በሌላ ሰው የተፃፈን መፅሀፍ የራሱ ለማድረግ ሲል ገዳዮችን በመቅጠር ያሰማራው ግለሰብና በአሰቃቂ ሁኔታ ግድያ የፈፀሙት አምስት ተከሳሾች በሞት እና እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ።
ተከሳሾች አበባየሁ ሳሙኤል፣ አስፋው አጌቦ፣ መካሻ ብርሃኑ፣ ኤፍሬም ዋደላ፣ ወጣት ሜሮን አየለና አብርሃም አቶታ ናቸው።
1ኛ ተከሳሽ አበባየሁ ሳሙኤል የመጀመሪያ ዲግሪ ያለውና የልብ ወለድ ፀሃፊ ሲሆን፥ ዶክተር ቢንያም ማሞ የፃፈውን መፅሃፍ የራሱ ለማድረግ ቀደም ብሎ የፍርድ ሂደት ካገኘው ከአቡሽ ተክሌ ጋር ያልማል።
በዚህም ከ2ኛ ተከሳሽ፣ ከ3ኛ እና 5ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን መፅሃፉን በእጃቸው በሚያስገቡበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ።
ለዚህም እንዲረዳቸው 5ኛ ተከሳሽ ሜሮን አየለ የዶክተር ቢንያም የፍቅር ጓደኛ ትሆናለች።
ነሃሴ 20 ቀን 2006 ዓ.ም ሜሮን፥ ሟች ዶክተር ቢንያምን እኩለ ሌሊት ላይ በስልክ ጠርታ አብረው ይቆያሉ።
ቦታውና ቀበሌው በማይታወቅ አካባቢም 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ ተከሳሾች ከአቡሽ ተክሌ ጋር በመሆን ሟችን በጉልበት በመያዝ የሞባይል ቀፎውን፣ የለበሰውን ጃኬትና ጫማ እንዲሁም የመፅሃፉን ረቂቅ ሰርቀው ይሰወራሉ።
ተከሳሾቹ ለ1ኛ ተከሳሽ የመፅሃፉ ባለቤት በህይወት እያለ መፅሃፉን መጠቀም እንደማይችልና ለዚህ እንዲረዳውም ዶክተር ቢንያም መሞት እንዳለበት ነግረውት በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
ለተልዕኮው ማስፈጸሚያም፥ ለ2ኛ ተከሳሽ 30 ሺህ ብር፣ ለ4ኛ ተከሳሽ 15 ሺህ ብር እንዲሁም ለ5ኛ ተከሳሽ 5 ሺህ ብር ከ1ኛ ተከሳሽ ይሰጣቸዋል።
ተከሳሾቹም ዶክተር ቢንያምን በመኪና በማፈን በሻሸመኔ ከተማ መልካ ኦዳ ወደ ሚባል ስፍራ በመውሰድና እንጨት ላይ በማሰር እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ አሰቃይተው ይገድሉታል።
ነሃሴ 30 ቀን 2006 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ አስከሬኑን አርሲ ነጌሌ ወረዳ፣ ዳካ ሃረቀሎ ቀበሌ ወስደው ይጥሉታል።
በመጨረሻም በህዝብና በፖሊስ ትብብር ተይዘው አቃቤ ህግ አሰቃቂና ዘግናኝ የግድያ ወንጀል በመፈፀም ክስ መስርቶባቸዋል።
ተከሳሾቹም ፍርድ ቤት ቀርበው የቀደመ የወንጀል ሪከርድ የለብንም በማለት የቅጣት ማቅለያቸውን አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንዳለባቸው በማረጋገጥ ማቅለያውን ውድቅ አድርጓል።
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የምዕራብ አርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የመጨረሻ ውሳኔውን አስተላልፏል።
አበባየሁ ሳሙኤል፣ አስፋው አጌቦ፣ መካሻ ብርሃኑ እና ኤፍሬም ዋደላ ላይ የሞት ቅጣት ከፍርድ ቤቱ ተወስኖባቸዋል።
አቡሽ ተክሌ እና ሜሮን አየለ ላይ ደግሞ እያንዳንዳቸው በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔውን አስተላልፏል።
6ኛ ተከሳሽ አብርሃም አቶታ ደግሞ በቀላል የስድስት ወር እስራት እንዲቀጣ ውሳኔውን አስተላልፏል።