ከ575 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ሲያዘዋውር የተገኘው የ29 አመቱ ወጣት ዛሬ በስምንት አመት ከአምስት ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ።
ተከሳሹ አብዱልፈታህ ሙስጠፋ የሚባል ሲሆን፥ በፌደራል ፖሊስ ነው በህገወጥ መንገድ ዶላር ሲያዘዋውር የተያዘው።
ጥቅምት 3 ቀን 2007 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰአት ላይ ከተለያዩ ግለሰቦች 29 ሺህ 551 የአሜሪካን ዶላር ይዞ በፖሊሶች የታየው ተከሳሹ፥ በእለቱ በቁጥጥር ስር ውሎ ለምርመራ ወደ ማዕከላዊ ፖሊስ ያመራል።
በ24 ሰአት ወስጥ ፖሊሰ ቃሉን ተቀብሎ በቀጥታ ወደ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድበ ችሎት ይወስደዋል።
ወንጀሉን መፈፀሙን ያመነው ተከሳሹ፥ ጥቅምት 3 2007 ከእጁ የተገኘው ብቻ ሳይሆን ቤቱ ሲበረበርም ሌላ ዶላር ተገኝቷል።
አብዱልፈታህ አራዳ ምድብ ችሎት 575 ሺህ 360 የአሜሪካን ዶላሩን እንደታቀፈ ነው የቀረበው።
የአራዳ ምድብ ችሎትም የአብዱልፈታህን ማመን ተከትሎ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል።
ችሎቱ ተከሳሹን በ8 አመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት የቀጣው ሲሆን፥ አጠቃላይ የተገኘው ገንዘብም ለመንግስት ገቢ ይሁን ሲል ትእዛዝ ሰጥቷል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው የትኛውም ሰው በእጁ ዶላር ይዞ ከተገኘ ያስቀጣል የሚል ነው።
ከውጭ ሃገር እንኳን ቢላክ ወዲያውኑ ደንበኛው ባንክ በመምጣት ሊመነዝር ይገባዋል ይላል አሰራሩ።