በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በትጥቅ ትግልና በኃይል ለማፈራረስ የሽብር ቡድን ከሆነው የአርበኞች ግንባር ጋር በመቀላቀል ሲያሴሩ በቁጥጥር ሥር ውለዋል በተባሉ ስድስት ተጠርጣሪ ወጣቶች ላይ፣ የሽብርተኝነት ክስ መጋቢት 29 ቀን 2007 .. ተመሠረተ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19 ወንጀል ችሎት በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመረሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ ሁሉም በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ እነሱም አምላኩ መስታዬት (ቅጽል ስም ባሪያው ጎይቶም) ኢሳያስ ማሩ (ለዛው) ጀጃው ዓለማየሁ፣ ወርቁ ዳኘው፣ አሳመረው አሰፋና አብነት ደሳለኝ ይባላሉ፡፡ ሁሉም ዕድሜያቸው 16 እስከ 28 ክልል ውስጥ ያለ ነው፡፡ 

ተከሳሾቹ የአገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማፈራረስ ከሚንቀሳቀሰው የአርበኞች ግንባር ከሚባለው የሽብር ቡድን ጋር መቀላቀላቸውንና መመልመላቸውን የቀረበባቸው ክስ ያስረዳል፡፡ ወጣቶቹ በግንባሩ ከተመለመሉ በኋላ ወደ ኤርትራ ሄደው ወታደራዊ ሥልጠና መውሰዳቸውን፣ ቀደም ብለው የሽብር ቡድኑን በተቀላቀሉ ዘመዶቻቸው መመልመላቸውንና ሥልጠና ወስደው ሲጨርሱ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ሌሎችን ወጣቶች ሲመለምሉ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ በሱዳን በኩል በማቋረጥ ኤርትራ ደርሰው ለመሠልጠን ከግንባሩ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበረም ክሱ ይገልጻል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች 2007 .. መጀመሪያ ወር ጀምሮ እስከ ታኅሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ጎንደር ከተማ ውስጥ የተያዙ መሆናቸውን የሚጠቁመው ክሱ፣ በአጠቃላይ በፈጸሙት በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ የመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን ይገልጻል፡፡ የአርበኞች ግንባር በፓርላማ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ የሽብር ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም፡፡

 

ፍርድ ቤቱ የጠበቆች ጽሕፈት ቤት ለተጠርጣሪዎቹ ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው፣ ክሱን የሚቃወሙ ከሆነ ከተከሳሾቹ ጋር በመነጋገር የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርብ ለግንቦት 24 ቀን 2007 .. ቀጠሮ ሰጥቶ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ አዟል፡፡