የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያና ቱርክ በመከላከያ ዘርፍ ሊተባበሩ የፈረሙትን ስምምነት በሙሉ ድምፅ አፀደቀው፡፡ በተመሳሳይም የምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይልን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. አፅድቋል፡፡
ኢትዮጵያና ቱርክ ከሁለት ዓመት በፊት የተፈራረሙት የመከላከያ ኢንዱስትሪ ስምምነት፣ የኢትዮጵያን የመከላከያ አቅምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመገንባት ባሻገር ሁለቱ አገሮች የጦር መሣሪያዎችን በጋራ በማምረት ለሦስተኛ ወገን ለመሸጥ እንደሚያስችላቸው ሕጉ ይደነግጋል፡፡
ሁለቱ አገሮችን በውስጥ አሠራራቸው መሠረት ስምምነቱን በአዋጅ ማፅደቅ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ይህን ሕግ ቀድማ ልታፀድቅ መነሳቷን በምክር ቤቱ ውይይት ወቅት ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይልን ለማቋቋም የተደረገውን ስምምነት አዋጅ አፅድቋል፡፡ የአዋጁ መፅደቅ በአገሪቱ ያለውን ሰላምና መረጋጋት በማስቀጠልና በቀጣናው ያለው አለመረጋጋት በአገሪቱ ሊኖረው የሚችለውን ሥጋት ለመቀነስ ይጠቅማል ተብሏል፡፡ በአዋጁ መሠረት የተጠንቀቅ ኃይሉ መቀመጫው በአዲስ አበባ ሲሆን፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ስምምነቱን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ፕሮቶኮሉ በይዘቱ የአፍሪካን የሰላምና የፀጥታ መዋቅር የሚዘረጋ ሲሆን፣ በዋናነት ግጭቶችን ስለመከላከል፣ ስለቅድሚያ ማስጠንቀቂያ፣ ጣልቃ ስላለመግባት፣ ሰብዓዊ ዕርምጃዎችን፣ እንዲሁም አደጋን ስለመከላከል የሚሉ ክፍሎች ይገኙበታል፡፡
ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች አራት ሕጎች ያፀደቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከቻይና መንግሥት ጋር የዲፕሎማቲክ ሰርቪስ ፖስፖርት ለያዙ ግለሰቦች ቪዛን ለማስቀረት የተደረገው ስምምነት ይገኝበታል፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ የኢትዮጵያ ፕሮቶኮል ማሻሻያም በምክር ቤቱ የፀደቀው ሌላው አዋጅ ነው፡፡