በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ማመን የሚያስቸግር የሕክምና ስህተት ተፈጽሟል

Apr 22 2016

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የተፈጸመው የህክምና ስህተት አነጋጋሪ ሆኗል

ችግሩ የተፈጠረው እንቅርቷን በቀዶ ጥገና ለማስወጣት የሁለት አመት ቀጠሮ በተሰጣት ሰላም ደሞዜ እና የሃሞት ጠጠሯን በቀዶ ጥገና ለማስወገድ የህክምና ቀጠሮ በያዘችው ሰላም ሃጎስ ላይ ነው፡፡

ጉሮሮዋ ላይ ከእንቅርት ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ያጋጠማት ሰላም ደሞዜ በዘውዲቱ ሆስፒታል ተከታታይ ህክምና ስታደርግ ቆይታ ከሁለት አመት በፊት በተሰጣት ቀጠሮ መሰረት በስፍራው ትደርሳለች፡፡ ሌላኛዋ ታካሚ ሰላም ሀጎስ ደግሞ የሃሞት ጠጠሯን ለማስወጣት በቀጠሮዋ መሰረት በሆስፒታሉ 112 ቁጥር አንደኛ ፎቅ ላይ ሰላም ደመወዜ ባለችበት ክፍል አልጋ ይሰጣታል፡፡

ማክሰኞ ሚያዚያ 11 2008 . ሌሊት የነርሶች ቡድን በክፍሉ በመግባት ሰላም ደመወዜን ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል በመውሰድ ቀደ ጥገናውን አከናውነዋል፤ ችግሩ ግን ከመጣችበት የእንቅርት ቀዶ ጥገና ባሻገር የሌለባትን የሃሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ሰርተውላታል፡፡ ከማደንዘዣ ነቅታ ሁኔታውን የተመለከተችውና በሁኔታው ግራ የተጋባችው ሰላም ደመወዜ፣የመጣሁት አንገቴ ላይ ያለውን እንቅርት ለማስወገድ እንጅ፣ የሀሞት ጠጠር በሚል ሰበብ እንዴት እንዲህ እሆናለሁ?” ብላ ብትጠይቅም የሀሞት ጠጠር ህክምናው በነጻ የተከናወነ ነው የሚል ምላሽ ይሰጣታል፡፡

ጉዳዩ ያሳሰባት ታካሚም የሀሞት ጠጠር ህክምና አድርጋ እንደማታውቅና ይህን መሰሉ ህክምና በዘፈቀደ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ብትናገርም፣በነጻ ታክመሽ እንዴት እንዲህ ታስቢያለሽ?” የሚል ምላሽን ሰጥተዋታል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላም መጀመሪያ ወዳረፈችበት ክፍል አስገብተዋት አልጋ ወደተሰጣት ክፍል ይዘዋት ተመለሱ፤ ይህ የሀሞት ጠጠር ህክምና ግን ከሰላም ደሞዜ ጎን ተኝታ የነበረችው የሌላዋ የሰላም ሀጎስ ህክምና ነበረ፡፡

የሀሞት ጠጠር አለብሽ ተብላ የመጣችው ሰላም ሀጎስ ደግሞ በሌላኛው አቅጣጫ ለቀዶ ጥገና ገብታለች፤ አስገራሚው ነገር ግን የሰላም ሀጎስን የሀሞት ጠጠር ህክምና የሚያሳየው የምርመራ ዶክመንት ነርሶቹ የት እንዳደረሱት ባይታወቅም ጠፍቷል፡፡ እናም ሰላም ደሞዜ ላይ የተሰራው የህክምና ስህተት አሁን ተራው የሰላም ሀጎስ ሆነ፤ የሀሞት ጠጠር ህክምና ማድረግ ሲገባቸው የእንቅርት ቀዶ ጥገናን ለሰላም ሀጎስ ሊሰሩ ይጣደፉ ጀመር፡፡ ምንም እንኳን ማደንዘዣ ብትወጋም የሀኪሞቹና የነርሶቹ ሁኔታ ያላማራት ሰላም ሀጎስ፣ እነሱን በማመን ማለፍ አልፈለገችምናምን ልታደርጉኝ ነው?” ስትል ትጠይቃለች፡፡

ነርሶቹና ሀኪሞቹምየአንገት ላይ ቀዶ ጥገና ልናደርግልሽ ነውበማለት ለህክምናው ያዘጋጇት ጀመር፤ሰላም ሀጎስም የታመምኩት የሀሞት ጠጠር ሆኖ ሳለ የአንገት ላይ ቀዶ ጥገናው ለምን?” በማለት ትጮሃለች፡፡ በሁኔታው የተደናገጡት ሀኪሞችና ነርሶች ሁኔታውን ሲያጣሩም፣ ሰላም ሀጎስ ዘወዲቱ ሆስፒታል የገባችው ለእንቅርት ህክምና ሳይሆን የሀሞት ጠጠሯን ልትሰራ መሆኑን አረጋግጠው የሀሞት ጠጠሯን አውጥተውላታል፡፡

አሁን ሰላም ሀጎስ በስህተት ሊሰራላት ከነበረው የእንቅርት ቀዶ ጥገና ስትተርፍ ሰላም ደሞዜ ደግሞ ሁለት ዓመት ሙሉ ጠብቃ ያገኘችው፣ ታማ የነበረውን የእንቅርት ቀዶ ጥገናና ያልታመመችውን የስህተት የሀሞት ጠጠር ቀዶ ጥገና ተሰርቶላት ጎን ለጎን ተኝተዋል፡፡ ሁለቱን ሰላሞች ቀዶ ጥገና የሰሩላቸው ሃኪሞች የሠሩትን ስህተት ከማስተካከል ይልቅ አሁንም ስህተት መሥራት መቀጠላቸውን ባለጉዳዮቹ ተናግረዋል፤ የአንዳቸውን የህክምና ውጤት ለሌላቸው በመስጠትም አነጋጋሪ ስህተታቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ባለሙያዎቹ ይህን እያደረጉ ያሉት ደግሞ የሰሩትን ስህተት ለመሸፈን ጭምር መሆኑንም ነው እነሰላም የሚናገሩት፤ ከዚህም በላይ ደግሞ የትም እንዳይሄዱ አስጠንቅቀዋቸዋል፡፡ መረጃ እጃቸው ላይ እንዳይኖርም ሁሉንም የህክምና ሂደት የሚያሳየውን መረጃ ከእጃቸው ነጥቀው ወስደውባቸዋል፡፡ በስህተት የሃሞት ጠጠር የተሰራላት ሰላም ደሞዜ የቀዶ ጥገናውን ህመም አልቻልኩትም ብላለች፤ ከፍተኛ ስቃይ እንዳለው በመግለጽ፡፡

ዛሬ ረፋድ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ባልደረባ የሆስፒታሉን ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተረፈ አሰፋን አናግሮ፣ የተፈጸመው ነገር እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው ይህን መሰሉ ስህተት በሆስፒታሉ ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የህክምናውን ስህተት የፈጸመው ዶክተር ቀዶ ጥገናውን ከፈጸመ በኋላ ጋውኑን አስቀምጦ እንደወጣ አለመመለሱን ጠቅሰው፣ ሆስፒታሉም ደመወዝ እንዳይከፈለውና ከሥራ ሙሉ በሙሉ ማገዱን ገልጸዋል፡፡

በዚህ የህክምና ሂደት ላይ የተሳተፉ ሌሎች ነርሶችና የህክምና ቡድኑ አባላት ላይም የማጣራት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመርማሪ ቡድን በሆስፒታሉ በማቅናት ጉዳዩን የማጣራት እየሠራ ነው፡፡ 

Read 51074 times Last modified on Apr 22 2016
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)