የግል የወንጀል ክስ አስፈላጊነት

Jan 04 2018

 

የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማ መሆኑ ከሚረጋገጥበት መንገድ አንዱ፣ የወንጀል ክሶች በአግባቡ ተጣርተው ለፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኞች ተገቢውን ቅጣት በተቻለ ፍጥነት ሲያገኙ ነው፡፡ ጥፋተኞች ነፃ የሚወጡበት ወይም ንጹሐን ጥፋተኞች የሚባሉበት ወይም ፍትሕ የሚዘገይበት የወንጀል አስተዳደር እንዳይኖር ማድረግ ከጥሩ አስተዳደር የሚጠበቅ ነው፡፡ በአገራችን ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አውዶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የዓቃቤ ሕግ የማስቀጣት አቅም (Conviction Rate) አነስተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ባንድ ወቅት በቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ለፍርድ ቤት ቀርበው ዕልባት ካገኙ መዝገቦች ውስጥ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው የቅጣት ውሳኔ የተሰጠው በ33.1 በመቶ መዝገቦች ብቻ ነው፡፡


በጥናቱ እንደተገለጸው፣ ብዙ የወንጀል ጉዳዮች በተለያዩ ምክንያቶች በየደረጃው ተንጠልጥለው እንደሚቀሩ ተገልጿል፡፡ ይህ ዝቅተኛ የማስቀጣት አቅም በጊዜ ሂደት እየተስተካከለ ስለመምጣቱ አመላካች ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታም የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ይታያል፡፡ በእርግጥ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የማስቀጣት አቅም ከ90 በመቶ በላይ መሆኑ ኮሚሽኑ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ላይ የሚገለጽ ቢሆንም፣ አጠቃላይ የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱን የሚወክል አይሆንም፡፡


የወንጀል ጉዳዮች ስለመዘግየታቸው፣ የማስቀጣት አቅምም ዝቅተኛ ስለመሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ይስተዋላል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ክፍተት፣ የሕጉ አተገባበር በልማድ ተፅዕኖ ውስጥ መውደቁ፣ የክስ፣ የጥፋተኝነትና የቅጣት ድርድር /Plea Bargaining/ ሥርዓት አለመኖር ወዘተ. የተወሰኑት ምክንያቶች መሆናቸው በጥናት ተገልጿል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች በባለድርሻ አካላት በሚገባ ታይተው የመፍትሔ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው (በፍትሕ አስተዳደር ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ፖሊሲ፣ በቢፒአር) ቢሆንም፣ ያልታዩ ክፍተቶች እንደሚኖሩ እሙን ነው፡፡ የፖሊስንና የዓቃቤ ሕግን ቢሮ ያጨናነቁ የግል አቤቱታ ሲቀርብ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች መበራከት የኅብረተሰቡ አጠቃላይ ሰላምና ደህንነት በይበልጥ የሚጎዱ ወንጀሎች ላይ የሚሠራውን ሥራ የተሻለ እንዳይሆን ማድረጉ አይቀርም፡፡ በግል አቤቱታ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች ቀላል የሚባሉ ወንጀሎች ሲሆኑ፣ የግል ጥቅምን የሚመለከቱ፣ በተበዳዩ ጠያቂነት ሊቋረጡ የሚችሉና ቅጣታቸውም አነስተኛ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ እነዚህ ጉዳዮች በግል ክስ ስለሚቀርቡባቸው ሁኔታ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በመመልከት የግል ክስ በሕጉ ሰፋ ያለ ቦታ ቢሰጠው ሊኖረው ስለሚችለው ጥቅም ለመዳሰስ ሙከራ ይደረጋል፡፡


የግል ክስ ምንድን ነው?


የግል ክስ ማለት አንድ ተበዳይ የተፈጸመበትን የወንጀል ድርጊት በራሱ ወይም በወኪሉ ለፍርድ ቤት ክስ የሚመሠርትበትና የሚከራከርበት ሥርዓት ነው፡፡ በእንግሊዝ የክራውን ፕሮሴኩሽን ሰርቪስም “A private prosecution is a prosecution started by a private individual who is not acting on behalf of the police or any other prosecuting authority or body which conducts prosecutions” በሚል ተመሳሳይ ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ 


የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት በየአገሮቹ ከመዋቀሩ በፊት የወንጀል ክሶች በተበዳይ ሲቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ በዘመናዊው ዓለም ግን በመርህ ደረጃ የወንጀል ጉዳዮችን የሚያጣራው፣ የሚመረምረውና ክስ የሚያቀርበው ዓቃቤ ሕግ በፖሊስ በመታገዝ ነው፡፡ ሆኖም የዓቃቤ ሕግ ከተቋቋመም በኋላ ተገቢ ባልሆኑ ምክንያቶች ዓቃቤ ሕግ ክስ አላቀርብም በሚልበት ወቅት ተበዳዮች ወይም ወኪሎቻቸው ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን ለማስከበር ክስ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እየዳበረ መጥቷል፡፡ ወሰኑ ቢለያይም የግል ክስ በተለያዩ አገሮች ሕግ የተካተተ ሲሆን፣ ዋናው ዓላማ የዓቃቤ ሕግን ፈቃድ ሥልጣን (Discretion) መቆጣጠርና ኅብረተሰቡ በፍትሕ አስተዳደር ያለውን ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የግል ክስ በአገራችን


በ1954 ዓ.ም. የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ የግል ክስን በሁለት ሁኔታዎች ይፈቅዳል፡፡ የመጀመሪያው የክስ አቤቱታ በማቅረብ ብቻ በሚያስቀጣ የወንጀል ነገር ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ጥፋተኛ ለማድረግ በቂ የሆነ መረጃ የሌለ መሆኑን ተረድቶ ክስ አላቀርብም ካለ ተበዳዩ ወይም ወኪሉ የግል ክስ እንዲያቀርብ በጽሑፍ የሚፈቅድበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ ተፈጻሚ የሚሆነው ቀለል ላሉ ወንጀሎች ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ስም ማጥፋት፣ ስድብ፣ ቀላል የአካል ጉዳት፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ አመንዝራነት፣ ዛቻ ወዘተ. ጉዳዮች ናቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዓቃቤ ሕጉ የፈቀደበትን ውሳኔ ግልባጭ ክሱን ለማየት ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ለመላክ እንደሚገደድ የሕጉ አንቀጽ 44(1) ያመለክታል፡፡ ሁለተኛው የግል አቤቱታ ሳያስፈልግ የሚያስቀጣ ወንጀልን የሚመለከት ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕጉ ማስረጃው ለማስከሰስ በቂ አለመሆኑን ሲወስን ተበዳዩ ወይም ወኪሉ ውሳኔውን ተቀብሎ በ30 ቀናት ውስጥ ዓቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ እንዲሰጠው ክሱ ቢቀርብ ኖሮ ለማየት ሥልጣን ይኖረው ለነበረው ፍርድ ቤት የሚያቀርብበት ሁኔታ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን አይቶ ዓቃቤ ሕጉ ክሱን እንዲያቀርብ ለማዘዝ የሚቻልበት ሁኔታ ስለመኖሩ በአንቀጽ 47 ላይ ተገልጿል፡፡ ሆኖም የክስ አቤቱታ ሳያስፈልግ የሚያስቀጣ ወንጀልን በተመለከተ የግል ክስ አቀራረብ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 44(2) እና 45 የተሻሩ በመሆናቸው በአሁን ወቅት ተፈጻሚነት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ከባድ በሆኑ ወንጀሎች ለምሳሌ ግድያ፣ መደፈር፣ ስርቆት፣ መጠለፍ፣ አታላይነት፣ እምነት ማጉደል፣ ወንበዴነት፣ ዘረፋ ወዘተ. ዓቃቤ ሕጉ በቂ ማስረጃ ስለሌለኝ ክስ አልመሠርትም ብሎ ከወሰነ ተበዳዩ ወይም የተበዳዩ ወኪል ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ (ወይም ለሚኒስቴሩ) አስተዳደራዊ አቤቱታ ከማቅረብ በስተቀር በፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት የመጠየቅ መብት አይኖረውም፡፡ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ የግል ክስ ከባድ በሆኑ ወንጀሎችና ክትትላቸው ልዩ ሥልጠና በሚጠይቁ ወንጀሎች ጭምር የሚፈቀድበት ሁኔታ ያለ ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንዳስሰው የግል ክስ በቀላል ወንጀሎች (የክስ አቤቱታ በማቅረብ ብቻ የሚያስቀጡ ወንጀሎች) ያለውን አፈጻጸም ነው፡፡


የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ የግል ክስ የሚቀርብበትን ሥርዓት በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን የተበዳዩን፣ የዓቃቤ ሕግንና የፍርድ ቤትንም ድርሻ አመላክቷል፡፡ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ስለግል ክስ የያዘውን ዋና ዋና ነጥቦች እንመልከት፡፡ በመጀመሪያ የግል ክስ የሚቀርበው ዓቃቤ ሕግ በጽሑፍ ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፡ ዓቃቤ ሕጉ ለመክሰስ በቂ ማስረጃ አለመኖሩን አምኖ ተበዳዩ የግል ክስ እንዲያቀርብ ካልፈቀደለት የግል ክስ አይኖርም፡፡ ስለዚህ በወንጀል የግል ክስ አፈጻጸም በአገራችን በቅድመ ሁኔታ የታሰረ (Conditional) በመሆኑ የግል ክስ መብት እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ በእርግጥ ዓቃቤ ሕግ ማስረጃውን መርምሮ አያስከስስም ያለውን ጉዳይ የግል ተበዳዩ ሊያስከስስ መቻሉን ማስረዳት የሚከብደው ቢሆንም፣ በጠበቃ በመታገዝ የዓቃቤ ሕጉ ስህተት ካለ ለማረም የሚያመች መሆኑ በጎ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ የግል ክስ እንደያቀርብ የተፈቀደለት የግል ከሳሽ የሚከራከረው በራሱ ኃላፊነትና ኪሳራ ነው፡፡ /አንቀጽ 47/፤ ክሱንም በ15 ቀን ጊዜ ውስጥ አቤቱታውንና የክሱን ማመልከቻ ለሚፈቅድለት ፍርድ ቤት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ /አንቀጽ 150/ ይህ ደንብ ተበዳዩ የማያስከስስ ጉዳይን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ተከሳሽን እንዳያጉላላ ተበዳዩ ገንዘብ ፍርድ ቤት የሚያስቀምጥበትን ሥርዓት ጭምር ያስቀምጣል፡፡ ሦስተኛ ዓቃቤ ሕጉ የግል ክሱ ከቀረበ በኋላ ጉዳዩን የመከታተል መብት አለው፡፡ በሕጉ አንቀጽ 48 ላይ እንደተገለጸው በግል ክስ ከቀረበው ወንጀል የበለጠ ከፍ ያለ ወንጀል ለመሠራቱ ለግል ክሱ በቀረበው ማስረጃ የተገለጸ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕጉ አዲስ ክሱን እስኪያቀርብ ድረስ የግል ክስ እንዲቆም ፍርድ ቤቱን ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቱም በዚሁ መሠረት ክሱን ማቆም አለበት፡፡ ስለዚህ የግል ክሱ በሚቀርበበት ጊዜም ዓቃቤ ሕጉ የክሱን ይዘት በማየት የራሱን ዕርምጃ የሚወስድበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሆኖም የግል ክስ ከመቅረቡ በፊት ስለሚደረገው የምርመራ ሁኔታና የፖሊስ እገዛ ሕጉ የሚለው ነገር ባለመኖሩ ክፍተቱ አፈጻጸሙን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ በአራተኛ ደረጃ የግል ክስ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ ለማስታረቅ ጥረት እንዲያደርግ ሕጉ ያመለክታል፡፡ በአንቀጽ 151 እንደተገለጸው፣ ፍርድ ቤቱ ማመልከቻውን ከማንበቡ በፊት ተከራካሪዎቹን (የግል ከሳሽንና ተከሳሹን) ለማስታረቅ ይሞክራል፡፡ ዕርቅ በተደረገ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ዕርቁን በመዝገብ ይጽፋል፡፡ ዕርቁም የፍርድ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ዕርቅ ካልተደረገ ግን ከሳሽ በቂ የኪሳራ ዋስትና እንዲሰጥ ተደርጐ ሙግቱ ይቀጥላል፡፡


የግል ክስን አተገባበር በተመለከተ በቂ ጥናት የለም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ኅብረተሰቡ የወንጀል ጉዳይ በሙሉ ለዓቃቤ ሕግ የተተወ መሆኑን በመረዳትና በቂ የአተገባበር ተሞክሮም ባለመኖሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ ለወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ የማሻሻያ ግብዓት ሲያዘጋጅ የግል ክስ አድማስን ለማስፋት የሚቻልበትን ሁኔታ በማጥናት ላይ የነበረ ስለመሆኑ ጸሐፊው መረጃ አለው፡፡ በጥናቱ ወቅት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በአምስት ክልሎች የግል ክስ ቀርቦ አያውቅም፤ መረጃውን የሰጡት ባለሙያዎች እንደገለጹት የግል ክስ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ውስጥ ስለመገኘቱም ያለው እውቀት አነስተኛ ነው፤ ዓቃቤ ሕግም የወንጀል ጉዳዮችን ለግል ክስ የሚመራበት አጋጣሚ አይስተዋልም፡፡ ሆኖም ብዙኅኑ ባለሙያዎች የግል ክስ በግል አቤቱታ ለሚያስከስሱ ወንጀሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ቢፈቀድ የዓቃቤ ሕግን ሥራ ከማቃለሉም በተጨማሪ ዓቃቤ ሕግ ኃይሉን አሰባስቦ ከበድ ያሉ ወንጀሎች ላይ በመሥራት የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ያስችለው ነበር ሲሉ አስተያየታቸውን ይገልጻሉ፡፡  


የሌሎች ልምድ ምን ይመስላል?


የተለያዩ አገሮች ዓቃቢያነ ሕግ ያሉባቸውን የሥራ ጫናና የጉዳይ መደራረብ መነሻ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል የተለያዩ ዘዴዎችን በሕግ ሥርዓታቸው ይተገብራሉ፡፡ የተወሰኑ አገሮች ጉዳዮችን ከዓቃቤ ሕግ ውጪ ላሉ የሕግ ባለሙያዎች በመስጠት (Outsourcing)፣ ተበዳዮች የግል ክስ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ አልፎ አልፎም ቀላል የሚባሉ ወንጀሎች በግል ድርድርና እርቅ የሚያልቁበትን ሥርዓት በመዘርጋት መፍትሔ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች የሕግ ሥርዓት ደግሞ ዓቃቤ ሕግ በመንግሥት አስፈጻሚ አካል ተጽዕኖ በሚወድቅባቸው የፖለቲካ ጉዳዮች የወንጀል ክስ ለመመስረት ቸል ሲል አንዳንዴም ኅብረተሰቡ በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ እንዲሳተፍ ማድረግ ከዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ አንጻር ስለሚታመንበት የግል ክስ የሚፈቅዱበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንዶቹ ለማንኛውም ዓይነት ክስ የሚፈቅዱ ሲሆን፣ ሌሎች (አብዛኛዎቹ) ደግሞ በግል አቤቱታ ለሚያስከስሱ ወንጀሎች ይፈቅዳሉ፡፡ የተወሰኑትን እንመልከት፡፡


እ.ኤ.አ. በ1985 የአውሮፓ የሚኒስቴሮች ኮሚቴ ካውንስል የወንጀል ሰለባዎች (ተበዳዮች) ዓቃቤ ሕግ ለመክሰስ አሻፈረኝ በሚልበት ወቅት ሥልጣን ባለው አካል እንደገና እንዲታይላቸው ካልሆነም የግል ክስ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በእንግሊዝ የወንጀል ተበዳዮች በዓመት እስከ ሦስት በመቶ የሚሆኑ የግል ክሶችን ያቀርባሉ፡፡ በጀርመን የግል ክስ በሁለት ሁኔታዎች ይፈቀዳል፡፡ የመጀመሪያው ግላዊነትን መጣስን (Domestic Trespass) የመሳሰሉትን ቀላል ወንጀሎች (Minor Offences) በተበዳዩ ክስ እንዲቀርብባቸው ይፈቅዳሉ፡፡ ሁለተኛው በወንጀል የተበደለ ሰው ዓቃቤ ሕጉ ክስ እንዲያቀርብለት ጠይቆ እምቢ ከተባለ ተበዳዩ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱ ክስ እንዲመሠርት ትዕዛዝ የሚሰጥ ከሆነ ተበዳዩ ‹‹ተጨማሪ ዓቃቤ ሕግ›› (Supplementary Prosecutor) ሆኖ ተሰይሞ ዓቃቤ ሕጉ ጉዳዩን በአግባቡ እያቀረበው መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ በሜክሲኮ በ2000 የተሻሻለው ሕገ መንግሥት ተበዳዮች ጠበቃ በመቅጠር ዓቃቤ ሕጉን በምርመራ፣ በመሰማትና በማስረጃ አቀራረብ ወቅት እንዲያግዙ የማድረግ መብት ደንግጓል፡፡ በካናዳ የግል ክስ በቀላል ወንጀሎች የሚፈቀድ ሲሆን፣ የሕግ ማሻሻያ ኮሚሽን የግል ክስ የሕዝብ ተሳትፎን ስለሚያረጋግጥ በተወሰኑ ሌሎች ወንጀሎችም ላይ እንዲፈቀድ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በማሻሻያው መሠረት ግለሰቦችን የሚወክሉ ቡድኖች (Public Interest Groups) በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ክስ የሚመሠርቱበትን ሁኔታ ያሰፋል፡፡ በደቡብ አፍሪካም በተግባር ብዙ ተሞክሮም ባይኖር በሕግ ለተገለጹ ወንጀሎች ዓቃቤ ሕግ ክስ ለማቅረብ ወደኋላ በሚልበት ጊዜ የግል ክስ የሚፈቀድበት ሁኔታ አለ፡፡የግል ክስ ጥቅም


የግል ክስ የተወሰኑ ጥቅሞች እንዳሉት በርዕሱ ላይ የተጻፉ መጽሐፍት ይገልጻሉ፡፡ ቀዳሚው በማንኛውም የሕግ ሥርዓት በተለይ ከወንጀል ጋር በተያያዘ ዜጎችን ማሳተፉ መሠረታዊ ጠቀሜታው ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ክሱን ወደ ፍርድ ቤት እንደማይወስድለት የተነገረው ተበዳይ ክሱን ፍርድ ቤት በማቅረብ የሥርዓቱ ተሳታፊ መሆን ይችላል፡፡ የግል ክስ መፍቀድ ከዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው፡፡ 

ሁለተኛው ተበዳዩ ወንጀል የፈጸመውን ሰው በሕግ አግባብ ለመበቀል ያስችለዋል፡፡ ተበዳዮች በፍርድ ቤት በሚያቀርቡት ክስ ጥፋተኛው የሚቀጣ ከሆነ ተገቢ ወዳልሆነ የራስ መፍትሔ (Self-help) እንዳይሄዱ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል የዓቃቤ ሕግንም ሥራ ቢሆን እጅጉን ያቀልለታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ሰላም የሚያናጉ ወንጀሎች ላይ አጽንኦት በመስጠት ጉዳዮችን በተቻለ ፍጥነት ለማስተናገድ ያስችለዋል፡፡ ዓቃቤያነ ሕግ ፖሊሶች አጣርተው ያመጡላቸውን ጉዳዮች በአግባቡ ለማስተናገድ የሚችሉበት የሰው ኃይል፣ የጊዜና ሌሎች ሀብቶች የሌላቸው መሆኑ በብዙ አገሮች መስተዋሉ የግል ክስን ጥቅም ከፍ ያደርገዋል፡፡

ሌላው የግል ክስ በአግባቡ ከተመራ የወንጀል ጉዳዮች በፍጥነት እልባት እንዲያገኙ ይረዳል፡፡ ለተጠረጠሩ ሰዎችም ቢሆን ጉዳዮች በፍጥነት መጠናቀቃቸው በመዘግየቱ የሚደርስባቸውን የገንዘብ ወጪና የስሜት መጐዳት ያቀልላቸዋል፡፡ 


የግል ክስ ያለውን ጥቅም ያህል ግን የራሱ አሉታዊ ጎኖች ይኖረዋል፡፡ በብዛት የሚጠቀሰው ተግዳሮት ተበዳዮቹ ተከሳሽን ለማንገላታት ሊጠቀሙበት መቻሉ ነው፡፡ ተበዳዩ ወይም ጠበቃው የክርክሩን ጊዜ በማርዘምና ያለአግባቡ ክርክሮችን በማንሳት ተከሳሹ እንዲጉላላ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሆኖም የግል ክስ የማቅረብ መብት ያለዓላማው ሥራ ላይ እንዳይውል የተወሰኑ ሥርዓቶችን መዘርጋት ግድ ይላል፡፡ የግል ክስ የማቅረቢያን ጊዜ መወሰን፣ የግል ክስ ከመቅረቡ በፊት በተከሳሽ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ከሳሹ ገንዘብ በፍርድ ቤት እንዲያስቀምጥ ማድረግ፣ የፍርድ ቤቱን ቁጥጥር ማስፋት፣ የግል ክስ ፍሬ አልባ ሲሆን ተከሳሹን በመካስ የግል ክስ መብት በአግባቡ እንዲሠራበት ማድረግ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል የግል ክስ ገንዘብ ላላቸው ተበዳዮች የሚሠራ ነው በሚል ተቀባይነቱን የሚያሳንሱ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ ይህም ቢሆን የግል ክስ የዓቃቤ ሕግን ሥራ በማገዝ ጎን ለጎን የሚሄድ ማድረግ የሚቻል ሲሆን፣ የተበዳይን መብት የሚወክሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማስፋት ተደራሽነቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

እናጠቃለው፤ ወንጀልን መከላከልም ሆነ ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ ክስ መሥርቶ መቅጣት የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡ ሆኖም በግል አቤቱታ የሚያስቀጡ ወንጀሎች በአብዛኛው የሕዝብ ጥቅምን የሚመለከቱ አይደሉም፡፡ በተበዳዩ አቤቱታ የሚከሰሱ፣ የሚቀጥሉ ወይም የሚቋረጡ ናቸው፡፡ የግል ክስ ለቀላል ወንጀሎች እንዲፈቀድ ማድረግ ሕዝቡን በፍትሕ ሥርዓት ለማሳተፍ የሚረዳ ሲሆን፣ የዓቃቤ ሕግንም የሥራ ጫና ያቃልላል፡፡ በብዙ አገሮች የሕግ ሥርዓት የግል ክስ ተካትቶ ውጤታማ ሆኗል፡፡ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ የግል ክስ ለቀላል ወንጀሎች የሚፈቅድ ቢሆንም፣ በዓቃቤ ሕጉ ፈቃደ ሥልጣን ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም የግል ክስን በብሔራዊ ደረጃ በማጥናት በሚሻሻለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ማካተት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡

Read 8795 times
Getahun Worku

The blogger is an advocate and consultant at law and he is a columnist in the "Behig Amlak" column of the Reporter Amharic version. He graduated from Addis Ababa University Law Faculty in 2001 for his undergraduate and 2010 for his masters in Human rights law. ጸሐፊውን በ getukow@gmail.com ማግኘት ትችላላችሁ::