Latest Blog posts
Editors Pick
Latest documents
Education and Training Policy of Ethiopia - Amharic version - 2023 7263 Downloads - policies and strategies | 7.6 MB | |
The Normative Basis for Decision on the Merits in Commercial Arbitration - the Extent of Party Autonomy 218 Downloads - Arbitration Law | 635.59 KB | |
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም የሰጠባቸው ውሣኔዎች ማውጫ ቅጽ 01-25 9026 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 10.72 MB | |
ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ እይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ FEATURED 408 Downloads - Criminal Law | 317.19 KB | |
Federal Supreme Court Cassation Decisions - Table of content Volume 1-25 10533 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 6.57 MB |
- Details
- Category: Legal News - የሕግ ዜናዎች
ስካይ ባስ ትራንስፖርት ባደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት
ስካይ ባስ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከሦስት ዓመት በፊት በመንገደኞች ላይ ላደረሰው ጉዳት ካሳ እንዲከፍል ተወሰነበት፡፡ ስካይ ባስ ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር 48 ሰዎችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ እያለ ዓባይ ድልድይ መዳረሻ ላይ ተገልብጦ ላደረሰው የሞት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ውሳኔ የሰጠው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ነው፡፡ በወቅቱ ሲጓዙ ከነበሩት ሰዎች መካከል 42 ግለሰቦች ሕይወታቸው ያለፈ ቢሆንም፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ከ308 ሺሕ ብር በላይ ካሳ እንዲከፈላቸው ውሳኔ ያገኙት ከፍተኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚናገሩት አቶ አገኘሁ መኮንን መሆናቸውን የውሳኔው ሰነድ ያስረዳል፡፡
የክሱ ጭብጥ እንደሚያስረዳው ከሳሽ ጥር 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ንብረትነቱ የተከሳሽ ማኅበር በሆነው አውቶቡስ ተሳፍረው ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር በሚጓዝበት ወቅት፣ ተሽከርካሪው ዓባይ በረሃ ወንዝ አካባቢ ሲደርስ በአየር ላይ ተወርውሮ በግምት 120 ሜትር ርዝመት ያለው ገደል ውስጥ ገብቷል፡፡
የተከሳሽ አሽከርካሪ በገደላማ፣ ጠመዝማዛ፣ አደገኛ ቁልቁለት የበዛበትና አስቸጋሪ መንገድ ላይ በሰዓት 100 ኪሎ ሜትር በላይ በሚገመት ከፍተኛ ፍጥነት እያሽከረከሩ እንደነበርና አሽከርካሪው አውቶቡሱን ሊቆጣጠሩት እንዳልቻሉ የክሱ ሰነድ ያስረዳል፡፡ አውቶቡሱ እንደተገለበጠ በፊት አካሉ ላይ እሳት ተነስቶ ተሳፋሪዎች ያጠለቁት ቀበቶ ከጥርሱ ሊላቀቅላቸው ስላልቻለ 42 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል በማለት ከሳሹ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡ ከሳሽም ያጠለቁት ቀበቶ ከጥርሱ ሊላቀቅላቸው እንዳልቻለና እሳቱ ደርሶ ልብሳቸውንና ከፊል አካላቸው እንደተቃጠለ፣ ቀበቶውም አብሮ ተቃጥሎ በመቆረጡ ከመኪናው ላይ ተወርውረው በመውጣት ሕይወታቸው እንደተረፈ ገልጸዋል፡፡
በቃጠሎው ምክንያት በደረሰባቸው ጉዳት ተደጋጋሚ ቀዶ ጥገና እንደተደረገላቸው ከሳሹ ተናግረዋል፡፡ የደረሰባቸውን የአደጋ ክብደት በተመለከተ የክሱ ሰነድ እንደሚያትተው ከሆነ፣ በሰውነታቸው ላይ 20 በመቶ ጉዳት የደረሰባቸው ስለመሆኑ በቦርድ ውሳኔ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከእግራቸው ላይ ተቆርጦ ጀርባቸው ላይ በተለጠፈ ሥጋ ምክንያት እግራቸው ለመንቀሳቀስ ችግር ስለነበረበት፣ እስከ ስምንት ወራት ድረስ መሥራት አለመቻላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በሕክምናቸው ወቅት ከፍተኛ ወጪ ያወጡ ቢሆንም ተከሳሹም በመድን ድርጅት አማካይነት የከፈላቸው 21,861 ብር ካሳ በቂ እንዳልሆነም ተቃውመዋል፡፡ ከሳሽ በሙያቸው ጠበቃ ሲሆኑ በሕክምና ወቅት ለስምንት ወራት ያህል ሥራ በማቋረጣቸው ዓመታዊ ገቢያቸውን 97,000 ብር እንዳጡ፣ ለጥብቅና ያወጡትን ኪሳራና ዕድሜያቸው አሁን 54 ሲሆን የጥብቅና ሥራቸውን የሚሠሩበት ዕድሜ እስከ 65 ሊሆን እንደሚችል፣ የ11 ዓመታት 213,400 ብር የሚያጡ መሆናቸው አስረድተው በአጠቃላይ 402,566.64 ብር ከነወጪ ኪሳራ ሊከፈለኝ ይገባል በማለት ተከራክረዋል፡፡ አጓጓዥ ለሚያደርሰው የአካል ጉዳትና ለሚጠፋ ዕቃ ኃላፊነት እንዳለበት፣ ጉዳቱ አጓጓዥ በፈጸመው ተግባር ወይስ ባደረሰው ጉድለት ከሆነ የኃላፊነቱ መጠን ከሕጉ ከተመለከተው ወሰን በላይ መሆን ባለበት መሠረት ጥፋቱ የአሽከርካሪው መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም የተከሳሽ ሾፌር በከፍተኛ ፍጥነት በማሽከርከር ጥፋት የፈጸመ በመሆኑ፣ ተከሳሽም በባለንብረትነቱ የመኪና ቀበቶ ከአደጋ በኋላ ቁልፉን በመጫን እንዲፈታ የራሱን ጥንቃቄ ባለማድረግ ጥፋት ፈጽሟል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ለከሳሽ ክስና ማስረጃ ተከሳሽ መልስ ያቀርብ ዘንድ ኅዳር 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት፣ ተከሳሽ በሰጠው ምላሽ አደጋው የደረሰ መሆኑን፣ ከሳሽ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ሳይክድ ተከሳሽ እንዳልተፀፀተና ምንም እንዳላደረገ አድርጎ ያቀረበው ፍጹም ስህተት ነውም ሲል አስረድቷል፡፡ ተከሳሽ ከፖሊስና ከማኅበረሰቡ ጋር ሕይወት ለመታደግ ጥረት እንዳደረገ፣ እንዲሁም የተረፉትን ለማዳን ተጨማሪ አውቶቡስ እንደመደበ ተገልጿል፡፡ ለሟች ወገኖች የሞራል ካሳም እስከ 125,000 ብር እንደሚከፍልም አስረድቷል፡፡
ክሱ እንደሚያስረዳውም በመኪናው ላይ የእንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ እንደገጠመና አደጋውም በአሽከርካሪው ጥፋት ወይም በቀበቶ እክል ምክንያት አለመሆኑን በማስረዳት፣ ለማናቸውም ጉዳት የሚከፍለው ካሳ በንግድ ሕግ ቁጥር 597 በሚደነግገው መሠረት ከ40,000 ብር መብለጥ እንደሌለበት ተከራክሯል፡፡ ተከሳሽ ጥፋት ባልፈጸመበት የኢንሹራንስ ውልና በአገሪቱ ባለው አስገዳጅ የመድን ሕግ መሠረት ከሳሽ 21,861.65 ብር የተከፈላቸው መሆኑን ስላረጋገጡ፣ የመንገደኛ የጉዳት ካሳም በሕግ የተገደበ በመሆኑ ተጨማሪ ካሳ የመክፈል ኃላፊነት የለበትም ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሳሽ የጥብቅና ሥራ በአብዛኛው የአዕምሮ ሥራ የሚሠሩ በመሆናቸው፣ የደረሰባቸውም የአካል ጉዳት ከሥራቸው እንደሚያስተጓጉላቸው የሕክምና ማስረጃ አልቀረበም ሲሉ የስካይ ባስ ተወካይ ተቃውመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በከሳሽ በኩል የዓመት ገቢ ተብሎ የቀረበውም የጥብቅና ገቢ ከፍና ዝቅ ማለት የሚታይበት በመሆኑ፣ ቢያንስ የአምስት ዓመት አማካዩን አለማሳየታቸውን ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ለአሥራ አንድ ዓመታት ያህል የሚያሠራኝ ገንዘብ ይሰጠኝ ብለው ያቀረቡትን ሐሳብ ከሳሽ እስከ 65 ዓመት እንደሚኖሩ አልተረጋገጠም፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያውያን አማካይ ዕድሜ 50 ዓመት መሆኑ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ሊያረጋግጠው ይችላል የሚል ክርክር አሰምተዋል፡፡ የንብረት ጉዳት ደርሶብኛል ብለው ያሰሙትን ክስ ተከሳሹ ያልተቀበለው ሲሆን፣ መንገደኛው በግሉ ይዟቸው የሚጓዘው ዕቃዎች ግምት፣ መጠንና ዓይነታቸው ያልታወቁና አጓጓዥ መዝኖ ላልተረከባቸው ዕቃዎች ኃላፊነት የለባቸውም ሲሉ የተከሳሹ ተወካይ ውድቅ አድርገውታል፡፡
የንግድ ሕግ ቁጥር 597 እና 599ን አፈጻጸም በተመለከተ የንግድ ሕግ ቁጥር 597 እና 595ን እንደሚለው መንገደኛውን በጉዞው ላይ ለሚደርስበት ጉዳት ወይም አደጋ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ መጠኑም 40 ሺሕ ብር ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የካሳው መጠን በንግድ ሕግ ቁጥር 599 መሠረት ከ40 ሺሕ ብር ሊበልጥ እንደማይችል መወሰኑን አስታውሰው ተከራክረዋል፡፡
የከሳሽ ምስክሮች ሾፌሩ በፍጥነት እያሽከረከረ የነበረ መሆኑን ቢመሰክሩም፣ በዚህ ረገድ በተጨማሪ የትራፊክ ፖሊስ ምርመራ ማኅደርና ሪፖርት እንዲቀርብ ቢታዘዝም፣ ወረዳው የተደራጀ ማኅደርም ሆነ ሪፖርት እንደሌለው በደብዳቤ ጽፈው ለፍርድ ቤቱ መልሷል፡፡ ከሳሽም ካሳው በቂ እንዳልሆነ በመጠየቅ ይገባኛልም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ከሳሽ ያጡትን ገቢና የደረሰውን ኪሳራ ሊወስን የሦስት ዓመት ገቢ ለስምንት ወር አካፍሎ ማስላቱን ክሱ ያትታል፡፡ ሕክምና በመከታተል ላይ ሳሉ የ51,444 ብር ገቢ ተቋርጦባቸዋል ሲል ወስኗል፡፡
የዕድሜ ጣሪያን በተመለከተ ከሳሹና ተከሳሹ የተለያየ መረጃ ቢያቀርቡም፣ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2012 ያወጣውን 65 ዓመት የዕድሜ እርከን ተቀብሏል፡፡ በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ ሰኔ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽ 308,777.76 ብር ከሚታሰብ ዘጠኝ በመቶ ሕጋዊ ወለድ ጋር እንዲከፍሉ እንዲሁም ጣልቃ ገብ በገባው የመድን ውል አስቀድሞ ከከፈለው 21,816.65 ብር፣ ከ40 ሺሕ ብር ጣሪያ ልዩነቱን 18,183.35 ብር መጠን እንዲከፍል ሲል ወስኗል፡፡
ይኼንን ውሳኔ ስካይ ባስ ይግባኝ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን፣ ይግባኙም እንደሚያትተው ካሳው የተጋነነ እንደሆነና በንግድ ሕግ ቁጥር 599 መሠረት አጓጓዥ ሊጠየቅ የሚገባው ሆን ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት ለሚፈጸም ጉዳት መሆኑን ከሳሽ አላስረዱም ብሏል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ኃላፊነት 40,000 ብር በመድን ድርጅት መሸፈኑን አቅርበው ተቃውሟል፡፡ ይኼንንም ይግባኝ አስመልክቶ ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ቅሬታውን ፍርድ ቤቱ ያልተቀበለው ሲሆን ውሳኔውም እንዲፀና ተወስኗል፡፡