Latest Blog posts
Editors Pick
Latest documents
Education and Training Policy of Ethiopia - Amharic version - 2023 7263 Downloads - policies and strategies | 7.6 MB | |
The Normative Basis for Decision on the Merits in Commercial Arbitration - the Extent of Party Autonomy 218 Downloads - Arbitration Law | 635.59 KB | |
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም የሰጠባቸው ውሣኔዎች ማውጫ ቅጽ 01-25 9027 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 10.72 MB | |
ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ እይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ FEATURED 408 Downloads - Criminal Law | 317.19 KB | |
Federal Supreme Court Cassation Decisions - Table of content Volume 1-25 10533 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 6.57 MB |
- Details
- Category: Legal News - የሕግ ዜናዎች
ኢትዮጵያ በፔትሮትራንስ ኩባንያ የተመሠረተባትን የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ክስ አሸነፈች
በፈረንሣይ ፓሪስ በሚገኘው የዓለም አቀፍ ንግድ ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት ፍርድ ቤት፣ ፔትሮትራንስ ኩባንያ ሊሚትድ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የመሠረተው የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ክስ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተደመደመ፡፡ የፍርድ ቤት ክርክሩ በጄኔቫ ስዊዘርላንድ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲካሄድ ቆይቶ፣ ፍርድ ቤቱ ሰኞ ጥር 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ መስጠቱን ከታመኑ የዜና ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በኦጋዴን የሚገኙ የነዳጅና የጋዝ ብሎኮችን ፔትሮትራንስ ሊሚትድ ለተሰኘ ኩባንያ ከአራት ዓመታት በፊት በአምስት ስምምነቶች መሠረት ስለመስጠቷ፣ ኩባንያውም በገባው ውል መሠረት ግዴታዎቹን ሊወጣ ባለመቻሉ አምስቱም የነዳጅ ፍለጋ፣ ምርትና ክፍፍል ስምምነቶች በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት ስለመሰረዛቸው፣ ይህንኑ የውሎች መሰረዝ አስመልክቶ የፔትሮትራንስ ኩባንያ ሊሚትድ የኢትዮጵያ መንግሥትን በፓሪስ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ስለመክሰሱና ክርክሩም በመካሄድ ላይ ስለመሆኑ፣ በሪፖርተርና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የዜና ምንጮች እንደጠቆሙት ፔትሮትራንስ ኩባንያ ሊሚትድ ለፓሪሱ ፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰረዛቸው አምስቱ የነዳጅ ፍለጋ፣ ምርትና ክፍፍል ስምምነቶች ሕገወጥ ናቸው ተብሎ ወደ ሥራው እንዲመለስ እንዲወሰንለት፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በጥቅሉ አንድ ቢሊዮን አራት መቶ ሺሕ ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ጠይቆ ነበር፡፡
ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርድ የኢትዮጵያ መንግሥት አምስቱን የነዳጅ ፍለጋ፣ ምርትና ክፍፍል ስምምነቶች የሰረዘው በሕግ አግባብ መሆኑን፣ ፔትሮትራንስ በአማራጭ በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲከፈለው የጠየቀው አንድ ቢሊዮን አራት መቶ ሺሕ ዶላር ሊከፈለው እንደማይገባ፣ በክርክሩ ሒደት ኢትዮጵያ ለዳኝነት ያወጣችውን ወጪ ከፊሉን ፔትሮትራንስ ኩባንያ እንዲመልስላት በመፍረድ፣ ኢትዮጵያን በታሪኳ ለቀረበባት ከፍተኛ ክስ ሙሉ በሙሉ አሸናፊ አድርጓታል፡፡
ታዳጊ አገሮች በተለይ የአፍሪካ መንግሥታት በዓለም አቀፍ የንግድና የኢቨስትመንት ፍርድ ቤቶች በሚቀርቡባቸው ክሶች ብዙውን ጊዜ በተሸናፊነት የሚሸኙ መሆኑ ቢታወቅም፣ በኢትዮጵያ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ በክሱ መጠን ግዙፍነት በመሪነት በሚጠቀሰው በዚህ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክርክር፣ ኢትዮጵያ በአሸናፊነት ማጠናቀቋ ለሌሎችም የአፍሪካ መንግሥታት ድል ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል የተከራከረው ዓለም አቀፍ የጥብቅና ቢሮ በአሜሪካ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውና በቀድሞ መጠሪያው አዲስ ኢንተርናሽናል አርቢትሬሽን ግሩፕ ኤልኤልፒ (Addis International Arbitration Group LLP) የተሰኘው፣ አሁን ደግሞ አዲስ ሎው ግሩፕ ኤልኤልፒ (Addis Law Group LLP) በመባል የሚጠራው ዓለም አቀፍ የጥብቅና ቢሮ፣ ግሪንበርግ ትራውሪግ ኤልኤልፒ (Greenberg Traurig LLP) ከተሰኘውና በዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ የጥብቅና ቢሮ ጋር በመቀናጀት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፔትሮትራንስ ኩባንያ ሊሚትድን በመወከል የተከራከሩት ዓለም አቀፍ የጥብቅና ቢሮዎች ደግሞ በመጀመርያ ኖርተን ሮዝ ፉልብራይት፣ በኋላ ደግሞ ይህን ቢሮ የተካው ላሊቭ (Lalve) የተሰኘው ዓለም አቀፍ የጥብቅና ቢሮ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የፔትሮትራንስ ኩባንያ ፕሬዚዳንት ጆን ቺን እ.ኤ.አ. በጁላይ 2011 በአዲስ አበባ በሸራተን አዲስ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት፣ ከቀድሞዋ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ ጋር አምስት የነዳጅ ፍለጋ፣ ምርትና ክፍፍል ስምምነቶች ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ፔትሮትራንስ ተቀማጭነቱ ሆንግ ኮንግ የሆነ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡