የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ አዲስ የመኖሪያ ቤቶች አስተዳደር አዋጅ ለማዘጋጀት ጥናት ማካሄድ ጀመረ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሚኒስቴሩ ከሚያዘጋጀው አዋጅ በመነሳት፣ ሲንጋፖርን ከመሳሰሉ አገሮች ልምድ በመቅሰም ደንብና መመርያ ለማዘጋጀት ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት የነበረው የመኖሪያ ቤት አስተዳደር አሠራር ቀርቶ አዲስ የቤቶች አስተዳደደር ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በቅርቡ ለጋዜጠኞች እንደገለጹትም፣ ከዚህ በፊት የነበረው የቀበሌ ቤቶች አስተዳደር ሥርዓት፣ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ቤቶች የሚተዳደሩበት አሠራር ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው፡፡
ከንቲባው እንዳሉት እየተገነቡ ላሉ መኖሪያ ቤቶች ራሱን የቻለ አዲስ የመኖሪያ ቤቶች አስተዳደር ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ አዲስ የመኖሪያ ቤት ሥርዓት ያስፈለገበትን ምክንያት ከንቲባ ድሪባ ኩማ ሲያስረዱ፣ ከአያያዝ ጉድለት የተነሳ አንዳንድ ቤቶች የባንክ ብድራቸው ተከፍሎ ሳያልቅ የሚበላሹበትን አጋጣሚ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ባንኮችን ትልቅ አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልጸዋል፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል የመኖሪያ ቤቶች ባለቤቶች ቤቶቹን በተመለከተ ማድረግ ያለባቸውንና ማድረግ የሌለባቸውን፣ ለይቶ መከታተልና መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ የቤቶች ኤጀንሲ የሚቆጣጠረው ጠንካራ ኮሚቴ እንደሚፈጠር ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ከዚህ ቀደም ለነዋሪዎች የተላለፉ 100 ሺሕ ቤቶች የየራሳቸው ኮሚቴዎች አሏቸው፡፡ ጠንካራ ኮሚቴዎች የመኖራቸውን ያህል የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ በርካታ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ በመኖሪያ ቤቶች ቀጣይ አገልግሎት ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም ባሻገር፣ የጋራ መጠቀሚያ የሆኑ ሕንፃዎችም ላልተፈለጉ አገልግሎቶች እየዋሉ መሆኑ ይነገራል፡፡ አስተዳደሩ ከሚኒስቴሩ አዋጅ በመነሳት የሚያዘጋጀው ደንብና መመርያ፣ እነዚህን ችግሮች እንደሚቀርፍ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡
በተለይ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከዚህ አዋጅ ጎን ለጎን ያዘጋጀው የመኖሪያ ቤቶች ግብይት አዋጅ ሲፀድቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ተዛብቶ የቆየው የቤቶች አስተዳርና ግብይት ዘርፍ ሥርዓት ይይዛል ተብሏል፡፡ በረቂቅ ደረጃ በሚገኘው የመኖሪያ ቤቶች ግብይት አዋጅ የሪል ስቴት ግብይትና የአከራይ ተከራይ ግንኙነትን በሚመለከት በርካታ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡ ለረቂቅ አዋጁ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንዳሉት፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይን በተመለከተ አከራዮችና ተከራዮች የሚመሩባቸው ጉዳዮች ተተንትነዋል፡፡
ትንታኔ ከተሰጠባቸው መካከልም አንድ የሚከራይ ቤት ማሟላት ያለበት አገልግሎቶችና የቤቶቹ ስፋት ተለይቶ፣ ከስንት ብር መከራየት እንዳለባቸው መደንገጉን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህ አሠራር ከመኖሪያ ቤቶች አስተዳደር አዋጅ ጋር ተደምሮ፣ በከተማው የሚገኘውን የተዘበራረቀ የመኖሪያ ቤት ግብይት አሠራርና አጠቃቀም ወደ አንድ የሚያግባባ አቅጣጫ ይወስደዋል ተብሎ እንደሚታመን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡