመጣጠን ለማጥበብ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ፍርድ ቤቶች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን የሚያስጠብቁበት አግባብ ብዙ ጥያቄዎችን እንደሚያሥነሳ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በዐቃቤ ሕግ ተከሰው የሚቀርቡ ተጠርጣሪ ግለሰቦች በፍርድ ቤቶች ተገቢን ሕጋዊ ጥበቃ ሳይሰጣቸው መታለፉን በተለያዩ አጋጣሚዎች ታዝበናል፡፡ በዚህ አጭር የዳሰሳ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ሕግ የተከሳሽን መብት ለማስጠበቅ የተቀመጡ የጊዜ ገደቦችን ለማየት ሙከራ ተደርጓል፡፡ በተለይ ከፖሊስ ምርመራ ጋር በተያያዘ የ14 ቀን የጊዜ ገደብ የተቀመጠበትን ዓለማና አተገባብሩን በይበልጥ ለማየት ተሞክሯል፡፡

  1. የተከሳሽ መብትን ለማስጠበቅ በሕጎቻችን ላይ የተቀመጡ የጊዜ ገደቦች

በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ከወንጀል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የተከሳሽ መብትን የሚመለከቱ ሕጎች ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ናቸው፡፡ በ1995 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት፤ በ1997 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ፤ በ1954 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግና በተለያየ ጊዜ የወንጀል ድንጋጌዎችን በመያዝ የወጡትን አዋጆች ያጠቃልላል፡፡ በአጠቃላይ አንድ በወንጀል ጉዳይ የተከሰሰ ግለሰብ መሰረታዊ የሆኑ መብቶች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት በግልፅ ተቀምጠዋል፡፡ የዚህ ፁሁፍ ዓለማ አይደለም እንጅ የተከሳሽ መብቶች በዝረዝር ድንጋጌዎች ማየት ይቻላል፡፡ የጉዳዩ አንኳር ወደ ሆነው ጉዳይ ስንገባ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 19 (3) ላይ እንደተቀመጠው የፍርድ ቤቶችና የተጠርጣሪዎች ግንኙነት የሚጀምረው ተጠርጣሪው በተጠረጠረበት ጉዳይ ምክንያት በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ በዋለ በ48 ሰዓት ውስጥ ነው፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህጋችን አንቀፅ 23 እና በተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት ፖሊስ በአንድ ግለሰብ ወንጀል መፈፀሙን ካወቀ ወይም ከጠረጠረ እስከ እስራት የሚደርስ እርምጃዎችን በመውሰድ የምርመራ ስራውን እንዲጀምር የሕግ ሥርዓት ተቀምጧል፡፡ ይሁን እንጅ ከላይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 19(3) ላይ እንደተመለከትነው እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 29 ላይ እንደተቀመጠው ፖሊስ ተጠርጣሪውን ግለሰብ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት የማቅረብ ሕጋዊ ግዴታ አለበት፡፡

በብዙ ሰዎች ዘንድ ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ውስጥ ካደረገው በኋላ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት መቅረብ አለበት ከሚለው መብት በዘለለ ፍ/ቤት ከቀረበ በኋላ የተከሳሹ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል የሚለውን ሁኔታ የፍርድ ቤቶችን የፍትሕ ምንጭነት ግምት በመውሰድ ጥያቄ ሲያነሱ አይታይም፡፡ ይሁን እንጅ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረቡ የአንድ ተከሳሽ መብቱ መጠበቅ ዋስትና ይሰጣል ወይ የሚለው ጥያቄ ከፍርድ ቤቶቻችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ጥያቄ የሚያሥነሳ ነው፡፡ ይሄንን ምላሽ ሊሰጥ በሚችል መልኩ ታሳቢ ተደርጎ የወጣ የሚመስለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 59 ለዚህ ጉዳይ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ አንቀፅ ንዑስ ቁጥር አንድ መሰረት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 29 እና በህገ መንግስቱ አንቀፅ 19(3) መሰረት ተጠርጣሪ የቀረበለት አንድ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪው በእስር መቆየት አለበት ወይስ የለበትም የሚል ውሳኔ እንዲሰጥ ሕጉ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ወሳኔ ላይ ከዋስትና ጋር የሚያያዙ  የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ድንጋጌዎችን (አንቀፅ 63 እና ተከታዮቹን) በመጠቀም ውሳኔ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡

ይሁን እንጅ ከዋስትና ጋር በተያያዘ ከተቀመጡ ድንጋጌዎችእና መስፈርቶች በመነሳት ዋስትና የተከለከለ ተጠርጣሪ ፖሊስ በአንቀፅ 59 ንዑስ ቁጥር 2 እና ሶስት እንዲሁም በህገ መንግስቱ አንቀጥ 19 (4) በተቀመጡት ድንጋጌዎች መሰረት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊጠይቅበት ይችላል፡፡ በሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 59 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ የተቀመጠውን ሁኔታ ስንመለከት ፖሊስ የሚያካሂደውን ምርመራ ካልጨረሰ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ በተከታዩ ንዑስ ቁጥር 3 ደግሞ ለምርመራ የሚሰጠው ጊዜ በአንድ ጊዜ ከአስራ አራት ቀን መብለጥ እንደሌለበት ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት በአንድ ወንጀል ጉዳይ ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት የቀረበ ግለሰብ ሁለት መሰረታዊ የጊዜ ገደብ መብቶች አሉት ማለት እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው መብት በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ በዋለ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍርድ ቤት ቀርቦ ዋስትና የሚከለከልበት አግባብ ካለ ለፖሊስ በአንድ ጊዜ የሚሰጠው የምርመራ ጊዜ ከ14 ቀን መብለጥ የለበትም የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ ድንጋጌዎች የአንድን ተከሳሽ መብት ለማስጠበቅ በቂ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ያሥነሳል፡፡ የጊዜ ገደቡ በሕግ የተቀመጠለትን ዓላማ እያሳካ ነው ወይ የሚሉትንና ተያያዥ ጉዳዮችን በቀጣዩ ክፍል እናያለን፡፡

  1. ፍትሕ የተነፈገው የ14 ቀን ገደብ

ከላይ ባየናቸው የጽሑፉ ክፍሎች እንደተረዳነው በወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ ያለ አንድ ግለሰብ መብቱን ለማስጠበቅ እንዲረዳ የተደነጉ የጊዜ ገደቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ ገደብ ተጠርጣሪው በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ በዋለ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅርብ ያለበት መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍርድ ቤት ቀርቦ የዋስትና መብቱ ከተከለከለ ለፖሊስ በአንድ ጊዜ የሚሰጠው የምርመራ ጊዜ 14 ቀን ብቻ መሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 59(3) ላይ የተቀመጠውን የ14 ቀን ገደብ ሊቀመጥ የቻለበትን ምክንያት ከተመለከትን እንደሚታወቀው  በፖሊስ ቁጥጥር ውስጥ የሚገኝ ግለሰብ ባልተረጋገጠ የወንጀል ጥርጣሬ ሕገ-መንግሥታዊ ነፃነቱን ተነፍጎ በእስር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ በሌላ በኩል ፖሊስ በቁጥጥር ውስጥ ያዋለው ግለሰብ ወንጀል መፈፀሙን የሚያምን ወይም የሚጠረጥር ሲሆን ተጠርጣሪው ከእስር ቢወጣ በምርመራው ሂደት ላይ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራት ሊፈፅም እንደሚችል አምኗል፡፡  በመሆኑም የአስራ አራት ቀን የጊዜ ገደብ የተቀመጠው በእነዚህ በሁለት ተፃራሪ የሆኑ የዐቃቤ ሕግና የተጠርጣሪ ፍላጎቶችን ለማስታረቅ ወይም ለማቀራረብ ነው፡፡

ይሁን እንጅ የተጠርጣሪን መብት ለማስጠበቅ የተቀመጠው የ14 ቀን የጊዜ ገደብ በተለያዩ ጊዚያት ፍትሕ ሲነፈገው ተመልክተናል፡፡ በአብዛኛው ዳኞች እና ዐቃቤ ሕጎች እንዲሁም ፖሊሶች የ14 ቀን የጊዜ ገደብ ለምን እንደተቀመጠ ባለመረዳትም ይሁን ለመረዳት ባለመፈለግ ለመቁጠር በሚያስቸግር ሁኔታ በአንድ ተጠርጣሪ ላይ እልፍ አላእፍ የአስራ አራት ቀን ቀጠሮዎች ሲሰጡ ማየት የተለመደ ነው፡፡ የአስራ አራት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ የሚሰጥ ከሆነ እና የአስራ አራት ቀን የጊዜ ገደቡ የሚሰጥበት አግባብ ምንም አይነት ገደብ ከሌለው ሕጉ የወጣለትን ዓላማ እያሳካ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ ጋር የሚስተዋለውን ችግር በሁለት መልኩ ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡  የመጀመሪያው እንደ ችግር የሚነሰው ከመጀመሪያው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በአንቀፅ 59(3) ገደቡን ሲያስቀምጥ ምንም አይነት መስፈርት ባለማስቀመጡ ነው፡፡ ይህ ማለት በዚህ ድንጋጌ ላይ እንደተቀመጠው አንድ ወደ ማረፊያ ቤት እንዲሄድ የተበየነበት ግለሰብ በእያንዳንዱ ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጠው ቀነ ገደብ 14 ቀን እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ከዚህ በግልፅ እንደምንረዳው ሕጉ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ፖሊስ በአንድ ጊዜ ከ14 ቀን በላይ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ እንደማይችል እንጅ በአጠቃላይ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የሚጠይቅበት ጣሪያ አያስቀምጥም፡፡ በመሆኑም አንድ መርማሪ በየአስራ አራት ቀኑ ምርመራ አልጨርስኩም እያለ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ በግልፅ በሕግ አውጪው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተብሎ የሚሰጠውን የ14 ቀን የጊዜ ገደብ መና የሚያስቀርና አላስፈላጊ ችግር ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለተኛው ችግር የፍርድ ቤቶቻችን የሕጉን ክፍተት ለመሙላት የሚያደርጉት ጥረት ደካማ መሆኑ ነው፡፡ ምንም እንኳ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 59 ላይ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት ምንም አይነት መስፈርት እንዳልተቀመጠ የተመለከትን ቢሆንም ከአጠቃላይ የሕግ መርሆች፤ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች እና በሥነ-ሥርዓት ሕጉ በተቀመጡ ሌሎች ድንጋጌዎችን መሰረት በማድረግ በሕጉ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል ሥልጣን ያላቸው ፍርድ ቤቶች በተደጋጋሚ ይሄንን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ያለምንም ገደብ ሲሰጡ እናያለን፡፡ በተለይ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 19(4) ለጉዳዩ ይበልጥ ጠቃሚ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት አንድ ፍርድ ቤት ፍትሕ እንዳይጓደል አንድን ተጠርጣሪ በጥበቃ ስር እንዲቆይ ካዘዘ ለምርመራ የሚሰጠው ተጨማሪ ጊዜ አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ መሆን እንደሚኖርበትና በተቻለ መጠን የተጠርጣሪውን በቶሎ ፍርድ የማግኘት መብቱን የሚጋፋ መሆን እንደማይኖርበት ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕጉ በአንቀፅ 37 ላይ በግልፅ እንደሚያስቀምጠው በፖሊስ የሚደረገው የምርመራ ሂደት አላስፈላጊ መዘግየት መኖር እንደሌለበት ይገልፃል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቶቻችን ከላይ ያስቀመጥነውን የተጠርጣሪና የፖሊስ ተፃራሪ ፍላጎቶችን ሊያስታርቁ የሚችሉባቸው የሕግ መሰረቶች አሏቸው፡፡

ይሁን እንጅ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በታዘብኳቸው አብዛኛው የወንጀል ጉዳዮች እንዲሁም ከተለያዩ የወንጀል ጉዳዮችን ከሚከታተሉ ጠበቆች በነበረኝ ቆይታ እንደተረዳሁት አብዛኛውን ጊዜ የአስራ አራት ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀ መርማሪ ፖሊስ በፍርድ ቤቶቻችን እንደሚፈቀድለትና በተለይ ጉዳዩ የፖለቲካ ጋር ግንኙነት ያለው ከሆነ ተጠርጣሪዎች ላይ አላስፈላጊ እንግልት እንዲደርስ እንደመሰሪያ አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል፡፡ በመሆኑም በሕጉ የተቀመጠው የአስራ አራት ቀን የተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ገደብ በሕግ አውጭው የታሰበለትን ዓለማ ሳያሳካ እንደቀረ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በተለይም ድንጋጌው የተቀመጠበትን አሻሚነት እየተረዱ ፍርድ ቤቶች ክፍተቱን የመሙላት ሚና መጫወት ሲገባቸው የተጠርጣሪዎችን መብት በሚጋፋ መልኩ ውሳኔዎች መወሰናቸው ጥያቄ የሚያሥነሳ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የተቀመጠውን ድንጋጌ የሚያብራራ ወይም አዲስ ሕግ እስከሚወጣ ድረስ ፍርድ ቤቶች የተጠርጣሪዎችን ነፃነት የማስከበር ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ፖሊሶች ለምርመራ የሚወስዱትን ጊዜ እንዲፋጠን የሚደረግበትን ሕጋዊ ጫና መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡

  1. መደምደሚያ

በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ በወንጀል ጉዳይ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ሰዎችን መብት ለማስከበር የሚረዱ ተለያዩ ድንጋጌዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች መካከል አንድ የፖሊስ ምርመራ ተግባር ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ የተቀመጡ የጊዜ ገደቦች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ የጊዜ ገደቦች መካከል የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 19(3) ላይ የተቀመጠው የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ እና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 57(3) ላይ የተቀመጠው ለተጨማሪ ምርመራ የሚሰጠው የ14 ቀን የጊዜ ገደቦች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጅ ሕጉ የጊዜ ገደቦችን የሚያስቀምጥበትን ዓላማ በሚፃረር መልኩ ከፍርድ ቤቶቻችን አሰራር እንደተረዳነው እነዚህ የጊዜ ገደቦች እየተከበሩ አይደለም፡፡ በተለይም የ14 ቀን የጊዜ ገደብ በአጠቃላይ ሊሰጥ የሚገባው ጣሪያ በሕጉ ስላልተቀመጠና ፍርድ ቤቶችም የሕጉን ክፍተት ለመሙላት ባለመቻላቸው ከፍተኛ የሆነ መጉላላት እና የመብት ጥሰት በተጠርጣሪና በተከሳሽ ግለሰቦች ላይ ሲደርስ ቆይቷል፤ እየደረሰም ይገኛል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው ፍርድ ቤት የጉዳዩን ከባድነት በመገንዘብ አስፈላጊውን ርምጃ በመውሰድ ተከሳሾች እና ተጠርጣሪዎች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን እንግልት እንደሚስቆም ተስፋ አድርጋለሁ፡፡

Read 8310 times Last modified on Oct 04 2018
Nigussie Redae

The blogger is currently working as Contracts and Litigation Manager at BGI Ethiopia PLC.