ከ5 ወራት በፊት በሃዋሳ ከተማ የአንድ ጠበቃን ህይወት ያጠፋው አና ረዳቱን ያቆሰለው ግለሰብ በሞት እንዲቀጣ የሃዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ አሳለፈ።
አቶ ታምራት ሙሉ የተባለው ግለሰብ መስከረም 28 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ ጠበቃው ቢሮ በማምራት ነበር ወንጀሉን የፈጸመው። ተከሳሹ ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ለጊዜው የተሰወረ ቢሆንም፥ ከ11 ቀናት ክትትል በኋላ በገላን ከተማ ሊያዝ ችሏል። በሃዋሳ ከተማ የብሉናይል እና ኢቭኒንግ ስታር ሆቴሎች ባለቤት መሆኑ የተገለጸው ግለሰቡ፥ በተለያዩ ክሶች ሲሞግተው የነበረውን ጠበቃ ነው በሽጉጥ የገደለው።
ተከሳሹ በተያዘበት ወቅትም ሽጉጥ፣ አምስት የጦር መሳሪያ እና ሁለት የእጅ ቦንቦች ተገኝተውበታል። በተጨማሪም ግለሰቡ ቀደም ሲል የገቢ ግብር ባለመክፈል ከድርጅቱ ሰራተኞች የተሰበሰበ የማህበራዊ ዋስትና ገቢ 200 ሺህ ብር ለግል ጥቅሙ በማዋል እና ደረቅ ቼክ በመቁረጥ ወንጀሎችም ጥፋተኛ ተብሎ በፖሊሰ እየተፈለገ ነበር።
ግለሰቡ ዛሬ በዋለው ችሎት ክስ በተመሰረተበት የግፍ አገዳደል፣ የግድያ ሙከራ መፈጸም፣ የጦር መሳሪያ ማከማቸት እና ዛቻና ማስፈራሪያ ጥፋተኛ ሆኗል ። በዚህም በሞት እንዲቀጣ የሃዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስኗል።
በሃዋሳ ከተማ በግለሰቡ ስም የተመዘገቡት ሆቴሎችም በባንክ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እንዲሁም በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ የተጣለባቸው መሆኑንም የባልደረባችን ፍርድአወቅ አጥቁዬ ዘገባ ያመለክታል።