የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ አዋጅ ሊሻሻል መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።
በአዲስ መልክ የሚሻሻለው አዋጅ ላለፉት 8 ዓመታት ተግባራዊ ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ያለ ነው።
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተርአቶ ጥላሁን ንጉሴ እንደተናገሩት፥ በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ክፍተት በጥናት በመለየት ነው ማሻሻያ የሚደረግበት።
በድሮውና በአዲሱ መንጃ ፈቃድ እየደረሰ ያለውን የአደጋ መጠን ለመለየትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገልጿል።
በአገራችን በአመት ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጣሉ፣ ከ8 ሺህ በላይ የሚሆኑትም ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደርሰው የመንገድ ትራፊክ አደጋ 61 በመቶ የሚሆነውም በእግረኞች ላይ የሚደርስ ነው።
በአገሪቱ ከሚከሰተው የትራፊክ አደጋ ከ70 በመቶ በላይ በአሽከርካሪዎች ብቃትና የሥነ ምግባር ጉድለት መሆኑንም ጥናቶች ያሳያሉ።
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ከመንጃ ፈቃድ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ህገወጥ አሰራሮችን መከላከል የሚያስችል ሀገር አቀፍ የመረጃ ማዕከል በ450 ሚሊዮን ብር ሊያስገነባ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።