Details
Category: Legal News - የሕግ ዜናዎች

ፍርድ ቤቱ በሃና ላላንጎ የክስ መዝገብ ላይ የአቃቤ ህግን ምስክር ለመስማት ቀጠሮ ያዘ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የወንጀል ችሎት የ16 ዓመቷ ሃና ላላንጎን አስገድደው ደፍረው ለህልፈተ ዳርገዋታል በሚል በተጠረጠሩ አምስት ተከሳሾች ላይ የአቃቤ ህግን ምስክር ለመስማት ቀጠሮ ያዘ።

ፍርድ ቤቱ ክስ አሰምቶ መቃወሚያ ካለ ለመቀበል ነበር ቀጠሮ ይዞ የነበረው።

የሟች ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀደም ብለው ነው ወደ ፍርድ ቤት የደረሱት።

ችሎቱ ተከሳሾች ላይ የተመሰረተው ክስ ተጣርቶ ለወደፊት ጥፋተኛ ናቸው አይደለም የሚለው ውሳኔ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የተፈፀመው ወንጀል ከሞራልም ሆነ ከሀይማኖት አንፃር ህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው ብሏል።

ይህ በመሆኑ እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥም ህጉ ችሎቱ ዝግ ይሁን ብሎ ስለሚደነግግ በዝግ መሆን አለበት ነው ያለው ፍርድ ቤቱ።

ለችሎቱ ሂደት አስፈላጊ ናቸው የተባሉ አካላት ብቻ ሲቀሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሌሎች ታዳሚዎች ችሎቱን በቀጥታ እንዳይከታተሉ ተደርጓል።

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ የሆነውን ሂደት ብቻ ጋዜጠኞች እንዲያገኙ ባመቻቸው መንገድ መሰረት ተከሳሾች በተመደበላቸው የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ አማካኝነት ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

ተከሳሾቹ ክሱ ተነቦላቸው በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል ወንጀሉን አልፈፀምንም ነው ያሉት።

ክደው በመከራከራቸው የአቃቤ ህግ ምስክርን ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለጥር 1፣ 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

FanaBC By FanaBC
FanaBC
Last Updated: 11 October 2022
Hits: 36841
Abyssinia Law | Making Law Accessible!
Abyssinia Law | Making Law Accessible!