የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት ሹመት አጸደቀ፡፡ ምክር ቤቱ አቶ ዳኜ መላኩ መሐሪን ፕሬዝዳንት፤ አቶ ጸጋዬ አስማማው ነጋን ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾሟል፡፡ ሹመቱ የጸደቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም ለፌዴራል ከፍተኛና አንደኛ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እጩዎችን ባቀረቡት መሠረት ነው፡፡ እጩዎቹ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 81 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መሠረት በሕግ ትምህርት የሰለጠኑ፣ በልምድም በቂ የሕግ ዕውቀት ያላቸው በታታሪነትና በሥነ-ምግባር መልካም ስም ያተረፉና እድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት አቶ ዳኜ መላኩ በ1980 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ አስተዳደር አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነትና በዳኝነት እንዲሁም በአዲስ አበባ የዞን ፍርድ ቤት እና በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከየካቲት 30 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ድረስም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተሾሙት አቶ ጸጋዬ አስማማው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1986 የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከ1987 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በመቀሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንዲሁም የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን አገልግለዋል፡፡ አቶ ጸጋዬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም የአዲስ አበባ ምርጫ ቦርድ ቢሮ ኃላፊ በመሆንም ሰርተዋል፡፡ ወደ ትግራይ ክልል በመመለስም የክልሉ የጸጥታና አስተዳደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ አማካሪም ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን ተሹመዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ሹመቱን ያጸደቀ ሲሆን እጩዎቹ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት በአቶ መድህን ኪሮስ አማካኝነት ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ስላሴ ተሿሚ ፕሬዝዳንቶችም ሆነ ዳኞችን በእጩነት ለማቅረብ ከአንድ አመት በላይ መውሰዱን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አስመላሽ ተሿሚዎቹ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማስታወቂያ በማውጣት በሁሉም ክልሎች የሚገኙ መስፈርቱን የሚያሟሉ ግለሰቦች እንዲወዳደሩ ተደርጓል፡፡
የጠቅላይ ፈርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን የተሾሙት አቶ ዳኜ መላኩ "በፍርድ ቤቶች አካባቢ የሚነሱ ችግሮችን ለማስወገድ ጠንክሬ እሰራለሁ" በማለት ተናግረዋል፡፡ "የመልካም አስተዳደር ችግርን በሂደት በማስወገድ የፍትሕ ሥርዓቱ አገሪቱ የተያያዘችውን እድገት ለማፋጠን የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ ከሌሎች አካላት ጋር በትበብር እንሰራለን" ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 34 ዳኞችን በዛሬው ዕለት የሾመ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 12ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም 37 ሴት ዳኞችን ጨምሮ 75 ዳኞች ተሹመዋል፡፡ ለሁለቱም ፍርድ ቤቶች የተሾሙት ዳኞች የሴቶች ተዋጽኦን በማስጠበቅ የተሻለ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በእጩ ዳኞች ዙሪያ የቀረበው የግል ሁኔታ መግለጫ ሰነድ ጥራት የጎደለውና ግድፈቶች የሚስተዋሉበት መሆኑን አመልክተዋል፡፡