መጥሪያ በመኖሪያ ቤቷ ላይ ቢለጠፍላትም አለመቅረቧ ተገልጿል
የቤጂንግ ኦሎምፒክ ድርብ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የእሷ መሆኑ የተገለጸው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ፣ በተሳፋሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት በማድረሱ ምክንያት በተመሠረተባት የፍትሐ ብሔር ክስ ቀርባ ባትከራከርም፣ በኦሮሚያ ክልል የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጉዳት ካሳ እንድትከፍል ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡
ክሱ የተመሠረተው በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ በባለቤቷ አትሌት ስለሺ ስህንና በአሽከርካሪው አቶ ታምራት ቤኛ ላይ መሆኑን ፍርድ ቤቱ የሰጠው የውሳኔ ሰነድ ያስረዳል፡፡
ንብረትነቱ የአትሌት ጥሩነሽ መሆኑ የተገለጸው የሰሌዳ ቁጥሩ 3-15723 ኦሮ የሆነው የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ፣ ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. በዓል ለማክበር ከአሰላ ወደ ሸንኮራ ዮሐንስ በመሄድ ላይ እያለ፣ ሞጆ አካባቢ ሉሜ ወረዳ ዳንሳ ሹምቡሬ በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ተገልብጦ፣ በተሳፋሪዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ማድረሱን የውሳኔው ሰነድ ያብራራል፡፡
በወቅቱ ተሳፍረው ከነበሩት ውስጥ ወ/ሮ አዱኛ ለሜቻ የተባሉ ግለሰብ የቀኝ ጆሮአቸው ሙሉ በሙሉ ሲቆረጥ፣ የግራ እጃቸው ሁለት ጣቶችም መቆረጣቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ የቀኝ እጃቸው ተሰብሮ ከጥቅም ውጪ መሆኑንና በአጠቃላይ በሕክምና የተረጋገጠ በአካላቸው ላይ 60 በመቶ ጉዳት እንደደረሰባቸው በአትሌቶቹና በሾፌራቸው ላይ የተመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
ዕድሜያቸው 44 እንደሆነና ወደፊት 70 ዓመት እንደሚኖሩ የገለጹት ከሳሽ፣ ጤነኛ በነበሩበት ጊዜ በሚሠሩት ሥራ በቀን 150 ብር እንደሚያገኙ ጠቁመው፣ ለሕክምና ካወጡትና ወደፊት ሠርተው ከሚያገኙት ጋር ተደምሮ 1,554,000 ብር ካሳ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
የቀረበውን ክስ የተመለከተው የአርሲ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አትሌት ጥሩነሽና አትሌት ስለሺ ቀርበው እንዲከራከሩ የመጥሪያ ደብዳቤ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ እንዲለጠፍ ትዕዛዝ ሰጥቶ የተለጠፈ ቢሆንም፣ አትሌቶቹ ሊቀርቡ አለመቻላቸውን ውሳኔው ያስረዳል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በፍ/ሕ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 70(ሀ) መሠረት አትሌቶቹ በሌሉበት ክርክሩ እንዲካሄድ በማዘዝ ክርክሩ ቀጥሏል፡፡
ሦስተኛ ተከሳሽ አሽከርካሪው አቶ ታምራት ቤኛ ተሽከርካሪው መገልበጡን፣ ነገር ግን ከአቅሙና ከሙያው በላይ በሆነ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ጉዳቱ መድረሱን ማረጋገጡን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው አካቷል፡፡ ከሳሽ በአትሌቶቹ ላይ የሰዎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ ታዘው፣ ያቀረቧቸው ምስክሮች ሾፌሩ ከአቅም በላይ በሆነ ፍጥነት ሲያሽከረክር በመገልበጡ፣ በከሳሽ ላይ የደረሰው ጉዳት ትክክል መሆኑን መመስከራቸውን አክሏል፡፡ የከሳሽን የቀን ገቢ በሚመለከት አንድ ምስክር 150 ብር ሲሉ ሌላኛው 100 ብር ማለታቸውን ለሕክምና፣ ለትራንስፖርትና ለቀለብ ገንዘብ ማውጣታቸንው መመስከራቸውን የውሳኔው ሰነድ ይገልጻል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን ሲመረምር ጉዳት መድረሱን ማረጋገጡን ጠቁሞ፣ ተሽከርካሪውም የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ መሆኑን ማረጋገጡንም አክሏል፡፡ በመሆኑም በ/ፍ/ብ/ሕ/ቁ 2081(1) መሠረት አትሌቷ ኃላፊነት ስላለባትና ንብረቱ የእሷ መሆኑ ስለተረጋገጠ፣ በከሳሽ ላይ ለደረሰው የአካል ጉዳት ኃላፊነት እንዳለባትም አስታውቋል፡፡
የከሳሽ የሰውነት ክፍሎች 60 በመቶ መጐዳታቸው በሕክምና ቦርድ መረጋገጡን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ በፍ/ሕ/ቁ/2012 መሠረት ተጐጂዋ በቀን 40 ብር ሊያገኙ እንደሚችሉ፣ በአገሪቱ ተጨባጥ ሁኔታ አንድ ሰው ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚገመተው 55 ዓመት ስለሆነ ይኸው ተይዞ፣ በአጠቃላይ ከነወጪያቸው 128,520 ብር አትሌት ጥሩነሽ እንድትከፍል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የወጪና ኪሳራ 2,000 ብርና የጠበቃ አበል አሥር በመቶ፣ እንዲሁም የዳኝነት እንድትከፍልም አክሏል፡፡
አትሌት ስለሺ የአትሌት ጥሩነሽ ባለቤት መሆኑ ከመገለጹ ባለፈ፣ አደጋ ያደረሰው ተሽከርካሪ ባለቤት ስለመሆኑ የቀረበበት ማስረጃ አለመኖሩን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ምንም ዓይነት ኃላፊነት እንደሌለበት አስታውቋል፡፡