Print this page

የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም መልበስ የተጠርጣሪዎች መብት ወይስ ግዴታ?

Feb 28 2018

 

 

Wearing prison uniform; - is it a right or duty of accused persons?

 

በዚህ መነሻ ጽሑፍ በዋነኝነት ማንሳት የተፈለገው በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች በፍርድ ቤት ንፁህ ወይም ጥፋተኛ ተብሎ እስከሚፈረድባቸው ድረስ በማቆያ “ማረፊያ ቤት” በሚቆዩበት ጊዜ የማቆያ “ማረፊያ” ቤቱን ዩኒፎርም መልበስ ግዴታ ነው ወይስ መብት የሚለው እና እንዲለብሱ ከተደረጉ ከተጠርጣሪው እንደ ንፁህ ተደርጎ የመቆጠር መብት (Presumption of Innocence) ጋር ምን ይመስላል የሚል ይሆናል፡፡

ማንኛውም ሰው በወንጀል ያለመጠርጠር መብት የለውም፡፡ ሆኖም አንድ ሰው በወንጀል ድርጊት ሲጠረጠር ተገቢ የሆነ የህግ ስርዓት በመከተል በፍርድ ቤት ጥፋተኛ እስከሚባል ድረስ እንደ ንፁህ ተደርጎ የመቆጠር መብት (Presumption of Innocence) አለው፡፡ ይህ መብት በየትኛውም ሃገር ያለ ሲሆን የመንግስት እና የተጠርጣሪው የመከራከር አቅምን መሰረት በማድረግ ለተጠርጣሪዎች የተሰጠ መብት ነው፡፡ በአብዛኛው ሃገራት የወንጀል ፍትህ ሥርዓት መሠረት ይህ መብት ተጠርጣሪው ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ በፍርድ ቤት ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ወይም ንፁህ እስከሚባልበት ድረስ ይዘልቃል፡፡

የተለያዩ ሃገራት የወንጀል ፍትህ ሥርዓት እንደሚያሳየው በተለይ የተጠረጠሩበት ወንጀል ውስብስብ  እና ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ በማለት ተጠርጣሪዎች ፍርድ እስከሚያገኙ ድረስ በማቆያ ወይም በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በተለይ በአንዳንድ ሀገሮች የተደራጀ የማቆያ ወይም የማረፊያ ስፍራ የሌላቸው ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ካገኙ ታራሚዎች ጋር ተቀላቅለው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ይደረጋል፡፡ በዚህን ጊዜ እነዚህ ተጠርጣሪዎች የማረሚያ ቤቱን ዩኒፎርም እንዲለብሱ የሚደረግበት እና በፍርድ ሂደታቸውም ወቅት ፍርድ ቤት ዩኒፎርሙን ለብሰው እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ የተጠርጣሪዎቹ ዩኒፈርም መልበስ እንደ ንፁህ ተደርጎ የመቆጠር መብታቸውን (Presumption of Innocence) ይጋፋል ወይ እንዲለብሱስ ይገደዳሉ ወይ የሚል ይሆናል፡፡  

ዩንፎርም ማለት ከልብስነቱ በተጨማሪ የለባሹን የማንነት፣ ስልጣን፣ ሃብት፣ የጤና ሁኔታ፣ የበታችነት እና የትምህርት ሁኔታ የሚገልፅ ሲሆን በሌላ መልኩ እንደ ተመልካቹ ልምድ፣ ግምት እና የትምህርት ሁኔታ ዩኒፎርሙን የለበሰው ሰው የተለያየ ስም እና ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡

የማረሚያ ቤት ዩኒፎርምንም በሁለት መልኩ ማየት ይቻላላ፡፡ ከማረሚያ ቤቱ በኩል ታራሚዎቹ ይህንን ዩንፎርም እንዲለብሱ የሚያደርግበት ምክንያት ታራሚዎቹ  እንደ ወንጀሉ ክብደት ከሌሎች ታራሚዎች ወይም ሰራተኞች በቀላሉ እና በርቀት እንዲለዩ፣ በቀላሉ እንዳያመልጡ፣ በራሳቸው ላይ አደጋ እንዳያደርሱ እና በተወሰነ መልኩ የታራሚዎቹን እንቅስቃሴ በአለባበስ ለመገደብ በማሰብ ነው፡፡ የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም እንደማረሚያ ቤቱ የተለያያ ከለር እና ስሪት ያለው ሲሆን እንደ ታራሚው ወንጀል አይነት የሚለብሰውም ዩኒፎርም ሊለያይ ይችላላ፣ አንዳንዴም ላይለብስ ይችላል፡፡ ከታራሚው በኩል ወይም ከማህበረሰቡ በኩል ያለው እይታ ይህንን የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም የለበሰ ሰው በወንጀል እንደተፈረደበት እና በእርምት ላይ እንዳለ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

በዚህ መሰረት ይህንን የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም ለብሶ ፍርድ ቤት የቀረበ ተጠርጣሪ ሙሉ ለሙሉ እንደ ንፁህ ተደርጎ የመቆጠር መብቱ ተከብሮለታል ቢባል አስቸጋሪ ነው፡፡ ተጠርጣሪው ይህንን የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም በመልበሱ እንደ ንፁህ ተደርጎ የመቆጠር መብቱ በተወሰነ መልኩ ቢሆንም ተሸርሽራል ማለት ይቻላላ፡፡ ምክንያቱም ይህ ተጠርጣሪ በፍርድ ቤት ውሳኔ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ እንደ ንፁህ ተደርጎ የመቆጠር መብት አለው፤ ስለዚህ ከመጀመሪያው ንፁህ ሆኖ ሳለ ይህንን ዩኒፎርም እንዲለብስ አይገደድም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ተጠርጣሪው ይህንን ዩኒፎርም ለብሶ ፍርድ ቤት በሚቀርብብት ጊዜ ማህበረሰቡም ሆነ በተለይ ዳኛው አዕምሮ ላይ ተጠርጣሪው ወንጀሉን እንደፈፀመ አድርጎ እንዲቆጥረው የስነልቦና ጫና ያሳድራል፡፡ እንደ ንፁህ ተደርጎ ከመቆጠር መብት ጎን ለጎን ተጠርጣሪው እራሱን በወንጀል ሊያስጠይቅ የሚችል ነገር ያለመናገር መብት(the right not to self-incrimination) ያለው ሲሆን የማረሚያ ቤት ዩኒፎርም መልበሱ በዳኛው እና በማህበረሰቡ ተጠርጣሪው ወንጀሉን መስራቱን የሚያሳይ እና ግምት የሚያስወስድ ከሆነ ዩኒፎርሙን ያለመልበስ መብት አለው፡፡ ከዚህ ባለፈ ተጠርጣሪው እራሱ ያንን ዩኒፎርም በመልበሱ የስነ-ልቦና ጫና እንዲደርስበት የሚያደርግ ከሆነ ዩኒፎርን እንዲለብስ አይገደድም፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎች በፍርድ ቤት ንፁህ ወይም ጥፋተኛ ተብለው እስካልተወሰነባቸው ድረስ የፍርድ ሂደታቸው እየታየ በማረሚያ ቤት በሚቆዩበት ወቅት የማረሚያ ቤቱን ዩኒፎርም እንዲለብሱ አይገደዱም፡፡ ስለዚህ ተጠርጣሪዎቹ በመደበኛ ልብሳቸው ወይም ደግሞ በራሳቸው ፍላጎት የማረሚያ ቤቱን ዩኒፎርም ለብሰው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

 

Read 7056 times Last modified on Mar 01 2018
በኃይሉ ግርማ

ጦማሪው ከመቀሌ ዩንቨርስቲ በ2000 ዓ.ም በህግ የመጀመሪያ ድግሪ፣ በ2006 ዓ.ም በወንጀል ፍትህ ስርዓት እና በሰብዓዊ መብት ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ሰርቷል፡፡ በአሁኑ ሰኣት በኢትዩጵያ ፖሊስ ዩንቨርስቲ ኮሌጅ በወንጀል ምርመራ ዲፕሎማ ፕሮግራም ማናጀር እና በመምህርነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ጽሐፊውን በኢሜል አድራሻው destabehaylu@gmail.com ማግኘት ይችላሉ፡፡