በአዲስ አበባ በተለያዩ አከባቢዎች በመንገድ ግንባታው ዘርፍ የተሰማራው የእስራኤሉ ትድሃር ኩባንያ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ሚናሼ ሌሺ ጉቦ በመስጠት እና በታክስ ስወራ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የፌደራል ስነምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤህግ ግለሰቡን ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያስደረገው በኢትዮዽያ ገቢዎች እና ጉሙሩክ ባለስልጣን ለሚሰሩ 3 ኦዲተሮች 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ሰጥተዋል እና ከ140 ሚሊየን ብር በላይ ታክስ አጭበርብረዋል በሚሉ ሁለት ወንጀሎች ነው።
ኮሚሽኑ በግለሰቡ ላይ በቅርቡ ክስ እንደሚመሰርትም ለማወቅ ተችሏል።
ኩባንያው በአዲስ አበባ ከሌሎች ተቋራጮች ጋር ተጫርቶ ከአቡነ ዽጥሮስ- ፓስተር-ዊንጌት፣ ከ6 ኪሎ- ፈረንሳይ ጉራራ እና ከመገናኛ- ካፒታል ሆቴል ያሉ መንገዶችን በመገንባት ላይ ይገኛል።