Latest blog posts

ብዙውን ጊዜ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ክስ ያቀረበ ከሳሽ እና መልስ የሚሰጥ ተከሳሽ በክሳቸውና በመልሳቸው እንዲሁም በክርክራቸው ላይ ወጪና ኪሳራ የማቅረብ መብት ይጠበቅልኝ፣ ፍርድ ቤቱ ወጪና ኪሳራ በቁርጥ እንዲከፈለኝ ይዘዝልኝ ሲሉ፤ ፍርድ ቤቶች በበኩላቸው እንደጉዳዩ ዓይነትና ሁኔታ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻሉ ወይም በክርክሩ የተረታው ወገን ለረታው ወገን እንዲከፍል በሚል ትዕዛዝ ሲሰጡ መመልከቱ የተለመደ ነው፡፡ ለመሆኑ ወጪና ኪሳራ ምንድን ነው? የወጪና ኪሳራ ዓላማውስ ምንድን ነው? ወጪና ኪሳራ ሊታሰብ የሚገባው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? ሕጉ ከወጪና ኪሳራ አንፃር ለፍርድ ቤቶች የሰጠው ሥልጣን ምንድን ነው? ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ በተግባር ያለው አሠራር ምን ይመስላል? የሚሉና ሌሎች ነጥቦችን በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡

ወጪና ኪሳራ ምንድን ነው?     

ወጪና ኪሳራ ማለት በፍርድ ቤት ክርክር የሚያደርጉ ተከራካሪ ወገኖች ከክርክሩ ጋር በተያያዘ የሚያወጧቸው የተለያዩ ወጪዎች እና በክርክሩ ምክንያት የሚደርስባቸው ኪሳራ ማለት ሲሆን ተከራካሪ ወገኖች ከሳሹ ክስ ያቀረበው በተከሳሹ ምክንያት በመሆኑ በአንፃሩም ተከሳሹ ወደ ክስ የገባው በከሳሽ ምክንያት መሆኑን በማንሳት በክርክር ምክንያት ያወጡት ወጪና ኪሳራ በሌላኛው ተከራካሪ እንዲሸፈን የሚጠይቁበት አግባብ ነው፡፡ ክርክር በባሕርይው ወጪ የሚያስወጣና ውድ ሲሆን በክርክር ምክንያት የሚወጣ ወጪም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ነው፡፡

የወጪና ኪሳራ ዓላማው ምንድን ነው?  

የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከአንቀጽ 462 እስከ 466 ድረስ ወጪና ኪሳራ ስለሚጠየቅበትና ፍርድ ቤቶችም ስለሚወስኑበት እንዲሁም ሌሎች የወጪና ኪሳራ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ነጥቦች ተመክተዋል፡፡ ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ የሕጉ ዓላማም ያለአግባብና ከቅን ልቦና ውጪ የሚቀርቡ ክሶችን መከላከል፤ ክርክር ከሕግ ውጭ የቀረበ መሆኑ ሲታወቅ ደግሞ ለክርክሩ ያለአግባብ የተዳረገ ወገን በክርክሩ ምክንያት ያወጣውን ወጪና ኪሳራ ለክርክር የዳረገው ወገን እንዲተካ ማድረግ መሆኑንና ከዚህ ውጪም ዓላማው የተረታውን ወገን መቅጣት አለመሆኑን ከሕጉ መንፈስና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 4 የሰበር መዝገብ ቁጥር 22260 እና በቅፅ 15 የሰበር መዝገብ ቁጥር 91103 ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ ከተሠጡ ውሳኔዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡      

ተከራካሪዎች በክርክር ወቅት የሚያወጧቸው ወጪና ኪሳራዎች ምን ምን ናቸው?    

የከሳሽ ወጪዎች ምንድን ናቸው?

ከሳሽ በተከሳሽ ላይ የሚያወጣቸውን ወጪዎች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡ -

 • በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 (1) እና ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በ1945 ዓ.ም. በወጣው ደንብ መሠረት በክሱ እንደሚጠየቀው የገንዘብ መጠንና እንደጉዳዩ ዓይነት መዝገብ ለማስከፈት የዳኝነት ክፍያ ለፍርድ ቤቱ ለመክፈል የሚወጣ ወጪ፤
 • የቴምብር ቀረጥን አስመልክቶ በወጣው አዋጅ ቁጥር 110/1990 አንቀፅ 3 እና 10  በአዋጅ ቁጥር 612/2001 አንቀፅ 14 እንደተሻሻለው ከክሱ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የሠነድ ማስረጃዎች ላይ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ተከፍሎባቸው ምልክት ሊደረግባቸው ስለሚገባ የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ለመፈፀም የሚወጣ ወጪ፤
 • ከክሱ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ሠነዶች ወደ ፍርድ ቤቱ የሥራ ቋንቋ መተርጎም ካለባቸው ፍቃድ ባላቸው የትርጉም ቤቶች ለማስተርጎሚያ የሚወጣ ወጪ፤
 • ክስን በኮምፒውተር ማስፃፊያ፣ የኮፒ ማድረጊያ፣ በክርክር ሂደት ላይ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ መወሰድ ያለባቸው ሠነዶችን፣ ትዕዛዝና ውሳኔዎች አስገልብጦ ለመውሰድ የሚወጣ ወጪ፤
 • እንደከሳሹ አድራሻና ሁኔታ ጉዳዩ ሊታይ በሚቀጠርባቸው ቀናት ከፍርድ ቤቱ እስከ ከሳሽ መኖሪያ ቤት ድረስ ለመጓጓዣ እና ተያያዥ ሁኔታዎች የሚወጣ ወጪ፤   
 • እንደከሳሹ ፍላጎትና ሁኔታ ጉዳዩን የምከታተለው በሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) አማካኝነት ነው ካለ ለጠበቃ አበል የሚወጣ ወጪ፤
 • በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 112 መሠረት ምስክሮችና የሙያ ምስክሮች ወጪ ለመጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች እንዲሁም አበል የሚከፈል ክፍያ ፍርድ ቤቱ በሚያዘው መሠረት የሚወጣ ወጪ፤
 • ለተከሳሽ መጥሪያ ከማድረስ ጋር በተያያዘ እንደሁኔታው በጋዜጣ ጥሪ የሚደረግ ከሆነ የጋዜጣ ጥሪ ማስደረጊያ የሚወጡ ወጪዎች፤
 • ይግባኝ የሚያስብል ነገር ካለ ለይግባኝ መዝገብ ማስከፈቻ እና ተያያዥ ወጪዎች፣ እና
 • ሌሎች እንደጉዳዩ ዓይነትና ሁኔታ በክርክር ሂደት ሊወጡ የሚችሉ ወጪዎችን ይጨምራል፡፡          

የተከሳሽ ወጪዎች ምንድን ናቸው?

ተከሳሽ ከከሳሽ ለሚቀርብበት ክስ በሚሠጠው መልስና በሚያደርገው ክርክር ላይ የሚያወጣቸው ወጪዎች የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ፡ -

 • በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 215 (2)፣ 236 እና ስለ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል በ1945 ዓ.ም. በወጣው ደንብ መሠረት ተከሳሽ በከሳሹ ላይ የማቻቻያ የተከሳሽ ከሳ ክስ የሚያቀርብ ከሆነ በተከሰሽ ክሱ እንደሚጠየቀው የገንዘብ መጠንና እንደጉዳዩ ዓይነት የዳኝነት ክፍያ ለፍርድ ቤቱ ለመክፈል የሚወጣ ወጪ፤
 • የቴምብር ቀረጥን አስመልክቶ በወጣው አዋጅ ቁጥር 110/1990 አንቀፅ 3 እና 10  በአዋጅ ቁጥር 612/2001 አንቀፅ 14 እንደተሻሻለው ከመልስ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ የሠነድ ማስረጃዎች ላይ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ተከፍሎባቸው ምልክት ሊደረግባቸው ስለሚገባ የቴምብር ቀረጥ ክፍያ ለመፈፀም የሚወጣ ወጪ፤
 • ከመልስ ጋር ተያይዘው የሚቀርቡ ሠነዶች ወደ ፍርድ ቤቱ የሥራ ቋንቋ መተርጎም ካለባቸው ፍቃድ ባላቸው የትርጉም ቤቶች ለማስተርጎሚያ የሚወጣ ወጪ፤
 • መልስን በኮምፒውተር ማስፃፊያ፣ የኮፒ ማድረጊያ፣ በክርክር ሂደት ላይ ከፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ መወሰድ ያለባቸው ሠነዶችን፣ ትዕዛዝና ውሳኔዎች አስገልብጦ ለመውሰድ የሚወጣ ወጪ፤
 • እንደተከሳሹ አድራሻና ሁኔታ ጉዳዩ ሊታይ በሚቀጠርባቸው ቀናት ከፍርድ ቤቱ እስከ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ድረስ ለመጓጓዣ እና ተያያዥ ሁኔታዎች የሚወጣ ወጪ፤  
 • እንደተከሳሹ ፍላጎትና ሁኔታ ጉዳዩን የምከታተለው በሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) አማካኝነት ነው ካለ ለጠበቃ አበል የሚወጣ ወጪ፤
 • በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 112 መሠረት ምስክሮችና የሙያ ምስክሮች ወጪ ለመጓጓዣ እና ሌሎች ወጪዎች እንዲሁም አበል የሚከፈል ክፍያ ፍርድ ቤቱ በሚያዘው መሠረት የሚወጣ ወጪ፤
 • ይግባኝ የሚያስብል ነገር ካለ ለይግባኝ መዝገብ ማስከፈቻ እና ተያያዥ ወጪዎች፣ እና
 • ሌሎች እንደጉዳዩ ዓይነትና ሁኔታ በክርክር ሂደት ሊወጡ የሚችሉ ወጪዎችን ይጨምራል፡፡ 

ኪሳራ ምንድን ነው? 

በክርክር ሂደት ኪሳራ ማለት ተከራካሪዎች ለክርክሩ ከሚያወጡት ወጪ በተለየ መልኩ በክርክሩ ምክንያት ያጡትን ገቢ የሚመላክት ነው፡፡ ብዙ ጊዜም የክርክር ረቺዎች ከረቺው ላይ ኪሳራ ሲጠይቁ አይስተዋልም፡፡  

ተከራካሪዎች የሚያወጧቸውን ወጪዎች የሚሸፍነው ማን ነው?

የግራ ቀኙ ክርክር ተደርጎ ፍርድ ቤት አንዱን ረቺ ሌላኛውን ተረቺ አድርጎ ውሳኔ ከሠጠ በኋላ የግራ ቀኙ ያወጧቸውን ወጪዎች በተመለከተ ተረቺው የረቺውን ወጪዎች እንዲሸፍን በሚል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 463 (1) ላይ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲሰጥም ረቺው ያወጣቸውን ወጪዎች በሙሉ የሚያሳይ ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ አቅርቦ እና ተረቺው አስተያየት ሰጥቶበት ፍርድ ቤቱ የሚቀበለውን ተቀብሎ የተጋነነውን አስተካክሎ ክፍያ እንዲፈፀም ትዕዛዝ እንደሚሰጥ በንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ተመልክቷል፡፡     

ተረቺ ሁልጊዜ የረቺን ወጪና ኪሳራ የመሸፈን ግዴታ አለበት?

በክርክር ሂደት ላይ የተረታ ወገን ሁሉ ሁልጊዜ የረቺውን ወገን ወጪና ኪሳራ የመሸፈን ግዴታ የሌለበት መሆኑን ወጪና ኪሳራ የመሸፈን ግዴታው የሚመጣው ተረቺው ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ረቺውን ለክርክር የዳረገው ከሆነ ብቻ መሆኑን ሕጉ እና የሰበር ውሳኔዎች ያመለክታሉ፡፡   

ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት ምንድን ነው?

የሥነ ሥርዓት ሕጉ እና የሰበር ውሳኔዎቹ ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ በፍርድ ቤቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ኃላፊነችን ይጥላሉ፡፡ ከኃላፊነቶቹ መካከልም፡ -

 • በክርክሩ ላይ አንዱን ረቺ ሌላኛውን ተረቺ አድርገው ከወሰኑ በኋላ ተረቺው ረቺውን ወገን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ረቺውን ለክርክር የዳረገ ስለመሆን አለመሆኑ በጥንቃቄ መመርመር፤
 • ወጪና ኪሳራን ሲወስኑ የወጪና ኪሳራውን ልክ ብቻ ሳይሆን በተጨማሪ ወጪና ኪሳራው የሚከፈልበትን የኃብት ምንጭ የአከፋፈሉን ሁኔታና ሌላም ተገቢ ሆኖ የሚገኝ ትዕዛዝ በተያያዥነት የመወሰን፤
 • ወጪና ኪሳራ ዝርዝር የማቅረብ መብት ከተጠበቀ በኋላ ረቺው የወጪና ኪሳራ ዝርዝር እንዲያቀርብ እንዲሁም ተረቺው በዝርዝሩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥበት የማድረግ፤
 • በረቺው የሚቀርበው የወጪና ኪሳራ ዝርዝር ላይ የተጋነነ እና ያልተገባ ብልፅግና ለረቺው ሊያስገኙ የሚችሉ አለመሆናቸውን በጥንቃቄ፣ በምክንያታዊነት እና በተቻለ መጠን በማስረጃ የመመርመር፤
 • የወጪና ኪሣራ ዝርዝር ባልቀረበ ጊዜ የኪሳራውን መጠን የተጋነነ እንዳይሆን ክርክሩ የወሰደውን ጊዜ፣ የክርክሩ ውስብስብነትና አስፈላጊውን ዳኝነት ለመከታተል ተገቢ ናቸው የሚላቸውን ወጪዎች አመዛዝኖ ተመጣጣኝ መጠን ያለው ኪሣራ የመወሰን እና ሌሎች ተያያዥ ኃላፊነቶች ይገኙበታል፡፡     

ፍርድ ቤቶች ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ የሚሰሩበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ፍርድ ቤቶች በአብዛኞቹ ጉዳዮች ላይ ወጪና ኪሳራን አስመልክቶ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ላይ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻቻሉ በሚል የሚወስኑበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ሆኖም በብዙ ጉዳዮች ላይ ወጪና ኪሳራ የየራሳቸውን ይቻሉ መባሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ተረቺው ረቺውን ወገን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ለክርክር ስላልዳረገው ነው ወይ የሚለው ጥያቄ በእያንዳንዱ መዝገብ ላይ ዝርዝር ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ጥቂት በማይባሉ መዛግብት ላይ ደግሞ ወጪና ኪሳራ ግራ ቀኙ ይቻቻሉ የሚሉበት አግባብ አሳማኝነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ወጪና ኪሳራ ይቻቻሉ የሚሉበትንና ተረቺው ረቺውን ከቅን ልቦና ውጭ በሆነ ተግባር ለክርክር አለመዳረጉን በሚገልፅ ሁኔታም ምክንያትም አይጠቅሱም፡፡ ፍርድ ቤቶች ወጪና ኪሳራ ሲወስኑም በሁሉም መዛግብት ላይ በሚያስብል መልኩ የወጪና ኪሳራ መጠኑን ከማመላከት ውጪ የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 462 በሚያዘው መሠረት ወጪና ኪሳራው የሚከፈልበትን የሀብት ምንጭ፣ የአከፋፈሉን ሁኔታና ሌላም ተገቢ ሆኖ የሚገኝ ትዕዛዝ በተያያዥነት የሚወስኑበት ሁኔታ የለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በረቺ ወገን የሚቀርቡ የወጪና ኪሳራ ዝርዝር ላይ በብዛት ተጋነዋል በሚል ማሻሻያ የሚደረግበት ሁኔታ ይታያል፡፡


Editors Pick

Family Law Blog
  ሁሉም ሰው ባዮሎጂካዊ አባት አለው ሁሉም ሰው ግን ህጋዊ አባት ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ አረፍተ ነገር በብዙዎቻችሁ ጭንቅላት እንዴ! የሚል ግርምት እንደሚያጭር እገምታለሁ፡፡ በተለይ ሁሉም ልጅ እኩል ነው ልጆች አባትና እናታቸውን የማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላችሁ የሚለው አነጋገር አብዝቶ ከመሰማቱ የተነሳ በሕ...
23956 hits
Human Rights, Public Policy and Law Blog
በአገር ውስጥ እና በተለይም ወደ ሌሎች አገራት የሚካሄድ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያ ውስጥ የላቀ ትኩረት እያገኘ መጥቷል፡፡ ይህም ትኩረት በቅርቡ ጉዳዩ እያገኘ ካለው ሰፊ የሚድያ ሽፋን ባሻገር ችግሩን ለመፍታት በተከታታይ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ የሕግ፣ የፖሊሲና የፕሮግራም እርምጃዎች ላይ ይንፀባረቃል፡፡ ...
17574 hits
Intellectual Property and Copy Right Blog
  መግቢያ የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎች የአንድ ሀገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ልማትን በማፍጠን ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የዚህ ሥራ ፈጣሪዎች የሚበረታቱበትንና አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያበረክቱበት ምቹ ሁኔታ...
13894 hits
Alternative Dispute Resolution Blog
መግቢያ አለም ዐቀፍ፣ የግልግል የዕርቅና የሽምግልና ተግባራት መሠረታዊ አላማ፣ ከተለያዩ  ሀገራት ዜጐች ወይም ኩባንያዎች ጋር የንግድ ግንኙነት በመሠረቱ ወገኖች መካከል የሚያጋጥም የንግድ አለመግባባትን ከመደበኛው የፍርድ ሂደት ወይም ሥነ-ሥርዓት ውጪ በገላጋዮች፣ በአስታራቂዎች ወይም በሽምጋዮች እንደተዋዋይ ወገኖች ...
11237 hits

Top Blog Posts

Taxation Blog
  በዚህ ጽሑፍ ስለ ግብር ስወራ ምንነት፣ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ሥር የግብር ስወራ ስለሚያቋቋሙ ድርጊቶች፣ ለግብር ስወራ መነሻ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምክንያቶች እንዲሁም የመከላከያ መንገዶቹ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጉምሩክና ታክስ ወንጀል ችሎት...
About the Law Blog
  መግቢያ የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረውና የተከራየን ሰው ማስወጣት (በርግጥ ደንቡ ይህን ድርጊት አልከለከለም) እና የኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 ማራዘሙን በድጋሜ አስታዉቋል፡፡ ይህ ደንብ የቤት አከራዮች ያከራዬት ቤት ላይ ዋጋ እንዳንይጨምሩ ...
Taxation Blog
It is perplexing for me, as a tax lawyer having worked for close to 10 years on Ethiopian tax laws, to see how the investment and finance community in Ethiopia is not worrying enough about the tax on ...
Succession Law Blog
መግቢያ ማንኛውም ሰው አንድ የፍርድ ውሰኔ ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ያለው እንደሆነ ጉዳዩን ለማየት በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ሊያቀርብ ሚችልበት የጊዜ ገደብ በልዩ ልዩ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡ ይህን መሰል የጊዜ ገደብ በሕግ አጠራር ይርጋ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጓሜውም በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደ...