የንግድ ሕጉን ለማሻሻል የፖሊሲ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው
በክርክር ሒደት ላይ እያሉ የሚቋረጡ የክስ መዝገቦች መበራከት ምክንያቱ ተከሳሾችንና ምስክሮችን ማቅረብ ባለመቻሉ መሆኑን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ የ2007 ዓ.ም. የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለምክር ቤቱ ባለፈው ማክሰኞ ባቀረቡበት ወቅት፣ በክርክር ሒደት የሚቋረጡ የክርክር መዛግብትን ለመቀነስ የተደረገው ጥረት አጥጋቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ሚኒስትሩ የሚቋረጡ የክስ ክርክር መዛግብትን ከ0.5 በመቶ በላይ እንዳይበልጡ ለማድረግ በታቀደው መሠረት፣ የስምንት ወራት አፈጻጸሙ ሲገመገም 25.87 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡
በከባድ ወንጀል ውሳኔ ከተሰጠባቸው 487 መዛግብት ውስጥ 126 የሚሆኑት መቋረጣቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
‹‹ዕቅዱን በተሟላ ሁኔታ ለማሳካት ያልተቻለበት ምክንያት ተከሳሾችንና ምስክሮችን በሚፈለገው ደረጃ አለማቅረብ እንደሆነ በመለየቱ፣ በቀጣይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ጉዳዩ በደንብ እንዲብራራለት ምክር ቤቱ በተወካዮቹ አማካይነት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ሚኒስትሩ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹በሪፖርቱ ላይ ለማመልከት እንደሞከርኩት ችግሩ ፈርጀ ብዙ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው፣ ‹‹በዋነኛነት ፈተና እየሆነ ያለው የተከሳሽና የምስክር በወቅቱ አለመቅረብ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ይህም ችግር በሁለት መንገድ የመነጨ መሆኑን የመጀመሪያውም፣ ‹‹በውስጣችን የሚታይ ብልሹ አሠራርን ባለማስወገዳችን ተከሳሽና ምስክር አልቀረበም በሚል መንገድ ተደርድሮ ክስ የማዘጋት ተግባር አለ፤›› ብለዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ኅብረተሰቡ ዘንድ ተከሳሽንና ምስክርን በማቅረብ ረገድ ያለመተባበር ችግር መኖሩን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ ተከሳሽንና ምስክርን የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለበት ፖሊስ ማቅረብ ባልቻለ ቁጥር፣ ፍርድ ቤት የሚያከራክረው ወገን ስለማይኖር ክስ ተቋርጦ ፋይል እንደሚዘጋ ተናግረዋል፡፡
‹‹ተከሳሾች አገር ውስጥ እንዲሁም እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እያሉ በተደጋጋሚ ተፈልጐ አልተገኘም በሚል መንገድ ክስ ይዘጋል፤›› ሲሉ ለፓርላማው ሪፖርት አድርገዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዓቃቢያነ ሕግና ፖሊስ ተቀናጅተው እንዲሠሩና በከፍተኛ አመራር በጥብቅ ቁጥጥር ያላግባብ የመጠቀም ፍላጐትን ለማጥበብ መጣር ተገቢ መሆኑን፣ በዚህ ሁኔታም ለመሥራትም ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
የፓርላማው የውጭና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ ለፓርላማው እየቀረቡ ያሉ ረቂቅ ሕጐች ጥራት ጉድለት ምክንያት ፍትሕ ሚኒስቴር ሕጐች እንዲፀድቁ ከመላካቸው በፊት የመመልከት ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ነው በማለት ላቀረቡት አስተያየት አዘል ጥያቄ፣ ችግሩን ለማስተካከል በሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ የመነጨው የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት የተሰጣቸውን ሕግ የማመንጨት ሥልጣን እንደ መጨረሻ አርቃቂነት በመውሰድ በቀጥታ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በመላካቸው ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሕግ አመንጪ አካላት ያዘጋጁትን ረቂቅ ለፍትሕ ሚኒስቴር በመጀመሪያ መላክ እንደሚገባቸው፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ያላየው ረቂቅ ሕግ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዳያልፍ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ለረጅም ዓመታት ሲንከባለል የቆየው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል ተጠናቆ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ሥር ባሉ የተለያዩ ክላስተሮች ውይይት እንዲደረግበት መላኩን ተናግረዋል፡፡
የንግድ ሕጉን ማሻሻል በተመለከተ አገሪቱ አሁን የምትከተለውን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዘላቂነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ ሕጉን ማሻሻል ከመጀመሩ በፊት ማዕቀፉን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የንግድ ሕጉን በተመለከተ ሦስት የፖሊሲ ማዕቀፎች የተዘጋጁ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ፖሊሲዎቹን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያፀድቀው ከሆነ የንግድ ሕጉን የማሻሻሉ ሥራ ጊዜ የሚፈጅ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡