-ማረሚያ ቤት ‹‹ተዘረፍን›› ላሉ ተጠርጣሪዎች ምላሽ እንዲሰጥ በድጋሚ ታዘዘ
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙትና የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለመሠረተባቸው ክስ ቅደመ መቃወሚያ ባቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብረሃ ደስታን ጨምሮ አሥር ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ውድቅ እንዲደረግለት ታህሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤትን ጠየቀ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክሱን እየመረመረ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የመቃወሚያ መልስ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቧቸው ቅድመ መቃወሚያዎች በወንጀል ሕግ መቅጫ ሥነ ሥርዓትን የተከተሉ አይደሉም፡፡
ግንቦት 7 የሚባለውን ድርጅት በሚመለከት ተጠርጣሪዎች፣ ‹‹ዓቃቤ ሕግ ማስረጃ አላቀረበም›› ማለታቸውን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ከሕጉ አኳያ ‹‹ተገቢነት የሌለው›› ካለ በኋላ፣ ሽብርተኛ ድርጅት መባል አለመባሉን ፍርድ ቤቱ ግንዛቤ የሚወስድበት መሆኑን ገልጾ፣ ተቃውሞው ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ በመጠቆም ተቃውሟል፡፡
የሽብር ቡድኑ ዓላማና ተግባርን የሚያሳይ ማስረጃ በክሱ ተያይዞ አለመቅረቡን በመግለጽ ተጠርጣሪዎቹ ላቀረቡት ቅድመ መቃወሚያ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው፣ መቃወሚያው የማስረጃ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከመጀመሪያ መቃወሚያና ከእምነት ክህደት ቃል መስጠት ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡ በፍርድ ቤቱ የሚመዘን እንጂ በመቃወሚያ ደረጃ የሚነሳ ጉዳይ ባለመሆኑ፣ ‹‹ማስረጃው በቂ ነው አይደለም›› የሚለው በችሎት የሚመዘን በመሆኑ መቃወሚያው ተገቢነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በክሱ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የተጠቀሱ አመራሮች መቼና የት ሽብርተኛ ሆነው እንደተፈረደባቸው ተጠርጣሪዎቹ እንዲገለጽላቸው በመቃወሚያቸው መጠየቃቸውን በሚመለከት፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ጥያቄው የማስረጃ ጉዳይ ነው›› ብሏል፡፡ በፍርድ ቤቱ ተመዝኖ የሚፈታ ጉዳይ ከመሆን ባለፈ በመቃወሚያ የሚቀርብ ጉዳይ አለመሆኑን በመጠቆም ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡
የሽብር ቡድኑ አባላትም ሆኑ አመራሮች በድርጅቱ ውስጥ ያላቸው ቦታና የሚሠሩት ሥራ ዝርዝር ለተጠርጣሪዎቹ መግለጽ አግባብ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕግ በመልሱ አስታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከግንቦት 7 ድርጅት አባላት ጋር መገናኘታቸው መገለጹ በቂ በመሆኑ፣ የግንቦት 7 ድርጅት አባላት የሽብር ቡድኑ አመራሮች ለመሆናቸው የቀረበ ማስረጃ እንደሌለ በመግለጽ፣ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡት መቃወሚያ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከሽብርተኛ ድርጅቱ ጋር ተያያዥነት እንደሌላቸው በመግለጽ ግንኙነት አላቸው በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሠረተ፣ በግልጽ አስረድቶ እንዲያቀርብ የጠየቁትን በሚመለከት በሰጠው ምላሽ፣ ከሽብርተኛ ድርጅቱ ጋር ያደርጉት የነበረውን ግንኙነት በክሱ ውስጥ በግልጽ መጥቀሱን አስታውሶ፣ ጉዳዩ በማስረጃ የሚጣራ እንጂ ለመቃወሚያ የሚበቃ ጥያቄ ባለመሆኑና አቀራረቡም ግልጽ ስላልሆነ፣ መቃወሚያው ውድቅ እንዲሆንለት ወይም ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ በመግለጽ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ችሎቱ በዕለቱ ሌላው መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው ተጠርጣሪዎቹ ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ባመለከቱት መሠረት፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ነበር፡፡ ኃላፊው የቀረቡ ቢሆንም ቀደም ባለው ችሎት ፍርድ ቤቱ በአብላጫ ድምፅ ሰጥቶት የነበረው ትዕዛዝ፣ ከድምፅ መቅረጫ ተገልብጦ እንዳልደረሳቸው ኃላፊው በማስረዳታቸው፣ በአስቸኳይ ተገልብጦ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ የኃላፊውን ምላሽ ለመስማት ለጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም.፣ እንዲሁም የተጠርጣሪዎቹን ቅድመ ክስ መቃወሚያና የዓቃቤ ሕግን ምላሽ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡