Latest Blog posts
Editors Pick
Latest documents
Education and Training Policy of Ethiopia - Amharic version - 2023 7210 Downloads - policies and strategies | 7.6 MB | |
The Normative Basis for Decision on the Merits in Commercial Arbitration - the Extent of Party Autonomy 187 Downloads - Arbitration Law | 635.59 KB | |
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የህግ ትርጉም የሰጠባቸው ውሣኔዎች ማውጫ ቅጽ 01-25 8541 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 10.72 MB | |
ስለ ወንጀል ተጎጂዎች - የአዲስ እይታ አስፈላጊነት በረቂቁ የወንጀል ሕግ የሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ላይ FEATURED 370 Downloads - Criminal Law | 317.19 KB | |
Federal Supreme Court Cassation Decisions - Table of content Volume 1-25 10258 Downloads - Federal Supreme Court Cassation Bench Decisions | 6.57 MB |
- Details
- Category: Legal News - የሕግ ዜናዎች
የታገዱ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች እንዲወዳደሩ የአማራ ክልል ሰበር ሰሚ ትዕዛዝ ሰጠ
-የፓርቲው ሊቀመንበር ፓስፖርታቸው ተመለሰላቸው
በአማራ ክልል በአምስት የምርጫ ወረዳዎች እንዳይወዳደሩ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሰጥቶባቸው የነበሩ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ ውሳኔው ተሽሮ እንዲወዳደሩ መጋቢት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ትዕዛዝ መሰጠቱ ታወቀ፡፡
ትዕዛዙን የሰጠው አምስት ዳኞች የሚሰየሙበት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሲሆን፣ ከአምስቱ ዳኞች አንደኛው በትዕዛዙና ውሳኔው ተለይተዋል፡፡ ጉዳዩን እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት በማድረስ ያሸነፈው ሰማያዊ ፓርቲ፣ በአማራ ክልል በመርዓዊና በገርጨጭ አምስት የምርጫ ወረዳዎች አምስት ለፓርላማና አሥር ደግሞ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ያቀርባል፡፡ የቀረቡት ዕጩዎች አባሎቹ መሆናቸውን በመግለጽ ለክልሉ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት አቤቱታ በማቅረብ እንዲሰረዙ ያደረገው ደግሞ፣ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ነው፡፡
በዕጩዎቹ መሰረዝ ቅር የተሰኘው ሰማያዊ ፓርቲ ለአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ በመመሥረት ዕጩዎቹ የራሱ መሆናቸውን ያስረዳ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን መርምሮ በሰጠው ውሳኔ፣ አንድነት ያቀረበው አቤቱታ ትክክል መሆኑን በመደገፍ መሰረዛቸው አግባብ መሆኑን አረጋግጦ ነበር፡፡
የክልሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም ሰማያዊ ፓርቲ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን በመግለጽ አፅንቶ ይመልሰዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ተስፋ ሳይቆርጥ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማቅረቡ፣ የሰበር ሰሚው ችሎት፣ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔን አስቀርቦ የውሳኔ መዝገቦችን መርምሯል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የተወሰነበት ውሳኔ በሕገ መንግሥቱና በተለያዩ የበታች ሕጎች የተደነገገለትን መብት ያጓደለ መሆኑን ጠቅሶ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ተሰይመው የሰጡት ውሳኔ ሕጋዊ አለመሆኑን በመዘርዘርም፣ የተሰጠው ውሳኔ ተሽሮ ለውድድር ያቀረባቸው ዕጩዎች መወዳደር እንዲችሉ መጠየቁን የሰበር ሰሚው ችሎት ውሳኔ ያስረዳል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ በሰበር ችሎቱ ቀርቦ ባደረገው ክርክር ደግሞ፣ ለሰማያዊ ፓርቲ አባል በመሆን ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት አባላት የአንድነት አባል የነበሩና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጠውን አስገዳጅ ድንጋጌ ሳያከብሩ ወጥተው፣ ለሰማያዊ ፓርቲ ሊወዳደሩ እንደማይችሉ አስረድቷል፡፡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትክክል መሆኑን ገልጾ ውሳኔው እንዲፀናለት ጠይቋል፡፡
ሰበር ሰሚ ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ መዝገቡን ሲመረምር፣ አንድነት ፓርቲ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን የማየት ሥልጣን እንደሌለው ያቀረበውን መቃወሚያ፣ በክልሉ የሚሰጥን ማንኛውንም ውሳኔ በሚመለከት በመጨረሻ የማየት ሥልጣን እንዳለው በመግለጽ ውድቅ አድርጎበታል፡፡
የመምረጥና መመረጥን ጉዳይ በሚመለከት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 እና በምርጫ አዋጅ ቁጥር 573/2000 መሠረት ሰማያዊ ፓርቲ የራሱ መሆናቸውን የገለጻቸው ዕጩዎች፣ ከአንድነት ፓርቲ መምጣታቸውን አለመካዱን ገልጿል፡፡ ነገር ግን ዕጩዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆኑት አሁን ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ በመሳተፍ ላይ ካለው አንድነት ፓርቲ ሳይሆን፣ ለሁለት ተከፍሎ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ሲጠይቁ ከነበሩትና ዕውቅና የተነፈገው የአንድነት ፓርቲ አባላት የነበሩ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ ካቀረባቸው ሰነዶቸች መረጋገጡን አስፍሯል፡፡ በመሆኑም አንድነት አባሎቹ እንደሆኑ በመግለጽና የፓርቲውን ሕገ ደንብ እንዳላከበሩ ተደርጎ እንዲታገዱ ያደረገበት አካሄድ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል፡፡
አንድነት አባሎቹ እንደሆኑ አድርጎ ቢወስድ እንኳን፣ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 31(3) በማንኛውም ጊዜ ያለ ቅድመ ሁኔታ አባልነትን መተው የሚቻል መሆኑን፣ የፓርቲዎች መተዳደሪያ ደንብም አዋጁን መፃረር እንደማይገባው በንዑስ አንቀጽ (4) መደንገጉን ጠቁሟል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲን ደንብ የተመለከተው ሰበር ሰሚ ችሎቱ በደንቡ አንቀጽ 5.3 ላይ የአንድን ሰው አባልነት ለመቀበል ስድስት ሳምንታትን መጠበቅ እንዳለበት እንደሚገልጽና የአንድነት አባላት ናቸው የተባሉትን ሰዎች ባስቀመጠው ጊዜ ውስጥ መቀበሉን እንደሚያሳይ ጠቁሞ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ‹‹ስድስት ሳምንታቱን አልጠበቀም›› በማለት ያስተላለፈው ውሳኔ ስህተት መሆኑን ገልጿል፡፡ በመሆኑም በሥር ፍርድ ቤቶች ለአንድነት ፓርቲ የተሰጡት ውሳኔዎች መሻራቸውን በመግለጽ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩዎች በመርዓዊና በገርጨጭ ምርጫ ወረዳዎች እንዲወዳደሩ ወስኗል፡፡ ለመወዳደር የሚከለክላቸው ነገር ስለሌለና ለዕጩነት ብቁ በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትና የምርጫ ወረዳዎቹ እንዲያስፈጽሙ አዟል፡፡
በውሳኔውና በትዕዛዙ የተለዩት የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኛ በእንግሊዝ ተፎካካሪ ፓርቲ የሆነውን የሌበር ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ ጠቅሰው፣ አንድ የፓርቲ አባል ፓርቲውን ሲለቅ ከ14 ቀናት ላላነሰ ጊዜ ማስታወቂያ ሳይለጠፍ፣ ለሌላ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡ በርካታ የአውሮፓ አገሮችም የምርጫ ሥነ ምግባርን ለመዳኘት የሚያስችል ‹‹Anti-Jumping or Anti-Defecting Law›› የሚባል ሕግ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዴት አባል እንደሚሆንና እንዴት እንደሚተው የሚደነግግ መሆኑን አክለዋል፡፡ አስቀድሞ አባል ለነበሩበት ፓርቲ ማሳወቅ እንዳለበትም እንደሚደነግግ አስረድተዋል፡፡ የአውሮፓ ሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽንም ‹‹European Convention on Human Right›› ፓርቲዎች አዲስ አባላትን እንዴት እንደሚቀበሉና እንደሚያጣሩ የሚያስረዳ መተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው እንደሚገባ አካቶ እንደሚገኝ ጠቃቅሰዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከጠቃቀሱ በኋላ የምርጫ አዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 31(1) እና ንዑስ አንቀጽ (4) ድንጋጌ ትክክለኛነትንም አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን አንድ የፓርቲ አባል አባልነቱን በፈቃዱ ሲተው፣ አባል ለነበረበት ፓርቲ እንዲያሳውቅ የሚደነግግ ቀላል የመተዳደሪያ ደንብ በፓርቲዎች እንዳይወጣ የሚከለክል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተለዩት ዳኛ ሰፋ ያለ ትንታኔ ሰጥተው ዕጩዎቹን በዕጩነት ያቀረቧቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሙሉ አባልነት ማዕረግ በሕጉ አግባብ ያገኙ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 532/99 አንቀጽ 41(1) እና 46(1) መሠረት መሥፈርት ያላሟሉ ዕጩዎች በመሆናቸው፣ ተቃውሞ ሊቀርብላቸው እንደሚገባም አክለዋል፡፡ በዕጩነት መቅረባቸውም ሕጋዊ ባለመሆኑ እንዲሰረዙ በሥር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ ትክክል መሆኑን ደግፈው ተለይተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ መጋቢት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ለመሄድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በኢሚግሬሽን ሠራተኞች ፓስፖርታቸው መነጠቃቸውን ገልጸው የነበሩት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ፓስፖርታቸው እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ለምን እንደተነጠቁ ምላሽ የሚሰጣቸው እንዳላገኙ ገልጸው፣ ‹‹ጉልበተኞች ያደረጉትን ያድርጉ እንጂ እኔ አሁንም ለመሄድ እሞክራለሁ፤›› በማለት፣ ሚያዝያ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ ለመሄድ ማሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡