በአዋጅ 47/67 ተወርሶ ንብረትነቱ ለመንግሥት እንደተዘዋወረ በመግለጽ፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በእነአምባሳደር ታደለች የቀረበበትን ክስ ያስተባበለ ቢሆንም፣ ያቀረባቸው ማስረጃዎች ፍርድ ቤቱን ሊያሳምኑ ባለመቻላቸው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ንብረቱን ለከሳሾች እንዲያስረክብና በክስ ሒደቱ ወቅት ያወጡትን ወጪና ኪሳራ እንዲከፍል ፈርዶበታል፡፡
እነአምባሳደር ታደለች ከሁለት ዓመታት የፍርድ ቤት ክርክር በኋላ አሸናፊ ሆነው ፍርድ ያገኙበት የንብረት ክርክር የጀመረው፣ ደርግ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅን ካወጀ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በአባታቸው አቶ ዋኬኔ ፊሊጶስ (በኋላ ኃይለ ሚካኤል ፊሊጶስ ተብሏል) ነበር፡፡
የኅብረተሰባዊ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. ባወጣው የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት፣ ማንኛውም ትርፍ ቤት ያለው ነዋሪ አንዱን መርጦ እንዲወስድ ሲደረግ፣ አቶ ኃይለ ሚካኤል በአሁኑ አራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ ወደ እሪ በከንቱ መውረጃና ወደ እቴጌ ጣይቱ ሆቴል መታጠፊያ አካባቢ የሚገኘውን ቤታቸውን (የአሁኑ ፓርክ ሆቴልን) ይመርጣሉ፡፡ በወቅቱ ቤቱ ኮሎኔል ሥዩም ኃይሌ የሚባሉ ባለሥልጣን ይኖሩበት ነበር፡፡ ቤቱ በባለሀብቱ የተመረጠ መሆኑ ተገልጾ ለኮሎኔል ሥዩም እንዲለቁ ደብዳቤ ይጻፍላቸዋል፡፡ አቶ ኃይለ ሚካኤል የመረጡት ቤት እስከሚለቀቅላቸው ድረስ፣ 160 ብር እየከፈሉ ተከራይተው ይኖሩበት የነበረው ቤት ኪራይ እንዲቆምም ተደርጓል፡፡ ኪራዩ እንዲቆም የተደረገው በሥራና ቤቶች ሚኒስቴር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ነው፡፡ ቤቱን የያዙት ኮሎኔል ሥዩም ኃይሌ ግን ቤቱን ሊለቁ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
በሌላ በኩል ኮሎኔሉ ቤት አለቅም ቢሉም፣ አቶ ኃይለ ሚካኤል ለጊዜው የሚኖሩበት ቤት ለሌላ ሰው ሊሰጥ መሆኑ ተገልጾ ቤቱን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከማስጠንቀቂያው ቀን በኋላ አቶ ኃይለ ሚካኤልን ከቤት አስወጥተው እንዳይጥሏቸው ሲባል በአስቸኳይ ቤት ተፈልጐ እንዲሰጣቸው፣ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ለነበሩት አቶ ኃይሌ ተድላ ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረጃነት የቀረቡ ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
ከላይ የተጻፉ ማስረጃዎች በእነአምባሳደር ታደለች በኩል የቀረቡ ሰነዶች መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ ፍርድ ቤቱ በደረሰበት ድምዳሜ በ1969 ዓ.ም. እና በ1978 ዓ.ም. የተሰጡ የሰነድ ማስረጃዎች (በተለያዩ የመንግሥት አካላት) የሚያመለክቱት ቤቱ የአቶ ዋኬኔ (ኃይለ ሚካኤል) ፊሊጶስ መሆኑን እንደሆነ ገልጿል፡፡
አቶ ኃይለ ሚካኤል ሕይወታቸው እስካለፈበት 1972 ዓ.ም. ድረስ የመረጡትና እንዲረከቡ የተወሰነላቸውን ቤት ማግኘት አልቻሉም፡፡ እሳቸውን በመተካት ባለቤታቸው ወ/ሮ ብርአልጋ አንብሬ ክርክራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ነገር ግን በ1978 ዓ.ም. ደግሞ ቤቱ መኖሪያ ቤት ሳይሆን ድርጅት መሆኑ ተገልጾ፣ ጉዳዩ እስከሚጣራ በሚል ለአቶ ኃይለ ሚካኤል ቤተሰቦች አንድ ቤት ተመርጦ እንዲሰጣቸው ትዕዛዝ ተላለፈ፡፡
ተከሳሽ የሆነው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ (ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት) ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑን የሚያስረዱለትን ማስረጃዎች ማቅረቡንም ፍርዱ ይገልጻል፡፡ በወቅቱ ቤቱ እንዲመለስላቸው ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አቤቱታ አቅርበው፣ በ1982 ዓ.ም. መመለስ እንደማይቻልና ማካካሻ ግምት እንዲሰጣቸው መወሰኑን የሚያሳይ ሰነድ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡንም አስረድተዋል፡፡
ኤጀንሲው ያቀረበው ሰነድ ግን አቶ ኃይለ ሚካኤል ወይም ቤተሰቦቻቸው ያቀረቡት ሰነድ ሳይሆን፣ ቤቱን አለቅ ብለው አሻፈረኝ ያሉት የኮሎኔል ሥዩም መሆኑን እንደሚያስረዳ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሥራ አመራር ቦርድ ማረጋገጡን ገልጾ ሰነድ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሰነዱ የሚያስረዳው ግን ስለቤቱ የተነሳው ጉዳይ ለኤጀንሲው ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ መሆኑን ጠቅሶ መዝገቡን እንደዘጋው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡
አዋጅ ቁጥር 47/67 አንቀጽ 16(1) የሚደነግገው፣ በአንድ ከተማ ውስጥ ከአንድ መኖሪያ ቤት ውጪ ትርፍ ቤት ያለው ሰው፣ በራሱ ፍላጐት አንድ መኖሪያ ቤት በመምረጥ መልሶ መረከብ እንደሚችል ነው፡፡ የንግድ ቤት ወይም ከአንድ ቤተሰብ በላይ የሚያስተናግድ መሆኑ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የተረጋገጠ ከሆነ፣ የማይመለስና ማካካሻ የሚሰጥ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ጠቅሷል፡፡
በመሆኑም ቤቶች ኤጀንሲ ቤቱ የንግድ እንደሆነና ከሳሾች ማካካሻ እንዲወስዱ የተከራከረ ቢሆንም፣ ማስረጃ አለማቅረቡን ገልጿል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 47/67ም ቤቱን እንደመረጡና ለአቶ ኃይለ ሚካኤል እንደተወሰነላቸው እንጂ፣ ንግድ ቤት ስለመሆኑ ምንም ያለው እንደሌለ አስረድቷል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲም ማረጋገጡን አክሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ በአጠቃላይ ከሳሾች ካቀረቡት የሰነድ ማስረጃ አኳያ ከሳሾች ቤቱን በውርስ ያገኙት ስለመሆኑ መገንዘቡን አውስቷል፡፡
የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 14ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የአቶ ኃይለ ሚካኤል ፊሊጶስ ወራሾች፣ አምባሳደር ታደለች ኃይለ ሚካኤልና አቶ ዓለማየሁ ኃይለ ሚካኤል ንብረቱ ይገባቸዋል የሚል ፍርድ የሰጠው ባደረገው የሰነዶች ምርመራ ነው፡፡
ክሱ በ2005 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍትሐ ብሔር ችሎት ቀርቦ ተከሳሽ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ፣ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑንና ከሳሾች ወራሾች ባልሆኑበት የመንግሥት ንብረት መከራከር እንደማይችሉ ገልጾ ያቀረበውን መከራከሪያ ሰምቶ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ክሱን ውድቅ አድርጐት ነበር፡፡ በክሱ ላይ ግን ከሳሾች አሁን ፍርድ እንዲያገኙ ያደረጓቸው ሰነዶችን አያይዘው አቅርበው ነበር፡፡
እነአምባሳደር ታደለች ግን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለታቸው፣ ፍርድ ቤቱ ሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ ከሳሾች ያቀረቧቸው ሰነዶች ቤቱ በአቶ ዋኬኔ (ኃይለ ሚካኤል) ፊሊጶስ ስም ነው፡፡ በመሆኑም ወራሾች የአቶ ዋኬኔ ፊሊጶስ ወራሾች ናቸው፡፡ በመሆኑም ክሱ ውድቅ የሚሆን ባለመሆኑና ብይኑ ግድፈት ያለበት መሆኑን በመጥቀስ፣ የሥር ፍርድ ቤት ወደ ፍሬ ነገሩ በመግባት ሁለቱን ወገኖች አከራክሮ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥ በማዘዝ መዝገቡን መመለሱን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡ ክሱ የተመለሰለት የሥር ፍርድ ቤት (አሁን ፍርድ የሰጠው ፍርድ ቤት) አምስት ጭብጦችን ይዟል፡፡ ከሳሾች ባለቤት መሆን አለመሆናቸውን፣ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መወረስ አለመወረሱን፣ ካልተወረሰ ተከሳሽ ለከሳሾች ቤቱን ማስረከብ አለበት የለበትም፣ በኤጀንሲውና ቤቱን በተከራየው ሁለተኛ ተከሳሽ አሁን ቤቱን ፓርክ ሆቴል ብሎ እየሠራበት ያለውና ከኤጀንሲው የተከራየው ነጋዴ መካከል ያለው የኪራይ ውል ካልፈረሰ፣ ቤቱን ለከሳሾች ማስረከብ አለበት የለበትምና ወራሾች የቤቱ ባለቤት ስለመሆናቸው የግድ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ማስረዳት አለባቸው የለባቸውም የሚሉ ጭብጦችን በመያዝ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን ምርመራዎች በማድረግ ፍርድ መስጠቱን ሰነዶቹ ያብራራሉ፡፡ ኤጀንሲው ቤቱን እንዲያስረክብ፣ የወጪና ኪሳራም ተሰልቶ ሲቀርብ እንዲከፍል ተፈርዶበታል፡