የኤግዚቢቶች አመዘጋገብና አቀማመጥ (የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 97 እና 124 (2))

Sep 10 2014

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 97 መሠረት ኤግዚቢት ወይም ከወንጀል አፈፃፀም ጋር በተያያዘ ወንጀል የተፈጸመበት ወይም ወንጀል ለመፈጸም በመሣሪያነት የዋሉ ቁሶች (ነገሮች) እንዴት ሊቀመጡና በማስረጃነት ሊያገለግሉ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

በዚሁ መሠረት ኤግዚቢቶች ላይ የፍርድ ቤት መዝገብ ሹም ቁጥርና ምልክት አድርጎባቸው በተጠበቀ ስፍራ ሊያስቀምጣቸው እንደሚገባና ከተቀመጡበት ስፍራም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደማይወጡ ተመልክቷል፡፡ ሆኖም በተግባር ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳዮች በኤግዚቢትነት የሚያዙ ንብረቶችን ተቀብለው አይመዘግቡም በተጠበቀ ስፍራም አያስቀምጡም፡፡

ፍርድ ቤቶች በዚህ ረገድ ኤግዚቢቶችን የሚመዘግብና በተጠበቀ ስፍራ ሊያስቀምጥ የሚችል አሠራር፣ የመዝገብ ቤት ሹም እና ኤግዚቢቶችን ለማስቀመጫነት የሚያገለግል የሚታወቅ የተጠበቀ ስፍራ የሌላቸው በመሆኑ ኤግዚቶችን የመመዝገብ እና የማስቀመጥ ኃላፊነት በፖሊስ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ፖሊስም በፌዴራል ደረጃ ወንጀል ምርመራን ከማጣራት ጋር በተያያዘ ኤግዚቢቶችን የመመዝገብና የማስቀመጥ ተግባራትን በወንጀል መርማሪዎችና ኤግዚቢቶችን ለማስቀመጥና ለመንከባከብ በተመደቡ የፖሊስ አባላት በኩል የመመዝገብና የማስቀመጥ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 124 (2) መሠረት ነገሩ በሚሠማበት ቀን ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ ኤግዚቢትን ጨምሮ ያሏቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ፍርድ ቤት የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡

በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሠረት ኤግዚቢቶች ጉዳዩን በሚያየው ፍርድ ቤት ተመዝግበው በተጠበቀ ስፍራ ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ ኤግዚቢት ባለባቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዐቃቤ ሕግ በሕጉ በተጣለበት ግዴታ መሠረት ጉዳዩ በሚታይበት ዕለት ኤግዚቢቶችን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግ ይችል ነበር፡፡

ሆኖም በተግባር ዐቃቤ ሕግ ኤግዚቢት ያለባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ኤግቪዚቱ ፍርድ ቤት ይቅረብ ብሎ ፍርድ ቤቱ ካላዘዘ በስተቀር የሚያቀርብበት ሁኔታ የለም፡፡ በመሆኑም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 97 እና 124 (2) በሕጉ በሚያዝዘው መሠረት እየተፈፀሙ ባለመሆናቸው ይህ ቢታሰብበት ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደሩ የተሻለ ጥቅም ይኖረዋል፡፡               

Read 10782 times Last modified on May 22 2015
Abiyou Girma Tamirat

Abiyou Girma is a qualified and a licensed lawyer. He obtained Bachelor of Laws (LLB), his first degree, from Saint Marry's University, Faculty of Law, in June 2007 and master's degree (MA), from Addis Ababa University Faculty of Law specializing in areas of Human Rights in 2012. He was at Ministry of Justice both as a public prosecutor and Legal adviser at International Co-operation on Legal Affairs Directorate. During his stay he has acquired an extensive experience in Civil law, commercial law and criminal Law, prosecutions, Human Rights and International Law.