ቢጂአይ ኢትዮጵያ ለደንበኞቹ የሚሸጥላቸውን የድራፍት መጠን አሳንሶ መግለጹንና መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ግብር ደንበኞቹ እየሰወሩ መሆኑን በመጠቆማቸው፣ በሕግ አግባብ የሚገባቸውን ክፍያ ለማግኘት ጠቋሚዎች ባደረጉት ክርክር የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን አሸነፉ፡፡
ባለሥልጣኑና በጠበቃ ተሻገር ደሳለኝ የተወከሉት ሦስት ጠቋሚዎች ክርክር፣ አምስት ዳኞች በሚሰየሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተጠናቀቀው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፉትን ተመሳሳይ ውሳኔ በማፅናት ነው፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ለደንበኞቹ የሸጠላቸውን የድራፍት መጠን አሳንሶ ለመንግሥት በመግለጹ፣ ደንበኞቹ ለመንግሥት መክፈል የሚገባቸውን ፍሬ ግብር፣ ወለድና መቀጮን ጨምሮ 72,467,971 ብር መሰወራቸውን ባለሥልጣኑ ማረጋገጡን የክስ ሒደቱ ያሳያል፡፡
ባለሥልጣኑ የተሰወረው ግብር መኖሩን ሊያረጋግጥ የቻለው፣ ሦስቱ ግለሰቦች ባደረሱት ጥቆማ መሠረት መሆኑንና የግብር ስወራው የሚከናወንባቸውን ኮምፒዩተሮች፣ ፍላሽ ዲስኮች፣ ዶክመንቶችና የሦስተኛ ወገኖችን የሽያጭ ሁኔታ የሚያሳዩ ዕቃዎችን በመመርመር መሆኑን፣ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ያስረዳል፡፡
ባለሥልጣኑ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ከሰበሰበው 72,467,971 ብር ላይ፣ ለጠቋሚዎች 5,886,693 ብር መክፈል የሚገባው ቢሆንም፣ 1,471,672 ብር ብቻ መክፈሉንም ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡
ነገር ግን ጠቋሚዎቹ በአዋጅ ቁጥር 286/1994ና በሐምሌ ወር 1996 ዓ.ም. የወጣውን መመርያ ቁጥር 3.3 በመጥቀስ፣ ቀሪ ክፍያቸው እንዲፈጸም ክስ ሲመሠርቱ፣ ባለሥልጠኑ እንኳን ቀሪ ክፍያ ሊከፍል ቀርቶ ቀደም ብሎ አምኖበት የከፈላቸው ገንዘብ አላግባብ መሆኑን በመግለጽ እንዲመልሱለት ሲከራከር ከርሟል፡፡
የሥር ፍርድ ቤት የክስ ሒደቱን ከተመለከተና ካከራከራቸው በኋላ፣ ቀሪውን 4,415,020 ብር እንዲከፍል በባለሥልጣኑ ላይ የወሰነበት ቢሆንም፣ ውሳኔውን በመቃወም ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ነበር፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግራና ቀኙን ካከራከረ በኋላ፣ በሥር ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ አፅንቶበታል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሠረታዊ የሕግ ጥሰት እንደተፈጸመበት በመግለጽ ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሏል፡፡
ሰበር ሰሚ ችሎቱ አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 84(1)ና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው መመርያ ገቢውን የሚደብቅ፣ አሳንሶ የሚያስታውቅ፣ የሚያጭበረብር ወይም በማናቸውም ሁኔታ ግብር ሳይከፍል በቀረ ላይ በተጨባጭ መረጃ በመደገፍ ሪፖርት ከቀረበ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን መደንገጉን በመጠቆም፣ የፌዴራል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችም ይኼንኑ ተከትለው መሥራታቸውን አስታውቋል፡፡ በመቀጠልም ቢጂአይ በሦስተኛ ወገን ሊከፈል ይገባ የነበረን ግብር እንዳይከፈል የሚያደርግ ተግባር መፈጸሙንና ዕዳውን አምኖ ክስ እንዲቀርለት መደረጉ የተረጋገጠ በመሆኑ፣ ባለሥልጣኑ የሚያደርገውን ክርክር ለመቀበል የሚያስችል የሕግ ምክንያት እንደሌለ በመግለጽ ውሳኔን አፅንቶታል፡፡ ለጠቋሚዎቹም ክፍያውን እንዲፈጽም በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ላይ ውሳኔ ሰጥቶ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡