የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ የወንጀል ችሎት በእነ አቡበክር አህመድ የክስ መዝገብ የዓቃቤ ሕግን እና የመከላከያ ምስክሮችን ቃል በንባብ አሰምቶ ማጠናቀቁን ተከትሎ ዛሬ በ18 ተከሳሾች ላይ ፍርድ ሰጥቷል።
በዚህም መሰረት አቡበከር አህመድ፣ አህመዲን ጀበል፣ ያሲን ኑሩ፣ ካሚል ሸምሱ፣ በድሩ ሁሴን፣ ሼህ መከተ ሙሄ መኮንን፣ ሳቢር ይርጉ፣ መሀመድ አባተ፣ አህመድ ሙስጠፋ፣ አቡበከር አለሙ፣ ሙኒር ሁሴን፣ ሼህ ሰኢድ አሊ፣ ሙባረክ አደም፣ ካሊድ ኢብራሂም በተከሰሱባቸው በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ አራት ላይ በተዘረዘሩት መቀስቀስ፣ ማነሳሳት እና ማሴር በሚሉ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለዋል። ቀሪዎቹ ሙራድ ሽኩር፣ ኑሩ ቱርኪ፣ ሼህ ባህሩ ኡመር እና የሱፍ ሄታቸው በፀረ ሽብር ሕጉ አንቀፅ ሰባት ላይ በተጠቀሰው በመሳተፍ ወንጀል ጥፋተኛ ተብለዋል።
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሀምሌ 27 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት ቀጠሮ ሲሰጥ። ተከሳሾቹ እና ዓቃቤ ሕግ እስከ ሐምሌ 10 የቅጣት ማቅለያ እና ማክበጃ አስተያየታቸውን እንዲያቀርቡም አዟል። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ጠዋት ከከሳሽና ከተከሳሽ በኩል በተካሄዱ ክርክሮች አምስት ጭብጦችን መመርመሩ ነው የተመለከተው።
ከአምስቱ ጭብጦች መካከል መንግስት በእስልምና ሃይማኖት ጣልቃ ገብቷል አልገባም? የሃይማኖቱ ተከሳሾችን ከፋፍሏል አልከፋፈለም? እና የመጅሊሱ ምርጫ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ተጋጭቷል? አልተጋጨም? የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው። ችሎቱ እነዚህን ጭብጦች ሲመረምር በተለያዩ ሃገራት ከኃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚራመዱ አሰራሮችን አይቷል።
ከዚህ ሰፊ ሃተታ በኋላ መንግሥት በኃይማኖት ጣልቃ አለመግባቱን፣ ተከታዮችን አለመከፋፈሉንና የመጅሊሱ ምርጫ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ሳይቃረን በኃይማኖታዊ ሥርዓት መካሄዱን ከምስክሮችና ከማስረጃ ቃል በማገናዘብ አረጋግጫለሁ ማለቱን ተከትሎ ነው ከሰዓት በኋላ ፍርድ የሰጠው። ተከሳሾቹ በችሎቱ ፊት ያልተገባ ባህሪ ቢያሳዩም ፍርድ ቤቱ በዝምታ አልፏቸዋል።