ተከሳሽ ምስክር መሆን ይችላል?

Jun 30 2015

 ተከሳሽ ምስክር መሆን ይችላል?

 

በእኛ ሀገር የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ተከሳሽ ምስክር መሆን ይችላል? ተከሳሽ ምስክር መሆን አለመሆን ጥቅምና ጉዳቱ ምንድነው?

በአንድ ወቅት አንድ አስታጥቄ የሚባል ሰው ማረሚያ ቤት ልንጠይቀው ሔደን የተናገረውን አልረሳውም፡፡ ይኼው ጓደኛችን በስድብና ማዋረድ፣ ዛቻና የእጅ እልፊት ወንጀሎች ስድስት ወር ቀላል እስራት ተወስኖበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከወረደ በኋላ፤ በክርከሩ ሂደት መመስከርና ምስክር መሆን አትችልም መባሉ እንዳሳዘነው ሲነገረን ተደንቄ ነበር፡፡

በሀገራችን የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ተከሳሽ ራሱ በተከሰሰበት ጉዳይ ምስክር መሆን እንደማይችል እንደ ዐቃቤ ሕግ እገነዘባለሁ፡፡ አንድ ተከሳሽ እንዲከላከል ከተበየነ በኃላ፣ የቆጠራቸው ምስክሮች ከመሰማታቸው በፊት የተከሳሽነት ቃሉን መስጠት ይችላል ነገር ግን ቃለ መኃላ አይፈጽምም፣ መስቀለኛ ጥያቄም አይጠየቅም፡፡ ባጭሩ ምስክር አይሆንም!

“የተከፋሁት በጥፋተኝነት ውሳኔው ወይም በቅጣቱ አይደለም፤ በጥፊ ተመታው፣ ተዛተብኝና ተሰደብኩ እንዳለው ከሳሽ እኔም ስለሆነው ነገር እንድተርክ ባግባቡ አድል ባለማግኘቴ እንጂ፡፡ እንደሱ ቃለ መኃላ ፈፅሜ መመስከርና ከዚያም በመስቀለኛ ጥያቄ መሯሯጥ ነበረብኝ፡፡ ለመስቀለኛ ጥያቄ አላንስም ነበር፡፡ የሱን ምስክርነት ሁሉም አምኗል፡፡ ርግጥ ነው የተከሳሽነት ቃል መስጠት ትችላለህ ብልው ትንሽ እንተባትበውኛል፤ ግን ማንም አልሰማኝም፣ ማንም አላመነኝም!” ሲል አስታጥቄ እያማረረ ማረሚያ ቤት ለተገኘነው ሰዎች አብራራልን፡፡

የምስክርነት ቃሉን እንዳይሰጥ የከለከለውን ሕግ ግራ እንዳጋባውና በመጨረሻ “ምክንያቱ ምንም ይሁን ምስክር እንዳልሆን ከከለከለኝ ሕግ ጋር አልስማማም፡፡ ከፍትሕ፣ ርትዕ፣ ዕኩልነትና ባጠቃላይ ከፍትሐዊ የዳኝነት መርሆዎች ጋር ይጋጫል ማለቱን አስታውሳለሁ፡፡

የአቶ አስታጥቄን አስተያየት እንዴት ያዩታል? በእኛ ሀገር የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ተከሳሽ ምስክር መሆን ይችላል? ተከሳሽ ምስክር መሆን አለመሆን ጥቅምና ጉዳቱ ምንድነው? 

Read 8904 times Last modified on Jul 07 2015
Ermias Melese

Ermias Melese earned his LLB Degree from Bahir Dar University in 2009. He is one of the founders of Ethiopian Young Lawyers Association. Currently, he is working at Ministry of Justice. He can be reached at ethiomias@gmail.com.