Latest Blog posts
Editors Pick
Latest documents
Education and Training Policy of Ethiopia - Amharic version - 2023 7259 Downloads - policies and strategies | 7.6 MB | |
The Normative Basis for Decision on the Merits in Commercial Arbitration - the Extent of Party Autonomy 203 Downloads - Arbitration Law | 635.59 KB | |
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም የሰጠባቸው ውሣኔዎች ማውጫ ቅጽ 01-25 8871 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 10.72 MB | |
ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ እይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ FEATURED 403 Downloads - Criminal Law | 317.19 KB | |
Federal Supreme Court Cassation Decisions - Table of content Volume 1-25 10454 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 6.57 MB |
- Details
- Category: Legal News - የሕግ ዜናዎች
ካንጋሮ ፕላስት በዋልያ ምሥል የንግድ ምልክት ላይ ባቀረበው ይግባኝ አሸናፊ ሆነ
-የአዕምሯዊ ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ተሽሯል
ታዋቂው ነጋዴ አቶ ይርጋ ኃይሌ የመሠረቱት ካንጋሮ ፕላስቲክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በሞጆ ከተማ በገነባው የቢራ ኢንዱስትሪ ፋብሪካ ለሚያመርተው የዋልያ ምሥል ያለው “IBEX” በማለት ያስመዘገበውን የንግድ ምልክት፣ ለሌላ አካል መሰጠቱን በመቃወም ባቀረበው አቤቱታ አሸናፊ ሆነ፡፡
ካንጋሮ ፕላስቲክ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረበው ይግባኝ አሸናፊ የሆነው ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በተሰጠው ፍርድ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት “IBEX” የሚለውን ካንጋሮ ፕላስት አስመዝግቦት የነበረውን የንግድ ምልክት ሰርዞ፣ ወ/ሪት ማህሌት ሀብተ ወልድ ለተባሉ ግለሰብ በመሰጠቱ ነው፡፡
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የሰጠውን ውሳኔ የሻረበት የፍርድ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ካንጋሮ ፕላስት የቢራ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም “IBEX” የሚለውን የንግድ ምልክት ከጽሕፈት ቤቱ ወስዷል፡፡ በሞጆ ከተማ የፋብሪካውን ግንባታ ጨርሶ ማሽን ለማስመጣት በእንቅስቃሴ ላይ እያለ፣ ለቢራ ፋብሪካው ግንባታ ገንዘብ የሚያገኝበት ኩባንያው ካንጋሮ ፎም ፋብሪካ በእሳት ቃጠሎ ይወድማል፡፡ በዚህ ምክንያት የቢራውን ማሽን ማስመጣት ለጊዜው አቁሞ፣ ሙሉ ኃይሉን ወደ ካንጋሮ ፎም ፋብሪካ በማድረግ በድጋሚ ገንብቶ መጨረሱን ያስረዳል፡፡
ካንጋሮ ፕላስት የወሰደው “IBEX” የሚለው የንግድ ምልክት አገልግሎት ላይ ሳይውል ሦስት ዓመታት ማስቆጠሩን የተከታተሉት ወ/ሪት ማህሌት ሀብተ ወልድ የተባሉ ግለሰብ፣ የንግድ ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 35ን በመጥቀስ ማለትም፣ በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት የተመዘገበ የንግድ ምልክት፣ በማንኛውም መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ በቂ ምክንያት ጥቅም ላይ ሳይውል ሦስት ዓመታት ካስቆጠረ፣ እንደሚሰረዝ የሚገልጸውን አንቀጽ በመጥቀስ “IBEX” የሚለው የንግድ ምልክት እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ማመልከታቸውን ፍርዱ ይዘረዝራል፡፡
ግለሰቧ የካቲት 18 ቀን 2006 ዓ.ም. ለጽሕፈት ቤቱ ያቀረቡትን አቤቱታ፣ የጽሕፈት ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት አቶ አብርዱ ብርሃኑ፣ አቶ ሔኖክ ተገኘ ወርቅ፣ አቶ ፈቃዱ ሽፈራው፣ አቶ ወንድወሰን ሂርጶና አቶ ደረጀ ጽጉ መመርመራቸውንም ፍርዱ ይገልጻል፡፡
ኮሚቴው ካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ የንግድ ምልክቱን ያልተጠቀመው ‹‹በበቂ ምክንያት ነው?›› የሚል ጭብጥ በመያዝ መርምሯል፡፡ ኮሚቴው ዓለም አቀፍ ልምድን መሠረት አድርጎ ሲመረምር ካንጋሮ ፕላስቲክ የንግድ ምልክቱን ያልተጠቀመው፣ ካንጋሮ ፎም ፋብሪካ በእሳት በመቃጠሉ ምክንያት አስገዳጅ የሆነ ነገር እንደገጠመው ያቀረበውን መከራከሪያ ነጥብ፣ ከፖሊስና ከኢንሹራንስ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ውድቅ አድርጎበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም ድርጅቶች ራሳቸውን የቻሉ የሕግ ሰውነት እንዳላቸው በመጥቀስ ነው፡፡ ካንጋሮ ፕላስት ያቀረበውን መከራከሪያ ነጥብ ውድቅ በማድረግ፣ በስሙ ተመዝግቦ የነበረው “IBEX” የንግድ ምልክት እንዲሰረዝ የውሳኔ ሐሳቡን በወቅቱ የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ለነበሩት አቶ ብርሃኑ አዴሎ አቅርቧል፡፡
ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ የተመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩም ‹‹በዚሁ መሠረት ይፈጸም›› በማለታቸው፣ ካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ያስመዘገበው “IBEX” የንግድ ምልክት ተሰርዞ ለወ/ሪት ማህሌት ሀብተ ወልድ ተሰጥቷል፡፡
የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ ያልተቀበለው ካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ፍርድ ቤቱም ያስቀርባል በማለት ጉዳዩን መመርመሩን ፍርዱ ይተነትናል፡፡
ወ/ሪት ማህሌት መልስ እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ሲያዛቸው፣ የንግድ ምልክቱን የሰረዘው አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት መሆኑን ገልጸው ወደ ክርክሩ መግባት እንደማይፈልጉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ደግሞ እንደገለጸው፣ ካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የንግድ ምልክቱን ለአራት ዓመት አልተጠቀመበትም፡፡ ያቀረበው ምክንያት ደግሞ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት እንደገጠመው በመግለጽ ነው፡፡ ምክንያቱ ግን በእሱ የሚተዳደር ሌላ ካንጋሮ ፎም ፋብሪካ በድንገት መቃጠሉ ነው፡፡ “IBEX” የሚለው የንግድ ምልክትን ያስመዘገበው ለቢራ ምርትና ሽያጭ አገልግሎት እንዲያውለው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ፍርዱ ይገልጻል፡፡
“IBEX” የሚለውን የንግድ ምልክት ለካንጋሮ ፎም ፋብሪካ የንግድ ምልክትነት ስላልወሰደው፣ የቢራ ፋብሪካውና የፎም ፋብሪካው “IBEX” የንግድ ምልክትን በጋራ እንደሚጠቀሙበት ገልጾ ባለመከራከሩ፣ በንግድ እንቅስቃሴው ውስጥ ያጋጠመውን ችግር መከላከያ ማድረግ እንደማይገባው በመናገር ጽሕፈት ቤቱ ተከራክሯል፡፡
ካንጋሮ ፕላስቲክ በሥሩ 15 ዓላማዎችን አስመዝግቦ እንደሚንቀሳቀስ የጠቆመው ጽሕፈት ቤቱ፣ ባንዱ ችግር ባጋጠመው ቁጥር ከአቅም በላይ እንደሆነ ተቆጥሮ ሌሎች ግዴታቸውን ላለመፈጸም መከላከያ ማድረግ እንደሌለበት አድርጎ መተርጐም፣ ተቀባይነት እንደሌለው ማስረዳቱን ፍርዱ ይገልጻል፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 1792 መሠረት ተገናዝቦ መተርጎም እንዳለበትም ጽሕፈት ቤቱ አክሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ ካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ‹‹IBEX በሚለው ቃልና የምሥል ንግድ ምልክት ያልተጠቀመው ከአምቅ በላይ በሆነ ምክንያት ነው?›› የሚለውን ጭብጥ ይዞ ፍርድ መስጠቱን ገልጿል፡፡ ወ/ሪት ማህሌት ሀብተ ወልድ የሚመለከተው ጽሕፈት ቤቱን በመሆኑ የክርክሩ ተካፋይ መሆን አለመፈለጋቸውን የገለጹ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አዋጁን መሠረት አድርገው ምልክቱ እንዲሰጣቸው ያመለከቱ በመሆናቸው ነው፡፡ ስለሆነም የክርክሩ ተካፋይ እንዲሆኑ ብይን ሰጥቷል፡፡
ካንጋሮ ፕላስቲክ የንግድ ምልክቱን ያልተጠቀመው የቢራ ፋብሪካውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ የገንዘብ ምንጭ የሆነው ካንጋሮ ፎም ፋብሪካ በመቃጠሉ፣ የቢራ ፋብሪካውን ለማስቀጠል ከአቅሙ በላይ መሆኑን መግለጹን ጠቅሷል፡፡ ፋብሪካው በእሳት መውደሙም እንደማያከራክር ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡ ካንጋሮ ፎም መቃጠሉ በመገንባት ላይ ባለው በቢራ ፋብሪካው ግንባታ ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ገልጿል፡፡ የተቃጠለው ፋብሪካና የሚገነባው ቢራ ፋብሪካ በተለያዩ ስሞች መሆናቸው እንጂ፣ ሁለቱም የሚተዳደሩት በአንድ ሰው መሆኑን ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡
የቢራ ፋብሪካው ገና በግንባታ ላይ ያለ መሆኑን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ካንጋሮ ፎም ግን ምርት እያመረተ ገቢ እያስገኘ የነበረ ፋብሪካ መሆኑን፣ የቢራ ፋብሪካውን ለማጠናቀቅ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ፣ የገንዘብ ምንጩ ደግሞ በድንገተኛና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በመቃጠሉና የገቢ ምንጭ ስለሚያሳጣው የተጀመረውን የቢራ ፋብሪካ ግንባታ ሳይፈልገውና ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት ለማቆም እንደሚገደድ በፍርዱ አብራርቷል፡፡ በመሆኑም በቃጠሎ የወደመው ካንጋሮ ፎም በግንባታ ላይ ለነበረው ቢራ ፋብሪካ እህት ኩባንያ መቆም ምክንያት መሆኑን አትቷል፡፡
ሁለቱ ድርጅቶች ካንጋሮ ፎምና በመገንባት ላይ የነበረው ቢራ ፋብሪካ የአንድ ሰው መሆናቸውን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ በእሳት የወደመው ፋብሪካ እያመረተ የሚያስገኘው ገቢ ለቢራ ፋብሪካው ግንባታ ይውል ስለነበር፣ ለግንባታው መቆም አስረጅ መሆኑን አብራርቷል፡፡ በአጠቃላይ ካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ፣ ከአቅሙ በላይ በሆነ ድንገተኛ ደራሽ በሆነ እሳት ቃጠሎ የወደመበት ፋብሪካ ለቢራ ፋብሪካው ግንባታ መቆም ምክንያት መሆኑን ፍርዱ ያስረዳል፡፡ ስለሆነም ግንባታውን ጨርሶ ወደ ምርት ተሸጋግሮ “IBEX” በሚባል የንግድ ምልክት ስሙ ያልተጠቀመው፣ ምርት ላይ የነበረው ካንጋሮ ፎም ፋብሪካ በድንገተኛ ደራሽ እሳት ቃጠሎ በመውደሙ መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ ማስረዳቱንም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በወ/ሪት ማህሌትና በካንጋሮ ፕላስቲክ መካከል የነበረው ክርክር ካንጋሮ ፎም እንዳላስረዳ በማድረግ ውሳኔ መስጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ “IBEX” በሚል መጠሪያ የነበረውን የንግድ ምልክት ለወ/ሪት ማህሌት እንዳይሰጥ በመሰረዝ ለካንጋሮ ፕላስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንዲመለስ ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ፈርዷል፡፡
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት የካንጋሮ ፕላስቲክ ፋብሪካ የግል ማኅበር ንብረት የሆነው “IBEX” ቢራ የዋሊያን ምሥል የያዘ የንግድ ምልክት የሚጠቀም ከሆነ፣ አሁን በሐይኒከን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ሥር በመመረት ላይ ያለው የዋሊያ ቢራ ስያሜና ምልክት ሊታገድ እንደሚችል የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ሕግ የንግድ ምልክትና ጥበቃ አዋጅ 501/98 መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡