የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/፣ 559/2/ እና የሰበር አስገዳጅ ትርጉም ከተደራራቢ ወንጀሎች አንጻር

Mar 05 2018

 

   የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 21 በመዝገብ ቁጥር 123046 በይግባኝ ባይ አቶ አዲሱ ገመቹ እና በመልስ ሰጭ የአ/ብ/ክ/መ ዓ/ህ መካከል በነበረው የወንጀል ክስ ላይ አንድ አሽከርካሪ በቸልተኝነት በተለያዩ ሰዎች ላይ አካል ጉዳት ሲያደርስ የወንጀል ሕግ ቅጣቱን ከፍ ከሚያደርግበት በቀር በቸልተኝነት ተደራራቢ አካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል እንደፈጸመ ተቆጥሮ ተደራራቢ ወንጀል ክስ ሊቀርብበት እንደማይችል እና ጥፋተኛ ተብሎ ሊቀጣም እንደማይችል ትርጉም ሰጥቷል፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ ባጭሩ

 ይግባኝ ባይ በሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ትን በመተላለፍ በሚያሽከረክረው ተሸከርካሪ ውስጥ ተሳፋሪ የነበሩትን ሁለት ሰዎች ሙያዊ ሀላፊነት እያለበት በቸልተኝነት ሰው መግደል ወንጀል በአንድ ክስ እንዲሁም የወንጀል ሕግ አንቀጽ 559/2/ትን በመተላለፍ በሚያሽከረክረው ተሸከርካሪ ውስጥ ተሳፋሪ የነበሩት ሰባት ሰዎች ላይ አካል ጉዳት በማድረስ ወንጀል ሰባት ክስ በአጠቃላይ በስምንት ክስ ተከሷል፡፡ የሞቱት ተሳፋሪዎች ሁለት ሲሆኑ ክሱ የቀረበው በአንድ ነው፡፡ የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀሉን በሚመለከት ሰባት ተሳፋሪዎች የተጎዱ ሲሆን ክሱ የቀረበው በሰባት የተለያየ ክስ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹን በስምንቱም ክሶች ጥፋተኛ በማለት በአስር ዓመት ጽኑ እስራት እና በ5000 ሺብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡ ይህ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ በተከሳሹ ይግባኝ ተብሎበት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያልተማረ መሆኑን አንድ የቅጣት ማቅለያ በተጨማሪነት ይዞለት እስራቱን ዘጠኝ አመት አድርጎታል፡፡ ቀጥሎም ይግባኙን ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያቀርብም ይግባኙ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በመቀጠል ይግባኙ የቀረበለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት/ከዚህ በኋላ ሰበር ሰሚው በሚል ይጠቀሳል / የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ ከአንድ በላይ ሰው በቸልተኝነት በትራፊክ አደጋ በገደለ ሰው ላይ ሕጉ አንድ ወንጀል እንደተሰራ በሚቆጥርበት ሁኔታ በቸልተኝነት በትራፊክ አደጋ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደረሰ አሽከርካሪም አንድ ድርጊት እንደፈጸመ መቆጠር አለበት በማለት የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰባት የግል ተበዳዮች እንደ አንድ ወንጀል ሊወሰድ ይገባል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት በሰባት ክስ ቀርቦ የነበረውን የአካል ጉዳት እንደ አንድ ወንጀል በመያዝ የቅጣት አወሳሰን መመሪያ 2/2006 የወንጀል ሕግ አንቀጽ 559/2/ን በሚመለከት በተጎዱት ሰዎች ቁጥር መብዛት ቅጣቱን አክብዶ ስላላስቀመጠው ፍትሀዊ ውሳኔ ለመስጠት ስለማያስችል በቅጣት አወሳሰን መመሪያው አንቀጽ 27/1/ መሰረት ከመመሪያው በመውጣት ለሰባት ክሶች መነሻ ቅጣት ሁለት ዓመት ቀላል እስራት በመያዝ ይህንንም ወደ አንድ አመት ጽኑ እስራት በመቀየር በ543/3/ ላይ ከተያዘው መነሻ ቅጣት ስምንት አመት ጽኑ እስራት ጋር በመደመር ዘጠኝ ዓመት መነሻ ቅጣት በመያዝ አራት ማቅለያዎችን ይዞ በእርከን 22 ላይ ስድስት አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እና በ 5000 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ ቀጥቶታል፡፡ ይህም ጽሁፍ የዚህን መደምደሚያ ህጋዊነት ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡

     ለሰበር ሰሚው ውሳኔ መሰረት የሆኑት የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው ፡-

1ኛ- የወንጀል ሕግ አንቀጽ 60 ማንም ሰው ተደራራቢ ወንጀል አድርጓል የሚባለው፡-

/60/ሐ/ በአንድ ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት ያደረገው ወንጀል አንድን የሕግ ድንጋጌ የሚጥስ ሆኖ ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆነ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ አንድ አይነት ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ነው፡፡

2ኛ -የወንጀል ሕግ 559/2/ ማንኛውም ሰው ያደረሰው የአካል ጉዳት በ 555 የተመለከተው አይነት ከሆነ ወይም ጉዳት አድራሹ የሌላ ሰውን አካል ወይም ጤንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ እያለበት እንደ ህክምና ባለሙያ ወይም አሽከርካሪ ያለ ሰው እንደሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማያንስ ቀላል እስራት እና ከ1000 ሺ ብር የማያንስ መቀጮ መሆኑን ይገልጻል፡፡

3ኛ -የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ ጥፋተኛው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የገደለው ወይም ወንጀሉን የፈጸመው ግልጽ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያ ተላልፎ እንደሆነ ወይም የሚያሰክሩ ወይም የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጦችን በመውሰድ እራሱን ካስገባ በኋላ ቢሆንም እንኳ ቅጣቱ ከ 5 እስከ 15 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር 10 እስከ 15 ሺ በሚደርስ ገንዘብ መቀጮ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡

     ተደራራቢ ወንጀሎች (Concurrence offences) በአንድ ሰው ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ወንጀሎች ተፈፅመው ሲገኙ ያለውን ሁኔታ የሚመለከት ሲሆን ይህም ግዙፋዊ የሆነ መደራረብ እና ሐሳባዊ (ጣምራዊ) መደራረብ  ተብሎ ይከፈላል፡፡ ግዙፍ የሆነ (ቁሳዊ) መደራረብ /Material concurrence/ አንድ ሰው ተመሳሳይ ድርጊቶችን በተለያዩ ጊዜያት በመፈጸም እንደ አንድ ወንጀል የማይቆጠሩ ወንጀሎችን ሲፈፅም ወይም ተመሳሳይ ያልሆኑ ማለትም የተለያዩ ድርጊቶችን በተለያዩ ጊዜያት በመፈጸም በተለያዩ የወንጀል ድንጋጌዎች ሥር የሚወድቁ ወንጀሎችን የፈፀመ እንደሆነ ግዙፍ የሆነ (ቁሳዊ) መደራረብ አለ ይባላል፡፡ የግዙፋዊ ተደራራቢ ወንጀሎች ዓይነተኛ መለያ የድርጊቶች መደጋገም ነው፡፡ የድርጊት መደጋገም እስካለ ድረስ የተፈፀሙት ወንጀሎች ዓይነታቸው አንድ ቢሆንም ወይም ባይሆንም የተደራረቡ ወንጀሎች ናቸው፡፡ እንደ አንድ ወንጀል የማይቆጠሩ ነገር ግን በአንድ አንቀጽ ስር የሚወድቁ በተለያዩ ጊዜያት የተፈፀሙ ተመሳሳይ ድርጊቶችም ቢሆኑ ግዙፍ የሆኑ ተደራራቢ ወንጀሎች ናቸው፡፡ሐሳባዊ (ጣምራዊ) መደራረብ /Notional concurrence/ - አንድ ሰው በአንድ ድርጊት ግዙፍነት ያላቸው ወይም የሌላቸው ውጤቶችን በማስከተል ከአንድ በላይ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን የጣሰ እንደሆነ ሐሳባዊ መደራረብ አለ ይባላል፡፡ የሐሳባዊ መደራረብ መለያ ባህሪ በአንድ ነጠላ ድርጊት ከአንድ በላይ የሆኑ ወንጀሎች መፈፀማቸው ነው፡፡ በድርጊት ደረጃ የተፈፀመው ተግባር አንድ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የተፈፀመው አንድ ድርጊት ከአንድ በላይ የሆኑ ግዙፍ የሆኑ ውጤቶችን ካስከተለ ወይም ደግሞ ድርጊቱ ከአንድ በላይ የሆኑ ግዙፍ ውጤቶችን ባያስከትልም ከሕግ አንጻር በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን የሚጥስ ተግባር ሆኖ ከተገኘ የተደራረቡ ወንጀሎችን ፈጽሟል ያስብላል፡፡

     ተደራራቢነትን በሚመለከት በኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 60 ላይ የተገለጸ ሲሆን በ አንቀጽ 60 /ሐ/ላይ በአንድ ወንጀል ሀሳብ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት በሚደርስበት ወቅት ተደራራቢ ወንጀል እንደሚሆን ያስረዳል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543/3/ ከወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል አንቀጽ 60/ሐ/ ጋር ተያይዞ ጥያቄ የሚነሳበት አንቀጽ ነው፡፡ ሕግ አውጪው በልዩ ሁኔታ በአንድ ድርጊት ከአንድ በላይ ሰው እየሞተ በሞቱት ሰዎች ቁጥር በአንቀጽ 60/ሐ/ መሰረት ጉዳት አድራሹ ሊከሰስ ሲገባ በአንድ ክስ እንዲሆን ማድረጉ በምን ምክንያት እንደሆነ አጥጋቢ መልስ ሲሰነዘር አይሰማም፡፡ ነገር ግን አንድ መሰረታዊ ነገር ማስቀመጥ የሚቻለው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543/3/ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60/ሐ/ ልዩ ሁኔታ ሆኖ መቀመጡን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሰበር ሰሚ ችሎቱ ተከሳሽ ያደረሰው ጉዳት ሁለት ሰዎች የሞቱበት ስለሆነ ይህንን መሰረት አድርጎ እንደ አንድ የወንጀል ድርጊት መቆጠር አለባቸው ያለበት አግባብ ተገቢ እና ሕጉም በግልጽ ያስቀመጠው ጉዳይ ነው፡፡ በስር ፍርድ ቤቶችም ከዚህ አንጻር ስህተት አልተሰራም፡፡ ነገር ግን በቸልተኝነት የተፈጸመውን አካል ጉዳቶች በሚመለከት ወንጀል ሕጉ 559/2/ የሚገልጸው ማንኛውም ሰው ያደረሰው የአካል ጉዳት በ 555 የተመለከተው አይነት ከሆነ ወይም ጉዳት አድራሹ የሌላ ሰውን አካል ወይም ጤንነት የመጠበቅ የሙያ ወይም ሌላ ግዴታ እያለበት እንደ ህክምና ባለሙያ ወይም አሽከርካሪ ያለ ሰው እንደሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማያንስ ቀላል እስራት እና  ከ1000 ሺ ብር የማያንስ መቀጮ መሆኑን ይገልጻል፡፡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 60/ሐ/ በአዲሱ የወንጀል ሕግ ውስጥ የተካተተበት ምክንያት አንድ ሰው በአንድ አይነት ወንጀል የማድረግ ሀሳብ ወይም ቸልተኝነት የፈጸመው ወንጀል አንድን የሕግ ድንጋጌ የሚጥስ ቢሆንም አንድ አይነት ጉዳት ያስከተለው ቁጥራቸው ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ሲሆን እንደ ተደራራቢ ወንጀል ሊቆጠር የሚገባ መሆኑ ታምኖበት ነው /የወንጀል ሕግ ሀተታ ዘምክንያት ገጽ 38/፡፡የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 60/ሐ/ ተደራራቢነትን በሚመለከት ካስቀመጠው ሀሳብ ጋር በልዩነት የተቀመጠ ድንጋጌ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ስንመለከት ደግሞ ይህ ጉዳይ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 559/2/ ስር የሙያ ሀላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ቢመለከትም እንኳ ከ1 በላይ ሰዎች ጉዳት ሲደርስባቸው አንድ ወንጀል በማድረግ ሀሳብ እንደተደረገ ተቆጥሮ እንደ አንድ ወንጀል አልተቀመጠም፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ ላይ ሕግ አውጪው ከአንድ በላይ ሰዎች የሞቱበትን ሁኔታ መሰረት አድርጎ ቅጣቱን አንድ ሰው ከሚሞትበት አንቀጽ 542 ከፍ አድርጎታል /የወንጀል ሕግ ሀተታ ዘምክንያት ገጽ 258/፡፡

በመሆኑም ሕጉ የሟቾችን መብዛት ከተከሳሹ የቸልተኝነት ድርጊት እንዲሁም የቸልተኛ አጥፊዎች ላይ ሕጉ ከሚወስደው የቅጣት ለዘብተኝነት አቋም አንጻር አብሮ የሚሄድ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ግን የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 559/2/ ላይ ይህ ሁኔታ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ከፍትሀዊነት አንጻር የወንጀል ሕጉ ከ አንድ ሰው በላይ ሲሞት በአንድነት እንደ አንድ የወንጀል የሀሳብ ክፍል በመውሰደው በአንድ ወንጀል እንዲጠየቅ ካስደረገ ለጠንካራ ምክንያታዊነት የአካል ጉዳቶችንስ ለምን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲካተቱ አላደረገም የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም ከላይ የተገለጸውን ትርጉም ለመስጠት መሰረት ያደረገው ይህንኑ አመክንዮ/logic/ ነው፡፡ የሰበር ሰሚው ውሳኔ ተከሳሽ በአንድ ድርጊት ሰባት ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረሱ እንደ ሰባት የተለያየ ወንጀል ሊታይ አይገባም ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ከአንቀጽ 60/ሐ/ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ተከሳሹ በአንድ የቸልተኝነት ድርጊት ሰባት የተለያዩ ሰዎች ላይ ጉዳት እስካደረሰ ድረስ በቸልተኝነት የተፈጸሙት የወንጀል ድርጊቶች ተደራራቢ ተብለው ሊያዙ ይገባዋል፡፡ ይህ አካሄድ የማይሰራው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ ሲሆን ነው፡፡ በአንቀጽ 543/3/ ላይ ሕግ አውጪው ከአንቀጽ 60/ሐ/ በልዩ ሁኔታ ተከሳሹ ከአንድ በላይ ሰው በቸልተኝነት በሚገድልበት ጊዜ ቅጣቱን አክብዶ በአንድ የወንጀል ድርጊት እንዲካተት አድርጎታል፡፡  ሕጉ በግልጽ ከአንድ በላይ ሰዎች ላይ አካል ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ ልክ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543/3/ ሊተረጎም እንደሚገባ ምንም አይነት ፍንጭ ባልተወበት እና የወንጀል ሕጉ ጠቅላላ ክፍል ወደ ሆነው አንቀጽ60/ሐ/ መመለስ ሲገባው ሰበር ሰሚ ችሎቱ ግልጽ የሆነ እና ትርጉም የማያስፈልገውን ድንጋጌ የፍትhዊነት ጥያቄ ስላስነሳ ብቻ ከወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543/3/ ጋር አያይዞ ትርጉም የሰጠበት መንገድ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕጉ ሁለት ሰው በሚሞትበት ጊዜ በአንቀጽ 543/3/ ላይ አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ካለው ድንጋጌ የተለየ ቅጣት አስቀምጧል፡፡ በአንቀጽ 559/2/ ስር ግን ይህ ነገር አልተመለከተም፡፡ የተቀመጠውም ቅጣት በተጎዱት ሰዎች መጠን አይደለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ አንቀጽ 559/2/ን በ አንቀጽ 543/3/ አንድምታ መተርጎም ስህተት ነው፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጠው ትርጉም እዛው ውሳኔ ላይ ቅጣት በሚወስንበት ጊዜ ስህተት እንደሆነ ፍንጭ አሳይቷል፡፡ ነገር ግን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህን ስህተት የቅጣት አወሳሰን መመሪያው እንደሆነ አደርጎ አልፎታል ይንን በዝርዘር እንመልከተው፡፡

ቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 ዓ/ም ላይ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 543/3/ ሶስት ደረጃ የወጣለት ሲሆን ሶስቱም ደረጃዎች መሰረት ያደረጉት በድንጋጌው ውስጥ የተመለከቱትን ፍሬ ነገሮች መሰረት አድርጎ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሰበር ሰሚ ችሎቱ አንቀጽ 559/2/ ትን በሚመለከት ቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉ ደረጃ ያወጣበት መንገድ የተጎጂዎችን ቁጥር መብዛት መሰረት ያላደረገ መሆኑን ገልጾ ከቅጣት አወሳሰኑ መመሪያ ወቶ ቅጣት ለመወሰን ተገዷል፡፡ እንግዲህ ቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉ 543/3/ትን በሚመለከት በወንጀል ሕጉ ላይ የሰፈሩትን መለኪያዎች መሰረት አድርጎ ደረጃ እና እርከኖችን አስቀምጧል፡፡ በሌላ በኩል 559/2/ ትን በሚመለከት ደግሞ በቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉ ላይ ደረጃ የወጣለት ሲሆን እስከ ሰባት ባሉት ደረጃዎች ላይ የተጎጂዎችን ቁጥር መሰረት ከማድረግ ይልቅ በአንድ ተጎጂ ላይ ስለሚደርስ ጉዳት መጠን መሰረት ያደርጋል፡፡  ሕጉ በፍሬ ነገሩ ላይ የጉዳተኞችን ቁጥር መብዛት መሰረት ባላደረገበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የተጎጂዎችን ቁጥር መብዛት እና ማነስ በልዩ ወንጀሉ ላይ ተለይቶ ቅጣት ባልተቀመጠበት ሁኔታ የተጎጂዎችን ብዛት ቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉ ላይ እንዲሰፍር መጠበቅ አግባብነት የለውም፡፡ ቅጣት አወሳሰኑ የደረጃ እና እርከን መመዘኛዎች ከልዩ ሕጉ ፍሬ ነገሮች እና ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸው መመዘኛዎች ጋር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ሰበር ሰሚው ትርጉም የሰጠበት የሕግ ድንጋጌ ላይ ሕግ አውጪው ያላሰፈረውን ሀሳብ እንዲጨመር በሚያስገድድ መልኩ ትርጉም የሰጠ መሆኑን ቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉን ሲጠቀም የሄደበት መንገድ በራሱ ያስረዳል፡፡ 559/2/ የተጎጂዎችን ብዛት መሰረት አድርጎ ቅጣት ሊከብድበት የሚችልበትን ሁኔታ አላስቀመጠም፡፡ ይህም ደግሞ የሚያስነቅፈው አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንቀጹ በራሱ መደራረብን በአንድ አንቀጽ ስር አካቶ የያዘ ስላልሆነ፡፡

ከቅጣት አወሳሰን ማኑዋሉ ጋር በተያያዘ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሌላ የሰራው ስህተት አለ፡፡ የማኑዋሉን አንቀጽ 27/1/ድን የሚጠቀም ወሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ ይህንን ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የማስተላለፍ ግዴታ ዳኞች ላይ ተጥሏል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰበር ሰሚ ችሎቱ አንቀጹን ቢጠቀምም የውሳኔው ግልባጭ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እንዲደርስ ማዘዝ የነበረበት ቢሆንም ይህንን አላደረገም፡፡ በእርግጥ ችሎቱ በራሱ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር ቢሆንም የፍርድ ቤቱ ሀላፊዎች ሊደርሳቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ እርግጥ ነው መመሪያው በአንቀጽ 27/3/ ላይ ከመመሪያው ወተው የሚሰጡ ቅጣቶች በስልሳ ቀናት ውስጥ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መተላለፍ እንዳለባቸው ከመግለጽ ባለፈ ለየትኛው አካል መቅረብ እንዳለበት አይገልጽም፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎቶች ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አካል እንጂ እራሳቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስላልሆኑ በተለይም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎቶች ከመመሪያው ወተው ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ ውሳኔው ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሀላፊዎች መቅረብ ይኖርበታል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

     እንደመውጫ ሰበር ሰሚ ችሎቱ አንቀጽ 543/3 እና 559/2/ ላይ በተመሳሳይነት ትርጉም የሰጠበት መንገድ ተገቢ አይደለም፡፡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 543/3/ ሕጉ በራሱ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 60/ሐ/ልዩ ሁኔታ እንዲሆን አድርጎ ያስቀመጠው ሲሆን ይህንንም መሰረት አድርጎ ከሁለት ሰው በታች በሚሞትበት ጊዜ ካለው ተጠያቂነት ከፍ ያለ ቅጣትን አስቀምጦለታል /የወንጀል ሕግ ሀተታ ዘምክንያት ገጽ 258/፡፡ ከዚህ አንጻር ከአንድ ሰው በላይ ሲሞት ተደራራቢነት መኖር አለመኖሩን መመለስ የሚገባን በራሱ በአንቀጽ 543/3/ ነው፡፡ በአንቀጽ 559/2/ ጊዜ ግን ሕጉ የጉዳተኞችን ቁጥር መሰረት አድርጎ ተደራራቢነትን በራሱ በአንቀጹ ስላላስቀመጠ እንዲሁም ልክ እንደ 543/3/ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች ከአንድ በላይ ሲሆኑ የተለየ ቅጣት ስላላስቀመጠ የተደራራቢነት ጉዳይ ሊታይ የሚገባው ከጠቅላላ ሕጉ አንቀጽ 60/ሐ/ አንጻር ሊሆን የሚገባ እና በአንቀጽ 559/2/ መሰረት ደግሞ አሽከርካሪው በአንድ የቸልተኝነት ድርጊት ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት ካደረሰ የእያንዳንዱ ጉዳት እራሱን ችሎ የወንጀል ድርጊት ሊሆን ይገባል፡፡ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 60/ሐ/ መሰረታዊ አላማውም በአንድ የወንጀል ድርጊት ቁጥራቸው ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ ጉዳት በሚደርስበት ጊዜ እራሳቸውን የቻሉ ተጠያቂነቶችን መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 61 የሚሸፍናቸው ጉዳዮችም በአንድ ሰው ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች እንጂ እንደ ወንጀል ሕግ 60/ሐ/ በአንድ የወንጀል ማድረግ ሀሳብ ብዙ ሰዎች ላይ ስለሚፈጸም ወንጀል ስላልሆነ ሰበር ሰሚው አንቀጾቹን በማይጣረሱበት ሁኔታ የሚጣረሱ አስመስሎ መውሰዱም ተገቢ አይደለም፡፡ አንቀጾቹ የፍትሀዊነት ጥያቄ የሚያስነሱበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም ባይባልም ሰበር ሰሚው በአዋጅ ቁጥር 454/97 አንቀጽ 2/1/ ከተሰጠው ስልጣን አንጻር በተቃሪኒ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ያለው ሕግ የማውጣት አይነት አዝማሚያ በዚህኛውም ውሳኔ ላይ ተንጸባርቋል፡፡

Read 14512 times
GETU KASSAHUN

ጦማሪው የፌደራል በጠቅላይ ዓ/ሕግ መሥሪያ ቤት በዐቃቤ ሕግነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ጸሐፊውን በኤሜል አድራሻው ytttegta@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡