ረቂቅ አዋጁ ‹‹ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ምክር ቤቱ ለሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ለማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቶታል፡፡ የረቂቅ አዋጁ መፅደቅ በአስቸኳይ የሚፈለግ መሆኑ በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የተገለጸ ሲሆን፣ ረቂቁ ፓርላማው ማክሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የሥልጣን ዘመኑን ከማብቃቱ በፊት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ረቂቅ አዋጁ በሃምሳ አንቀፆችና በሰባት ምዕራፎችም የተከፋፈለ ነው፡፡ ምዕራፎቹም ጠቅላላ ድንጋጌዎችን፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን፣ የመከላከል፣ የምርመራ፣ የክስና የማስረጃ ሥነ ሥርዓት ድንጋጌዎችን፣ የተጎጂዎችን ጥበቃ፣ መልሶ ማቋቋምና ካሳ፣ ስለፈንድ መቋቋም፣ የባለድርሻ አካላት ትብብርና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ በጥብቅነቱና አወዛጋቢነቱ ከሚታወቀው የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ሁሉ እጅግ የጠበቀ የሚያደርጉ አንቀጾችን ይዟል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱና በዋነኝነት የሚጠቀሰው ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን ስለመጠቀም የሚፈቅደው አንቀጽ 18 ይገኝበታል፡፡
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎች በባህሪያቸው በቡድን የሚፈጸሙ በመሆናቸው፣ የወንጀል ድርጊቱ ከአንድ አገር በላይ በተደራጀ የወንጀል ቡድን የሚፈጸም በመሆኑ፣ በተለይም ከምልመላ ጀመሮ እስከ መጨረሻው ሒደት ያለው የወንጀሉ አፈጻጸም በቅብብሎሽና በቅንጅት የሚሠራ በመሆኑ፣ በዚህ ወንጀል ውስጥ የሚሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በተሟላ ሁኔታ ለመያዝ መደበኛውን የምርመራ ሒደት መጠቀም አዋጭ እንዳልሆነ የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
እነዚህን ወንጀሎች ከሥር ከመሠረታቸው ለመረዳትና በወንጀል ድርጊት አፈጻጸሙ የሚሳተፉ ሰዎችን ማንነት፣ የወንጀሉን ማስረጃ፣ የአፈጻጸም ሥልት፣ የሚፈጸምበትን ሁኔታና ጥቅም ላይ የዋሉ የጉዞ አቅጣጫዎች በአግባቡ ለማወቅና በመረጃ ላይ የተመሠረተ የምርመራ ሒደትን ለማከናወን ልዩ የምርመራ ዘዴዎች መጠቀም እንደሚያስፈልግ ማብራሪያው ያስረዳል፡፡
ከእነዚህም ቴክኒኮች መካከል ሰርጎ የመግባት ማለትም በአንድ የተደራጀ የዚህ ወንጀል ቡድን ውስጥ ራሱን የዚያ ድርጊት ደጋፊ በማድረግ፣ በወንጀል ቡድኑ ውስጥ አባል በመሆን መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ይገኝበታል፡፡
ሌላኛው ደግሞ በድብቅ ክትትል ማድረግ ወይም ወንጀል የሚፈጽሙ ሰዎችን ቢያንስ በሁለት ዓይነት መንገድ ክትትል ማድረግን እንደሚመለከት ማብራሪያው ይገልጻል፡፡ አንደኛው ዘዴ ተጠርጣሪው ላይ በአካል የሚደረግ ክትትልና መረጃ የመሰብሰብ ሒደት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እንደ አመቺነቱ የሚኖርበትን አካባቢ፣ ቤት፣ የሥራ ቦታ፣ ወዘተ በድብቅ የስለላ ካሜራዎች በመጠቀም እንቅስቃሴውን የመከታተል ሒደት ነው፡፡ ሌላኛው የምርመራና መረጃ የመሰብሰብ ዘዴ ደግሞ የይምሰል ግንኙነት መፍጠርን የሚመለከት ነው፡፡ ‹‹የይምሰል ግንኙነት ማለት በሕግ ውጤት የሌለው ነገር ግን በወንጀል ድርጊቱ የሚሳተፉ አካላት ላይ ማስረጃ ለማሰባሰብ የሚረዳ ግንኙነት ሲሆን፣ ለምሳሌ የወንጀል ቡድኑ ወንጀሉን ለመፈጸም ገንዘብ የሚያስፈልገው መሆኑ ከታወቀ ቀድሞ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሚገኝ ፈቃድ አንድ ሰው የወንጀል ድርጊቱን በገንዘብ እንዲረዳ በማድረግ ማስረጃ ማሰባሰብ›› መሆኑን የረቂቁ አባሪ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡
ሌሎች ዓይነቶችን የይምሰል ግንኙነቶችን መፍጠር እንደሚቻልም ማብራሪያው ያትታል፡፡ ከእነዚህም መካከል ‹‹ከተጠርጣሪዎች ጋር ጋብቻ መፈጸም››፣ ‹‹የንግድ ተቋም በጋራ መመሥረት››፣ ወዘተ ሊያጠቃልል የሚችል ሲሆን፣ ዋነኛ ዓላማው ከሌሎች ወገን ወንጀሉን አስመልክቶ መረጃ ለማግኘት ታሳቢ ተደርጎ የሚፈጠር ግንኙነት እንደሆነና በሕግ ፊት ተጠያቂነትን እንደማያስከትል ይገልጻል፡፡
አንድ መርማሪ ሠርጎ በገባበት የወንጀል ቡድን ውስጥ አባልነቱን እንዲቀበሉት፣ የወንጀል ቡድኑ አባላት ይህንን ሠርጎ ገብ መርማሪ በግልጽ ወንጀል እንዲፈጽም ሊያደርጉት እንደሚችሉ የሚያትተው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ፣ መርማሪው በተግባር ወንጀል እየፈጸመ ቢሆንም ዓላማው ማስረጃ ለማሰባሰብ በመሆኑ በወንጀል እንደማይጠየቅ ያስረዳል፡፡
ለዚህም ሲባል መርማሪው አስቀድሞም የወንጀል ነፃ ስምምነት መፈራረም እንደሚኖርበትና ይህን የወንጀል ነፃ መብት አለ በሚል ግን ግድያ ከመፈጸም፣ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉት ከባድ ወንጀሎች መፈጸም እንደሌለበት ያብራራል፡፡
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ማለት፣ በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛን ለማገናኘት ወይም ለሥራ፣ ለሥራ ልምምድ ወደ ውጭ አገር መላክ በሚል ሽፋን የሚፈጸም፣ በጉዲፈቻ ስምምነት በማድረግ ወይም በጉዲፈቻ ሽፋን፣ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ ለምሳሌ ዛቻን፣ ኃይልን፣ ጠለፋን፣ ማታለልን፣ የተስፋ ቃልን፣ ስለሌላው ኃላፊነት ያለበትን ሰው ፈቃድ ለማግኘት በመደለል፣ ጥቅም በመስጠት ሰዎችን የመመልመል፣ የማጓጓዝ፣ የማዘዋወር፣ የማስጠለል፣ የመቀበል ወንጀል መሆኑን ረቂቅ አዋጁ ይገልጻል፡፡
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የራሱንም ሆነ በይዞታው ሥር ያለውን ቤት፣ ሕንፃ ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዓላማ ያከራየ፣ እንዲጠቀሙ የፈቀደ ወንጀሉን በመደገፍና በማመቻቸት ተጠያቂ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡
በተፈጸመ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ድርጊት በተጎጂው ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ያስከተለ እንደሆነ ወንጀል አድራጊው ድርጊቱን የፈጸመው በተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል በመሆን፣ ቡድኑን በመምራት ወይም በማስተባበር እንደሆነ ወይም ወንጀሉ የተፈጸመው በብዛትና በስፋት ከሆነ ቅጣቱ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም ሞት እንደሚሆን በረቂቁ ተካቷል፡፡
በዚህ ወንጀል ዓይነት ላይ ይርጋ እንደማይኖር የተቀመጠ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው ወንጀል መፈጸሙን ወይም ሊፈጽም መሆኑን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለሕግ አካል የማሳወቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በተመሳሳይም ለዚህ የወንጀል ድርጊት ዓላማ የቤተሰቡ አባል የሆነ ሰው ከመደበኛ የመኖሪያ አካባቢው የጠፋ መሆኑን ያወቀ ከሆነ፣ ወዲያውኑ ለሕግ አካል እንዲያሳውቅ ረቂቁ ያስገድዳል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት የተከሰሰ ሰው ወንጀሉን ስላለመፈጸሙ ለፍርድ ቤት የማስረዳት ሸክም እንደሚወድቅበትም ይደነግጋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ እጅግ በጣም ጥብቅ የሆነ የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅም ለፓርላማው ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ወደ ውጭ አገር በቤት ሠራተኝነት ለመሄድ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ደረጃ ሊኖር እንደሚገባና ይህንኑም በማስረጃ ማስደገፍን ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መያዝ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ በሠራተኝነት መሄድ የሚቻለው ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ስምምነት ያደረገችባቸው አገሮች ብቻ ነው፡፡
በዚህ የሥራና ሠራተኛ የማገናኘት ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኤጀንሲዎች በግለሰብ ደረጃ ከሆነ አንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልግ፣ በአክሲዮን ደረጃ ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ረቂቁ ያስረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ኤጀንሲ ለሠራተኛው መብትና ደኅንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል 100,000 ዶላር ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር በዝግ ሒሳብ በባንክ እንዲያስቀምጥ ይገደዳል፡፡
እንዲሁም ሠራተኛን የሚቀጥር አካል ሠራተኞች በሥራ ውል መጣስ ምክንያት የሚያነሱትን የገንዘብ ክፍያ ጥያቄዎች መሸፈን እንዲቻል፣ የውጭ አሠሪዎች የዋስትና ፈንድ እንደሚቋቋምና ለዚሁ ይረዳ ዘንድ እያንዳንዱ ቀጣሪ ለአንድ ሠራተኛ 50 ዶላር ወደ ፈንዱ እንዲያስገባ ይገደዳል፡፡
ይህ አዋጅ በተጠናቀቀው የፓርላማው የሥልጣን ዘመን ይፀድቃል ተብሎ የማይጠበቅ ቢሆንም፣ የፓርላማው የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ እንዲያዩት ተመርቶላቸዋል፡፡