በምርመራ ወቅት በፖሊስ ጣቢያ የተሰጠ የምስክሮች ቃል በፍ/ቤት ያለው ተቀባይነት

May 24 2018

 

በምርመራ ወቅት በፖሊስ ጣቢያ የተሰጠ የምስክሮች ቃል በፍ/ቤት ያለው ተቀባይነት፤ ሕጉ፣ ትግበራው እና የሰበር ችሎት አቋም

አንድ ወንጀል ስለመፈጸሙ እና ድርጊቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጣሪው ሰው የድርጊቱ ፈጻሚ ስለመሆኑ ፖሊስ ምርመራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ከሚያጣራባቸውና ከሚያረጋግጥባቸው የማስረጃ ዓይነቶች መካከል አንዱ የሰው ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ የዚህ ጹሁፍ ዓላማ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145ን ህጉን ፣በፍ/ቤት ትግበራ ያለውን የህጉን ትርጉም እና የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም አቋምን ከተከሳሽ መብት አኳያ በማመዛዘን ያስዳስሳል፡፡

የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145

በፖሊስ ምርመራ የተሰጠ ቃል በማስረጃነት ሊቀርብ ስለመቻሉ

(1) ዐቃቤ-ህጉ ወይም ተከሳሹ ሲያመለክት በፖሊስ ምርመራ ጊዜ የተሰጠውን የምስክርነት ቃል ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው ይችላል፡፡

(2) ከዚህ በኃላ ለትክክለኛ ፍርድ አሰጣጥ የሚጠቅም መስሎ ከታየው የዚህ ቃል ግልባጭ ለተከሳሹ እንዲደርሰው አድርጎ በዚህ መሰረት ምስክሩ የሰጠውን ቃል ለማስተባበል ይቻላል፡፡

የአንቀጹ ርእስ እንደሚያስረዳው በፖሊስ ምርመራ የተሰጠ የምስክርነት ቃል በፍ/ቤት እንደ ማስረጃ ተደርጎ ሊወሰድ የሚቻል ስለመሆኑ በግልጽ ያስቀመጠና ጥያቄ የማያስነሳ ጉዳይ ቢሆንም መቼና በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ይህ በምርመራ ወቅት የተሰጠ የምስክርነት ቃል በፍ/ቤት ተቀባይነት የሚኖረው የሚለውን በተመለከተ ግን ህጉ የገለጸው ነገር ባለመኖሩ ይህ አንቀጽ ለትርጉም ክፍትና እስካሁን ድረስ ገዢ የሆነ ትርጉም ያላገኘ አከራካሪ ጉዳይ ስለመሆኑ እንደሚከተለው አስረዳለሁ፡፡

  1. የሕጉ ትርጉም

በፖሊስ ምርመራ ወቅት የተሰጠ የምስክሮች ቃልን እንደ ማስረጃ ፍ/ቤት ሊቀበለው የሚችልበት ሁኔታዎችን በምንፈትሽበት ጊዜ ሁኔታዎቹ በተለይ የተከሳሹን መብት ከመጠበቅ አኳያ ያሉትን መሰረታዊ መብቶች በጠበቀና ባከበረ መንገድ ሊተረጎሙ የሚገባ መሆን አለበት፡፡ እነዚህም ሊከበሩ የሚገባቸው የተከሳሹ መሰረታዊ መብቶች፡-

  • አንደኛ ህገ-መንግስታዊ ነው፡፡ ይህም ስለመሆኑ ማንኛዉም በወንጀል የተከሰሰ ሰው ያሉትን መብቶች አስመልክቶ በህገ-መንግስቱ አ.ቁ 20 ላይ የተዘረዘረ ሲሆን ከያዝነው ጉዳይ አኳያ ጠቃሚ የሚሆነው ንዑስ ቀ. 4 “የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ…”መብት ያለው ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህንን የህገ-መንግስት ድንጋጌ በተመለከተ ብዙ ጊዜ በፍ/ቤት ክርክር የተነሳበት በመሆኑ ( በእርግጥ ክርክር የተነሳው በሽብር እና በሙስና በተጠረጠሩ ተከሳሾች ላይ ሲሆን ምክንያቱም ዐቃቤ-ህግ ያቀረበውን ክስ ላይ አለኝ ያላቸውን ምስክሮች ለደህንነታቸው ሲባል በሚል ምክንያት ስም ዝርዝር ባለማስፈሩ የተነሳ ነው) ህገ-መንግስት ጉዳይ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የማየትና ትርጉም የመስጠት ብቸኛው ባለስልጣን የሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተረጎመው ይህ አንቀጽ ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ምስክሮች አስመልክቶ ያላቸው ህገ-መንግስታዊ መብት የመጠየቅ (cross-examine) ማድረግ ብቻ ስለመሆኑ አስረድቷል፡፡ የተከሳሾች ይህ የመጠየቅ መብት የሚከበረው ደግሞ ምስክሮቹ ቃላቸውን የሰጡት ተከሳሾች የመጠየቅ መብታቸው በሚከበርላቸው ፍርድ ለመስጠት በተቋቋሙ ተቋም ውስጥ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በፖሊስ በምርመራ ወቅት ምስክሮች ቃላቸውን ሲሰጡ ተጠርጣሪዎቹ የመገኘትም ሆነ የመጠየቅ መብት የላቸውም ስለዚህ የወ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 ልዩ ሁኔታዎች ሲተረጎሙ ይህን የተከሳሽ ህገ-መንግስታዊ የመጠየቅ መብት ያከበረ መሆን አለበት፡፡

 

  • በሁለተኛ ሰብአዊ መብቱ ሲሆን ይህም ስለመሆኑ ኢትዮጵያ በህገ,መንግስቱ ቁጥር 13(2) ላይ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች(UDHR) አ.ቁ 10 እና 11 ላይ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና ሲቪል መብቶች የቃል-ኪዳን ሰነዶች(ICCPR) አ.ቁ 14 እና 16 ላይ በዝርዝር የተከሰሱ ሰዎችን የመሰማት እና የሚቀርባቸውን ምስክሮች የማወቅና የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ተዘርዝሮል፡፡

 

  • በሶስተኛ ደረጃ የምስክሮች ግዴታ ነው፡፡ አንድ በምስክርነት የተጠራ ሰው የሚሰጠው ቃል እንደ ማስረጃ ለመቆጠር ከሚያስፈልጉት ቅድሚያ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ምስክሮቹ እውነቱን ለመናገር ወይም ለማረጋገጥ መማል ያለባቸው መሆኑ ነው( የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 136(2))፡፡ በመሆኑም በፖሊስ ምርመራ ወቅት ምስክሮች ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት የሚሰጡት ቃል እውነት ስለመሆኑ የሚምሉበት ሁኔታ የሌለ በመሆኑ ፍ/ቤቶች ያለ ቃለ-መሀላ የተሰጠን የምስክርነት ቃል ሊቀበሉ የማይገባ ስለሆነ የወ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 ይህን መሰረታዊ የወንጀል ክስ-ስነስርዓት ሂደት ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡

 

ስለሆነም የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145ን በመተርጎም በምርመራ ወቅት በፖሊስ የተሰጠን የምስክረነት ቃል ፍ/ቤቶች ሲቀበሉ እንደ ማነጻጸሪያ ማዕቀፍ( as reference frame) ከላይ የተዘረዘሩትን የተከሳሹን መሰረታዊ መብቶችና ስነ-ስርዓታዊ የምስክር ግዴታን ባከበረ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በመነሳት ህጉ ተፈጻሚነት ሊኖረው እና ሊተገበረው የሚገባበት ሁኔታ በተመለከተ ብ/ጀነራል ታጠቅ ታደሰ “የማስረጃ ህግ መሰረተ ሀሳቦች” (ገጽ.182) በሚለው መጽሀፋቸው፣ ስሜነህ ኪሮስ “Criminal Procedure Law፡ Principles ,Rules and Practice”pp.383 እና ቸርነት ሆርዶፋ እና ስሜነህ ኪሮስ በአንድነት በጻፍቱ “የወንጀል ምርመራ፣የክርክር አመራርና ቅጣት አወሳሰን” ገጽ 189 ላይ የገለጹት ሁኔታ አንድ እና ብቸኛ ሲሆን ሲሆን ይህም ዐቃቤ-ህጉ ያቀረበው ምስክሩ አስጠቂ (hostile witness) በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በእርግጥ የሁሉም ጠበቃም ሆነ ዐቃቤ-ህግ ስጋት ሲሆን በዚህም ለመምህሩ የተገጠመው ተቀይሮ

“አወይ የጠበቃ/ዐ.ህግ አባዜ

የምስክር አስጠቂ በገጠመው ጊዜ”

የሚያስብል ነው፡፡

በመሆኑም ዐቃቤ-ህግ ምስክሩ በፖሊስ ምርመራ ወቅት የሰጠውን ቃል በመቀየር አስጠቂ በሚሆንበት ጊዜ የምርመራውን መዝገብ በማስቀረብ መሪ ጥያቄ ለመጠየቅ የሚያስችለውን መብት እንዲያገኝ ዐቃቤ-ህጉን እንዲያስችለው ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ዐቃቤ-ህጉ በምንም ዓይነት ሁኔታ አስጠቂ የሆነበት ምስክሩን መሪ ጥያቄ መጠየቅ አይችልም፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ሙስናን በተመለከተ የቀረበ ክስ ከሆነ ዐቃቤ-ህጉ በምርመራ ወቅት ለፖሊስ የተሰጠውን የምስክረነት ቃል ማቅረብ ሳያስፈልገው መሪ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችል የተሻሻለው የጸረ-ሙስና ልዩ የስነ-ስርዓትና የማስረጃ ህግ አዎጅ.ቁ 434/1997 አንቀጽ 41 ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም ከሁሉ በላይ ሊሰመርበት የሚገባው ፍ/ቤቶች ምስክር አስጠቂ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145(2) መሰረት የምርመራው ቃል መቅረቡ ለፍትህ አሰጣጥ ጠቃሚ የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው የተሰጠውን ቃል ለማየት መፍቀድ ያለባቸው፡፡

  1. በፍ/ቤቶች ያለውን ትግበራ

በፍ/ቤቶች ያለውን የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 አተረጓጓም አስመልክቶ ከላይ በዘረዘርኳቸው መጽሀፍ ላይ የተገለጹትን ትግበራዎች እንድታነቧቸው እየጋበዝኩ ጸሀፊውን በቀጥታ በገጠመውና ለዚህ ጽሁፍ ምክንያት የሆነውን አጋጣሚ እንዲህ ይገልጻል፡፡

ተከሳሹ የወንጀል ህግ አ.ቁ በመተላለፍ በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን የግል ተበዳይ ለፖሊስ በምርመራ ወቅት የምስክርነት ቃላቸውን ከሰጡ በኃላ ለተወሰነ ጊዜ ከሀገር ውጪ ይወጣሉ፡፡በዚህም ምክንያት በፍ/ቤት ቃላቸውን እንዲሰጡ ሲፈለጉ ሊገኙ ባለመቻላቸው ዐቃቤ-ህግ ምስክሩ ከሀገር ውጪ መሆናቸውን ከኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ መምሪያ ማረጋገጫ በማቅረብ በፖሊስ የሰጡት ቃል በማስረጃነት እንዲያያዝለት በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 መሰረት ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሎ በምርመራ ወቅት የተሰጠውን የምስክርነት ቃል በማስረጃነት አያይዞ ተከሳሽ ላይ የሶስት ዓመት እስራት ፍርድ ሰጥቷበታል፡፡

በወቅቱ የወ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 ሊተረጎምበት የሚገባበት ሁኔታ የምስክር በሀገር ውስጥ ያለመገኘት ሁኔታ አይደለም በማለት ለቀረበው መከራከርያ በዐቃቤ-ህግ የቀረበው እና በፍ/ቤቱ ተቀባይት ያገኘው የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 144(1) በመጥቀስ ምስክሩ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ አለመኖሩ አንድ ምክንያት በመሆን ምስክሩ ለፍ/ቤቱ ተገኝቶ ቃሉን ባልሰጠበት ጊዜ ቀድሞ የሰጠው ቃል እንደ ማስረጃ ሊወሰድበት የሚችልበት ሁኔታ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንደዚሁም እነዚህ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 144 ላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ከወ/መ/ስ/ስ/ቁ 145 ጋር በአንድ ምዕራፍ ስር የሚወድቁ በመሆኑ ተደጋግፈው ሊተረጎሙ ይገባል በማለት በማቅረቡ ነው፡፡

ነገር ግን የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 144 በቀዳሚ አድራጊ ፍ/ቤት ምስክሮች የሰጡትን ቃልን በሚመለከት ሲሆን በዚህ ሁኔታ የምስክርነት ቃል ሲሰጥ ተጠርጣሪው ምስክሮቹን የመጠየቅ መብቱ በተረጋገጠበት ሁኔታ የሚፈጸምና ምስክሩም መሀላ በመፈጸም ፍርድ ለመስጠት በህግ በተቋቋመ ተቋም የሚሰጠው ቃል ነው፡፡ በመሆኑም በቀዳሚ አድራጊ ፍ/ቤት የሚሰጡን ቃሎች በማስረጃነት ለመቀበል የሚቀርቡ ሁኔታዎችን ፍጹም ተከሳሹ በሌለበት፣የመጠየቅ መብቱ ባልተከበረበት እና ምስክሮቹ መሀላ ባልፈጸሙበት ሁኔታ በፖሊስ ምርመራ የሚሰጡት የምስክርነት ቃል እንደ ማስረጃ በፍ/ቤት ለመውሰድ ተመሳሳይ ሁኔታዎችን መመዘኛ ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው፡፡

በእርግጥ ይህን የመሰለ ነጠላ ጉዳይን በመያዝ በፍ/ቤቶች ያለው የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 ትግበራ ይህን ይመስላል ማለት ሎጂኩ እንደሚለው Hasty Generalization ሲሆን የጸሀፊው ዓላማ ግን የገጠመውን በማካፈልና ከአንባቢው የዕውቀትና የሀሳብ ግብአት ማግኘት ነው፡፡ ስለሆነም አንባቢዎች የገጠማቸውን እንዲያካፍሉን በማድረግ ስለትግበራው የተሻለ እይታ እንዲኖረን እንዲያስችለን ነው፡፡

 

  1. የፌ/ሰ/ሰ/ችሎት አቋም

የፌ/ሰ/ሰ/ችሎት የሚሰጠው ውሳኔ በሀገራችን ባሉ ፍርድን ለመስጠት በተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ሁሉ አስገዳጅነት ያለው የህግ ትርጉም እንዲሆን ያስፈለገበት ዋና ዓላማዋች፡-

  1ኛ/ፍ/ቤቶች እራሳቸውን በራሳቸው ለመቆጣጠር እንዲችሉ

  2ኛ/ መሰረታዊ የህግ ስህተት ያለበት ፍርድ ጸንቶ እንዳይቆይ ለማድረግ እና

  3ኛ/ ተመሳሳይ ጉዳዮች በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲተረጎሙ ወይም ወጥነት ያለው ፍትህን በመዘርጋት ተገልጋዩ በፍ/ቤት ላይ ታማኝነት እንዲኖረው መሆኑን አንጋፋው አቶ ዩሀንስ ኅሩይን ጠቅሰው አቶ ዮሴፍ አዕምሮ “The Cassation Question in Ethiopia” በሚለዉ ጆርናል ላይ ላይ ‘በኢትዮጵያ የሰበር ስርዓት የመጨረሻ ውሳኔ ምንነት’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ ላይ በደንብ ያስረዳሉ፡፡

 ነገር ግን ችሎቱ በመ.ቁ 111498 (ቅጽ 19) ላይ በሰጠው ውሳኔ ምንም እንኳ ችሎቱ የያዘው ጭብጥና ውሳኔ የሰጠበት ጉዳይ የወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 136/4/ እና 143 እንዲሁም 194/1/ ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ውጪ ፍርድ ቤት ወይም ዳኛው የቀረበለትን ጉዳይ በተመለከተ ማስረጃ ለመፈለግ የግሉን ምርመራና የምርመራ ስራ ለማድረግ የሚችልበት የዳኝነት አሰጣጥ ስርአት ስላለመኖሩ ቢሆንም በውሳኔ ሀተታ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 ትርጉምና የተፈጻሚነት ሁኔታዎች በተመለከተ ወጥነት ያለው ለስር ፍ/ቤቶችም ሆነ ለተገልጋዩ የሚረዳ ትርጉም ከመስጠት በመቆጠብ ነገር ግን

“በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 ላይ አንድ ምስክር በፖሊስ ምርመራ ወቅት የሰጠው ቃል ዓቃቤ ሕግ ወይም ተከሳሹ ባመለከተ ጊዜ የተሰጠውን ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ሊመለከተው እንደሚችል የተደነገገ ቢሆንም የዚህ ድንጋጌ መሰረታዊ አላማም በምርምራ ጊዜ ተሰጠ የተባለውን የምስክርነት ቃል በፍርድ ቤት ምስክሩ ቀርቦ ቢለውጠው ይኼው ምስክርነት እንዲቃናና ፍርድ ቤት ለያዘው ክስ ሁልጊዜ ከብደት እንዲሰጠው ለማድረግ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡”

በማለት ከላይ የወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 145 ተፈጻሚነት አስጠቂ ምስክር ባገጠመ ጊዜ ብቻ ሲሆን ዓላመውም መሪ ጥያቄ በመጠየቅ ምስክሩ ቀድሞ የሰጠውን የምስክረነት ቃል በማስረጃነት በማቅረብ ነገሩን ለማስተባበል ነው የሚለውን ዕይታና ጸሀፊውም የሚያምንበትን የህግ ትርጉም ሰበር ሰሚው ችሎት ውድቅ በማድረግ አቋም የያዘ ቢሆንም የአቋሙን አቅጣጫ ግን ምንም ያላመላከተን በመሆኑ ችሎቱ ከተቋቃመለት ወጥ የሆነ ፍትህ መዘርጋት ዓላማ ጥሶ በባለሙያው ዘንድ ትልቅ ብዥታን ፈጥሯል፡፡ ይህም ሊታረም ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

ማንም ሰው በፍ/ቤት የጥፈተኝነት ውሳኔ እስካልተሰጠበት ድረስ ነጻ ሀኖ የመገመት መብት ህግ-መንግስታዊ በመሆኑ ፍ/ቤቶች የተከሳሹን መሰረታዊ መብቶች ሳይሸራረፍ እንዲከበሩ መቆጣጠር አንዱና ዋነኛው ሀላፊነታቸው ነው፡፡ ነገር ግን የፌ/ሰ/ሰ/ች ከዚህ አቋም ፈቀቅ ባለሁኔታ ከፍርድ ቤት ውጪ የተሰጠን የምስክርነት ቃል በፍ/ቤት ተቀባይነት እንዲኖረው በሚስችል መልኩ በር በመክፈት በተከሳሾች ላይ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ብቻ እየታየ በቅጣት ከቀላል እስር እስከ ሞት ሊያስቀጡ በሚያስችሉ ድርጊቶች ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያበረታታ የህግ ትርጉም አቋም መያዝ የፍ/ቤትን መአዘን ድንጋይ ማንሸራተት ነው፡፡

ስለሆነም ለማጠቃለል በፖሊስ በምርመራ ወቅት የተሰጠ የምስክርነት ቃል ምስክሩ በምንም ዓይነት ሁኔታ ላይ ቢሆንም የምስክርነቱን ቃል በፍ/ቤት ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡

ተከሳሹ የምርመራ መዝገቡን የማየት መብት አለው

Read 11187 times Last modified on May 29 2018
Dagim Assefa

ጦማሪው በሕግ የመጀመሪያ ድግሪውን (LLB) ከቅ/ማርያም ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በ1999 ዓ.ም ያገኘ ሲሆን ሁለተኛ ድግሪውን (LLM) ደግሞ ከባህር ዳር የኒቨርስቲ በ2005ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በአቃቤ-ሕግነት፣ በመምህርነትና በነገረ-ፈጅነት ያገለገለ ሲሆን አሁን ደግሞ ጠበቃና የሕግ አማካሪ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡