የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት ሰሚት ምድብ በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የተጠቀሱ 18 ተከሳሾችን ዛሬ ከ7 አመት እስከ 22 አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ቀጥቷቸዋል።
22 አመት የተቀጡት ፍርድ ቤቱ በሽብር ወንጀሉ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው ያላቸው አቡበክር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ እና ከሚል ሸምሱ ናቸው።
ችሎቱ በመዝገቡ የተጠቀሱ 5ኛ፣ 7ኛ፣ 8ኛ፣ 11ኛ እና 15ኛ ተከሳሾችን፤ በድሩ ሁሴን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሃመድ አባተ፣ አቡበክር አለሙ እና ሙኒር ሁሴንን እያንዳንዳቸውን በ18 አመት ጽኑ እስራት ቀጥቷቸዋል።
ሼህ መከተ ሙሄ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ ሼህ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም እና ካሊድ ኢብራሂም የ15 አመት ጽኑ እስራት ተወስኖባቸዋል።
እንዲሁም ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ዑመር እና የሱፍ ጌታቸውን በ7 አመት ጽኑ እስራት ቀጥቷቸዋል።
ተከሳሾችም ይሁን ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየት እንዲያቀርቡ የ10 ቀን ጊዜ በችሎቱ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን፤ ዓቃቤ ሕግ ቀድሞ ማቅረቡን ችሎቱ አትቷል።
ተከሳሾች የዓቃቤ ሕግን የቅጣት አስተያየት ካላየን አናቀርብም ማለታቸውን ተከትሎ ችሎቱ የዓቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየት እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ይሁን እንጂ ከተሰጣቸው የመጀመሪያው 10 ቀን ሌላ ተጨማሪ ቀን ቢሰጣቸውም የቅጣት ማቅለያ ሊያቀርቡ አልቻሉም።
ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን ያስተላለፈው ዓቃቤ ሕግ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸሙት በስምምነትና በአንድነት ነው የሚለውን የቅጣት ማክበጃ ተቀብሎ ነው።
ችሎቱ ከእስራት ቅጣት በተጨማሪ ተከሳሾች ይህ ውሳኔ ከፀናበት እለት ጀምሮ ለአምስት አመታት እንዳይመርጡ፣ እናዳይመረጡ፣ በየትኛውም ቦታ ዋስም ምስክርም እንዳይሆኑ በአጠቃላይ ከማህበራዊ መብታቸው አግዷል።